1950ዎቹ ጀምሮ በአዲስ አበባ የኅብረት ሥራ ማህበራት መቋቋም እንደጀመሩ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማህበራት እና የዕደ ጥበብ ኅብረት ሥራ ማህበራት በከተማዋ ውስጥ እያበቡ መጥተዋል:: ዓላማውም በግል መወጣት ያልተቻለውን ችግር በኅብረት እና በአንድነት መወጣት የሚቻልበት፣ የሚወስኑበት፣ የሚቋቁሙበት የጋራ ተቋም ነው:: ይህም አደረጃጀት አመሰራረቱ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ነው::
ከእነዚህ ኅብረት ሥራ ማህበራት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የኅብረት ሥራ ሸማቾች አንዱ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በቢሮ ደረጃ፣ በሥራ ሂደት እና በመሣሠሉት ተደራጅቶ ነበር:: በመቀጠል ደግሞ በደንብ ቁጥር 85/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባወጣው ደንብ መሠረት በኤጀንሲ ደረጃ ተቋቋመ:: መዋቅሩን በወረዳ እና ክፍለከተማ በጽሕፈት ቤት ደረጃ በከተማ ደግሞ በኤጀንሲ ደረጃ አዋቅሯል:: በዛሬ ዕትም የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሣይ አረጋ እንግዳችን ናቸው::
አዲስ ዘመን፡– የኅብረት ሥራ መመስረት ዓላማ ምን ነበር?
አቶ ሲሣይ፡– ዓላማው በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ታች ድረስ ያሉት 9000 ኅብረት ሥራ ማህበራት አሉ:: እነዚህን የኅብረት ስራ ማህበራት በመሰረታዊነት እንዲደራጁ ግንዛቤ መፍጠር፣ ግንዛቤ ከተፈጠረ በኋላ ማደራጀት፣ ግንዛቤ ከተፈጠረ በኋላ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠት እና ከስልጠና በኋላ ደግሞ በተቻለ መጠን የኦዲት፣ ኢንስፔክሽን አገልግሎት መስጠት፣ የገበያ ትስስር ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡና እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው:: ከዚህ ባለፈ ደግሞ የብቃት ምዘና ውስጥ እንዲገቡ ማድረግና የሕግ አገልግሎት ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል:: በዚህ ደረጃ እስከ ታችኛው መዋቅር እየሠራ ይገኛል::
አዲስ ዘመን፡– ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት ምን እየሠራ ነው?
አቶ ሲሣይ፡– በአሁኑ ወቅት በዋናነት ከሚሠራቸው ነገሮች መካከል የሸማቾች ኅብረት ስራ ማህበራትን እየደገፈ ነው:: አሁን በከተማችን 148 ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት አሉ:: በ10 የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበር ዩኒየኖች ይመራሉ:: ዩኒየኖች ማለት ደግሞ መሰረታዊ ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት ተሰብስበው የሚፈጥሩት ኅብረት ነው:: እነዚህ አስር ዩኒየኖች በዋናነት አተኩረው እየሰሩ ያሉት በህብረተሰቡ አላስፈላጊ የኑሮ ጫና እየበረታ ስለመጣ ገበያው መቆጣጠር ሳይሆን ጫናውን ለማርገብ እየሰሩ ነው:: በዚህም አማራጭ ገበያ መፍጠር ላይ በሰፊ እየሰሩ ነው::
አዲስ ዘመን፡– የገበያው ጫና የሚያረግቡት ምን ያህል የገበያ ድርሻ ቢኖራቸው ነው?
