ከመደበኛው የቢዝነስ ተቋም ልትለያቸው የሚያዳግቱ የኅብረት ስራ ማህበራት መኖራቸው የሚካድ ሃቅ አይደለም አምራቹ ህብረተሰብ በተናጠል ከሚያካሂደው ግብይትና የግብዓት ግዥ ባለፈ በኅብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ይታመናል ። የኅብረት ስራ ማህበራት በስራቸው የተደራጁ አምራቾችን ከመጥቀም ባለፈ ለሸማቹም ዜጋ ቁርጥ ዋጋ የተተመነለትና ጥራቱን የጠበቀ ምርት በሰፊው በማቅረብ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ።
በመላ አገሪቷ የሚገኙ የኅብረት ስራ ማህበራትን በመምራት ረገድ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው ። እኛም ኤጀንሲው የተቋቋመበትን ዓላማ ከማሳካት አንጻር፣ በስሩ የሚገኙት ማህበራት የዋጋ መናርን ከመከላከል አንጻር የሰሯቸው ስራዎች፣ ማህበራቱን ለማጠናከር ምን ያስፈልጋል በሚሉና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከኤጀንሲው ከፌዴራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡– የፌዴራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ምን አይነት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው?
አቶ ኡስማን፡– ኤጀንሲው እንግዲህ የአርሶአደሩን የግብርና ምርት ለማሳደግ እና በሜካናይዜሽን፣ በኬሚካል እንዲሁም በሌሎች የግብርና ግብአት አቅርቦቶች በተበታተነ መንገድ ከማቅረብ ይልቅ በማዕከላዊነት መምራት ያስፈልጋል በሚል ነው በመጀመሪያ የተቋቋመው።
ተቋሙ በ1996 ዓ.ም ሲቋቋም በተበታተነ መንገድ የሚከናወኑ የኅብረት ስራ ክንውኖችን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ ታምኖበት ነው ። በኋላም ኤጀንሲው እስከ ዞን እና ወረዳ የደረሰ መዋቅር እንዲኖረው ተደርጓል ።
የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ በማህበራቱ መካከልም ሆነ ከውጭ አገራት የልምድ ልውውጦችን በማመቻቸት እንዲሁም የውጭ እና የአገር ውስጥ ግብይት አማራጮችን በማቅረብ ረገድ በየዓመቱ ለውጥ ያመጣ ስራ እያከናወንን ይገኛል ። የአገራችን አርሶና አርብቶ አደር ዜጋ ምርትና ምርታማነቱ እንዲጨምር፣ የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም እንዲችል እያገዝን ነው ።
የፋይናንስ ተደራሽነትን ከማሳደግ ባለፈ በከተማ በመካከለኛ እና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል በተለያዩ ኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ በመሰማራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን እንዲቀርፉ በማስቻል ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል።
ከዚህ ባለፈ የኅብረት ስራ ማህበራትን የሚያግዙ ሕጎች እና ፖሊሲዎች እንዲዘጋጁ በባለሙያ የተደገፈ ስራ እናከናውናለን ። የኅብረት ስራ ማህበራት ያለባቸውን የአመራር እና የክህሎት ደረጃ ለማሻሻል በቴክኖሎጂም ሆነ በሰው ኃይል ስልጠና እና የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ድጋፎችን እየሰጠን ነው ። ይህም የኅብረት ስራ ማህበራትን በማጠናከር ረገድ አይነተኛ ውጤት አምጥቷል ።
አዲስ ዘመን፡– የኅብረት ስራ ኤጀንሲ በሥሩ ምን ያክል አባላትን ይዟል?
