
ዩሮ ዞን አስራ ዘጠኝ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትን በዩሮ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ያቀፈ ቀጠና ነው። ቀጠናውም አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ቆጵሮስ፣ ኢስቶኒያ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ አየርላንድ፣ ጣልያን፣ ላቲቪያ፣ ሊቱኒያ፣ ሉክዘምበርግ፣ ማልታ፣ ኔዘርላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ስሎቬኪያ፣ ስሎቬኒያናንና ስፔንን ያካትታል። ቀሪ ሂደቶችን ካጠናቀቀች ዴንማርክም ሌላኛዋ የቀጠናው አባል ሀገር እንደምትሆን ይጠበቃል።
ሌሎች ሀገራትም ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟሉ የዚሁ ቀጠና አባል ሀገራት እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን የቀጠናው አባል ሀገራት አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 12 ነጥብ 712 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚገመት ይነገራል። ከዚህ አኳያ የቀጠናው አባል ሀገራት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩት ተፅእኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነም በተደጋጋሚ ይገለፃል።
የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀሰቀሰበት ወቅት ክፉኛ ኢኮኖሚያቸው ከተመታ ቀጠናዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ዩሮ ዞን በተለይ በሁለተኛው የኮሮና ወረርሽኝ ማእበል ወቅት የቀጠናው አባል ሀገራት ኢኮኖሚ ክፉኛ ተኮማትሮ ቆይቷል። በሶስተኛው የኮሮና ወረርሽኝ ማእበል ወቅትም የቀጠናው ኢኮኖሚው ዳግም እንዳይንሸራተት ስጋት የነበረ ቢሆንም ከተያዘው የፈረንጆቹ ግማሽ ዓመት ሶስት ወራት ወዲህ ኢኮኖሚው በሁለት ከመቶ በማደጉ ከኩምታሬ ተላቋል ሲል ቢ ቢ ሲ ከትናት በስቲያ በድረገጹ ጽፏል።
ዘገባው የቀጠናው ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት አጋማሽ ሶስት ወራት ውስጥ የሁለት ከመቶ እድገት በማስመዝገቡ የቀጠናው ኢኮኖሚ ከኩምታሬ መውጣቱን አስታውቋል። አሃዞች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ደግሞ በሁሉም ሀገራት በብሄራዊ ደረጃ የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት የቀጠናው ኢኮኖሚ ከኩምታሬ እንዲወጣ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልጿል።
አስራ ዘጠኝ ሀገራት የሚገኙበት የዩሮ ቀጠና ቀደም ባሉት ሁለት ሩብ ዓመታት ኢኮኖሚው በሁለት እጥፍ ተኮማትሮ እንደነበርም ዘገባው አስታውሶ፤ ይሁንና ቀጠናው በ 2019 መገባደጃ ላይ ከቀዳሚው ወረርሽኝ ወቅት ከነበረበት ደረጃ በሶስት ከመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቁሟል። በክረምቱ ወቅት ከተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ማእበል በኋላ የቀጠናው ኢኮኖሚ እያገገመ ስለመምጣቱም ጠቅሷል።
በተለይ ደግሞ በወረርሽኙ ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ በተመታባቸው ሁለቱ ሀገራት ጣልያንና ስፔን አሁን ላይ ኢኮኖሚው የሶስት ከመቶ እድገት ማሳየቱንም ዘገባው በአብነት አንስቷል። በተመሳሳይ በኦስትሪያና ፖርቹጋል ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ማገገም መታየቱንና ኢኮኖሚያቸው የአራት ከመቶ እድገት ማሳየቱንም ጠቁሟል። በተለይ በፖርቹጋል የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጿል።
ከዚህ በዘለለ የዩሮ ዞን ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤቶች በሆኑት ጀርመንና ፈረንሳይ በእያንዳንዳቸው የ 1 ነጥብ 5 ከመቶ እና ዜሮ ነጥብ 9 ከመቶ መካከለኛ የኢኮኖሚ እድገት መመዘገቡንም ዘገባው አስታውቋል። የቀጠናው ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ስታትስቲክሳዊ መረጃ የመጀመሪያ ግምት መሆኑንም የጠቀሰው ዘገባው፤ ኢኮኖሚያዊ ማገገሙን በትክክል የሚያሳይ ጥልቅ ትንታኔ የሚፈልግ መሆኑንም ጠቁሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ በፈረንሣይ ፣ ጀርመን እና በተለይ ደግሞ በስፔን ለቤት ውስጥ ፍጆታ በሚውሉ እቃዎች ላይ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ መሆን ለቀጠናው ለኢኮኖሚው ማገገም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ዘገባው አመልክቷል። በፈረንሳይ የሆቴልና ሬስቶራንት ንግድ የ 29 ከመቶ መሻሻል ማሳየቱንም በአብነት ጠቅሷል።
ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ ለንደን በሆነውና ‹‹ካፒታል ኢኮኖሚክስ›› በተሰኘው የኢኮኖሚ ጥናትና ማማከር ማእከል ውስጥ የአውሮፓ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አንድሪው ከኒንገሃም የፖርቹጋል ኢኮኖሚያዊ ማገገም ከስፔን በተሻለ ሁኔታ የቱሪዝም ዘርፉ በወረርሽኙ በአነሰ መልኩ መጎዳቱን የሚያንፀባርቅ መሆኑን መግለፃቸውን ዘገባው አመልክቷል። በቅድመ ወረርሽኝ ወቅት ከነበረው በታች ቢሆንም በሶስተኛው ሩብ ዓመት የቀጠናው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ጠንካራ እንደሚሆንና ከበፊቱ ጋር እንደሚጠጋጋም ባለሙያው መተንበያቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
በአንፃሩ አሜሪካን የነበረባትን የኢኮኖሚ ክፍተት የሞላች ቢሆንም የሀገሪቱ የስራ ቅጥር ሁኔታ አሁንም ዝቅተኛ መሆኑንና የኢኮኖሚው እንቅስቃሴም በቅድመ ወረርሽኝ ወቅት ከነበረው ጋር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑንም ዘገባው በንጽጽር አስቀምጧል።
ሌሎች አዳዲስ የዩሮ ቀጠና አሃዞች እንደሚያሳዩት ከሆነ ደግሞ ስራ አጥ የሆኑ ሰዎች ቁጥር በሰኔ ወር ከ400 ሺ በላይ ቢቀንስም አሁንም ባለፈው አመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የአንድ ሚሊዮን ብልጫ እንዳለውም ዘገባው አያይዞ ገልጿል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2013