የግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ችግሮችና መጓተቶች በብዙ ዘርፎች ላይ ቢስተዋልም የተሻለ ስራ የሚሰራባቸው ዘርፎችና አካባቢዎች አሉ። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጠንካራ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እየታየባቸው ካሉ አካባቢዎችና ዘርፎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ መንገድ ግንባታ እና ጥገና ተጠቃሽ ነው:: ባለስልጣኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በርካታ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ግንባታ በማከናወን እንዲሁም የጥገና ስራዎችን በመስራት መልካም ውጤትን ማስመዝገብ ችሏል:: የባለስልጣኑ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በግንባታና ጥገና ረገድ ከእቅድ በላይ ማሳካት ችሏል::
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተለያዩ የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል:: 217 ነጥብ ሶስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የተለያዩ የግንባታ እንዲሁም 568 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ፤ በአጠቃላይ ወደ 787 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራዎችን ለማከናወን አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል::
ከአጠቃላይ የግንባታ ስራዎች አንጻር በድምሩ ወደ 209 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እና ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ከእቅዱ 96 በመቶ ማሳካት መቻሉን የባለስልጣኑ ምክትል ሀላፊ አቶ ኢያሱ ሰለሞን ይገልጻሉ። ከጥገና አንጻር ደግሞ 623 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የሚደርሱ ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ስራዎችን በማከናወን ከእቅዱ በላይ ማሳካት ችሏል:: በአጠቃላይ ወደ 835 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራዎችን በማከናወን የእቅዱን 106 በመቶ አከናውኗል::
ከአስፋልት መንገዶች ግንባታ አንጻር ወደ 35 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት መንገድ ግንባታ እንዲሁም 62 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጠጠር መንገዶች ግንባታ ተከናውኗል፤ (ይህም በኮንዶሚኒየም ቤቶች እና በሌሎች አካባቢዎችም) የተከናወኑትን የሚያጠቃልል ነው::
ከግንባታ አንጻር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራባቸው ቦታዎች አንዱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የመንገድ ግንባታ ነው:: በዚህም ወደ 21 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የመንገድ ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ 24 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት እና የኮብሊስቶን መንገዶችን በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ በማከናወን ከእቅድ በላይ መስራት መቻሉን ነው የጠቆሙት::
በከተማዋ ውስጥ የነበረው የእግረኛ መንገድ ሁኔታ ለእግረኞች ምቹ ስላልነበረ በበጀት ዓመቱ ከተሰሩት ትልቅ ስራዎች አንዱ የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ ስራ ነው። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ሰፊ የእግረኛ መንገዶች ግንባታ መከናወኑን ጠቁመዋል:: በዚሁ መሰረት ወደ 41 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የእግረኛ መንገድ ለመገንባት ታቅዶ እስከ በጀት ዓመቱ ማለቂያ ድረስ 27 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ ስራ ተሰርቷል::
ነባር መንገዶች ጥገና ተደርጎላቸው የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዲራዘም ከማድረግ አንጻር አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውን ያብራሩት አቶ ኢያሱ፤ ከአስፋልት መንገድ ጥገና አንጻር ወደ100 ኪሎ ሜትር የሚደርስ አስፋልት መንገድ ለመጠገን ታስቦ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች 113 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ መጠገኑን ነው ያብራሩት::
አቶ ኢያሱ እንደሚሉት፤ በበጀት ዓመቱ 39 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገዶች ተጠግነዋል:: ወደ 50 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የንጣፍ ድንጋይ መንገድ ጥገና ለማከናወን ታቅዶ 55 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የጥገና ስራ ተከናውኗል::
ለመንገዶች ብልሽት ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው የድሬኔጅ መስመሮች ደህንነት አለመጠበቅ ነው። በተለይም ድሬኔጅ መስመሮች ላይ የሚጣሉ ደረቅ ቆሻሻዎች እንዲሁም የድሬኔጅ መስመሩ ከአገልግሎት ውጭ መሆንና ከአጠቃቀም ጉድለትም የሚደርስበት ጉዳት ችግር እየፈጠረ በመሆኑ በበጀት ዓመቱ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የድሬኔጅ መስመሮች ጥገና እና ጽዳት ስራ ነው::
ስኬታማ የመንገድ ስራ ጊዜ እንደነበር የገለጹት አቶ ኢያሱ በአጠቃላይ ከመንገድ ግንባታ አንጻር ከ37 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍኑ 24 መንገዶችን በማጠናቀቅ ለምረቃ በቅተዋል:: በርካታ መንገዶች በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል::
ዘንድሮ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ እና ጥገና ስራዎች የተሰራበት ዓመት ቢሆንም ሁሉም ነገር በሚፈለገው እና ህዝቡም በተሟላ መልኩ አገልግሎት አግኝቷል ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። በመሆኑም አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ አቶ እያሱ ይናገራሉ::
በበጀት ዓመቱ ለመንገድ ግንባታና ጥገና እንቅፋት የሆኑ በርካታ ችግሮች ነበሩ:: አንዱና ዋነኛው ችግር ቀድሞ የለማ ከተማ ውስጥ የሚከናወን የመንገድ ግንባታ እና ጥገና በመሆኑ አዳዲስ የሚሰሩ መንገዶችም ሆኑ ነባሮቹ የማሻሻል ስራዎች በሚሰሩበት ወቅት ሰፊ የወሰን ማስከበር ስራዎችን መስራት ይጠይቃል:: በዚህ ሂደት ውስጥ ቀደም ብለው የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች እና ቤቶችም መነሳት የግድ ይላል::ይህን ከማድረግ አንጻር በበጀት ዓመቱ ሰፊ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም በስራው ላይ ተፅዕኖ ነበራቸው:: ኮንትራት ወስደው የሚሰሩ ድርጅቶች በተባለላቸው ጊዜ አለማጠናቀቅ ሌላኛው ተግዳሮት ነው::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013