በተለያየ አቅጣጫ ፈተናዎች የበረቱ ይምሰሉ እንጂ የኢትዮጵያውያን አንድነት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየጠነከረ መጥቷል፡፡ ይህን ጥንካሬና ህብረት የማይወዱ አካላት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ማበር የእነሱ ውድቀት በመሆኑ እያስፈራቸው ይገኛል፡፡ በጣረሞት ላይ የሚገኘው ሽብርተኛው ህወሓትም በአገር ውስጥ ጦርነት ፈጥሮ የኢትዮጵያን እድገት ከማይፈልጉ አካላት ጋር ለማሴር የያዘው ህልም እየመከነበት ነው፡፡ አዲስ ዘመን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር አያይዞ የቀድሞውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜናን አነጋግሮ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ከትግራይ ክልል ጦሩን ይዞ ለመውጣት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ መድረሱንና ለክልሉም የጥሞና ጊዜ መስጠቱን እርስዎ እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- የኢትዮጵያ መንግስት ግጭቱ ቆሞ ሁሉም ወገን በሰከነ መንፈስ እንዲያስብበት ያደረገው ተግባር በጣም የሚመሰገን ነው።ምክንያቱም በኢትዮጵያውያኑ መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ነው፡፡ይህም የእርስ በእርስ ግጭት ነው።እንዲሁም በወንድማማቾች መካከል የሚካሄድ ግጭት ነው፡፡ስለዚህም ይህ ግጭት መያዝ ያለበት በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ነውና አግባብነት ያለው ውሳኔ ነው፡፡
ሌላው ወገን በስህተት ይሁን በውል አስቦበት ያደረገው ነገር ቢኖር እንደገና ቆም ብሎ ተመልክቶ ጉዳዩን አስቦበት የተለየ እርምጃ እንዲወስድ ያስችለዋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ያደረገው መንግስት እንደመሆኑ መጠን እንደ አባት የሚታይ ነው።ለዚህም ነው እኔ መንግስት የወሰደው እርምጃ ልክ ነው ብዬ የምናገረው። የሚመሰገንም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረገው ለክልሉ ህዝብ በማሰብ ከመሆኑም በተጨማሪ ሁሉም የጥሞና ጊዜ እንዲኖራቸው ነበር፤ ነገር ግን በተሰጣቸው የጥሞና ጊዜ አልተጠቀሙበትምና እርስዎ ይህን እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- አንዳንድ ጊዜ አመራር ሊሳሳት ይችላል፤ ህዝብ እንኳ ይሳሳታል ብዬ አልገምትም። አመራር ግን ይሳሳታል። ህዝቡን መምራት ያለበት አመራር ነው።አመራሩ በአንድ ነገር ላይ ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ በህዝቡ ላይም በአገሪቱ ላይም የሚደርሰውን ጉዳት አመዛዝኖ እና ገምቶ ነው ውሳኔ ማድረግ የሚጠበቅበት፡፡
እኔ እንዳሰብኩት የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የጥሞና ጊዜ በሚያስቀምጥበት ጊዜ በዛ በኩል ያለውም ወገን ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማል የሚል ተስፋ ነበረኝ።ይህ ተስፋ ግን በውል አልተከሰተም።ከዚህ በኋላም ቢሆን ሊፈጽሙት ይችላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።አሁንም ቢሆን ተስፋ አልቆረጥኩም።ምክንያቱም ትክክለኛና ትክክለኛ ያልሆነ ነገር ለሰው ልጅ ግልጽ እየሆነ ይሄዳል።መጥፎውና መልካሙ ነገር እየተለየ የሚሄድበት ሁኔታ አለ፡፡
