ትውልደ ኢትዮጵያዊው መኮንን ተክለአብ በካናዳ መኖር ከጀመረ 18ዓመታትን አስቆጥሯል። በአሁኑ ወቅት ኑሮውን ከተለያዩ አገራት ስፖርተኞችን በመምረጥ የውድድር መድረክ እንዲያገኙ እድሉን ያመቻቻል። 20ዓመታትን በትዝታ ወደ ኋላ ተጉዞ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበረው የማርሻል አርት የስፖርት ሁነቶች ደካማነትን ያስታውሳል። በወቅቱ በተለይ የማርሻል አርት የስፖርት ትጥቅ ችግር መኖሩንና ስፖርተኞች ሲማረሩበት እንደነበረም ይገልጻል። የነበረው ችግር በአእምሮ ውስጥ ተስሎ ከውስጡ ባለመጥፋቱ ዛሬ ላይ በለስ ቀንቶት አገር ቤት ውስጥ ላሉት ስፖርተኞች ድጋፍ ለማድረግ ከካናዳ ተነስቶ አዲስ አበባ ከትሟል። በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በኩል ለሚመለከታቸው አካላት የትጥቅ ድጋፍም አድርጓል።
ይህንን ጅምር ተግባር ለማስፋትም ከመሰል ዳያስፖራዎች ጋር በአብሮነት እንደሚሰራ ይናገራል። አገር ቤት ላሉት ስፖርተኞች ከቁሳዊ ድጋፍ ባሻገር ሙያዊ እገዛ ያስፈልጋል የሚለው መኮንን፤ ይህን በመስራት ረገድ የዳያስፖራው ጥረት ከፍተኛ እንደሆነ፤ እርሱና መሰል ባለሙያዎች በተለያዩ አገራት የሚካሄዱ ውድድሮችን ለመካፈልና ውጤት ለማስገኘት የሚያስችል ሥልጠናዎችና የውድድር መድረኮችን እንደሚያመቻቹ ጠቅሷል። ‹‹በሌላው አገር የሚሰጠው የስፖርቱ ሳይንስ በአገር ቤትም በሚገባ እንዲለመድና የእውቀት ሽግግሩ እንዲኖር አገሩን ከሚወድ ዳያስፖራ የሚጠበቅ በመሆኑ ለስራው መሳካት ወደ ኋላ አንልም›› በማለት ከዘርፉ ባለሙያ የሚጠበቀውን ተግባር አስታውቋል። መኮንን፤ በቅርቡ የ‹‹ሚክስድ ማርሻል አርት›› ባህልን ሊያስተዋውቅ የሚችል የስፖርት ሁነቶች በኢትዮጵያ ደረጃ እንደሚዘጋጁ ገልፆ፤ የሚክስድ ማርሻል አርት ስፖርታዊ ውድድር በአፍሪካ ደረጃ ያለው ይዞታ አነስተኛ በመሆኑ ስፖርቱ በሌሎች አህጉራት ተወዳጅነትን ስላገኘ ልምዶችን በመቅሰም ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው አፍሪካ ታዋቂ እንዲሆንና ተወዳጅ እንዲሆን ለማድረግ የቅድመ ዝጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጿል።
እንደ መኮንን ማብራሪያ፤ የሚክስድ ማርሻል አርት ስፖርት በዓለም ላይ ተወዳጅነትን ካገኘ 20ዓመታት ቢሆነውም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ተግባራዊ አልተደረገም። ስፖርቱ እንዲተዋወቅ ውድድሮችን እ.ኤ.አ በ2018 ለማካሄድ ታስቦ የነበረ ሲሆን፤ ምቹ ሁኔታዎች ባለመፈጠራቸው ምክንያት በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ይሳካል። በሚካሄደው ውድድር ላይም ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸውን የውጭ አገራት ተጫዋቾች በመጋበዝ ልምድ እንዲያካፍሉ ይደረጋል። ለዚህ ስኬት የሚክስድ ማርሻል አርት ቢሮውን አዲስ አበባ ላይ በማድረግ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የማስፋፋት ስራም ያከናውናል። ስፖርተኞችን ከአገር ቤት በዘለለ በአለም አቀፍ ደረጃ በኦሊምፒክ የውድድር መድረኮች ላይ ለማብቃት የሙያው ባለቤት የሆኑ ዳያስፖራዎችን መጠቀም ያስፈልጋል። ‹‹በአገሪቱ አሁን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ የተሻለ በመሆኑ በስፖርቱ ዘርፍ ያሉ ዳያስፖራዎችም ለአገራቸው የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፉ ይገባል። ጊዜው ሰላምና አንድነት የሚሰበክበት እንደመሆኑ ማንም ሰው ችሎታውን ይዞ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያየ መስኩ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