አቶ ሲሣይ፡– በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ ካለው ግብይት ውስጥ 10 ከመቶ ያልበለጠ ድርሻ እንዳላቸው ነው መረጃዎች የሚያሳዩት:: ከክልል አምራች ነጋዴዎች፣ የፋብሪካ ውጤቶች፣ የግብርና ውጤቶች፣ ሥጋ እና የሥጋ ውጤቶች፣ የምግብ ሰብሎች ከክልል አምራች ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ይገባሉ:: ከእነዚህ ውስጥ ኅብረት ስራ ድርሻቸው 10 ከመቶ አይበልጥም:: እንዲህም ሆኖ ሚናው ቀላል አይደለም:: በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ለሚገኝ የከተማው ነዋሪ በጣም እየደገፈ ነው:: በሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት ምርት መኖሩ ሲታወቅ የንግዱ ማህበረሰብም ዋጋ ለማስተካከል የሚገደድበት ሁኔታም አለ:: አላስፈላጊ የዋጋ ጫና እንዳይኖር እያደረገ ነው::
በድጎማ የሚገኙ ምርቶች አሉ:: መንግስት ከፍተኛ ድጎማ አሳርፎባቸው የሚያስገባቸው ምርቶች አሉ:: ስኳር፣ የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት እና የመሳሰሉት ወደ ከተማ የሚገቡት በድጎማ ነው:: እነዚህን ምርቶች እንዲያሰራጩ ፈቃድ ያገኙት የኅብረት ሥራ ማህበራት ናቸው:: ምክንያቱም ይህ ከፍተኛ የሆነ ድጎማ የተደረገበት ሃብት በትክክል ለነዋሪዎች በተፈለገው ሁኔታ እንዲደርስ የታመነባቸው የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ነው:: እስከ ቀጣና ድረስ ባሉት ሱቆች ተደራሽ ስለሆነም ተመራጭ ነው:: ቢያንስ በየቀጠናው አንድ ሱቅ አለው:: በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ ከ640 ያላነሱ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት አገልግሎት መስጫ ሱቆች፣ ከ205 በላይ የሕዝብ መዝናኛ ማዕከላት፣ 225 ስጋ ቤቶች እንዲሁም 125 የእህል ወፍጮ አገልግሎት መስጫ ተቋማት አሉ::
ከዚህም አልፎ መዕዋለ ህፃናት፣ ክሊኒኮች፣ መፀዳጃ ቤቶች እና ሻወር ቤቶች አሉት:: በመሆኑም በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መሰረት እነዚህ ድጎማ የተደረገባቸው ምርቶች ወደ ህብረተሰቡ የሚደርሱት በሸማች ኅብረት ሥራ አማካኝነት ነው:: በተለይም ከኮሮና ወረርሽኝ ወዲህ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል:: የአገልግሎት ስርዓት በማስተካከል፣ የሥራ ሰዓታቸውን በመጨመር ብዙ ሥራ ማከናወን ችለዋል:: እንደዚህም ሆኖ ግን ችግሮች እንዳሉ ይታመናል:: እዚህ ላይ ግን ወጣ ገባ የሚሉ ችግሮች ማስተካከል ይገባል::
አዲስ ዘመን፡– የኅብረት ሥራ ማህበራት ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ሲሣይ፡– በዋናነት በጥናት የተለዩት ሦስት ችግሮች ናቸው:: አንደኛው የመጋዘን ችግር ነው:: ሁለተኛ የፋይናንስ ችግር ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ከአምራች ዩኒየኖች በቂ ምርት የማግኘት ችግር መሆናቸው በጥናት የተለዩ ናቸው:: የመጣንባቸው ዓመታትም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው:: እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ጥረት ተጀምሯል::
የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ከክልል አምራች ዩኒየኖች ጋር የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር ተደጋጋሚ መድረክ በመፍጠር ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ነው:: አሁንም በዚህ ላይ ችግሮች ቢኖሩም ትልቅ ተስፋ የሚሰጡ ለውጦች አሉ:: የመጋዘን ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታት በየክፍለ ከተማው ያሉና የተዘጉ አዳራሾች እና ሼዶች ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው:: ጎን ለጎን ደግሞ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ደግሞ መጋዘን እንዲገነቡ የከተማ አስተዳደሩ ፈቃደኛ ሆኖ የቦታ ርክክብ እያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ያለው ዩኒየን የቦታ ርክክብ ያደረገ ሲሆን ሌሎችም በሂደት ይገቡበታል ብለን እናምናለን::
የፋይናንስ ችግራቸውን ለማቃለል ፍላጎታቸው ተለይቶና ይህም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ብሎም ለጊዜው ምን ያክል ድጋፍ ቢያገኙ አቅማቸው ይጎለብታል የሚለው ጉዳይ በጥናት ተለይቷል:: ለዚህም 1ነጥብ2 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋቸዋል:: በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶት በመጀመሪያ ዙር 500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ወስኖ ወደ ተግባር ገብቷል:: ለአስሩም ዩኒየኖች ለእያንዳንዳቸው 30 ሚሊዮን ብር ያለወለድ ሦስት ከመቶ ባልበለጠ ኮሚሽን ተሰጥቷል:: በሁለተኛው ዙር ደግሞ 200 ሚሊዮን ብር የተለቀቀ ሲሆን እንደ አፈፃፀማቸው ድልድል እየተደረገ ነው:: በመሆኑም የፋይናንስ ችግራቸውን በዚህ መንገድ ለማቃለል ወደ ሥራ ተገብቷል::
አዲስ ዘመን፡– ዩኒየኖቹ የፋይናንስ ድጋፍ ካገኙ በኋላ ለውጥ ማሳየት ችለዋል?