አቶ ኡስማን፡– አሁን በደረስንበት ደረጃ 99 ሺህ 500 መሰረታዊ የሕብረት ስራ ማህበራት አሉን ። ከዚህ ባለፈ 385 የሕብረት ስራ ዩኒየኖች እና አምስት ፌዴሬሽኖችንም ይዘናል ። በማህበራቱ ውስጥ ደግሞ 24 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎችም አባል ሆነዋል ።
ከማህበራቱ አባላቶቻቸው ውስጥ 33 በመቶዎቹ ሴቶች ሲሆኑ 28 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ደግሞ ወጣቶች ናቸው ። በዚህም በርካታ ቤተሰቦች በኅብረት ስራ ማህበራት ውስጥ ሆነው ገቢያቸውን ለማሳደግ እና ምርት ለማሳደግ እንዲሁም የቁጠባ አቅማቸውን ከፍ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን መረዳት ይቻላል ።
የኅብረት ስራ ማህበራቱ ያሏቸው ኢንዱስትሪዎች፣ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያዎች፣ ህንጻዎቻቸው እና ተሽከርካሪዎቻቸውን ጨምሮ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶቻቸው አጠቃላይ ካፒታል 32 ቢሊዮን ብር ደርሷል ። አሁን ላይ ማህበራቱ ለሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች የስራ እድል ፈጥረዋል ።
ቁጠባና ብድር ማህበራቱ በዋነኛነት ሊያገለግሉት የተነሱት አባላቸውን በመሆኑ፣ አባሉ ወደመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ደርሷል ወይ የሚለው አንኳር የውጤታማነታቸው መመዘኛችን ነው ።
በቀጣይም በኅብረት ስራ ማህበራት ስር ለመሳተፍ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የአባላት እና የካፒታል መጠኑ እያደገ እንደሚመጣ አያጠራጥርም። አሁንም አዳዲስ የህብረት ስራ ማህበራት በተለይ በብድርና ቁጠባ ዘርፍ ወደስራ ለመግባት ምዝገባ በማከናወን ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– በብድርና ቁጠባ ኅብረት ስራ ማህበራት ምን ያክል ገንዘብ እየተንቀሳቀሰ ነው? አባሎቻቸውን በኢኮኖሚ እያገዙ መሆኑን ምን ያክል ትከታተላላችሁ?
አቶ ኡስማን፡– ኢትዮጵያ ውስጥ በተቋም ደረጃ ቁጠባ የተጀመረው ከዛሬ 60 ዓመት በፊት ነው ። የዛሬ አምስት ዓመት ከሶስት ቢሊዮን ያለፈ ቁጠባ በማህበራት አይሰበሰብም ነበር ። በ2013 በጀት ዓመት 5ነጥብ 9 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው የቁጠባ ብድር ማህበራቱ 25 ቢሊዮን ብር በቁጠባ አሰባስበዋል ።
የብድርና ቁጠባ ማህበራት የፋይናንስ ሃብት በማሰባሰብ መልሰው ለህብረተሰቡ በብድር መልክ የሚያቀርቡ ተቋማት ናቸው ። ለገጠሩም ሆነ ለከተማው ኗሪ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉ ተቋማት መሆናቸው ይታወቃል ።
ቁጠባው ዞሮ ዞሮ ስራ ላይ የሚውል በመሆኑ ኅብረት ስራ ማህበራቱ ብድር በመጠቀም እና በእራሳቸው ፋይናንስ 1 ሺህ 700 የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ባለቤቶች ሆነዋል ። ለውጡን የሚያዩ ሌሎች ዜጎችም በየማህበራቱ ተመዝግበው ለመቆጠብ ያላቸው ተነሳሽነት እየጨመረ ነው ።
ከዚህ በተጨማሪ በቁጠባ መርሐ ግብር ታግዘው አምራች ማህበራት 1ሺህ 300 የግብርና ምርት ማሳደጊያ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችንም ገዝተው እየተጠቀሙ ይገኛል ። የሸሪዓ ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟሉ እና የወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ቁጠባ ማህበራትም አሉ ።
በስልጤ ዞን የሚገኘውን ፍርቄ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኀብረት ስራ ዩኒየን በወለድ አልባ አገልግሎት በርካታ አባላትን ማየት ቢቻል ሰፊ ለውጥ ያመጡ ማህበራት መኖራቸውን እንረዳለን ። ለአብነት በዩኒየኑ ስር የሚገኙ አንድ እናት ከአነስተኛ ወለድ አልባ ቁጠባ ተነስተው በመበደር የእራሳቸው ዘመናዊ ተሽከርካሪ ባለቤት ሆነው በመስራት ላይ ናቸው፤ እንደዚህ እና ሌሎች ተመሳሳይ ስራዎችን እናያለን ።
ከትግራይ ክልል የተገኘውን የህጻናት ቁጠባን ልምድ በማየት የቁጠባ ባህሉ ያደገ በእራሱ የሚተማመን ትውልድ መፍጠር አለብን በሚልም የህጻናት ቁጠባን በመላ አገሪቷ እንዲስፋፋ እያደረግን ነው ። በአጠቃላይም የብድርና ቁጠባ ማህበራት አቅም ማደጉን ብቻ ሳይሆን ምን ያክል አባላቶቻቸው ተጠቅመዋል የሚለውን በመረጃና ማስረጃ መመልከት በመመልከት ጠንካራ ጎኖቻቸውን ለማስፋት ጥረት እናደርጋለን ።
አዲስ ዘመን፡– ኅብረት ስራ ማህበራት በከተሞች አካባቢ ያለውን የዋጋ ንረት ማረጋጋት እንዲችሉ ምን አይነት ጥረት አድርጋችኋል?