የአገር መጎዳት፣ በተለይ ደግሞ የሰው ህይወት መጥፋት፣ (በሁለቱም ወገን ማለቴ ነው) ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት። በግጭቱ ውስጥ የሚጎዱት ኢትዮጵያውያኑ ናቸው። ስለዚህም በሁለቱም ወገን ጉዳዩ በጥሞና ቢስተዋል መልካም ነው የሚል አስተያየት አለኝ።ታስቦበት ወደ ሰላም የሚመጣበት መንገድ መኖር አለበት። በዚህ ሁሉ መሃል ስሜታዊነት ሊኖር ይችላል። መናደድም ሊኖር ይችላል።ነገር ግን ትልቁ ነገር ህዝብ እንዳይጎዳ ማድረግ ነው።ይህ ጉዳይ በጥሞና ታስቦ ወደሰላም ይመጣል የሚል አለኝ።የኢትዮጵያ መንግስት እንዳደረገው ሁሉ የትግራይ አስተዳደርም ይህንኑ መንገድ ተከትሎ ነገሩ በሰላም የሚያልቅበት አካሄድ ይፈጠራል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእርዳታ እህል ወደትግራይ ክልል እንዳይደርስ በሚል በሽብርተኛው ህወሓት አጋጅነት የቆመበት ሁኔታ እንደነበር እናስታውሳለን፤ ይህን አካሄዳቸውን ከሰብዓዊ መብት አኳያ እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- ይህ ሁኔታ መቼም ተፈጽሞ ከሆነ በጣም ከፍ ያለ ስህተት ነው።ምክንያቱም ለሰው ልጅ መኖር የመጀመሪያው መሰረታዊ ነገር ምግብ ነው፤ ምግብ ካላገኘ መኖር አይችልም። ሰው እንዲራብ ማድረግ በጣም ከፍተኛ ወንጀል ነው።የሰው ልጅ እንዲራብ ማድረግ የመግደል ያህል ይቆጠራል። ሰው ያለእህል ተርቦ ሊኖር አይችልም። ደግሞም ትግራይ ውስጥ ባለፉት ስምንትና ዘጠኝ ወራት በተፈጸመው ሁኔታ የእህል እጥረት አለ።ህዝብ እየኖረ ያለው በእርዳታ እህል ነው።ያ ህዝብ ደግሞ የእርዳታ እህል ካልደረሰው የሚደርስበት ጉዳት በጣም ከፍተኛ ነው የሚሆነው።በዚህ ሁሉ መሃል ህጻናትም አቅመ ደካማዎችም አሉ።እነዚህ ሁሉ በጣም በቀላሉ የሚጎዱ ናቸው።
ስለዚህም የእርዳታ እህል መከልከል እኔ ‹ለምን› ብዬ ራሴን ብጠይቅ መልስ ያላገኘሁለት ጉዳይ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ምክንያቱም እህሉ የሚሄደው ለትግራይ ህዝብ ነው። ስለዚህም ሲሆን ሲሆን የእርዳታ እህሉ እንዲመጣ ሁኔታዎችን የማመቻቸት እና ግፊት የማድረግ እንዲሁም ህዝቡ በልቶ እንዲያድር ለማድረግ ቅድሚያ በመስጠት መስራት ነው እንጂ የመጣውን እህል መከልከል የሚጠበቅ አይደለም።ይህ በጣም ከፍተኛ ስህተት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ህወሓት የትግራይ ክልል አመራር አይደለም፤ እርስዎም እንደሚያውቁት በሽብርተኛነት ተፈርጇል፤ የገዛ ወገኔ ነው ለሚለው ህዝብ እህል እንዳይደርስ ማድረግ ማለት ምን ማለት ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- በምንም አይነት ተቀባይነት የለውም። በትግራይ አካባቢ ያለሁት አመራር ነኝ ብሏል። ምንም አይነት ቡድን ቢሆን እንግዲህ አመራር ሊኖረው ይችላል።ሽብርተኛም ቢሆን ዓላማዬ ነው ብሎ ከያዘው አመራር አለው።እንዲያም ሆኖ እህሉ እንዳይደርስ ማድረጉ ተገቢ ያልሆነ ነገር ነው።ለምን እንዲህ አደረገ የሚለውን ስለማላውቅ በዚህ ጉዳይ ብዙ ለማለት አልችልም። ነገር ግን ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ በጣም ከፍተኛ ወንጀል ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ድርጊቱ ስለመፈጸሙማ የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ያረጋገጠው ጉዳይ ነው፡፡
