ጳውሎስ ኞኞ «አጤ ምኒልክ» በተሰኘ መጽሐፉ ተከታዩን አስነብቧል። አጼ ምንልክም አሉ፤ «አንድ ነገር ሰማሁ። ይሄ የሰማሁት ነገር እኔን ትንሽ ያደርግና ከነቤተመንግሥቴ፣ ሌላው ቤት ሁሉ፣ ህዝቡ፣ በቅሎው እና ፈረሱ ሁሉ ሳይቀር እትንሽ ጥቁር ሳጥን ውስጥ ይጨምረናል አሉ። ይሄ ነገር ፈፅሞ የማይቻል ነገር ነው እንዴት ሊሆን ይችላል?» ከዚህ በኋላ ካሜራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ታዝዞ ካሜራው ከነ ፎቶግራፍ አንሺው በ1875 ዓ.ም. መጣ። ያኔም የፎቶግራፍ ማንሻው አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ አጼ ምኒልክ ፎቶ እንዳይነሱ ቀሳውስቱ አስፍራርተዋቸው ነበር። ሆኖም ግን አጼ ምኒልክ ምክሩን ሁሉ ወደ ጎን በመተው የመጀመሪያውን ፎቶ በግንቦት 13 ቀን 1875 ዓ·ም ተነሱ። እንግዲሀ ያኔ በዛን ዘመን የጀመረ የፎቶግራፍ ጥበብ አድጎ የ«ሰልፊ» ዘመን ላይ ደርሰናል።
ምናልባት ያኔ ሳይሆን አሁን ነበር መሰለኝ ቀሳውስቱም ሆኑ ሕዝቡ ተነሺዎችን ማስፈራራት ያለባቸው። ለምን ብትሉ ይሄ ሰልፊ የሚባል ነገር ስንት ጣጣ እያስከተለ እንደሆነ ዜናው ይቆጠር የሚያስብል ሆኗል። አሁን ከሰሞኑ ባህርማዶ በአሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ የሆነው ዜና ጉድ ያስብላችኋል። የሆኑ ጓደኛማቾች ሰብሰብ ብለው ራሳቸውን ካፍታቱና ከተዝናኑ በኋላ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ አንዱ ጦሰኛ አንድ ሃሳብ ይመጣለታል። ይህም በከተማው ከሚገኘው ትልቁ ድልድይ ላይ ወጥተው ከተማዋን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይና እነርሱንም ያካተተ ፎቶ መነሳት የሚል ነው። ጓደኞቹም ሃሳቡን ተቀብለውና ተስማምተው መኪናቸውን አቁመው ማርጋሬት ማክዴርሞት ወደሚባለው ወደዚህ ድልድይ ይወጣሉ። ከጓደኛማቾቹ መካከል ትሪስተን ቤይሊ የተባለው የ18 ዓመት ልጅ ይገኛል። ቡድኑ ሰብሰብ እንዳለ ሁሉም ድልድዩ ላይ በጋራ ወጡ። ይህም ልጅ ለፎቶ አመቺ የሆነውን እይታ እየፈለገ ሳለ ድንጋይ አደናቀፈውና ይወድቃል። ጓደኞቹም በየፊናቸው ጥሩ የሚባልና ለፎቶ ጥሩ እይታ የሚሰጠውን አቅጣጫ ሲፈልጉ ስለነበር ልብ አላሉትም፤ ጩኸቱን እስኪሰሙ ድረስ። ጩኸቱም ቢሆን ቀልድ ነው የመሰላቸው። ይሁንና ያሰቡትን ፎቶ አንድ እንኳ ሳይነሱ ጓደኛቸውን አንቡላንስ ደርሶ አነሳው።
ወደ ሆስፒታል ተወስዶ የህክምና ባለሙያዎቹ ሲመለከቱት እንደ እኛ አገር ሰው ከንፈር አልመጠጡም እንጂ በልባቸው ይተርፋል የሚል ሃሳብ አልነበራቸውም። ዶክተር ዮሴፍ የተባሉና በህክምና ማዕከሉ ኃላፊ የሆኑ ሰው በንግግራቸው ልጁ በወደቀ ጊዜ ሳንባው እንደተጎዳ፣ አጥንቱም እንዳልተረፈ ተናግረዋል። እንዲያውም ፎክስ4 ለተባለው የዜና አውታር «ይሄማ ተዓምር ነው» ነበር ያሉት። ሌሎችም ዶክተሮች ቢሆኑ የሆነውን አይተው «አንገቱስ አለመቀጨቱ!» አሉ። ብቻ እነዚህ የህክምና ባለሙያዎች ልጁ እንደአወዳደቁ ቢሆን ከመሞት በባሰ ሊደርስበት ስለሚችለው ጉዳት ሁሉ ዘርዝረው ተናግረዋል። ግን በሚገርም ተዓምር በሕይወት ተርፏል። የ18 ዓመቱ ቤይሊ «ኧረ መትረፍህም ትልቅ ነገር ነው፤ በል ዝም በል!» የሚሉት ሳይበዙ አልቀሩም እንጂ፤ በሰልፊ ምክንያት የደረሰበት አደጋ በአገሩ አየር ኃይል አባል ለመሆን የነበረውን እቅድ እንዲያዘገይ አድርጎታል። በየሳምንት ሁለት ጊዜም ቴራፒ እንዲከታተል ተነግሮታል። አሁን ጤናው መለስ ሲል ያንን የወደቀበትን ድልድይም ሄዶ ጎበኘ።
ድልድዩን ብቻ አይደለም ፎቶ ሊነሳበት የነበረውን ተንቀሳቃሽ ስልኩ ያለአንዳች ጉዳት በሙሉ ደኅንነት ላይ መሆኑን ሲያይም የሆነውን ሁሉ ያስታውሳል። «ከሰልፊ በፊት ሴፍቲ» ብሏልም አለ፤ ዜናውን የዘገበው ፎክስ ኒውስ ነው። «ሌላ ሰው ሰልፊ ሊነሳ ከፍታ ቦታ ላይ ሲሆን ሳይ ቆም ብዬ ‘ጥሩ ሃሳብ አይመስለኝም’ ማለት ጀምሬአለሁም» አለ። ይህንና ሌሎችን ራስን ፎቶ ለማንሳት በሚደረግ ጥረት የሚደርስ አደጋ ለመቋቋም ጥናት መደረጉንም በዛው ሰምተናል። የጥናት ባለሙያዎቹ አንዳንድ ቦታዎች በተለይም ጎብኚዎች በብዛት የሚገኙባቸው ከሆነ፤ «ሰልፊ ክልክል ነው» የሚል ማሳሰቢያ ሊኖር ይገባል ብለዋል። እንግዲህ ይህ ዛሬ በአውሮፓ የተሰማ ዜና በቅርቡ የአገራችን ዜና እንዳይሆን ያሰጋል። ሰዎች ገንዘብ ሲሰጡና ሰው ሲያጎርሱ ብቻ ሳይሆን በግርግር መካከል መገጫጨቱን ሳይፈሩ፣ እየበሉ ትንታ ሳያሰጋቸው፣ አስፋልት መካከል ሆነው መኪና አደጋን ረስተው «ሰልፊ» ሲለቁ እናያለን። ይሄ እየሰመጠና እየሞተ ያለን ሰው ከማዳን ይልቅ ፎቶ ለማንሳት ካለው ውድድር የባሰ ነው። እየሰመጡ ራስን ፎቶ ወደማንሳት ስለሚወርድ። እና ምን ለማለት ነው፤ «ከሰልፊ በፊት ሴፍቲ» ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
ሊድያ ተስፋዬ