በኢትዮጵያ በፖለቲካ ጫና ምክንያት በታሪክ አረዳድ በተደጋጋሚ የአስተሳሰብ ህጸጾች ይስተዋላሉ። ይህ ደግሞ በመጭው ትውልድ የአስተሳሰብ መርህ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩ አይቀርም። ይህንን ተከትሎ ራሱን በትክክለኛው የታሪክ አረዳድ ውስጥ ያስገባ ትውልድ ማነጽ እንደሚያስፈልግ ምሁራን ይመክራሉ። ታሪክን በትክክለኛ መንገድ ከትክክለኛ ምንጭ የመረዳትን እሳቤ ከግምት በማስገባት፤ የታሪክ ምንነትና ጠቀሜታ፣ታሪክን በዜግነትና በብሄር የፖለቲካ መነጽር የማየት ሁኔታ፣ የታሪክ አረዳድ መንሸዋረር መንስኤዎችና ውጤቶች እንዲሁም እንዴት ይቃኑ ለሚሉ መሪ ሀሳቦች ማብራሪያ እንዲሰጡን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የታሪክና ሥነ ጥበብ መምህር ከሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የታሪክን ምንነትና ፋይዳውን በማስቀደም ቆይታችንን እንጀምር?
ረ/ፕሮፌሰር አበባው፡- ታሪክ በሁለት ነገሮች ሊታይ ይችላል። የመጀመሪያው ያለፈውና ከዚህ ትውልድ በፊት የነበረው ማኅበረሰብ ሥልጣኔ ከጀመረበት አነሰ ቢባል ከ5ሺ ዓመተ ዓለም ጀምሮ አሁን እስካለው ትውልድ የተከናወኑትን ድርጊቶች አጠቃልሎ የያዘ ነው። ይህም የታሪክ ዘመንና ቅድመ ታሪክ ተብሎ በሁለት ይከፈላል። የታሪክ ዘመን የሚባለው ከ5ሺ ዓመተ ዓለም በፊት የነበረው የሰው ልጅ ወደ ሥልጣኔ ከመጣበት ጊዜ እስካሁን ያለው ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የሰው ልጅ ድርጊቶች በሙሉ ታሪክ ተብለው ይወሰዳሉ። በእርግጥ ያለፈን ድርጊት በዚህ ጊዜ ‹‹ይህ ተከናወነ፤ ይህ ህዝብ ይህን አደረገ›› ብሎ የሁሉንም ሙሉ ነገር ማወቅ አይቻልም። ሥለዚህ ይህ ጠበብ ወዳለው ሁለተኛው የታሪክ ትርጉም ይወስደናል። ይኸውም ታሪክ የምንለው እንደገና ‹‹ይህ ተደርጎ ነበር›› ወይም ‹‹ሪኮንስትራክሽን›› ብለን ወደ እውቀት የምናመጣው ያለፈ ሁነት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የግድ ምንጭ ያስፈልጋል።
በአንድ ወቅት አንድ ድርጊት የፈጸመ፣ አገር የመሰረተ፣ ስልጣኔን የጀመረ፣ ጦርነት ያደረገ፣ የተለያዩ አምልኮዎችን ሲያከናውን የነበረ ማኅበረሰብ እንዲያው ዝም ብሎ በንኖ አይጠፋም። የጽሁፍም ሆነ የቁስ ምንጮችና መረጃዎች ይኖራሉ። የቆየ ህንጻ በወቅቱ ስለነበረው ማኅበረሰብ ይነግረናል። ስለዚህ ታሪክ የሚባለው ሁሉንም ነገር ስለማናውቅ ከመረጃዎችና ከምንጮች ተነስተን የተከናወኑትን ድርጊቶች ፈልገንና መርምረን እውቀት አድርገን የምናመጣው ነው። ታሪክ ብዙ ጥቅም አለው። አሁን ያለው ማኅበረሰብ ዝም ብሎ ድንገት ከሰማይ የመጣ አይደለም። ያለፈው ማኅበረሰብ ውጤት ነው። አሁን የደረስንበት የቴክኖሎጂው ውጤት ካለፈው ጋር የተያያዘ ነው። ሥለዚህ ያለፈ ነገር የማንኛውም ህብረተሰብ ሀብትና ውርስ ነው። በመሆኑም አልፏልና አይጠቅምም ተብሎ የሚተው ሳይሆን በየትኛውም አገር ያሉት ህዝቦች ትልቅ ሀብት አድርገው እንደሚወስዱት ተገንዝቦ መጠቀም ያሻል። ስለዚህ ያለፈ ነገር ታሪክ ተደርጎ ተዘክሮ መታወቅ አለበት። ፋይዳውም ትልቅ ነው። የሰው ልጅ በረጅም ዘመን ታሪኩ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። ጦርነቶችን አካሂዷል፣ መጥፎ አጋጣሚዎች ተከስተውበታል፤ በተቃራኒው ደግሞ በጎ ነገሮችንም ተምሮበታል። ታሪክም እንደሚያሳየን ከበጎ ነገር እንማራለን፤ ከመጥፎ ነገር ደግሞ እንቆጠባለን። የናዚ ጀርመኖች ጭፍጨፋ ሲታሰብ ጥሩ ነገር ተሰርቷል ተብሎ አይደለም። መጥፎም ቢሆን ታሪክ በመሆኑ ይዘከራል። መዘከሩ ደግሞ የሰው ልጅ ወደ ፊት ከእንደዚህ አይነት መጥፎ ድርጊት እንዲቆጠብ መማሪያ እንዲሆነው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ታሪክን በዜግነትና በብሄር ፖለቲካ መነጽር እንዴት ያዩታል?
ረ/ፕሮፌሰር አበባው፡- ታሪክ በዜግነትም ሆነ በብሄር ፖለቲካ የሚታይ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ታሪክ ውስብስብ ነው። አንድ ህዝብ ለብቻው ተለይቶ የራሱ ብቻ የሆነና የሌላውን የማይነካ ታሪክ የለውም። አንዱ ከሌላው ህዝብ ጋር መስተጋብር ነበረው። ስለዚህ ከመጀመሪያው ጀምሮ ይብዛም ይነስም በታሪክ ውስጥ ብዙ ህዝቦች ይገናኛሉ። የኢኮኖሚ፣ የባህልና የፖለቲካ መስተጋብር አለ። ይህን ሁሉ አጠቃለን ነው ታሪክ ብለን የምንወስደው። ነጥሎ የዚህ ህዝብ ታሪክ ሊባል አይችልም። በእርግጥ እዚህ ላይ የባህል፣ የወጉና የልማዱ ታሪክ ከሌላው ለየት ሊል ይችላል። በዚህ ብቻ ቢለይም በሌለው ግን የተሳሰረ ነው። በመሆኑም ወጥ የሆነ የአንድ ጎሳ ታሪክ ወይንም አንድን ብሄር ይዞ የዚህ ህዝብና ብሄር ታሪክ ሊባል አይችልም። ሁሉም የብቻዬ የሚለው ታሪክ ሊኖረው አይችልም። ከዚህ አልፎ አገራትም በታሪክ ይተሳሰራሉ። የህዝብ ትስስሩን መለየት አይቻልም። የኢትዮጵያ ታሪክ ብለን ስንወስድ ብዙ ውጣ ውረድ አለበት። ኢትዮጵያ አሁን ያላትን የጂኦ ፖለቲካ ቅርጽ የያዘችው በቅርብ ጊዜ ነው። ማዕከላዊ መንግስቱ ደግሞ ከጥንቱ ጀምሮ ሲወራረስ የመጣ ነው። በወቅቱ ማዕከላዊ መንግስቱ አንዴ ሲሰፋ አንዴ ሲጠብብ ነበር። ከድሮ ጀምሮ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ወሰን ሁሉ ሲያስተዳድር አልነበረም። ከዚያም አልፎ ከማዕከላዊ መንግስት ውጭ በየቦታው ትንንሽ መንግስታትም ነበሩ። ለምሳሌ የሀዲያ፣ የከፋ፣ የሀረር ወዘተ… ሱልጣኖች የሚያስተዳድሩት መንግስታት ነበሩ።