ለዚህ መልካም ህዝብ እውቀትን መለገስ የአንድነቱን ውጤት የሰመረ እንዲሆን ያደርገዋል›› በማለት የተደረገውን ጥሪ ተቀብሎ እየሰራ መሆኑንም መኮንን ይናገራል። ‹‹የሰው ልጅ በአንድ እጁ አያጨበጭብም። ሁለተኛውን ከጨመረበት ነው የበለጠ ድጋፍ የሚኖረውና ድምጽ ማውጣት የሚቻለው። ነገሩን በስፖርት አይን ብንመለከተው በስደት ምክንያት ከአገር የወጡና አገርን ሊረዱ የሚችሉ በርካታ የስፖርት ባለሙያዎች ስላሉ እውቀታቸውን በመጠቀም አገርን መለወጥ ስለሚቻልበት አቅጣጫ ላይ መነጋገር ተገቢ ነው›› ሲል ያብራራል። አክሎም ‹‹እኛ ውጤታማ ተጫዋቾችን ከየአገራት በመመልመል የውድድር ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ ስለሆንን ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች የዚህ እድል ተቋዳሽ እንዲሆኑ እንሰራለን›› በማለት በቀጣይ ስለታሰበው ሥራም ያስረዳል። የመኮንን ሀሳብና ፍላጎት መነሻ በማድረግ ባላቸው ሙያ ስፖርቱን ለመደገፍ አሜሪካ ሜሪላንድ ስቴት ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የሚናገሩት ሌላኛው ዳያስፖራ አቶ ኢሳያስ ጸጋዬ ‹‹አገር ቤት ገብቶ ይህንን ድጋፍ ለማድረግ ብዙ ጥሪዎች ነበሩ።
እነዚህን ጥሪ ተቀብለን ነው የመጣነው። በዚህም መሠረት ከተማዋ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን ከጎንዮሽ ሱሶችና አልባሌ ሥፍራ ከመዋል እንዲቆጠቡ እንሰራለን›› ብለዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብዙ የማርሻል አርት ስፖርተኞች ወጣቶች የሆኑና የተሻለ ተስፋ ያላቸው በመሆናቸው ሊታገዙ የሚችሉበትን አጋጣሚ በመፍጠር ሚናችንን እንወጣለን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚተገበሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት የተገኘባቸው ስፖርቶች ውስን ናቸው። በተለይ በማርሻል አርት ስፖርት ከተሳትፎና ስልጠና የዘለለ ብዙ ውጤት አይታይበትም። ይህንን ከማጠናከር አንጻርም ለአገሩ እንደሚቆረቆር ዳያስፖራ በሁሉም ደረጃ ድጋፍ ለማድረግ እንሰራለን። ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም በቂ ባለመሆናቸው በቀጣይ በሙሉ አቅም ወደ ተግባር እንገባለን።
እስከ ዛሬ መሳካት ያልተቻለው አገር ቤት ገብቶ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የመስራት እድሉ ስላልተገኘ ነው።›› በማለት የዳያስፖራ ስፖርተኞችን ዓላማ ለማሳካት ወቅቱ የተመቻቸ መሆኑን አስረድተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ስፖርትን በማገዝ ወደ አገር ቤት የመምጣቱ ዋና ዓላማ የሚክስድ ማርሻል አርት ስፖርትን በአገር ውስጥ ከማስተዋወቅ በዘለለ ወጣቶቹ የስፖርቱን ህግጋት ጠንቅቀው እንዲረዱና ከዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ጋር ተፎካካሪ እንዲሆኑ ነው። በሰለጠኑት አገራት እየተስፋፋ የመጣውን የሚክስድ ማርሻል አርት ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ግንባር ቀደም በማድረግና ‹‹የሚክስድ ማርሻል አርት ማዕከል›› ለማድረግ ታስቧል። ይህ እንዳለ ሆኖ ስፖርቱን በማስለመድ ሂደት ውስጥ ፈተናዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ዳኞችና ቴክኒካል ባለሙያዎች ያስፈልጓታል።
ይህንን ለማሳካት በቅደም ተከተል የሚሰሩ ስራዎች ይኖራሉ። «ስፖርተኞችን ከልጅነታቸው ኮትኩቶ ማሳደግ ይገባል» የሚሉት አቶ ኢሳያስ፤ ልክ እንደ ሩጫና እግር ኳስ በሚክስድ ማርሻል አርትም ከልጅነታቸው ጀምረው ውጤታማ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የሥልጠና ሂደቱ ከሚመለከተው የስፖርት ቢሮና ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር እንደሚከናወንም አስረድተዋል። አቶ ኢሳያስ፤ የሚክስድ ማርሻል አርት ስፖርት በሌላው አገር ከተወዳጅነቱ አልፎ ወደ ቁማርነትም እያመዘነ መሆኑን ጠቁመው፤ ስፖርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲስፋፋ ትኩረቱን የሚያደርገው ጨዋታ ላይ ብቻ እንደሆነና ለሌላ ዓላማ መጠቀሚያ እንደማይሆን አስታውቀዋል። ለዚህም ዳያስፖራዎች በፍላጎት እንጂ ለግል ጥቅም እንደማይሰሩ አሳስበዋል። ሚክስድ ማርሻል አርት ራሱን የቻለ ህግጋትና መርኆዎች ያሉት የብዙ ማርሻል አርት ስፖርቶች ጥምረት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
አዲሱ ገረመው