አቶ ኡስማን፡– ማህበራቱ በገበያ ሰንሰለት መርዘም በማሳጠር በሰው ሰራሽ ምክንያቶች እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ሰፊ ጥረት እያደረጉ ነው ። መለስ ብለን ብንመለከት እንኳን በ2008 ዓ.ም ተፈጥሮ በነበረው በኤልኒኖ አየር ንብረት ለውጥ ጊዜ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መናር እንደተከሰተ ይታወቃል ።
በዚያን ጊዜም ክልልን ከክልል እንዲሁም ገጠሩን ከከተማው በማስተሳሰር ገበያው በተቻለ መጠን እንዲረጋጋ ተደርጓል ። ከ2010 ጀምሮ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲያጋጥምም ከአርሶአደሩ ምርት ወደከተማው በኅብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ባይቀርብ አሁን ካለው የበለጠ የዋጋ መናር ሊከሰት እንደሚችል አያጠራጥርም ።
በኮቪድ ወቅትም ሆነ በምርጫ ወቅቶች ላይ አርቴፊሻል የዋጋ ንረትን በመፍጠር ችግሩን ለማባባስ የሚጥሩ አካላት እኩይ አላማቸው እንዳይሳካ ጥረት ተደርጓል። አገሪቷ ወደከፋ ያለመረጋጋት ሁኔታ እንዳታመራ ኅብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርቶችን ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪ ምርቶችንም በማቅረብ ረገድ ሲሰሩ ቆይተዋል፤ አሁንም እየሰሩ ይገኛል ።
ወቅትን ጠብቀው የሚፈጠሩ የምርት እጥረቶችን ለመከላከል የግብርናና የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን በብዛት እንዲያቀርቡ ጥረት እያደረግን ነው ። ኅብረት ስራ ማህበራት የዋጋ ማረጋጋት ክንውናቸው ሁል ጊዜም የሚተገበር ቢሆንም በተለይ በቀውስ ወቅቶች እና በተለዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች ላይ ሚናቸው ጎልቶ ይታያል ።
ማህበራቱ የገበያ ሰንሰለቱ ባጠረ እና ከአርሶአደሩ በቀጥታ ወደሸማቹ ምርት እንዲደርስ በማድረግ በኮቪድ ወቅትም ሆነ በምርጫ ወቅቶች ላይ ሆን ተብሎ የተፈጠረን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የማስተባበር ስራ አከናውነናል ። ከተማ አስተዳደሩ በመደበው 500 ሚሊዮን ብር ማህበራቱ መሰረታዊ ፍጆታ ምርቶችን በስፋት እንዲያቀርቡ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡– ማህበራቱ ሰፊ ሥራ ቢኖራቸውም ከመደበኛው ገበያ ያልተለየ ዋጋ በማቅረብ እንዲሁም አንዳንዶቹም ለከፍተኛ ትርፍ የመሯሯጥ ችግር ይታይባቸዋል የሚል ቅሬታ ይቀርብባቸዋል?