አምባሳደር፡- ያንን ጉዳይ ፈጽሞ ከሆነ ከባድ ስህተት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል ጁንታው ህጻናትን ለጦርነት መማገዱን ተክትሎ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዓለም አቀፍ ተቋማት ህወሓትን አለመተቸታቸው ምንን ያሳያል ይላሉ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- እንግዲህ ለምን ብለው ዝም እንዳሉና ምን አስበው እንደሆነ ሊያውቁ የሚችሉት እነርሱ ናቸው። ነገር ግን ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን በጦርነት ማሳተፍ ማለት በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ህግ መሰረት ወንጀል ነው።ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ይህን የሚወስደው እንደወንጀል ነው። ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ መደረግ የሌለበት ነው። የዓለም አቀፉም ማህበረሰብ ሊያወግዘው የሚገባ ነው።
ህጻናቱ ወደጦርነት አውድማ በሚገቡበት ጊዜ ከሌሎቹ ይልቅ የሚደርስባቸው ጉዳት ከፍ ያለ ነው። በስነ ልቦናቸውም ሆነ በአዕምሯቸው ላይ ጠባሳ ጥሎ ነው የሚያልፈው። ስለሆነም ህጻናቱ ጤናማ አዕምሮ ይዘው ሊያድጉ አይችሉም። ህጻናቱን በዚህ አይነት ችግር ውስጥ መክተት ከፍተኛ ጥፋት ነው።ከፍተኛ ወንጀልም ነው።ስለሆነም ይህን የሚያደርግ ወገን ማንም ይሁን ማን የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ዝም ብሎ የሚያየው መሆን የለበትም። የተፈጸመው ነገር ስህተት መሆኑን መግለጽና ስህተት ነው ከሚለው አካል ጎን መቆም ከዓለም አቀፍ ህብረተሰብ የሚጠበቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አገሪቱ የገባችበት ቀውስ ማህበራዊ ውንም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ሂደቱን የሚያስተጓጉል ነው፤ ለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– በመጀመሪያ ለማለት የምፈልገው ጦርነት መጥፎ ነገር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ የእርስ በእርስ ጦርነት እጅግ የከፋ ነው። ኢትዮጵያ ከሌላ አገር ጦርነት ብታደርግ የሚጠፋው የሌላ አገር ንብረት ነው። የሚጎዳው የሌላ አገር ህዝብ ነው። በእርግጥ ህዝብ እንደ ህዝብ መጎዳት የለበትም። እርስ በእርስ በሚደረገው ጦርነት ውስጥ የሚጎዳው የራስ ነገር ነው።
በትግራይ እየሞቱ ያሉ ወጣቶች ነገ ኢትዮጵያ በሚገጥማት ፈተና ከጎኗ ሊቆሙላት የሚችሉ ናቸው። አንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ኢትዮጵያዊ መግደል የግዴታ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። አንዱ ወገን አጥፊ ሆኖ ከተገኘ አብዛኛውን ህዝብ የሚጎዳ ነገር ፈጽሞ ከተገኘ በፍርድም ይገደላል። በጦርነትም ጉዳዩ ይፈጸማል።ነገር ግን በሁለቱም በኩል ያለው ያው ኢትዮጵያ ነው።ተፈርዶበትም ሆነ በጦርነት ቢሞት እየሞተ ያለው ኢትዮጵያዊ ነው።በመጨረሻም የምትጎዳው ኢትዮጵያ ራሷ ትሆናለች።
