እርዳታን ማንም አይጠላም፤ በተለይ የተቸገረ ሰው ደግሞ ዕርዳታን አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ ያለው ለሌለው ቢመጸውት ነውር አይደለም። አገራችን አሁን ካለችበት ፈታኝ ወቅት በፊትም ቢሆንም ከለጋሽ አገሮች የተለያዩ እርዳታዎችን ተቀብላለች፤ እርሷም ቢሆን ያላትን መለገሷን ታሪክ ይመሰክርላታል።
ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ለኢትዮጵያ ‹‹በእርዳታ ስም›› የሚደረገው እንቅስቃሴ ብዙ የሚያስብል ሆኗል። አንዳንድ ‹‹ለጋሽ ነን›› ባዮች በእርዳታ ስም ጤናማ ያልሆኑ ሃሳቦችን መያዛቸው እየተስተዋለ እና ነገሩን በንቃት ለመመልከት አስገዳጅ የሆነበት ወቅት ላይ ተደርሷል።
‹‹በበጎ ፈቃድ›› ስም የተመሰረቱ አንዳንድ ድርጅቶች፤ ይህንን ፈታኝ ወቅት እንደ አንድ ጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር አላማቸውን ለማስፈጸም አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በማስታጠቅ በኩልም የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰሩ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር ግንባር ቀደም ተጠያቂው አሸባሪው ህወሓት ነው። ሆኖም ግን ‹‹ሽብርተኝነት እንዋጋለን› የሚሉት አገራት ከአሸባሪው ጎን ቆመው መታየታቸው የሚሰጡትን እርዳታ እያስተጓጎለ አለንልህ ማለታቸው የሚያስተዛዝብ ሆኗል፡፡
ለዚህም ማሳያዎችን እንመልከት። ከሰሞኑም መንግስት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በአገሪቱ ይሠሩ የነበሩ የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ፣ ኖርዌጂያን ሪፉጂ ካውንስል እና አል ማክቱም ፋውንዴሽንን ለሦስት ወራት ማገዱ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረቱ ድርጅቶች መንግስት ከሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ነው።
የእርዳታ ድርጅቶቹ ሥራቸው የተራበን ማብላት፣ የታረዘን ማልበስ፣ የተጠማን ማጠጣት፣ የተጎዳን ማከም ብቻ አልነበረም ፡፡ ይልቁኑ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ተጠመዱ እንጂ። የዕርዳታ ድርጅቶቹ ስለምን ጁንታውን የሙጥኝ አሉት? ቢባል አላማቸውን በውክልና ለማስፈጸም እንደሆነ መገመት አይከብድም።
በተባበሩት መንግስታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአደጋ ጊዜ አስተባባሪ ቶሚ ቶምሰን ከጁንታው ከፍተኛ አመራሮች (ጌታቸው ረዳ ) ጋር መታየታቸውን አንዳች የሚያሳየው ነገር ሊኖር እንደሚችል መጠርጠሩ አይከፋም። ነገሩ በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ሲንሸራሸር ነበር። ቢቢሲም የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቃል አቀባይን አናግሮ ነበር። በምን አጋጣሚ ነበር ጌታቸው ረዳ እና ቶማስ ቶምሰን የተገናኙት? ብሎ ቢጠይቅም ቃል አቀባዩ ምላሽ ከመስጠት መቆጠባቸውን አንዳች የሚያመላክት ነገር አለው።
አሸባሪው ቡድን ከ170 በላይ ተሽከርካሪዎችን በማገት፤ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ እርዳታ የሚሹ ዜጎችን ለከፋ አደጋ ማጋለጡ አይዘነጋም። በዚህ ሳቢያ አጥፊው ቡድን እታገልለታለሁ የሚለው የትግራይ ህዝብ ለከፋ ስቃይ፣ ረሃብ እና እንግልት መዳረጉ ሳይበቃ ህጻናቱን እንደ ዕድሜ እኩዮቻቸው ወደ ትምህርት ቤት እንዳያቀኑ እውቀት እንዳይገበዩ ለጦርነት ሲያሰማራ፤ በእርዳታ ድርጅቶቹ ሳይቀር መወቀስ ሲገባው እየተሞገሰ ከእነርሱ ጋር መተሳሰሩ አስገራሚ ነው።
ህፃናትን ለጦርነት ከማሰለፍ በተጨማሪ የስለላ ሥራን እንዲሰሩ በማድረግ የትግራይ ህዝብ ላይ ቁማር እየተጫወተ ይገኛል። ሕዝቡን ሆን ብሎ በማጎሳቆል አንድ ጊዜ ‹‹ህዝቡ ተርቧል›› ሲል ሌላ ጊዜ ደግሞ ለተረጂዎች ‹‹እርዳታ ለማስገባት በሱዳን በኩል ያለው መተላለፊያ ኮሪደር ይከፈት›› ማለቱ ብቻ ሳያበቃ አንዳንድ ለጋሽ ድርጅቶች ተመሳሳይ ሃሳብ ማንጸባረቃቸው እና እርዳታ እንዳይገባ ሲከላከል የነበረ አሸባሪ ቡድን የሚሰጠውን ሃሳብ መደገፋቸው ምን አላማ ቢኖራቸው ነው ? የሚል ጥያቄን ማስነሳቱ አይቀርም።
የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው አጥፊ ቡድን፤ በዚህ ዘመን እንኳን ዘመኑን ከመዋጀት ይልቅ ወደ ማይበጀውና ያለፈበትን አምባገነንነት ሥርዓት በመመለስ እኔ ካልመራሁ አገሪቱን አፈራርሳታለሁ በማለት ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› የሚለው የዶሮዋን ተረት እንድናስታውስ ያስገድደናል ።
ሌላም የሚነሳ ጉዳይ ደግሞ አንዳንድ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ‹‹ወደ ትግራይ ሄደን ሕዝቡን እንዳንረዳ መንግስት አላሰራንም›› አሉ፤ ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያዎች እና በጁንታው አፍቃሪዎች አማካኝነት የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ድጋፍ በሚያስፈልገው ህዝብ ላይ ድራማ እየሠሩና ይልቁንም ድጋፋቸውን በግልጽ ለጁንታው እንደሚያደርጉ ሲገልፁ ተስተውሏል። የውጭ አገር ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ጁንታውን ሲደግፉ በስፋት ይታያል። ሕጻናትን በጦርነት ሲያሰልፉ ምንም እንዳለዩ እና ምንም እንዳልሰሙ ሆነው አልፈዋል። ‹‹አሸባሪ›› ብለው እንደ ማውገዝ፤ ዓለም አቀፍ ህግ ሲጣስ ግድ አልሰጣቸውም። ይባስ ብለው አማጺውን ቡድን በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል ጥቃት ሲያደርስ ሠዎችን ሲገድል፣ ጉዳት ሲያደርስና ሲያፈናቅል እንዴት መረጃው አልደረሳቸው? ስለምን ዝምታን መረጡ? ድርጊቱንስ እንዴት አላወገዙም? ቢባል ሞኝነት ይመስላል። ከዚህ ባስ ሲልም ትግራይ ውስጥ የሚገኙትን የኤርትራ ስደተኞች በጁንታው ጥቃት እና ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው ጉዳዩን በጥልቀት አለመመከታቸው ትዝብት ውስጥ የሚከታቸው ነው።
አሸባሪው ህወሓት በመንግስት የቀረበለትን የተናጠል የተኩስ አቁም ከመቀበል ይልቅ እታገልለታለሁ የሚለውን ሕዝብ እርዳታ እንዳያገኝ አድርጓል። ነገር ግን ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶቹ ጉዳዩን ካለማውገዛቸው ባሻገር ዛሬም በቃል ተቀባዮቻቸው በኩል እንደ ጌታቸው ረዳ እና ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ያሉ የጁንታው አመራሮች ወደ ሚዲያ እየወጡ ሲሸልሉ እና ሲፎክሩ እየታየ ነው፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶች ተግባራቸው ለተራበ ሕዝብና የጦርነት ገፈት ቀማሽ ለሆኑት ሕጻናት አንዳች ነገር አልፈየደም።
በመንግስት በኩል ወደ ክልሉ እርዳታዎች እንዲደርሱ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ከሰሞኑም ወደ ትግራይ ክልል 157 ሰብዓዊ እርዳታ የያዙ መኪናዎች መቀሌ ደርሰዋል። ከያዙት ድጋፎች መካከል ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው። ድጋፎቹ ከዓለም የምግብ ድርጅት፣ ከዩኒሴፍ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተገኘ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውና ከመንግስት ኃለፊዎች ጋር መነጋገራቸው ምናልባትም ጁንታው ምን አይነት ጥፋቶችን እያደረገ አንደሆነ ለመመልከትም አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥርላቸዋል የሚል ግምት አለ። ‹‹ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› እንደሚሉት ዓይነት ካልሆነ በስተቀር መንግስት የህወሓት አሸባሪ ቡድን ስርአት የሚይዝ ከሆነ በየትኛውም አማራጭ ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚችል አሳውቋል።
የህወሓት አሸባሪ ቡድን በደቀነው የሀገር የህልውና አደጋ መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱ ይታወቃል። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ብዙ የቤት ሥራዎች አሉባት እንደ አገር የገጠሟትን ፈተናዎች በድል ለመወጣት አሁንም ቢሆን አጥፊው ቡድን የኢትዮጵያን ህልውና ለመፈታተን የማያደርገው ነገር አይኖርም። የአገሪቱን መበታተን ከሚሹት ጋርም በርትቶ ይሠራል፤ ስለዚህ ለጋሾችን በትኩረት መመልክት ብሎም ተገቢውን ክትትልና ተገቢውን ፍተሻ ማድረጉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም