“በፕሮጀክቶች ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ከማቅረብ ይልቅ መፍትሔ እየሰጡ መሄድ ያስፈልጋል”-ኢንጂነር መሐመድ አብዱረሃማን

ኢንጂነር መሐመድ አብዱረሃማን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር

ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት የማይተካ ሚና ከሚጫወቱት ጉዳዮች መካከል የመንገድ መሠረተ ልማት አንዱ ነው:: ኢትዮጵያም ይህን እውነታ በመረዳት ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ምዕራፎች የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የሕዝቡን ልማት ጥያቄ ለመመለስ ጥረት እያደረገች ነው::

የመንገድ መሠረተ ልማት በባህሪው ትልቅ የፋይናንስ አቅም የሚጠይቅ መሆኑም ይታወቃል:: የዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን ፍትሃዊ የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነት እንዲኖር መንግሥት ምን እየሰራ እንደሆነ፤ ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታ ያለባቸው የተጓተቱ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ለማጠናቀቅ በምን መልኩ እየሰራ እንደሆነና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱረሃማን ጋር ቆይታ አድርገናል:: መልካም ምንባብ::

 አዲስ ዘመን፡- በ2016 በጀት ዓመት አስተዳደሩ ምን አቅዶ ምን አሳካ? በምን ያህል በጀት?

ኢንጂነር መሐመድ፡- በ2016 በጀት ዓመት ላይ በዋናነት የጥገና፣ የማጠናከር እና የመንገዶችን ደረጃ ማሻሻል የተሰኙ ሶስት የፕሮጀክት የካፒታል ሥራዎችን ለመሥራት ሰፊ እቅድ በመያዝ ወደ ሥራ ተገብቷል::

በ2016 በጀት ዓመት ላይ በመጀመሪያው ምድብ መንገዶችን ማጠንከር፤ ማሻሻልና አዳዲስ ግንባታን በፍጥነት መጨረስ በሚሉት ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው:: ከዚህ አንጻር አንድ ሺ 247 ኪሎ ሜትር መንገዶችን ለመሥራት እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል:: በጥገና ዘርፍም በተለይም ከከባድ ጥገና ጋር በተያያዘ 15 ሺ 698 ኪሎ ሜትር ለመጠገን እቅድ ተይዞ ነበር::

የመንገድ ሥራ ካፒታልና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው:: በዚህ አግባብ በመንግጭትና በልማት አጋሮች በኩል ከፍተኛ የሚባል በጀት ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል:: በመንግሥት ብቻ 60 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን ከብድርና ከርዳታ ሰባት ነጥብ 6 ቢሊዮን፤ ከመንገድ ፈንድ ለመንገድ ጥገና ሥራዎች የሚውል ስምንት ነጥብ 17 ቢሊዮን ብር ተመድቧል:: አጠቃላይ የበጀት ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም 80 በመቶ ነው::

ከፕሮጀክት ሥራዎች ጎን ለጎን ተቋማዊ ሥራዎችን ማከናወን እንደ አንድ ስትራቴጂክ እቅድ በማድረግ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል:: በዚህ አግባብ የአስተዳደር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች፤ ባለሙያዎች፤ መሃንዲሶችን በአቅም ለመገንባት ከፍተኛ ሥራዎች ተሰርተዋል::

በተለይ ፕሮጀክቶች አካባቢ የሚሰሩ መሃንዲሶችን አቅምን ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በሰፊው ተሰርቷል:: ተከታታይነት ያለው የአቅም ማሳደግ ፕሮግራም ተቀርጾ ሁሉም መሃንዲሶች በስልጠናው እንዲያልፉ በማድረግ የፕሮጀክትና የኮንስትራክሽን የማስተዳደር አቅማቸው እያደገ እንዲሄድ ሰፊ ሥራ የተሰራበት ዓመት ነበር::

በተጨማሪም ተቋማችን ዓለም አቀፋዊ ባህሪያ ያላቸው ተቋራጮች (ኮንትራክተሮች) የሚያስተዳድር ከመሆኑ አንጻር በፕሮጀክት ማኔጅመንት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሰርተፍኬት ባለሙያዎቻችንና መሃንዲሶቻችን እንዲያገኙ ከኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር እንዲሁም ከከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በጣምራ በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል:: የትም ሀገር ቢሄዱ ፕሮጀክቶችን የማስተዳደር ብቃት አላቸው ተብሎ የሚመሰከርላቸው ስለሚሆን በዚያ ልክ የምስክር ወረቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ ሥራዎች ተከናውነዋል:: በዚህም መሃንዲሶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እውቅና እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል::

በዚህ ዓመት ብቻ 10 የሚሆኑ መሃንዲሶች የዓለም አቀፍ እውቅና ሰርተፍኬት ባለቤት ሆነዋል:: ይህም ለተቋማችን ፕሮጀክቶችን በማስተዳደር ሂደት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር ነው::

በመንገዶች አስተዳደር ከሚሰሩ ሥራዎች ስፋት አንጻር በተለመደው መንገድ ብቻ ሥራ መሥራት አዳጋች እንደሚሆን እሙን ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ሥራዎችን ማዘመን አስፈላጊ ነው:: ስለሆነም ባለፈው በጀት ዓመት ሥራዎቻችን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ አከናውነናል::