ጦርነት እስካለ ድረስ ልማት ሊኖር አይችልም። እድገትም አይታሰብም። ጦርነት አውዳሚ ነው። በመሆኑም ያለው አማራጭ ጦርነቱን ማቆም የሚቻለው እንዴት ነው የሚል ነው። ምክንያቱም ችግሩ አንድና አንድ ነው። እንደሚታወቀው በአገሪቱ ውስጥ የዋጋ ግሽበት አለ። የዋጋ ግሽበቱ የመጣበት ምክንያት ግልጽ ነው። ምክንያቱም እህል ወደጦር ሜዳ መሄድ አለበት። በርካታ ህዝብ በጦር ሜዳ ተሰልፏል።ያ ህዝብ ደግሞ ግማሹ አምራችም ሊሆን የሚችል ነው። ከማምረት ወደሌላ ስራ ተሰማርቷል። ስለዚህ መመገብ የግዴታ ነው። አገሪቱን ለማዳን የተሰለፈ ኃይል እንደመሆኑ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ስለዚህ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የዋጋ ግሽበቱ የግድ ይመጣል። ጦርነት ውስጥ እያለን እነዚህንና መሰል ጉዳዮች አይኖሩም ብሎ ማሰብ አይቻልም። በጦርነት ውስጥ በሚደረገው ውጊያ ከሚሞተው ሌላ በተያዥነት በረሃብም ሆነ በበሽታ ሰዎች የሚያልቁበት ሁኔታ አለ።
ይህን ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል በሚባልበት ጊዜ የመጀመሪያው ለጦርነቱ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ጉዳይ ላይ መወያየት ነው። ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ማንኛውም ጦርነት በግጭት ብቻ ሊያልቅ አይችልም። መጨረሻ ላይ ሰው ነንና ከሌላው እንስሳ የሚለየን ነገር አለ።እሱም መነጋገር ነው።ያሉትን ችግሮች በንግግር ለመፍታት መሞከር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ቀደም ሲል በንግግርና በውይይት ለመፍታት ተነሳሽነቱ ባላቸው አካላትም ሆነ በመንግስት ብዙ ርቀት በመሄድ ብዙ ተሞክሯል፤ እሱ ሙከራ ሁሉ ታልፎ እዚህ ተደርሷል።በንግግር የሚፈታ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ስለምንድን ነው መፍትሄ ማግኘት ያልተቻለው? ከንግግርስ የዘለለ መፍትሄ ከአሁን በኋላ ይኖራል ወይ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- እኔ አንድ ያልተፈታ ነገርን በጦርነት ብቻ ይፈታል ብዬ ላስብ አልችልም።ስለዚህ በጦርነት ብቻ አያልቅም ብለን ካሰብን ሌላ መንገድ ምንድን ነው የሚለውን ማጤን ተገቢ ነው።ሌላው መንገድ መወያየት፤ መነጋገር ነው።ሰው ደግሞ የችግሮቹን ጥልቀትና የጥፋቶቹ ክብደት እያየለ መሄዱን በሚያይበት ጊዜ ይህ አካሄድ ትክክል አይደለም ብሎ ሊያስብ ይችላል።
በአንድ ወቅት የያዝኩት መንገድ ትክክል ነው ብሎ የሚያምን አካል ሁልጊዜ የያዘው መንገድ ትክክል ነው ብሎ ሊደመድም አይችልም። ሐሳቡን ይለውጣል።ነገሮችን ከግራም ከቀኝም በኩል ማየት ይጀምራል።የሰው አዕምሮ ደግሞ በተለያየ ጊዜ ያጋጠመውን ነገር በተለያየ መንገድ መርምሮ የተለያየ ውሳኔ መስጠት የሚችል ነው።በመሆኑም ሰው እንደመሆናችን መጠን እንደእሱ አይነት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።
በጥቅሉ ለሰላም የሚደረገው ጥረት ምንም ጊዜ መቆም የለበትም ሊያስብል የሚያስችለን አንዱ መንገድ ይኸው መወያየትና መነጋገር የሚለው ነው።ሰላምን ለማምጣት ሰዎች መወያየትና መነጋገር አለባቸው እንጂ ሌላ መንገድ የለም። የሰላም መንገዱ ይኸው ነው።ለዚህም ነው መልሼ መላልሼ ውይይትና ንግግር እያልኩ የምመልስልሽ።ሰላምን ለማምጣት ከውይይት ውጭ ብዙ ነገር አለ ብዬ አላስብም።
አዲስ ዘመን፡- ከምንጊዜውም በላይ በአሁኑ ውቅት ምዕራባውያኑም ሆኑ አሜሪካውያን በኢትዮጵያ ላይ የተቻላቸውን ያህል ተጽዕኖ እየፈጠሩ ነው፤ ይህን ማድረጋቸው ምንን ለማትረፍ ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– ኃያላን አገሮች ኃይልነታ ቸውን ለማሳየት የሚያደርጉት ነገር አለ። እሱም ምንድን ነው ቢባልም እነሱ የሚፈልጉትና የሚሹት ነገር ተፈጽሞ እንዲገኝ ለማድረግ ነው። እነሱ የሚፈልጉት ነገር በኢትዮጵያ ላይ የተለያየ ሊሆን ይችላል።አንደኛው ምናልባት ኢትዮጵያ የምንናገረውን ወይም የምንነግራትን ነገር እንዴት እምቢ ትላለች፤ ይህን እምቢታዋን ዝም ብለን የምናይ ከሆነ ሌሎቹም ያንን ፈለግ ሊከተሉ ይችላሉና የእኛ የበላይነት እየቀነሰና እየዘቀጠ ሊሄድ ይችላል ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። የኃያላን ስነ ልቦና ደግሞ ይህን የኢትዮጵያ አይነት አካሄድ ለመቀበል ይከብደዋል።