አቶ ሲሣይ፡– ይህ የፋይናንስ ድጋፍ ከተደረገ በኋላ በጣም በከፍተኛ ደረጃ በሕብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት አግኝተዋል:: መታመን የቻሉበትና አቅም አላቸው ተብሎ ምርት መለቀቅ ‹‹እንልካለን ልቀቁልን ብለው ጥያቄ በሚያቀርቡበት ሰዓት አምራች ዩኒየኖችና እና ፋብሪካዎችም ምርቶችን በፍጥነት ማግኘት ችለዋል:: ህብረተሰቡም ያልተቋረጠ አገልግሎት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል:: በዚህም በ10 ክፍለ ከተሞች ያሉ ዩኒየኖች ክረምቱን የሚያሻግር ጤፍ አቅርቦት ማከማቸት ችለዋል፤ የከተማ አስተዳደሩ ባደረገው ጥናት:: በወርሐ የካቲት የጤፍ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ባሻቀበበት ወቅትም 68ሺ ኩንታል ባስገቡበት ቅጽበት የጤፍ ገበያ ባለበት ማቆየት ተችሏል:: በአሁኑ ወቅትም እስከ መስከረም ድረስ የሚያሻግር ከ43ሺ ኩንታል ጤፍ በመጋዘናቸው አላቸው:: በየወረዳው ደግሞ ከ50 እስከ 100 ኩንታል አለ::
አዲስ ዘመን፡– ይህ የጤፍ ክምችት እንዴት በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠር የአዲስ አበባ ነዋሪ ክረምት ያሻግራል ብለው ይናገራሉ?
አቶ ሲሳይ፡– መጀመሪያ ስናገር ሰምተህ ከሆነ እነዚህ የኅብረት ሥራ ማህበራት ለመላው የአዲስ አበባ ከተማ ጤፍ ያቀርባሉ ተብሎ የተቋቋሙ አይደሉም:: ቅድሚያ ለአባሎቻቸው ነው:: 430ሺ አባላት አሉት:: ሌላው ነዋሪ መጥቶ ጤፍ ቢጠይቅ አይከለክሉትም:: ግን ብክነት እንዳይኖር ከ50 ኪሎ ግራም በላይ አይሰጥም:: በመሆኑም ከአባል ውጭ ሁሉንም ዘግተው መስራትም አይችሉም:: አማራጭ ገበያ ለድሃ ታስቦ ነው::
አዲስ ዘመን፡– የጎዳና ተዳዳሪዎችና የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌላቸው፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ ብሎም የሲቪል ሠራተኞች እንዴት መገልገል ይችላሉ?
አቶ ሲሣይ፡– አዎ! አጠቃላይ የመንግስት ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን በግል ድርጅትም ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችልና በ10 ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤቶች ሥር የክፍለ ከተማው አስተዳደር ባመቻቸው ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ጀምረናል:: በሸማች ኅብረት ስራ ማህበራት የሚተዳደሩ ሙሉ አገልግሎት የሚሰጡ ሱቆች ተከፍተዋል:: በከተማዋ 121 ወረዳዎች አሉ:: ባለን መረጃ መሰረት 114 ሱቆች አሉ:: በዚህም መንግስት ሠራተኞች እንዲገለገሉ እየተደረገ ነው:: የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌላቸው ዜጎችም በሚኖሩበት ግቢ አስመስክረው መጠቀም ይችላሉ:: ዜጎች ስለሆኑ ይስተናገዳሉ:: የጎዳና ተዳዳሪዎችም የከተማ አስተዳደሩ የሚሄድበት መንገድ አለ:: ሸማች ኅብረት ስራ ማህበራት በራሳቸው የሚረዷቸው ዜጎችም አሉ::
አዲስ ዘመን፡- ኅብረት ሥራ ማህበራት ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ምን ያክል ሚናቸውን እየተወጡ ነው?
አቶ ሲሣይ፡- ኅብረት ሥራ ማህበራት ወልጅ አልባ ህፃናትን፣ አዛውንቶችን ያግዛሉ:: እቅድ አላቸው:: በአሁኑ ወቅት 1ሺ700 በላይ ህፃናት እና አረጋውያንን በቋሚነት ይረዳሉ:: ለምሳሌ ኮልፌ አጋር፣ ቦሌ ፋና፣ አዲስ ከተማ ደራሽ በመርካቶ፣ ኮልፌ ራዕይ ለአብነት ማንሳት ይቻላል:: በረንዳቸው ላይ አቅም የሌላቸውን ይረዳሉ:: እነርሱ ፈልገውት ብቻ ሳይሆን ፕሮግራሙ የሚለው ራሱ ኅብረት ሥራ ማህበራት ችግራቸውን ከማቃለል ጎን ለጎን ማህበራዊ ተሳትፎ ላይ ሚናቸውን ይወጣሉ ይላል:: ይህ ስለሆነ በእቅዳቸው በዓመቱ መጀመሪያ ላይ በጠቅላላ ጉባዔ ወጪያቸውን ያፀድቃሉ:: በዚህም መሠረት ማህበራዊ ኃላፊነት ይወጣሉ:: ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርገዋል:: ለኮሮና ወረርሽኝ፣ በአፋር ለተከሰተው የጎርፍ አደጋ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ ገዝተዋል:: በአገሪቱ ብዙ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎም አላቸው::
አዲስ ዘመን፡– ኅብረት ሥራ ማህበራት የከተማው 10 ከመቶ የገበያ ድርሻ ብቻ ይዞ አገልግሎቱ ተደራሽ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ሲሣይ፡– ሙሉውን እሸፍናለሁ ብሎ መንቀሳቀስ የለበትም፤ ማሰብም የለበትም:: ሆኖም በቂ ነው እያልን ሳይሆን አሁን ባለንበት ሁኔታ ጥናቱ የሚያሳየው የገበያ ድርሻው 10 ከመቶ የሚበልጥ አይደለም ለማለት ነው:: አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ ናት፤ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እና የሕዝብ ብዛት ያላት ከተማ ናት:: ከዚህ አኳያ ገበያው 10 ከመቶ የዘለለ አይደለም::
ማዕከላዊ ነጥቡን መያዝ ይገባል:: የኅብረት ሥራ ማህበራት በአዋጁ እንደተደነገገው ከሥራ ግብር ነፃ ናቸው:: ይህ ማለት ግብር አይከፍሉም ማለት ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ ግብር እየከፈሉ ንግዱን የሚያንቀሳቅሱ ብዙ ማህበረሰብ አካላት አሉ:: አባሎቻቸውን ማስተናገድ አላቃተቸውም:: የአባሎቻቸው ቁጥር እያደገ በሄደ ቁጥር አቅርቦታቸው ከፍ እያለ ይመጣል:: አቅርቦታቸውም የሚወሰነው በአባሎቻቸው እንቅስቃሴ ነው:: ስለዚህ ይህ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት:: ይህ ያድጋል፤ ግን ጤናማ ሆኖ ማደግ አለበት:: የአባላቶቹን ፍላጎት ጎን ለጎን እያጣጣመ ማደግ አለበት:: ግን የከተማዋን ገበያ ይቆጣጠራል ብሎ ማሰብ አደገኛ ነው::
አዲስ ዘመን፡– የሸማች ማህበረሰብ ዘይት ላይ የሚሠራው ስራ እያስወቀሰው ነው:: እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሲሣይ፡– ፈሳሽ ዘይት የለም:: እኛ አሁን ያለውን የተጋነነ ገበያ አናበረታታም:: ፈሳሽ ዘይት በብዛት የሚገባው ከውጭ ሲሆን ፈቃድ ያገኙ የንግዱ ማህበረሰብ ናቸው:: ይህ ደግሞ ለኅብረት ሥራ ማህበራት በሰፊው እየደረሰ አይደለም:: ፊቤላ፣ ሃማሬሳ እና አገር ውስጥ ከሚመረቱ የፓልም ዘይት አምራቾች ጋር ነው የምንሰራው:: ይህ የሚስተካከለው የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ነው:: በአሁኑ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ላይ የገበያው ሁኔታ እንዳዛባው ተመልክተናል:: አሁንም ይህ በሽታ ካልጠፋ ወይንም መስመር ካልተበጀለት የገበያ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም:: በአሁኑ ወቅትም የዘይት ዋጋ እንዲህ እንዲንር ያደረገው ከዚህ ጫና የተነሳ ነው:: አስመጪዎችም የኮቪድን ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ አስገብተው ነው::
አዲስ ዘመን፡– የኮሮና ቫይረስ ስርጭትና ወረርሽኝ ተፅዕኖ በዘይት ላይ ብቻ ነው የሚስተዋለው?
አቶ ሲሣይ፡– ይህ ችግር በዘይት ላይ ብቻ ሳይሆን በምግብ ሰብሎች ላይም ጭማሪ እንዲመጣ አስገድዷል:: መፍትሄው የአገር ውስጥ ምርት በሰፊው ማምረትና መጠቀም ላይ በጥልቀት መሥራት ነው:: አገር ውስጥ የሚመርቱትም ጥሬ ዕቃ ከውጭ ነው የሚያመጡት:: ጥሬ ዕቃ ከማግኘት አኳያም በሙሉ አቅም እያመረቱ ነው የሚል ግምገማ የለም:: ይህን ለማቃለል መንግስት በድጎማ ማህበረሰቡን እያገዘ ነው:: የዳቦ ዱቄት አሁን አንድ ኪሎ ግራም 40 ብር ደርሷል:: ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ አንድ ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄት 27 ብር ባልበለጠ እንዲያገኙ መንግስት ትልቅ ድጎማ አድርጎ እየሠራ ነው::
አዲስ ዘመን፡–የሕዝብ መዝናኛ ተቋማት ብዛት እንጂ ጥራትና ውበት የላቸውም በተጨማሪም ለጤና ጠንቅ የሆነ አሰራር ይከተላሉ የሚል ወቀሳ እንደሚነሳባቸው ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ያውቀዋል?
አቶ ሲሣይ፡– በከተማዋ ውስጥ 205 የሕዝብ መዝናኛ ተቋማት አሉ:: የባለ አደራ ቦርድ ደንብ ያስተላለፋቸው አሉ:: በ2012 ዓ.ም አጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን አስጠንተናል:: ደረጃቸው ምን ይመስላል የሚለውንም ለማየት ሞክረናል:: አገልግሎት አሰጣጥ የራሱ ሚና አለው:: በጥናቱ የሚሳየው የቦታ ችግር ሳይኖር በጣም ሰፊ ቦታ ይዘው በቂ አገልግሎት የማይሰጡ በርካቶች ናቸው:: ከሚያቀርቧቸው ምርቶች አያያዝ፣ የሠራተኛ ባህሪ፣ ከግቢ ንጽህና እና አገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ብዙ እንደሚቀራቸው አይተናል:: ይህን ማዘመን እንዳለባቸው መተማመን ላይ ተደርሷል:: ለዚህም ፕሮጀክት ቀርጸው አካባቢን የመቀየር ሥራ መስራት አለባቸው:: በአረጀ አሰራርና አያያዝ ከአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት ጋር ይሄዳሉ ተብሎ አይታሰብም:: ይህን ወደ ማስተካከል የገቡ አሉ::
