በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪ ያዎቹ ዓመታት ወቅት ትልቅ ሚናና ወሳኝ አስተዋፅዖ የነበራቸው ራስ ደስታ ዳምጠው ከተማ የተገደሉት ከ82 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (የካቲት 16 ቀን 1929 ዓ.ም) ነበር። ራስ ደስታ ዳምጠው በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ለአገራቸው ነፃነትና ክብር ከጠላት ጦር ጋር የተፋለሙ አገረ ገዢና አርበኛ ናቸው። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ሲወር ራስ ደስታ ዳምጠው የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት አገረ ገዢ ነበሩ።
ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የከፋ ገዢ ሆነው አስተዳድረዋል። በነገሌ ቦረና በኩል የመጣውን የጠላት ጦር ለመመከትም ወደአካባቢው ዘምተው ተዋግተዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ በሶማሊያ በኩል ከመጣው የፋሺስት ጦር ጋር በተደረገው ውጊያና በማይጨው ጦርነት ተሳትፈው ለአገራቸው ሉዓላዊነት ተፋልመዋል። ራስ ደስታ ከአርበኝነታቸው በተጨ ማሪ፣ የአውሮፓንና የአሜሪካን ዘመናዊነት ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት መንገድ፣ የንፁህ ውሃ አገልግሎት፣ የህክምና፣ የትምህርት ወዘተ… ተቋማትን ለማስፋፋት የበኩላቸውን ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። የነጮችን ዘመናዊነት ለመቅሰም ፍላጎት ቢኖራቸውም ‹‹ነጮችን አያምኑም›› ይባል ነበር። ራስ ደስታ በ1923 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ተጉዘው እንደነበርና ከወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት ጋር ተገናኝተው እንደተመለሱ ታሪካቸው ያሳያል። ራስ ደስታ ለአንድ ዓመት ያህል የፋሺስትን ጦር እየተፋለሙ ቆይተው የካቲት 16 ቀን 1929 ዓ.ም በባንዳዎች ተይዘው ለፋሺስት ጦር ተላልፈው ተሰጡ። የፋሺስት ጦርም በጥይት ደብድቦ ገደላቸው።
በዚሁ ዕለት የፋሺስትን ጦር ሲዋጉ የነበሩትና ከራስ ደስታ ጋር አብረው በፋሺስቶች እጅ የወደቁት የባሌና ጋሞ ጎፋ አገረ ገዢው ደጃዝማች በየነ መርዕድም ተገደሉ። የፋሺስት ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ አፅማቸው በቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያንበክብር እንዲያርፍ ተደርጓል። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ‹‹ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል›› ለእርሳቸው መታሰቢያ የተሰራ ነው። የራስ ደስታ አባት፣ ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ፣ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ጀብዱ የፈፀሙ ጀግና እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። ሕይወታቸውም ያለፈው በዓድዋ ጦርነት ወቅት ነው። የራስ ደስታ ዳምጠው ባለቤት የንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ልጅ ልዕልት ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ ነበሩ። ከትዳራቸ ውም ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታን (የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የባ ህር ኃይል አዛዥ)ን፣ ልዕልት አይዳ ደስታ (የልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ባለቤት)ን፣ ልዕልት ሰብለወንጌል ደስታ (የደጃዝማች ካሳ ወልደማርያም ባለቤት)ን፣ ልዕልት ሶፍያ ደስታ የካፒቴን ደረጀ ኃይለማርያም (በ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት የተገደሉ የጦር ኃይሉ ባልደረባ ባለቤት)ን፣ ልዕልት ኂሩት ደስታ (የጀኔራል ነጋ ተገኝ ባለቤት)ን አፍርተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
አንተነህ ቸሬ