ሌላው ደግሞ ከሚናገሩት ውስጥ የሚያገኙት ጥቅም አለ፤ ለምሳሌ አሁን በኢትዮጵያ ላይ ጫና እየፈጠሩያሉ ካሉ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የህዳሴ ግድብ ሁኔታ ነው።በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ እነሱ በሚናገሩት መንገድ ብትሄድላቸው እነሱ ደግሞ ከአረቡ አካባቢ የሚያገኙት ጥቅም አለ።ስለዚህ ኢትዮጵያ እኔ የአገሬንና የህዝቤን ጥቅም ለማንም አሳልፌ የምሰጥበት ሁኔታ የለም።በመሆኑም የመጣው ቢመጣም እጋፈጣለሁ እንጂ ጥቅም ማስነካት አልችልም በምትልበት ጊዜ እነሱ ደግሞ በወዲያ በኩል ለማግኘት ያሰቡትንና የፈለጉትን ነገር ሳያገኙት ይቀራሉ።ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ጫናውን ይቀጥላሉ ማለት ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እያደገች ያለች አገር ናት።በታሪኳም ቢሆን የአይበገሬነት መንፈስ ከመላበሷም በተጨማሪ የሚጫኑባትን ነገር አልቀበልም የማለት እንጂ እንደሌላው አንገቷን አሳልፋ የመስጠት ሁኔታ አይስተዋልባትም፤ አሁንም እያካሄደች ያለችው ይህንኑነው።ይህ አካሄዷ ደግሞ ለሌሎቹም የአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው።ኢትዮጵያ ደግሞ ሁልጊዜም ምሳሌ የምትሆን አገር ናት፤ ለዚህ ማሳያ ደግሞ አድዋን መጥቀስ ይቻላል።ይህ በመሆኑ ኢትዮጵያ አሁንም ምሳሌ ሆናእንዳትቀጥል ማድረግ አለብን ያስብላል፤ በኢትዮጵያ ላይ ጫናው የበረታውም ከዚህ ከዚህ አኳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ትንሽ አገር ብትሆን የዚህን ያህል አይረባረቡባትም ነበር፤ ንቀውም ያልፉ ነበር።ኢትዮጵያ ግን 100 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ነች።ይህ ህዝብ እንዲህ አይነት አቋም ይዞ በኢኮኖሚው ደግሞ ካደገና ከበለጸገ ትልቅ አገር በሚሆንበት ጊዜ ጡንቻው እየፈረጠመ ይሄዳል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ እምቢተኝነቱም በዚያ ልክ እየበረታ ይሄዳልና እሱ እንዳይሆን ተጽዕኖ መፍጠር እና መንገዶቹን ሁሉ መዝጋት ግድ ይለናል ብለው አስበዋል።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ ኢትዮጵያን በተመለከተ በአሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ውስጥም በሌላም ቆይታ አድርገዋልና በወቅቱ አሜሪካውያን ኢትዮጵያን በተመለከተ ያላቸውን ግምት እንዴትይገልጹታል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– እኔ የቆየሁት በተለያየ ጊዜ ነው።በተለያየ ደረጃም ነው።ሁል ጊዜ ከፍተኛ ጥላቻ አለ ብዬ ለመናገር አልደፍርም፤ በተመሳሳይ ደግሞ በጣም ቅርበትና ፍቅር አለ ብዬ ለመግለጽም አልችልም። አንዳንድ ጊዜ አብረን በትብብር መስራት የሚያስችለንን ነገር በምንፈጽምበት ጊዜ በመካከላችን ጥሩ ግንኙነት ይፈጠራል። መቀራረብም ይኖራል። ለምሳሌ ሽብርተኞችን አብረን በምንዋጋበት ጊዜ፤ በአካባቢው ሰላም ለማስፈንበምንጥረበት ጊዜ የጋራ ስራ ስለሆነ እንከባበራለን፤ እንቀራረባለን፤ እንረዳዳለንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእኛ ጥቅም ያልሆነ የሌላ አገር ጥቅም ወይም የእነሱ ቀጥታ ጥቅም የሆነ እኔ ባለሁበት በተባበሩት መንግስታት ይህን ውሳኔ ደግፋችሁ ከእኛ ጎን ቁሙ በሚሉበት ጊዜ ያ ውሳኔ ለእኛ ጉዳት የሚያስከትል ሊሆን ይችላል።ለእኛ ጥቅም የማይሰጥ ሊሆን ይችላል።