አዲስ ዘመን፡- ሥራዎችን ዲጂታላይዝ ማድረጉ በአስተዳደሩ ሥራ ላይ ምን አቅም ፈጠረለት?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ዲጂታላይዝ በመደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ ያለው የዕለት ተዕለት አፈጻጸም ዋና መሥሪያ ቤት ላይ ሆኖ መከታተል የሚቻልበት ሥርዓት ተፈጥሯል:: ዘመናዊ አሠራሩ ፕሮጀክቶች ላይ ያለውን አፈጻጸም በተሻለ ሁኔታ ድጋፍን እና ቁጥጥሩን መሥራት እንዲቻል ትልቅ አቅም ፈጥሯል:: ይህ ብቻ ሳይሆን ከአስተዳደሩ ጋር በጋራ የሚሰሩ ሥራ ተቋራጮች፣ አማካሪ መሃንዲሶች እና ድርጅቶች፣ አሠራራቸውንና አፈጻጸማቸውን ዲጂታላይዝ በሆነ መንገድ በመከታተል መረጃ መያዝንና ሪከርድ ማድረግ ያስቻለ በመሆኑ በቀጣይ ለሚኖሩ ሥራዎች እንደ ግብዓቶችን መያዝ የሚያስችል አሠራር (ሲስተም) ተግባራዊ ተደርጓል:: በዚህ ሲስተም አሠራሮችን መመዘን፤ መስተከካል ያለባቸው ፕሮጀክቶችና ጨረታዎችን ለመሥራት የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር መዘርጋት ተችሏል::

ከምህንድስና ግዥ ጋር በተያያዘ አምስት ፕሮጀክቶች ላይ ግዥ የተፈጸመ ሲሆን ወደ አተገባበር ተሸጋግረዋል:: ለአብነት ዲንቂ-ሳውላ፤ ቧሂት-ድል ይብዛ፤ አስጎሪ- ደምቢ መገንጠያ፤ ነቀምት-ሶጌ፤ ቢሾፍቱ-ጬፌ ዶንሳ የሚባሉ ፕሮጀክቶች የግዥ ሂደታቸውን በማጠናቀቅ ወደ ግንባታ ሂደት እንዲሸጋገሩ ተሰርቷል:: ሌሎች በርከት ያሉ ፕሮጀክቶች ደግሞ የግዥ ሂደታቸው በማጠናቀቅ ደረጃ ላይ ይገኛል:: በአጠቃይ 17 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች የግዥ ሂደታቸው በማጠናቀቅ ወደ ግንባታ ለማስገባት እቅድ የተያዘ ሲሆን አምስቱ ተጠናቀዋል፤ ቀሪዎቹም በማጠናቀቅ ሂደት ላይ ይገኛሉ:: ቀሪዎቹን ከእነዚህ በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅና በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ግንባታ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል::

አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ምን ያል የሚሆኑት ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ይገኛሉ?

ኢንጂነር መሐመድ፡- አሁን ላይ 188 የካፒታል ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ናቸው:: የእነዚህ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ርዝመት 12 ሺ 05 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ነው:: በበጀት ዓመቱ አንድ ሺ 126 ፕሮጀክቶች ለማከናወን እቅድ ተይዞ ነበር:: አጠቃላይ ክንውኑ 80 በመቶ ሲሆን የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም 73 በመቶ ነው:: በበጀት ዓመቱ በልዩ ሁኔታ እንዲስተዳደሩ የተደረጉ ስምንት የሚደርሱ ፕሮጀክቶች አሉ::

19 የሚሆኑ የጥገና ፕሮጀክቶች በልዩ ትኩረት በማኔጅመንት በየሳምንቱ እየተገመገሙ አቅጣጫ እየተቀመጠ ሲሆን እነዚህም በሕዝብ ቅሬታ የሚነሳባቸው ነበሩ:: አሁን ላይ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በሚያስችል አግባብ ለማስተዳደር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ በአስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ተደርጓል:: በተጨማሪም 18 የካፒታል ፕሮጀክቶችና 12 የድጋፍ ፕሮጀክቶችን በመለየት ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ማስተካከያዎች እየተደረጉ ነው::

ከመንገድ ሀብት አንጻር ዋና ዋና መንገድ የሚባሉት መንገዶ ላይ የነበረው የጥገና ክፍተት እንዲስተካከል ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበት ዓመት ነው:: በዚህ አግባብ ከአዳማ እስከ አዋሽና ሚኢሶ ባለው መንገድ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል:: በተመሳሳይ ከሰበታ ወልቂጤ፤ ጊቤ ድረስ ያሉ መንገዶች የጥገና ሥራዎች ተሰርተዋል:: ከዓለም ገና እስከ ቡታጅራ፤ ከአዲስ አበባ ፊቼና ከሚዛን እስከ ጅማ ያለውን መንገድ ለመጠገን ጥረት ሲደርግ ቆይቷል:: ዋና ዋና መንገዶች ላይ የነበረው የመንገድ ብልሽትን ለመጠገንና ለማሻሻል በዘመቻ መልክ ጭምር በመሥራት የመንገዶች ደረጃ የማሻሻል ሥራ ተሰርቷል::