በዋነኛነት ግን ቤቶቹን መቀየር ብቻ ሳይሆን አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኛ አስተሳሰብ ላይ መስራት እንዳለበት ታምኖ የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ:: ይህም በራሳቸው አቅምና በእኛም ድጋፍ እየተከናወነ ነው:: ህብረተሰቡ እዚህ አካባቢ በተመጣጣኝ ዋጋ የተለያዩ ምግብና መጠጦች ይገኛሉ ብሎ ነው የሚያስበው:: በዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ነው:: በመሆኑም እዚህ ቦታ የሚመጣው በሥርዓት መስተናገድ አለበት:: ለዚህም የሠራተኛው አስተሳሰብ፣ አሠራርና ባህሪ መስተካከል አለበት:: በዚህም ወደ ተግባር የገቡም አሉ:: የከተማ አስተዳደሩም ትልቅ እገዛ አድርጓል:: ይዞታቸው ካርታ እንዲወጣባቸውና ማረጋገጫ እያገኙ ነው:: ቀደም ሲል የይዞታ ማረጋገጫም አልነበራቸውም:: ይህ ችግር በአሁኑ ወቅት እየተቃለለ ነው:: የተወሰኑት ወደ ግንባታ እየገቡ ነው:: እነዚህ ተቋማት ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑም ችግሮቹ መስተካከል አለባቸው::
አዲስ ዘመን፡- የሸማች ኅብረት ሥራ ለከተማዋ የሚያስገቧቸውን የግብርና ምርቶችን ከየት ያገኛሉ?
አቶ ሲሣይ፡– በብዛት የግብርና ምርቶች ከአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ካሉ አማራጭ ዩኒየኖች የሚገኙ ናቸው:: 60 ከመቶ ያላነሰ ስንዴ እና ጤፍ ከአማራ ክልል ነው:: ከ38 እስከ 40 ከመቶ የሚሆነው ከኦሮሚያ ክልል ነው:: ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ ከደቡብ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አምራች ዩኒየኖች ያገኛሉ:: እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖችን ደግሞ ከኦሮሚያ፣ አማራ፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ያገኛሉ:: ምርቱ ወጣ ገባ ሊል ይችላል:: ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የጤፍ ምርት የተገኘው ከኦሮሚያ ክልል ነው::
አዲስ ዘመን፡– ከአዲስ አበባ ውጭ ካሉ አምራች ዩኒየኖች ጋር ያለው መስተጋብር ምን ይመስላል?
አቶ ሲሣይ፡– የገበያ ትስስርና የስምምነት መድረኮች በተደጋጋሚ አሉ:: ክልሎች በፕሮግራም ይጠራሉ፤ እኛም እንጠራለን:: በእነዚህ ሥምምነቶች ላይ ቅድሚያ የፍላጎትና አቅርቦት ልውውጥ ይደረጋል:: ምርት ሳይደርስ ወይንም የተዘራው ምርት ማሳ ላይ እያለ ፍላጐታችንን እንገልፃለን የሚያቀርቡትንም ይገልፁናል:: አቅርቦትና ፍላጎት ተጣጥሞ ግብይት ይፈፀማል:: በዚህ ፍጹም ጤናማ የሆነ ገበያ እና ተግባቦት አለ:: መተማመኑም ከፍተኛና ጠንካራ ነው:: በአካል መሄድ ሳያስፈልግ ናሙና ብቻ በማየት ግብይት ይፈፀማል:: ምርት የላከው ዩኒየን በአካውንቱ ገንዘብ ወዲያውኑ ይገባለታል:: በተፈለገው መጠን ምርት የማግኘት ችግር አልፎ አልፎ ይከሰታል እንጂ በግብይት ላይ ጥሩና ጤናማ ተግባቦት አለ:: መሆን ያለበትም መሰል ጠንካራ አሠራር ነው:: ችግር ሲገጥመንም በጋራ ወዲያውኑ እናርማለን:: የፌደራል መንግስት እና ባለሙያዎችም ጋርም በመናበብ የምንሠራው ነው:: በየጊዜው እያደገና እየዘመነ የመጣ የቅብብሎሽ ሥርዓትም ተዘርግቷል::
አዲስ ዘመን፡– አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ስጋት የሚነሱና መልካም አጋጣሚ የሚባሉት ምንድን ናቸው?