የእኛን የፖለቲካ መርህ የማያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል። በዚያን ጊዜ እኛ አምቢ እንላለን። በዚያን ጊዜ በእነሱ በኩል የማኩረፍ ሁኔታ አለ፤ ጉዳዩ እንደየሁኔታዎቹ ነው የሚለያየው።ከኢትዮጵያ ምንድን ነው የሚፈልጉትሲባል ምናልባት ቀደም ባሉ ጊዜያት ደካማ በነበርንበት ጊዜ ሁሉንም ነገር እሽ የማለቱ ሁኔታ ነበር። በተለይ በንጉስ አጼ ኃይለስላሴ ዘመን፤ ማድረግ ያልነበረብንን አድርገናል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከእነርሱ ጋር ሆነን ለእነሱ ጠቃሚ በሆኑ ውሳኔዎች አብረናል።እሱ እሱ ጉዳት አስከትሎብናል። ለምሳሌ ግብጽ ሲውዝ ካናሉን ናሽናላይዝድ ባደረገችበት ጊዜ የምዕራብ አገሮች ተሰብስበው ግብጽን ለማውገዝ በተሰበሰቡ ጊዜ በዛ መድረክ ከምዕራባውያኑ ውጪ የተገኘችው ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች፡፡
ይህ ነገር ግብጾች በእኛ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ቂም እንዲይዙብን አድርጓል። ይህ አይነቱ አካሄዳችን በአረቡም ዓለም በጥላቻ እንድንታይ አድርጎናል።ምዕራባውያኑ ከእነሱ ጋር ስንተባበር ችግር እንደሚያመጣብን ያውቃሉ።ነገር ግን ጉዳያቸው አይደለም።ዋናው ነገር ጥቅማቸው እንዳይጎዳ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ በኢህአዴግ ዘመን አይሆንም ብለንያለፍንበት ሁኔታ ደግሞ ነበር።ለምሳሌ እኛ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይ.ሲ.ሲ)አባል አይደለንም። አሜሪካኖችም አባል አይደሉም።እኛን አባል ሁኑ በሚል በጣም ይገፋፉን ነበር።እናንት አሜሪካኖችስ ፈርማችኋል ወይ፤ ብዬ ስጠይቃቸው እኛ አልፈረምንም አሉኝ፤ ምክንያታቸውን ሲገልጹም የእኛ ወታደሮች በተለያዩ አገሮች ሄደው ስለሚዋጉ በሌላ አገር ዳኛ እንዲፈረድብን ኮንግንሱ ስለማይቀበለውና ስለሚቆጣ ይህን ለማድረግ አንችልም ነው ያሉት።
እኔም ቀበል አድርጌ ኢትዮጵያስ የዚያን አይነት ችግር ቢያጋጥማትስ ብዬ ጠየኳቸው። እንደሱ አይነት ችግር እንደማያጋጥማት መለሱልኝ። እኔም ጉዳዩን በማጤን እነሱ አባል ካልሆኑ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ጥቅም ምንድን ነው የሚለውን አስተውዬ ጉዳዩን ለአገሬ መንግስት አሳውቄ ነበር። በወቅቱም የኢትዮጵያ መንግስት አልፈርምም ነው ያለው፤ እስካሁንም አልፈረመም፡፡
የእኛ ጉዳይ ችግር የሆነባቸው አንድ ትልቅ ጉዳይ አለ። እኛ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ነን።በታሪኩ ደግሞ እሺ ብሎ እጁን የማይሰጥ ህዝብ ነው።ይህ ህዝብ ተዋጊ ህዝብ ነው። አፍሪካውያኑ በምሳሌነት የሚከተሉት ህዝብ ነው።
ይህን ዝም ብሎ ማየትና በፈለገበት መንገድ እንዲሄድ ማድረግ እንዲሁም በኢኮኖሚው እንዲዳብር ማድረግ ከዚህም አልፎ እኛ ከማንፈልጋቸው መንግስታት ጋር አብረው እንዲገኝ ማድረግ ለእኛ አደገኛ ነው በሚል ነው ይህን ሁሉ ጫና የሚያሳድሩት። ይህን ማድረግ በእነሱ በኩል ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም እንደማለት ነውየሚከታተሉን።
በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ችግርም ሆነ የውጭ ምንዛሬው ለኢትዮጵያ ጭንቅ እንደሆነ በማወቃቸው ያንንገመድ ጎተት ያደርጋሉ።ነገ ግን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን አሳድጋ ከውጭ ምንዛሬ ችግር ብትወጣ ግን የሚጎተትገመድ አይኖርም።ነገ ኢትዮጵያ ዱቄትና ስንዴ የማትፈልግ ብትሆንስ አሁንም የሚጎተት ገመድ የለም።ስለዚህ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለማስገባት ገመዶቹ እንዲኖሩ ማድረግ ነውና አገራችን እንድትለማ አይፈልጉም። ገመዶቹሲኖሩ ነው ኢትዮጵያን ማዳከም የሚቻለው። ስለሆነም የሚጎተት ገመድ እንዳይኖር ማድረግ የግድ ይለናል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው አቅጣጫ ትክክል ነው ብለው ያስባሉ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– እኔ ትክክል ነው ብዬአስባለሁ። በመጀመሪያ አካባቢ ፍርሃት ብጤ አድሮብኝ ነበር። ፍርሃቴም የነበረው ምናልባት ወደንጉሱ ጊዜ ወደነበረው ስርዓት እንመለስ ይሆን እንዴ በሚልነው።እሱ ግን አልሆነም፤ ሁኔታዎች በተሻሻለ ሁኔታ በመጓዝ ላይ ናቸው ብዬ አስባለሁ። ዝም ብለን በጭፍን ወዳልተገባ ነገር ሳንገባ፤ እንዲሁም ጥቅማችንን አሳልፈን ሳንሰጥ እያደረግን ያለነው ሁኔታ መልካም የሚባል ነው። በአንድ ወቅት የአሜሪካንን ባንዲራ እናቃጥላለን ሲባል ነበር ይህ ግን ፍጹም ስህተት ነበር፤ መሄድ የሚገባን በጥበብ ነው፤ እነሱ ቪዛ ስለከለከሉን እኛ ወደማይሆን ነገር መግባቱ አግባብ አይደለም። ያልተገባ ነገር ብንፈጽም የምንጎዳው እኛው ነን። ምክንያቱም ድሃ አገር ስለሆንን።
አዲስ ዘመን፡– በብዙ ጫና እና ፈተና ውስጥ አልፋ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ መሙላቷ ይታወቃል፤ ይህ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ትርጉሙ ምንድን ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- በጣም ትልቅ ትርጉም አለው።ምክንያቱም የአባይን ጉዳይ በተመለከተ ውስጥ የነበርን ሰዎች ጉዳዩን እናውቃለን፤ የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት በአደባባይ ይሉ የነበረው ‹‹ኢትዮጵያውያን ካለእኛ ፈቃድ ውሃውን በጭልፋ ይንኩና አዲስ አበባን አመድ እናደርጋታለን›› ነው።እኛ በወቅቱ እናደርግ የነበረው መግለጫ ማውጣት ብቻ ነው። ምክንያቱም በወቅቱ ወኔው እንጂ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም አልነበረንም። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያደገው ትናንት ነው።በአገር ደረጃ ለመጠንከር እየሞክርን ያለነው በቅርብ ጊዜ ነው፤ ከዛ በፊት ኢኮኖሚው ዝቅተኛ ነው። በወቅቱ ከ163 አገሮች መካከል እኛ 160ኛ ነበርን። በአሁን ወቅት ከ190 አገሮች መካከል 30ኛ ላይ እንገኛለን። ይህቺ ጦርነት ባትኖር ለውጡ በጥሩ ሁኔታ ነበር የተጀመረው። በአሁኑ ወቅት የህዳሴ ግድብ መሞላቱም አንዱ የአቅም ማሳያ ጉዳይ ነው ማለት ያስደፍራል።ድሮ እኮ ኢትዮጵያ ሲባል ተዋቸው፤ እርሷቸው እንባል ነበር።አሁን ግን እንደዛ ልንባል አንችልም። በአሁኑ ወቅት ከየአቅጣጫ የሚያደርጉብን ርብርቦሽ ትልቅና ጠንካራ ስለሆንን ነው።የበለጠ ደግሞ እንዳንሄድ ነው።