በፋይናንስ ረገድ በአለፉት አስር ወራት ያለው ክንውን በዓመቱ ከተመደበው 60 ቢሊዮን ብር በጀት ክንውኑ 41 ቢሊዮን ብር ሲሆን የእቅዱን 78 በመቶ ነው:: ከልማት አጋሮች አንጻር ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን አፈጻጸሙ አንድ ነጥብ8 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው:: ይህም የእቅዱን 28 በመቶ ነው:: በድምሩ 66 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ የነበረ ሲሆን በ10 ወራት የነበረው አፈጻጸም 47 ነጥብ 4 ቢሊዮን ወይም ደግሞ 62 በመቶ አካባቢ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለው አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል:: ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ከአጋር ድርጅቶች ጋር የምንሰራቸው ሥራዎች በባህሪቸው ረዘም ያለ የጨረታ ሂደት ያላቸው ናቸው:: በዚህም እያንዳንዱ ሥራ ተከታታይ የሆነ የጨረታ ሂደትን እንዲያልፍ ይደረጋል:: አልፎ አልፎም ከሚገመተው በላይ ጊዜ ይወስዳሉ:: አንዱ ሂደት ሲያልቅ ሰነድ ይላክና ታይቶ ግብረ መልስ ይቀርባል:: ታይቶ ድጋሚ ወደ ሂደቱ የሚመለስበት ሁኔታ ስላለ ከታቀደው በላይ ጊዜ ይወስዳል:: ስለዚህ ከአመራሮቹ ጋር በመነጋር ሂደቱን በተሻለ መንገድ ለማስኬድ የታሰቡ እቅዶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ታሳቢ ያደረገ ሥራ የተሠራ ሲሆን በተለይም ከዓለም ባንክ ጋር ውይይት ተደርጓል:: የነበሩ ማነቆዎችንና ምልልሶችን በጋራ በመሥራት በጨረታ ላይ የሚወስደው ረጅም ጊዜ በማሳጠር ወደ ግንባታ እንዲሸጋገሩ የተያዙ እቅዶችን በተሻለ ሁኔታ እንዲሰሩ መግባባት ላይ ተደርሷል::

ከዓለም ባንክ ጋር ያለው ፈንድ አለቃቀቅ ላይ ክፍተቶች ነበሩ:: አሽካን ዴቨሎፕመንት፤ ሳውዲ ፈንድ፤ አቡዳቢና ሌሎች ተቋማት ጋር የተያያዙ ድርጅቶች በሚፈለገው ልክ ሳይሆን የመዘገየት ሁኔታዎች ነበሩ:: ይህን ችግር ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ለድርጅቶቹ አመራሮች ጉዳዩ ደርሶ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነው:: ስለሆነም ሙሉ በሙሉ ችግሩ ተፈቷል ማለት ቢያስቸግርም ቀጣይ ችግሮቹ እንዳይደገሙ ጥረቶችን ማድረግ ያስፈልጋል::

አዲስ ዘመን፡- የመንገድ መሠረተ ልማት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ መሆኑ ይታወቃል:: ስለሆነም ከ10 ዓመቱ የዘላቂ የልማት ግቦች ጋር አቀናጅቶ ከመሥራት አንጻር በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ አስተዳደሩ የመንገድ ተደራሽነትን ምን ደረጃ ለማድረስ አቅዶ እየሠራ ነው?

ኢንጂነር መሐመድ፡- እንደ ሀገር የመንገድ ልማት ፕሮግራም ከተጀመረ 26 ዓመታትን አስቆጥሯል:: የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮግራም የተጀመረው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 1989 ዓ.ም ላይ ነበር:: ባለፉት 26 ዓመታት ሲተገበር የነበረ ፕሮግራም ነው:: ፕሮግራሙ ሲጀመር የመንገድ ሽፋን በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነበር:: 1989 ዓ.ም ጀምሮ የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ስትራቴጂ ተቀርጾ ሲተገበር ቆይቷል:: አሁን ላይ አምስት የመንገድ ልማት ስትራቴጂ በማጠናቀቅ ስድስተኛው መርሃ ግብር ላይ ተደርሷል::

ስድስተኛው የመንገድ ልማት ፕሮግራም ከ10 ዓመቱ የመንገድ ልማት ፕሮግራም ጋር እንዲቀናጅ እና እንዲናበብ ተደርጎ ተቀርጿል:: አሁን ላይ እንደ ሀገር የተቀመጡ የ10 ዓመት የልማት ግቦች ያሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የመንገድ ልማት ፕሮግራም አንዱ ነው:: ከዚህ ጋር በማናበብ የአምስት ዓመታት እቅድ ተሰርቷል:: ይህም የመንገድ ልማት እቅድ ከ2013 ዓ.ም እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቅ ነው::

ከመንገድ ሽፋን አንጻር ሲታይ የመንገድ ልማት በ1989 ዓ.ም ሲጀመር በሀገር ደረጃ የነበረው መንገድ ሽፋን 26 ሺ 550 ኪሎ ሜትር ብቻ የነበረ ሲሆን ይህም በጣም አስቸጋሪ የሚባል መንገድ ነበር:: በአሁኑ ሰዓት ይህን የመንገድ ሽፋን 165 ሺህ 863 ኪሎ ሜትር ማድረስ ተችሏል:: ይህ የሆነው ባለፉት ዓመታት በተከታታይ በተሠራው የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ነው::