አቶ ኡስማን፡– ችግሩ የለም ብሎ መውሰድ አይቻልም ። ላልተገባ ትርፍ የመሯሯጥ ሁኔታ አለ። ኅብረት ስራ ማህበራት የሚደራጁበት አንደኛው አላማ የአባሎቻቸውን ችግር ለመፍታት ነው ። ቢዝነስ እየሰሩ አባሎቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ በተመሳሳይ ህብረተሰቡን መጥቀም ይጠበቅባቸዋል ።
ነገር ግን ከስንዴ ፍሬ ውስጥ እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ ከኅብረት ስራ ማህበራት ውስጥ በአሰራራቸው ችግር የሚፈጥሩም እንዳሉ መታወቅ አለበት ። የአሰራር ጉድለት፣ የአመራር ችግር ያለባቸው እና በባለሙያ የማይመሩ በርካታ ማህበራት አሉ ። አንዳንዶች ከመደበኛው የቢዝነስ ተቋም ልትለያቸው የሚያዳግቱ የኅብረት ስራ ማህበራት መኖራቸው የሚካድ ሐቅ አይደለም ።
ለዚህ ደግሞ ሥርዓቱና አሰራሩ ሳይሆን ግለሰቦች ናቸው ጥፋቱን የሚፈጽሙት ። በፊት ለፊት በር ስኳር ገብቶላቸው በኋላ በር የሚያስወጡ የህብረት ስራ ማህበራት አመራሮችና ሰራተኞች አሉ ። በመዲናችን ብቻ 144 የማህበራት ሰራተኞች ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ተብለው እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
እንደአገር 99 ሺህ 500 ማህበራት አሉን ስንል ሁሉም ጥሩ ስራ ይሰራሉ ማለት አይደለም ። ከዚህ ውስጥ 50 ሺው ጥሩ ቢሰራ 20 እና 30 ሺው መሐል የሚያርፉ ቢሆኑ አስር ሺው ግን ደካማ ሊሆን ይችላል ። የተቀረው አስር ሺህ ደግሞ ሙሉ በሙሉም ሥራ ላይ ላይኖሩ ይችላሉ ። ይህን ከግምት ስናስገባ ቅሬታው መሬት ላይ ያለ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል ።
ጥፋት የሚፈጽሙትንም የሚመለከተው አካል በመለየት እርምጃ ይወስዳል ። እኛም በበኩላችን ችግሩን ለማስተካከል አሰራራቸውን የማዘመን፣ በባለሙያ እንዲመሩ የማድረግ እና የአደረጃጀት ችግሮቻቸውን ለመፍታት ከስልጠና ጀምሮ ሕግ ተግባራዊ እስከማድረግ የዘለቀ ሰፊ ሥራ እያከናወንን ነው ።
አዲስ ዘመን፡– አምራቹ ከሸማቹ በቀጥታ የሚገናኝበት መንገድ በመፍጠር ረገድ ምን አይነት አዳዲስ አሰራሮችን ለመዘርጋት አቅዳችኋል?
አቶ ኡስማን፡– አሁን ገበያችን ላይ የሚታየው የዋጋ መናር ምክንያቱ ምንድነው ብለን ብናይ በአምራቹ እና በሸማቹ መካከል ትልቅ ክፍተት በመኖሩ ነው ። አምራቹና ሸማቹ ሩቅና ሩቅ በመሆናቸው አይገናኙም። በአምራቹና ሸማቹ ኪሳራ በመሐል ያለ ምንም እሴት የማይጨምር አካል ነው ትርፍ የሚያጋብሰው ።
በመሐል ምንም ሳይሰራ አምስትና ስድስት አካል በዋጋው ላይ እጁን ያስነካል ይህን ለመከላከል ደግሞ ማህበራት በቀጥታ ተረክበው ማቅረብ አለባቸው ቢባልም ይህንን የማይፈጽሙ ናቸው በከፍተኛ ዋጋ ገበያው ላይ ካልሸጥን የሚሉ ። ችግሩ መዲናችን ላይ ቢከፋም በየአካባቢው ግን የሚታይ ነው ።
ማህበራት ምርት ማምጣት ያለባቸው በቀጥታ ከአምራቹ ሆኖ ሳለ ከአትራፊ ሸምተው ሲያቀርቡ ችግር ይፈጠራል ። ስለዚህ የግብርና ምርት ከሆነ ከአርሶአደሩ የኢንዱስትሪ ምርት ከሆነ ቀጥታ ከፋብሪካዎች አሊያም ከጅምላ አከፋፋዮች ላይ ነው ገዝተው ለህብረተሰቡ ማቅረብ ያለባቸው የሚል አሰራር ነው ያለን ።
አምራች ማህበራት ከሸማች ማህበራት ጋር በቀጥታ መተሳሰር አለባቸው የሚል መመሪያ እያወጣን ነው። ቀድሞም እየሰራንበት ቢሆንም በመመሪያ የታገዘ ባለመሆኑ አሁን ላይ በአስገዳጅነት እንዲተገበር ነው እቅዳችን ። ይህንን ደግሞ እንደምንተገብረው እርግጠኛ ነኝ።
የትኛውም የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርት ከአምራች ማህበራት ጋር በትስስር በወቅቱ የገበያ ሁኔታ የሚያቀርብ ከሆነ ችግር የሆነውን የዋጋ ንረትም ሆነ የጥራት ችግር መቅረፍ እንችላለን። መመሪያውን ስናጸድቅ ለውጥ ይመጣል ብለን እናስባለን ።
በሌላ በኩል የኅብረት ስራ ማህበራት አጠቃላይ ሪፎርም እንዲኖር እያስተባበርን ይገኛል ። ኦሮሚያ ላይ በከፊል ተጀምሯል፣ ሪፎርሙ በመላ አገሪቷ ይተገበራል ። በባለሙያ እና በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ ማህበራት እንዲመሩ በማድረግ የማዘመን ውጥን ነው ። ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቆዩ ሥርዓት እየዘረጋን ነው ። ይህም ፍትሐዊ የገበያ ምህዳር በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ መውጫ በሮች ላይ አምራቾች ምርት የሚያቀርቡባቸው ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጾ ነበር፤ ሥራው ምን ደረጃ ላይ ደረሰ?
አቶ ኡስማን፡– አዲስ አበባ ድሮ መግቢያ በሮቿ አራት ነበሩ ። አሁን ከተማችን ሰፍታለች። እንደ ባንኮክ እና ቶክዮ የመሳሰሉ ከተሞች መግቢያና መውጪያ በሮቿ በዝተዋል ። የመዲናዋ መውጫዎች ከአስርም አልፈው ወደ12 ደርሰዋል ።
እነዚህ በሮች ላይ ስትራቴጂካሊ የህብረት ስራ ማህበራት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የግብይት ተዋንያን በቀጥታ መጥተው ምርት የሚያቀርቡበት ሁኔታ ለመፍጠር እቅድ ነበረ ። ከአርሶአደሩም ሆነ ከአርብቶ አደሩ ሁሉንም አይነት ምርቶች በመውጫ በሮች ላይ አምስት ግዙፍ ማዕከላት በማስገንባት ለማገበያየት ነው ፍላጎታችን።
አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተገነቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ማዕከላትም የበለጡ እና የእንስሳት መገበያያ ጭምር ቦታ ያላቸው ማዕከላትን ነው ለከተማዋ የሚያስፈልጓት ። ይህን ትልቅ እቅድ ደግሞ በእኛ አቅም ልናስፈጽመው አንችልም ። የፕሮጀክቱ ግዙፍነት ከእኛ አቅም በላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከእኛ የስልጣን ወሰንም በላይ የሆነ ሥራ ነው ።
ስለዚህ ግንባታውን ማካሄድ ያለበት ወገን የከተማ መስተዳደሩ አሊያም የፌዴራል መንግሥት ቢሆንም እኛ ደግሞ ሃሳቡን አቅርበናል ። ሃሳብ ከየትም ይምጣ ከየትም ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ ደግሞ በጋራ እንሰራበታለን ብዬ አስባለሁ ።
ሃሳቡን ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከተማዋን በሚመሩበት ወቅት አቅርበንላቸው በሃሳቡ ተስማምተዋው ነበር ። እርሳቸው ወደሌላ ቦታ ሲሄዱ እና ኮቪድም አገራችን ላይ ሲመጣ እና ተያያዥ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ሲከሰቱ ግዙፉ ፕሮጀክት በይደር መቆየቱ አልቀረም።
አሁን ደግሞ ከተማዋን የሚመሩት ወይዘሮ አዳነች አቤቤን አግኝቼ ስለጉዳዩ አወያይቻቸዋለሁ ። ሃሳቡን እርሳቸውም ደግፈውታል ። በቀጣይ ጊዜያት ስለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሁኔታ የበለጠ ገለጻ እንድናደርግላቸው ተስማምተን ተለያይተናል ። ስለዚህ ሃሳቡን ተቀብለውት በቂ በጀት ሲመደብለት ወደፊት ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ።
አሁን አገር አጥፊው ጁንታ ስለእንደዚህ አይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንዳናስብ ነው እንቅፋት ለመሆን የተነሳው ። ዓላማው አገር ማዳከም የሆነው አጥፊ ቡድን ጋር ያለው ሁኔታ ሲስተካከል በቂ ገንዘብ ተመድቦ ይሰራል ብዬ እጠብቃለሁ ።
ፕሮጀክቱ እውን ሲሆን አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ እንዲሁም ኢንቨስተሩ በቀጥታ ማዕከላቱ ላይ በሚገኙ ሱቆች ምርቶችን ለከተማዋ ነዋሪ በቀጥታ ያቀርባል ። ነዋሪዎችም የሚፈልገውን ምርት በቀጥታ ከምንጩ በመሸመት ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በተሻለ መጠን ያገኛል ብለን እንጠብቃለን ።
አዲስ ዘመን፡– ማህበራት እና ዩኒየኖች የተሻለ የገበያ አማራጭ በማስፋት ረገድ ምን አይነት ዘዴዎችን ትጠቀማላችሁ?