አቶ ሲሣይ፡– መልካም አጋጣሚ ብለን የምናነሳቸው ነገሮች የኅብረት ሥራ ማህበራት በማህረሰቡ ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል:: ሁለተኛው የከተማ አስተዳደሩ የሰጠው ትኩረትና በየጊዜው የሚወስናቸው ውሳኔዎች ትልቅ አቅም እየፈጠሩ ነው:: መታገዝ አለባቸው ብሎ ቦታ በመስጠት፣ ገንዘብ በመስጠት ትልቅ ሥራ እየሠራ ነው:: ከዚህ ውጭ የፌደራል እና የከተማ አስተዳደሩም በጋራ ግብረ ኃይል እየገመገሙ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሠሩ ነው:: ለህብረተሰቡ ጥቅም በሚገባ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው::
ፈተናዎች ይሆናሉ ብለን ያሰብናቸው መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮችም አሉ:: ዘላቂ የገበያ ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ ምርት የመከዘን አቅማቸው እንዲያድግ መሰረት ልማት ግንባታዎች ፈታኝ ናቸው:: በቂ ምርት በመኸር ወቅት ቢያገኙም ከተወሰነ ምርት በላይ መያዝ አልቻሉም:: ስለዚህ መጋዘን መገንባት አለባቸው:: ምክንያቱም ህብረተሰቡን ዓመቱን ሙሉ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅብናል:: ይህን እየሄድንበት ነው::
ከዚህ በተጨማሪ የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ እና በአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በጋራ በተጠና ጥናት በአምስት ዋና ዋና የአዲስ አበባ መግቢያና መውጫዎች ላይ ዘላቂ የሆኑ ትልልቅ መጋዘኖች እንዲኖሩ ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጡ የገበያ ማዕከላት መገንባት አለባቸው:: ስለዚህ አምራቹ ያመረተውን ምርት በፈለገው ጊዜ አምጥቶ አስመዝግቦ የሚያስገባበትና መሸጥ በሚፈልግበት ጊዜ የሚሸጥበት የከተማው ማህበረሰብም በፈለጉ ጊዜ መገብየት አለባቸው ተብሎ የገበያ ማዕከላት ግንባታ መከናወን አለበት ተብሎ የቦታ ርክክብ እየተከናወነ ነው:: ክልሎችና የአዲስ አበባ ኅብረት ስራ በጋራ የሚመሯቸው ተቋማት ናቸው:: እነዚህ ሰፋፊ ሲሆኑ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ነው:: በአንድ ጊዜ ላይጠናቀቅ ይችላል:: ይህ በዘላቂነት ታስቦ እየተንቀሳቀስን ነው::
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ እያመሰገንኩ መጨመር የሚፈልጉት ሃሳብ አለ?
አቶ ሲሣይ፡– አመሰግናለሁ:: በአጠቃላይ መልካም አጋጣሚዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ ነው:: ሕብረተሰቡም በአካል እየመጣ በነፃነት አስተያየት እየሰጠ ሲሆን እኛም ለማሻሻል እየሠራን ነው:: ተቋሙ የማደግ ተስፋው እየለመለመ ነው:: የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ከተማ አስተዳደሩ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በከፍተኛ ደረጃ እያገዘ መሆኑን መገንዘብ አለበት:: ይህም የሆነው ለህብረተሰቡ ጥቅም በማሰብ መሆኑን ሊያውቁ ይገባል:: በመሆኑም እነዚህን ተቋማት ማገዝና አባል መሆን ይገባል:: ሕብረተሰቡም የእኔነት ስሜት ሊሰማው ይገባል::
የኅብረት ሥራ ማህበራትም የቁጥጥር ሥርዓታቸው ጤናማ እና እርምጃ አወሳሰዳቸው ሕጋዊ መሆን አለበት:: ተቋሞቻችን መዘመን አለባቸው ብለው በፍጥነት መሥራት አለባቸው:: ባለሙያዎቻችንም ለውጥ የሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፤ እኛም እየሠራንበት ነው:: እነዚህን አቆራኝተንና አጠናክረን ከሄድን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን፤ የኅብረት ሥራ አቅምም እናጎለብታለን የሚል እምነት አለኝ
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2013