የ10 ዓመት የልማት እቅድ ሲጀመር እንደ መነሻ ተደርጎ የተወሰደው የ2012 ዓ.ም የነበረው የመንገድ ሽፋን ነው:: በ2012 ዓ.ም 144 ሺህ 027 ኪሎ ሜትር ነበር:: በሶስቱ ዓመት በተከናወነው የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ሥራ በ2015 ዓ.ም ወደ 165 ሺህ 863 ኪሎ ሜትር ማሳደግ ተችሏል::

ከሌሎች አመላካች እቅዶች አንጻር ሲፈተሽ የመንገድ ጥግግት በዓለም አቀፍ መለኪያ በ2012 ዓ.ም በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩዬር 130 ነጥብ 9 ነበር:: አሁን ላይ 144 ነጥብ 5 ደርሷል:: በአንድ ሺ ኪሎ ሜትር ውስጥ ምን ያህል መንገድ አለ? ተብሎ ሲታይ በ2012 ዓ.ም ላይ በአማካይ ወደ 130 ኪሎ ሜትር መንገድ ይገኛል:: አሁን ላይ ከ130 ወደ 144 ኪሎ ሜትር ስኩዬር አድጓል:: ይህም በዘርፉ ላይ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን የሚያላመክት ነው::

በ2012 ዓ.ም ላይ 56 በመቶ የሚሆነው ማህበረሰብ ክረምት ከበጋ የሚያስኬድ መንገድ ለማግኘት አምስት ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር:: ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወኑ የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች ወደ 32 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል:: ይህ ማለት አሁን ላይ ክረምት ከበጋ የሚያስኬድ መንገድ ለማግኘት አምስት ኪሎ ሜትር የሚጓዘው ሕዝብ ብዛት 32 ነጥብ 7 በመቶ ነው:: በሁሉም መለኪያዎች ከታየ ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ የመንገድ ዘርፉ ላይ ተጨባጭ ውጤት መጥቷል::

አዲስ ዘመን:- በሰው ኃይል ልማት ላይ እንደተሠራ ገልጸዋልና በበጀት ዓመቱ ለነበረው የሥራ አፈጻጸም የነበረው ሚናን እንዴት ይገልጹታል?

ኢንጂነር መሐመድ:- በሰው ኃይላችን ላይ የተሠራው ሥራ በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ሳይሆን እንደ ተቋም ብሎም እንደ ሀገር ስትራቴጂክ እቅዶችን ለማሳካት የሚያስችል ነው። የሰው ኃይል ብቃት ባለው መንገድ ሥራን መፈጸም የሚያስችል ነው። በቀጣይ በዘርፉ ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን በመቅረፍ የተቋሙን ተልዕኮ ማሳካት የሚያስችል አላማ የያዘ ነው። ፕሮጀክቶች ላይ ያለው አፈጻጸም እየተሻሻለ እንዲመጣ የሚያስችል ነው። ስለሆነም በተቋሙ የሥራ አፈጻጸም ላይ የራሱ የሆነ በጐ ተጽእኖ ይኖረዋል።

አዲስ ዘመን፡- የመንገድ መሠረተ ልማት ሲገነባ ለምን ያህል ዓመት ያገለግላል ተብሎ ነው? የተገነቡ መንገዶ ተበላሽተው የሚታዩት ከጥራት መጓደል ወይስ መስጠት ከሚችሉበት ዕድሜ በላይ ስላገለገሉ?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ሁለቱም ጉዳዮች መታየት የሚገባቸው ናቸው:: ብዙዎቹ መንገዶች ከ26 ዓመት በፊት የተሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ናቸው:: በተለይም ዋና ዋና መንገዶች የሚባሉት አዲስ አበባን ከተለያዩ የክልል ዋና ከተሞች፤ ከገቢ ወጪ ምርቶች ኮሪደር ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ናቸው:: ይህም አገልግሎት መስጠት የጀመሩበት ጊዜ ሲታይ ከ20 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል::

መንገድ ሲሠራ ዋና ዋና መንገድ ከሆነ 20 ዓመት እንዲያገለግል ታሳቢ የሚደረግ ሲሆን ከዋና ዋና መንገዶች ጋር መጋቢ የሚባሉት ደግሞ 15 ዓመት ዕድሜ እንዲኖራቸው ተደርጎ ይገነባሉ:: የሚጠገኑ መንገዶች በብዛት የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ ናቸው:: ምናልባትም ከጥገናም ባሻገር እንደገና መገንባትን የሚጠይቁ ናቸው:: ነገር ግን እስከሚገነቡ ድረስ የተሻለው አማራጭ ጥገና ማድረግ ነው::

የጥራት ችግር ያሉባቸው መንገዶች ስላሉ ችግሩን ለማስተካከል የሚሠሩ ሥራዎች አሉ:: ይሁን እንጂ መንገዶችን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን መንገዶች ሲሠሩ በተገቢው የጥራት ደረጃ መሥራት የሚያስችሉ ተግባራትን እየተከናወኑ ነው::