አቶ ኡስማን፡– ገበያ አማራጭ በመፈለግ ረገድ ለቡና አምራቾች እና ለሌሎች የግብርና ውጤቶች አቅራቢዎች በውጭ አገር ጭምር ገበያ እንዲያገኙ የማስተዋወቅ ስራ እናከናውናለን ። የምርት ናሙና ወስደን እስከማቅረብና የደረሰ ጥረትም አለን ።
ከውጭው ባለፈ የአምራችና ሸማች ማህበራት በማገናኘት ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ሸማች ማህበሩ በዚህ ወቅት እንዲህ አይነት ምርት እፈልጋለሁ በሚል ለአምራች ማህበሩ እያሳወቀ ዘላቂነት ባለው መልኩ በጋራ ውል ፈጽመው መስራት የሚችሉበት ደረጃ ማድረስ ነው አላማችን ።
ለዚህም ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት የትኛው ማህበር ጋር ምን አይነት ምርት ይገኛል የሚለውን እናስተዋውቃለን ። በኤግዚቢሽኖች ላይ በርካታ ሸማችና አምራች ማህበራት ግንኙነት ፈጥረው በዘላቂነት በመስራት ላይ ናቸው ። በተገኘው መድረክም ሆነ የጉዞ አማራጮች ላይ አምራቾች በዩኒየኖች በኩል የተሻለ ዋጋ እና ገበያ እንዲያገኙ ባለሙያዎቻችን ጥረት ያደርጋሉ።
ምንም እንኳን አምራች ዩኒየኖች ወደውጭ የሚልኳቸው ምርቶች አነስተኛ ቢሆኑም በውጭ ምንዛሪ ረገድ ግን ከፍተኛ ገቢ የሚያስገቡ ናቸው ። አብዛኛው የአገር ውስጥ ግብይት ላይም አምራች ማህበራት ዋነኛ አቅራቢዎች ናቸው ። ይህን በቴክኖሎጂ እና አሰራር በማዘመን አርሶአደሩንና አርብቶ አደሩን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን ይገኛል ።
አዲስ ዘመን፡– ማህበራት አሳታፊነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ምን አይነት ጥረት አድርጋችኋል?