እንደወትሮው ሊንቁን ስለማይችሉ ነው። አጀንዳ የሆንነው ጠንካራ በመሆናችንና ጠንክረን ስለተገኘን እንዲሁም እምቢ ብለን ስለተጓዝን ነው። ይህ የህዳሴ ግድብ ደግሞ አንዱ የጥንካሬያችን ምልክት ነው። ይቅርታ ይደረግልኝና ጂቡቲ አንድ ነገር ብታደርግ ኢትዮጵያ ላይ የተረባረቡትን ያህል እሷ ላይ አይረባረቡም። በመሆኑም ግድባችን የኢትዮጵያን የአቅጣጫ መስመር ለዋጭ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ በኋላ ይህንን ጦርነት በሰላም ከጨረስንና እንደገና ሳንፍረከረክ ከቀጠልን እኛን ሊያስቆመን የሚችል ምንም ነገር አይኖርም።ዝም ተብለንም የምንታይ አገር አንሆንም። አንድ ነገር ከማሰባቸውና ከመወሰናቸው በፊት ስለኢትዮጵያ ቀድመው ማሰብን ይጠይቃቸዋልማለት ነው። ምንም ነገር ከመወሰናቸው በፊት ኢትዮጵያስ ምን ትላለች በሚል ከግምት ውስጥ የምንገባ አገር ነው የምንሆነው።
አዲስ ዘመን፡– ማለት የሚፈልጉት ጉዳይ ካልዎ እድሉን ልስጥዎ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- ማከል የምፈልገው ነገር በኢኮኖሚው መስክ አቅማችንን ለማሳደግና ነጻ ለመሆን እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ በኢኮኖሚው ዙሪያ ያንን የሚያስደርግ ስራ እየሰራን አይደለንም። ሁል ጊዜ ከውጭ ገዝተን ነው በመጠቀም ላይ ያለነው። ሰሞኑን የአሜሪንን ፕሬዚዳንትን ንግግር ሳደምጥ ነበር፤ ጆ.ባይደን ብዙ ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን ተናግረው መጨረሻ ላይ ሐሳባቸውን በሁለት ቃላት ነው ለመቋጨት የሞከሩት፤ ይኸውም ‹‹የአሜሪካንን ግዙ›› በሚል፤ ታላቅ አገር ነኝ የምትለዋ አሜሪካ ከውጭ አገራት አንግዛ ነበር ያለችው። ይህ ማለት የአሜሪካንን ሸቀጥ በመግዛት የአሜሪካን ኢኮኖሚ እናሳደግ ነው።ይህ እየሆነ ባለበት እኛ ግን የውሃ ማማ የምንባለው አገር ውሃ ጭምር ከውጭ ለማምጣት እየዳዳን ነው።ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ቀረርቶና ፉከራ እንጂ የመንግስትን ሐሳብ ለማጠናከር ምንም አይነት እንቅስቃሴ እያደረግን አይደለም። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአርሶ አደሩ ትራክተርአምጥተን እንዲያርስ እናደርጋለን ብለዋል፤ ትራክተር እኮ የሚመጣው በዶላር ነው። ከባለዶላሮቹ ሰዎች ጋር ደግሞ በደንብ የማንግባባ ከሆንን የዶላሩን ወጪ መቀነስ አለብን። እኛ የሚያስፈልገን ትራክተር ብቻ አይደለም፤ ለጊዜውምቢሆን ማረሻችንን ማዘመንና በእሱ መጠቀም ይቻላል። ይህንን ለማድረግ የሚያስችለን የሰው አቅም አለን። በየዩኒቨርስቲው ብዙ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች አሉን። በጣም በርካታ የተማረ ዜጋ አለ። ስለዚህ ኋላቀር የሆነውን ግብርናችን መለወጥ አለበት። በንጉሱ ጊዜ ካዱ በሚባል በአርሲ ስራ እሰራ ነበር። በወቅቱ አንዲት ላም የምትሰጠውን አንድ ሊትር ወተት ወደ አስር ሊትር ወተት ከፍ አድርገን ለአርሶ አደሩ እናዳርስ ነበር። የእነሱን አንድ ሊትር የምትሰጠዋን ላም ወስደን አስር ሊትር የምትሰጠዋን በምትኩ እንሰጣቸው ነበር።
ይህ ኢኮኖሚን እንደማሻሻልነው።አሁን ለምን ይህ አይነት ስራ አይሰራም። ለምንስ በየቦታው አይስፋፋም ነው የምለው። ቻይናውያኑ፣በዚህ ሁኔታ ነው አገራቸውን በማሳደግና ከአሜሪካ ጋር ተፎካካሪ በመሆን ላይ ያሉት። ስለሆነም በመጀመሪያ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ራሳችንን በአግባቡ ለመቻል መጣር ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡– የሁልጊዜ ተባባሪያችን አምባሳደር ጥሩነህ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013