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ከለውጡ ወዲህ ምን ያህል የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጀመሩ፤ የግንባታ ሂደታቸውስ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ከለውጡ ወዲህ በጣም ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: ከ2011 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ሲታይ ወደ 79 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ የግንባታ፤ የማጠናከሪያ መንገድ፤ የማሻሻያና የጥገና ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዶ ሰፊ ሥራዎች ተሰርቷል:: ከግንባታ ሥራዎች ጋር በተያያዘ 8 ሺህ 311 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመሥራት በእቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን ከዚህም 3 ሺህ 295 ኪሎ ሜትር ያህሉ በከባድ ግንባታ ለመሥራት የታቀደ ነው:: በተመሳሳይ ወቅታዊና መደበኛ ጥገና ጋር በተያያዘ 67 ሺህ ኪሎ ሜትር ገደማ ለመሥራት እቅድ ተይዟል:: በተጨማሪም ሰፊ ቁጥር ያላቸው ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ተፈራርመናል::

በአጠቃላይ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 159 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ገብተዋል:: ከለውጡ ወዲህ ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን የጨረስን ሲሆን ቀድሞ የተጀመሩትን መጨረስ ተችሏል:: ስለሆነም በአዲስ ተነሳሽነት በለውጡ 86 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ተችሏል:: በአጠቃላይ በእነዚህ ዓመታት የነበረው አፈጻጸም 75 በመቶ ነው::

አዲስ ዘመን፡- የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታና ጥገና እቅድ ሰፊና የተለጠጠ ነው:: ከዚህ አኳያ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች የግንባታ መሠረተ ድንጋይ ከተቀመጠላቸው በኋላ ምንም ያልተጀመሩ እንዲሁም ተጀምረው ግንባታቸው የተቋረጡ፤ በሁለት ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብለው ከአምስት ዓመት በላይ ያስቆጠሩ መንገዶች አሉና አስተዳደሩ ችግሩን እንዴት እየፈታው ነው?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ችግር የተፈጠሩባቸውን ፕሮጀክቶች ለይተናል:: እያንዳንዱ ፕሮጀክት የራሱ ልዩ ባህሪ ስላለው ባህሪያቸውን መሠረት በማድረግ ሥራዎችን ለመጨረስ ልዩ ስትራቴክጂ እና እቅድ አዘጋጅተናል:: በዚህም ችግሮች በሚስተዋልባቸው ፕሮጀክቶች ላይ በጣም የቅርብ ክትትል እንዲደረግ፤ አፈጻጸማቸውም ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ በእኛ በኩል ከፍተኛ ጥረት አድርገናል:: ነገር ግን ሙሉ በሙሉ የሕዝብን ጥያቄ መልሰናል ብለን አናምንም:: አሁንም በጣም ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባን እንረዳለን:: እንደዚያም ሆኖ ግን ባስቀመጥነው እቅድ መሠረት ልውጦችን እያመጣን ነው። ለዚህም በተጨባጭ ማሳያ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ማንሳት እንችላለን:: ለምሳሌ ከጅማ – ሊሙ መገንጠያ አንደኛው ነው:: በዚህ ፕሮጀክት ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ በዘንድሮው ዓመት ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የአስፋልት ሥራዎችን መሥራት ችለናል:: ከጅማ እስከ አጋሮ ባለው መስመርም እንዲሁ ሰፋፊ ሥራዎችን መሥራት ችለናል:: ከቴፒ – ሚዛንም እንዲሁ ከ12 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድ እንዲሰራ አድርገናል:: ነገር ግን ይህ በቂ ነው ብለን አንወስድም:: ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እናምናለን::

በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን እና ኮንትራክተሮችን በአግባቡ በማስተዳደር እና በመደገፍ እንዲሁም ተገቢ የኮንትራክት ርምጃዎችን በመውሰድ ፤ ጥብቅ የሆነ የፕሮጀክት አመራር ፤ ጥብቅ የሆነ የኮንትራክት አስተዳደር በመከተል የተሻለ ውጤት እያመጣን መሄድ አለብን የሚል አሠራርን እየተከተልን ነው:: ይህም ለሕዝብ ጥያቄዎች የተሻለ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው:: ስለሆነም ይህን ዓይነት አሠራር አሁንም ግን አጠናክሮ መሄድ ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ከዚህ በተሻለ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ አለበት::

አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ የመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት ተያይዞ የሚሰጡት ምላሾች የኮንትራክትሩ አቅም ማነስ፣ የአየር ንብረት እና መሰል ምክያንቶች ናቸው:: ከዚህ አንጻር ፕሮጀክቶችን የምታስጀምሩት የአየር ሁኔታውን ሳታስጠኑ እና የኮንትራክተሩን አቅም ሳታውቁ ነው?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ፕሮጀክቶች ላይ ያለንን ፕሮጀክት የማስተዳደር አቅም ከፍ ማድረግ በዘላቂነት ለችግሮቹ መፍትሔ ይሰጣል ብለን እናምናለን:: አስተዳደራችንም ከዚህ በበለጠ ተደራሽ መሆንም እንዳለበት እናምናለን። ቀደም ብሎ በነበረው ጊዜ በመላ ሀገሪቱ የነበሩ ፕሮጀክቶቸን በአንድ ማዕከል ላይ ብቻ በመሆን እናስተዳድር ነበር:: አሁን ላይ ግን በመላ ሀገሪቱ 27 የሚሆኑ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤቶችን ከፍተናል:: በዚህም ፕሮጀክቶችን በቅርበት ለመደገፍ እና በቅርበት ችግሮችን መፍታት፤ ስለ ፕሮጀክቶቹ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እና በግልጽ በመነጋገር ግልጸኝነት በመፍጠር ያጋጠሙን ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚለው ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመውሰድ ፤ አፈታቱ ላይም ህብረተሰቡን ያሳተፈ ለማሳደግ የሚያስችል አሠራር ዘርግተናል::

ፕሮጀክቶች ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፤ መፍትሔዎቹ ላይ ግን መሥራት ያስፈልጋል የሚል አሠራር እየተከተልን ነው:: በፕሮጀክቶች ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ከማቅረብ ይልቅ መፍትሔ እየሰጡ መሄድ ያስፈልጋል:: ይህን ለማድረግ ግልጽ የሆነ የአሠራር ሥርዓትን ዘርግቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በግልጽ መነገጋር እና ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት መሥራትን ያማከለ አሠራርን መከተል ያስፈልጋል::

ኮንትራት ሰነዶች ላይም የሚነሱት ቅሬታዎች አግባብነት ስላላቸው ማሻሻያዎችን ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል። እንደየአካበቢው ሁኔታ የኮንትራት ጊዜው መገደብ ወይም መወሰን አለበት:: ሁሉም አካባቢ ተመሳሳይ የአየር ጠባይ የለውም:: አንዳንድ አካባቢዎች ረዘም ላለ ጊዜ ዝናብ ይኖርባቸዋል:: አንዳንዶቹ ደግሞ ዝናብ አጠር ሊሆኑ ይችላሉ:: ስለዚህ በሁለቱም አካባቢዎች ተመሳሳይ ኮንትራት ሊኖረን አይችልም:: ከዚህ አኳያ በበርካታ ፕሮጀክቶች ላይ ማሻሻያዎችን አድርገናል::

ከኮንትራክተሮች አቅም ጋር በተያያዘም አሁን በሥራ ላይ ያሉ የሥራ ተቋራጮች አፈጻጸማቸውን ጥብቅ በሆነ አኳኋን እየመዘን በቁ የሆኑትን ብቻ በጨረታዎች ላይ እንዲሳተፉ እያደረግን ነው:: አሁን ላይ የአፈጻጸም ችግር ያለባቸውን ተቋራጮች በቀጣይ በሚኖሩ ጨረታዎች ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታዎችን የሚገድብ አሠራር እያስቀመጥን ነው::

ሌላው ከኮንተራክትር ጋር ተያይዞ ለሚነሳው በተመለከተ በሀገር አቀፍ ደረጃ የግዥ ሥርዓቱ እና የግዢ ሕጉ የሚያስቀምጠው የኮንትራክተር ማወዳደሪያ መስፈርቶች አሉ። እኛም በዚያ ሕግ የምንገዛ እስከሆን ድረስ በዚያው አግባብ እያንዳንዱን ሥራችንን እናከናውናለን:: ይሁን እንጂ ሀገር በቀል ተቋራጮች ላይ በጣም ጠንክር ያሉ ሥራዎችን መሥራት እንዳለብን ግንዛቤ ወስደናል::

አዲስ ዘመን፡- የፕሮጀክቶችን መጓተት ምክንያት በማድረግ የውጭ ዜጎች በወረዳ አመራሮች እስከ መታሰር ደርሰዋል:: እንደዚህ ዓይነት አካሄዶች የውጭ ግንኙነቶችን እንዳይጎዳ ምን እየሰራችሁ ነው?

ኢንጂነር መሐመድ፡ –ከውጭ የሥራ ተቋራጮች ጋር ያለን ሥራ ግንኙነት ውልን መሠረት ያደረገ ነው :: እንደመንግሥት መደረግ ያለበትን ድጋፍ ለእነርሱም ቢሆን እንደርጋለን:: ያላቸውን አፈጻጸም እንገመግማለን:: ከቻይና የሥራ ተቋራጮች ጋር በሚመለከት ከቻይና ኢምባሲ ጋር የጋራ መድረክ አለን:: በዚህም በእነሱ እና በእኛ በኩል የሚነሱ ችግሮችን አቅርበን እንወያያለን:: በየሶስት ወሩ እየተገናኘን አጠቃላይ አፈጻጸም እንገመግማለን:: የውጭ ዜጎችም ቢሆኑ ሕግን አክብሮ መሥራት ይገባቸዋል:: ኮንትራት ቢሆንም በሀገሪቱ ሕግ መገዛት ይገባቸዋል:: አንዳንድ ጊዜ ችግሮች ሲጋጥሙ ከእነሱ የበላይ የማኔጅመንት አባላት ጋር፤ አለፍ ሲልም ከኤምባሲያቸው ጋር የምንነጋገርበት አግባብ አለ። በዚህ ማዕቀፍ ሥራዎች እንዲሰሩ እያደረግን ነው:: የአፈጻጸም ግምገማችን ግን ከሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በተጨማሪ በውጭ ሀገራት ኮንትራክተሮችም ላይ ተፈጻሚ ይሆናል:: አፈጻጸም ላይ ጉድለት ካለ እንዲያሻሽሉ እና እንዲያስተካክሉ ማሳሰቢያዎችን እንሰጣለን:: በማያስተካክሉት ላይ ርምጃ እንወስዳለን::