አቶ ኡስማን፡– በቁጠባው ዘርፍም በርካታ ቢሮዎችን እንዲከፍቱና ሰፊ ቁጥር ያላቸው አባላትን እንዲያሳትፉ በማድረግ አገልግሎታቸውን ለማስፋት ጥረት እናደርጋለን። አካታችነታቸውን የሚረጋገጠው በሚያሳትፏቸው እና ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው ዜጎች አይነትና መጠን ነው።
ከህጻን እስከ አዛውንት በርካታ አባላት ያሏቸው ማህበራት ማንሳት ብንችል ለአብነት በአዲስ አበባ አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ማህበር፤ አዳማ ላይ አዲ ጉዲና ዩኒየን አለ፣ አማራ ክልል ጣና ዩኒየን እና ልደት ዩኒየኖችን እናገኛለን ።
ደቡብ ክልል ላይ ጉራጌ ዞን ውስጥ ነፃነት ፋና የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ስራ ዩኒየን ማየት ቢቻል 76 በመቶ አባሎቻቸው ሴቶች ሲሆኑ ሶስት አራተኛ አመራሮቹ በተመሳሳይ ሴቶች ናቸው ። አሳታፊ በሆነ መልኩ የሴቶችን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ያወጀት ከ25 ሺህ በላይ አባላት ያሏት ዩኒየን ነች ።
በርካታ አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን አቅፈው የያዙ ማህበራት በመላ ሀገሪቷ አሉ ። በ2013 ዓ.ም ከማህበራቱ ብድር ወስደው የተለያየ ስራ ካከናወኑ 700 ሺህ ዜጎች ውስጥ በርካታ እናቶችና ወጣቶች ይገኙበታል። ይህ ማለት አካታችነት ባለው መልኩ ህብረተሰቡ ለተሻለ ለውጥ እንዲነሳሳ ተሰርቷል ማለት ነው።
የኅብረት ስራ ማህበራት በቀጥታ የስራ እድል በመፍጠር፣ በስልጠና ፣ በሙያዊ እገዛ እና በቁጠባ አቅርቦት እንዲሁም ምርት በማሳደግ ረገድ በየአካባቢያቸው የሚገኙ ዜጎች ባሳተፈ መልኩ እየሰሩ ይገኛል ። እኛም ይህ አሳታፊነታቸው እንዲጎለብት የአቅም ማሳደጊያ መርሃ ግብሮችን እያዘጋጀን ነው ።
አዲስ ዘመን፡– በትግራይ ክልል የሚገኙ የኅብረት ስራ ማህበራት ያሉበትን ሁኔታ የምትከታተሉበት መንገድ አለ? በምን ሁኔታ ላይ ናቸው?
አቶ ኡስማን፡– በትግራይ ክልል በርከት ያሉ የህብረት ስራ ማህበራት አሉ ። እስከ 7ሺህ የህብረት ስራ ማህበራት እና 38 ዩኒየኖች ነበሩ ። ህወሓት እኩይ ተግባሩን እስከፈጸመበት እለት ድረስ መሰረታዊ ማህበራቱ በተለይም በብድርና ቁጠባ ረገድ ውጤታማ ስራ እያከናወኑ ነበር ።
ጥቅምት ላይ ህወሓት መከላከያ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ማህበራቱ የደረሱበትን ደረጃ ሄደን ለማየት ሞክረናል። በኋላም መንግሥት ትግራይን መልሶ የማቋቋም ስራ ሲያከናውን መቀሌ ላይ የባለሙያዎቻችን ቡድን ለሁለት ወራት ቆይተው በጋራ ሥራዎችን አከናውነዋል ።
በወቅቱ እንደተረዳነው አብዛኛዎቹ የመንግስት ተቋማት ሲዘረፉ የብድርና ቁጠባ ማህበራት እና ሸማች ማህበራት ግን ጥቂቶቹ ናቸው የተዘረፉት ። የተወሰነ ንብረታቸው ላይ ጉዳት ከመድረሱ ባለፈ ገንዘባቸው እንዳልተዘረፈ አውቀናል ። መከላከያ ትግራይ ውስጥ እራሱን ዳግም ባደራጀበት ወቅት ማህበራቱ ንብረታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ሰፊ ጥረት ተደርጓል ።
ባይሆን የማህበራቱ አንዳንድ አመራሮቻቸው አብረው ከጁንታው ጋር መኮብለላቸው እርግጥ ነው ። ይህን ለመተካት ደግሞ ህብረተሰቡ አዳዲስ አመራሮችን መርጦ እንዲሰይም ጥረት ተደርጓል።
መንግስት የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ግን ጁንታው እያደረሰ ባለው ጥፋት ምን ላይ እንደሚገኙ ማወቅ አንችልም ። አሁን ላይ ጁንታው ሕዝቡ ከማምረት ተግባር ውጪ ሆኖ ለምግብና ለድህነት እንዲጋለጥ እያደረገው በመሆኑ ማህበራቱም ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ይገመታል።
ከዚህ ውጭ ግን ቦታው ላይ ያለው ምን እንደሆነ በእርግጠኝነት ማረጋገጥ አይቻልም። መንግሥት እያከናወነ ያለው አገር የማዳን የህልውና ስራ መልክ ሲይዝ የማህበራቱም ጉዳይ አብሮ የሚታይ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ኡስማን፡– እኔም እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2013