አዲስ ዘመን ፡- በፕሮጀክቶች ላይ አንዱ የሚስተዋለው ችግር የወሰን ማስከበር ነው ? ከወሰን ማስከበር ጋር የሚነሱ ችግሮችን አስወግዶ ለኮንትራክትሮች ሁኔታዎቸን ምቹ ከማድረግ አንጻር በተጨባጭ ምን እየሠራችሁ ነው ?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕግ ማሻሻያ ተደርጓል:: ሊያሰራ የሚችል ወጥ የሆነ የሕግ ማሻሻያ መኖር እንዳለበት ስለታመነ ረቂቁ ለሕዝብ ተወካዮች ቀርቦ ጸድቋል።

ካሳን በሚመለከት በሁለት ዓይነት መልኩ ማየቱ ተገቢ ነው:: አንደኛው አግባብነት ያለው የካሳ ክፍያ የሚጠየቅበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አግባብነት የሌላው የካሳ ክፍያ የሚጠየቅበት ሂደት ነው:: አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሕገወጥ ግንባታዎች አሉ:: ይህ ማለት ካሳ ለማግኘት ሲሉ መንገዶች በሚያልፉባቸው ቦታዎች ላይ አዲስ ቤት ይሰራሉ:: አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ በጣም የተጋነነ ካሳ የሚጠይቅበት ሁኔታ አለ:: ይህን ደግሞ ማጣራት ግድ ይላል:: ስናጣራ ደግሞ የሚመለከተውን የዋጋ እና የሌሎች ጉዳዮችን ማስተካከያ እንጠይቃለን:: ማስተካከያ ስንጠይቅ ደግሞ ማስተካከያ የተጠየቀው አካል በአፋጣኝ ምላሽ የማይሰጥበት ሁኔታ ይኖራል:: በዚህም ፕሮጀክቶች ላይ መጓተቶችን ሲፈጥሩ ይስተዋላል:: የሕግ ማስተካከያው የተደረገውም ይህን ለማስታረቅ ጭምር ነው:: የተደረገው የሕግ ማሻሻያ ከካሳ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመሠረቱ ይቀርፋል ብለን እንናስባለን:: የሕግ ማሻሻያው እንዲጸድቅ እኛም እንደተቋም ከፍተኛ ድርሻ ነበረን:: በነገራችን ላይ ከካሳ ጋር በነበሩ ግጭቶች የእኛ ፕሮጀክቶችም ገፈት ቀማሽ ሆነዋል::

አዲስ ዘመን፡- ከሚዛን ቴፒ ያለውን መንገድ የሚሰራው የቻይና ተቋራጭ የኢትዮጵያ መንገዶች አገልግሎት በውላችን መሠረት የዶላር ክፍያውን ባለመፈጸሙ ማሽኖቻችን በመጠገን እና ወደ ሥራ መግባት አልቻልንም ይላሉ፤ በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው ?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ከክፍያ ጋር የተወሰነ መዘግየቶች ገጥመውን ነበር:: በዚህም በተወሰነ ደረጃ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ነበር :: አሁን ላይ ግን ተስተካክሏል:: ቅሬታ ሲያነሱ የነበሩ ተቋራጮችን ብትጠይቁ አሁን ላይ ችግሩ ተቀርፏል:: ይህን እውነታ ቅሬታውን ካነሱ ተቋራጮች ጭምር ጠይቃችሁ ማረጋገጥ ትችላላችሁ::

በዶላር የሚፈጸመው ክፍያ በአንድ ጊዜ መፍታት አዳጋች ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን አሁን ላይ ክፍያዎችን ጀምረናል:: በየደረጃው ለሁሉም የሥራ ተቋራጮች መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየከፈልን እንገኛለን::

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዓለም የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር መሐመድ፡- የዋጋ ግሽበት አጋጥሞናል፤ ፈትኖናልም:: ይህ በአጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመ ችግር ነው:: በኮቪድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር ተያይዞ የነዳጅ ዋጋ እና ሌሎች ግብዓቶች ላይ በተለይም ብረት ላይ ከፍተኛ የዋጋ መጨመርን አስከትሏል:: ይህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በፕሮጀክቶቻችን ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮብናል::

ከኮንትራት ጋር ተያይዞ በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ማሻሻያ እንድናደርግ የሚጠይቅ የኮንትራት ሁኔታ አለ:: ይህ ማሻሻያ በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ግሽበቱን እንድንቋቋም አድርጎናል:: ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ያካክሳል ተብሎ አይወሰደም::

የዋጋ ግሽበቱ በሥራ ተቋራጮችም ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳድራል:: ስለሆነም ለችግሩ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ መስጠትን ይጠይቃል::

አዲስ ዘመን፡- ለመንገዶች ጥራት መጓደል በተቋራጩ እና በተቆጣጣሪው መካከል የሚኖር ‹‹ሳቦታጅ›› አንዱ ምክንያት መሆኑ ይነሳል:: ከዚህ አንጻር ፕሮጀክቶች በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመሩ ለማድረግ በእናንተ በኩል ያለው አሠራር ምን ይመስላል?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ጥራት ጉዳት በእኛ በኩልም ትልቅ ትኩረት የምሰጠው ጉዳይ ነው:: ሰፋፊ ሥራዎች ሲሰሩ በባህሪው የጥራት መጓደል ያጋጥማል:: ነገር ግን ያጋጥማል ብለን ብቻ የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። መንገድ በትልቅ ካፒታል የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ትንሿ ጉዳት ትንሽ አይደለችም:: ስለሆነም በጣም ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት ሊኖር ይገባል:: እየሠራን ያለውም በዚያ ልክ ነው::

ከጥራት ጋር የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሶስት ነገሮችን ማከናወን ይጠይቃል:: አንደኛው የተቋሙን አጠቃላይ አቅም ማሳደግ ነው። ተቋሙ የሚሠራው ሥራ በርካታ ከሆነ እና ያለው አቅም ደግሞ ትንሽ ከሆነ የጥራት ጉድለት መፈጠሩ አይቀርም:: ስለዚህ ጥራቱን የጠበቀ መንገድ ለመሥራት የተቋሙን አቅም መገንባት ያስፈልጋል። ጥራት ያለው ሥራ ለመሥራት መጀመሪያ የምንሰረውን ሥራ እና ያለንን አቅም ማወቅ ያስፈልጋል :: በነበሩን ፕሮጀክቶች ላይ አንድ ፕሮጀክት ስንጨምር በዚያው ልክ አቅምስ ጨምረናል ወይ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል:: ፕሮጀክቶችን መጨመሩ ቀላል ሊሆን ይችላል አቅም መጨመር መቻል ግን ከባድ ነው::

ሌላው ከጥራት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ አሠራራችን መፈተሽ ያስፈልጋል:: ከዚህ አንጻር እኛም እንደ ተቋም አሠራራችንን እያየን እና መስተካከል የሚገባቸውን እያስተካከልን ነው::

በሶስተኛነት የጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ ጥራትን ኦዲት የሚያደርግ ክፍል ያስፈልጋል:: ከዚህ አንጻር ተቋማችን ጥራትን ብቻ የሚያይ የውስጥ ‹‹የኳሊቲ›› ክፍል አቋቁሟል:: ይህ ክፍል ዋና ሥራው መጠየቅ እና የአሠራር ሂደቱን ኦዲት ማድረግ ነው::

አሁን ላይ እንደ ተቋም ሶስቱን የችግር መፍትሔዎች ያማከለ ሥራ እየሠራን ነው:: ነገር ግን አሁንም በሚፈለገው ያህል ለውጥ አምጥተናል ማለት አንችልም::

አዲስ ዘመን፡- ለሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው ቡና እና ሌሎች ምርቶች የሚመረቱባቸውን አካባቢዎች የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ መንገዶችን ከመገንባት አንጻር ምን እየተሠራ ነው?

ኢንጂነር መሐመድ፡- ከመንገድ ፍትሃዊ ሥርጭት ጋር በተያያዘ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን:: የ10 ዓመት እቅድ ስናዘጋጅ በአጠቃላይ በመንገድ ዘርፉ ላይ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ነው:: የፍትሃዊነት ጥያቄዎችንም ሊያስተናግድ የሚችል አሠራር እየዘረጋን ነው::

አሁን ላይ በ10 ዓመት ውስጥ የሚሠሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለይተናል:: ፕሮጀክቶቹም የሚኖራቸውን የኢኮኖሚ ፋይዳ ለይተናል:: በአጠቃላይ ወደ 10 መስፈርቶችን በማውጣት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን ለይተናል:: ወደፊት እያየን የሚቀነሱ የሚጨመሩም ቢኖሩም በቀጣይ 10 ዓመትታ 108 ፕሮጀክቶችን በፌዴራል ደረጃ ለመሥራት አቅደናል:: የዲዛይን ሥራውም ተጀምሯል::

አዲስ ዘመን፡- በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት እንዲቋረጡ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ ምን ዓይነት ሥራዎች እየተሠሩ ነው?

ኢንጂነር መሐመድ፡– በግጭቱ ወደ 64 ፕሮጀክቶች ተቋርጠው ነበር:: 15ቱን ማስቀጠል ችለናል:: በ15 ፕሮጀክቶች ላይ የደረሰው ጉዳት በጣም ከፍተኛ ስላልነበር ማስጀመር ችለናል:: የሚቀሩትን ፕሮጀክቶች ተነጋግረን በየደረጃው ወደ ጨረታ እንዲገቡ ተወስኗል:: ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማስጀመር ስለማይቻል በየደረጃው እንዲሠሩ ይደረጋል::

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመስግናለን::

ኢንጂነር መሐመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ

በሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You