ይህን ሁሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ያጠቃልለዋል። ሲያጠቃልል ደግሞ ለምሳሌ ጋምቤላ ወደ ኢትዮጵያ ክፍል የገባው በ1902 በመሆኑ ታሪኩ መነሻው ከዚህ ዓመት ጀምሮ ነው ሊባል አይችልም። በዚያ ወሰን ውስጥ ያለው የኑሮ ታሪክና አፈ ታሪክ እስከ ጥንት የሚሄደው ሁሉ የኢትየጵያ ታሪክ አካል ሆኖ ይጠቃለላል። በአጠቃላይ ታሪክ ሲታሰብ ሰፊ ነው። ዝም ብሎ የጂኦግራፊ ወሰን ለማበጀት እንጂ ኢትዮጵያ እንኳን ለብቻዋ አይደለችም። ታሪክን ለማጥናት እንዲመች በሁለት እንከፍለዋለን።
የመጀመሪያው በጂኦግራፊ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ ታሪክ ወዘተ… በማለት መውሰድ ይቻላል። ኢትዮጵያና ግብጽን የሚያስተሳስራቸው ቢኖርም በመልክዓ ምድር እንከፋፍለዋለን። ሌላኛው ዘመነ መሳፍንት፣ መካከለኛው ዘመን፣ ወዘተ…ብለን በዘመን የምንከፍለው ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ ስናነሳ አሁን ባለው ወሰን ውስጥ ያለውን የህዝብ ታሪክ ከመሰረቱ ጀምሮ የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ ይወሰዳል። ኢትዮጵያዊ በመሆን የተወረሰ ስለሆነ ታሪካችን ነው እንጂ እንደ ፖለቲካው የብሄርም ሆነ የዜግነት ተብሎ አይወሰድም።
አዲስ ዘመን፡- በቀደመው ጊዜ ታሪክን በከፊል በሚያውቀውና ከ27 ዓመት ወዲህ ባለው ህብረተሰብ መካከል ያለውን የታሪክ አረዳድ ምን ይመስላል?
ረ/ፕሮፌሰር አበባው፡- በቅርብ ጊዜ የመጣው የፖለቲካ ጫና የፈጠራቸው የሀሰትና የተዛቡ ታሪኮች አሉ። በአገራችን ላይ በታሪክ አረዳድ፣ በታሪክ ትምህርትና በታሪክ እውቀት ላይ ትልቅ ውዝግብ እየፈጠረ ያለው ፖለቲካው ራሱ የሚፈጥራቸው ታሪኮች ናቸው። መገለጫዎቹም ታሪክን በተሳሳተ መንገድ መተርጎም፣ ታሪክ መፍጠር፣ ታሪክን ለይቶ የእገሌ ታሪክ ነው በማለት ከፋፍሎ መስጠት ናቸው። የሰው ልጅ በታሪኩ ብዙ ውጣ ውረዶችን ስላለፈ አንዱ በአንዱ ላይ ይነሳል።
በአንድ ወቅት አንዱ ሌላውን ሊበድል ይችላል። የፖለቲካ ኢኮኖሚ ታሪኩንም ስናይ የመጋፋት፣ የመበዝበዝና የመገዛት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። የኢትዮጵያ ታሪክ ስንል ኢትዮጵያ እስካሁን ለደረሰችበት ዘመን በየዘመኑ የተደረጉ ነገሮች ይጠቀሳሉ። ይህንን ለፖለቲካ ጥቅም ብቻ ብሎ ለአገሪቱ አለማደግና ኋላ ቀር መሆን ተጠያቂው እገሌ ነው በማለት ታሪክን መመንዘር አይገባም። ፖለቲካ ታሪክን ሁልጊዜ ከመሠረቱ አይመረምርም። አንዲት ነገር ይወስድና ለራሱ ጊዜያዊ ግብአት ይጠቀማል።
ይህ ከ1966ዓ.ም ሶሻሊዝም ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ በስፋት ሲደረግ የነበረ ነው። አሁን ላይ ነገሩ ተባብሶ ታሪክን የብሄር ብሄረሰብ በማለት ከፖለቲካው ጋር እኩል የማስኬድ ሁኔታ መጣ። የኢትዮጵያ ታሪክ የሚለው ቀረና እያንዳንዱ በየፊናው የእገሌ ታሪክ እያለ ትስስሩን ትቶ ለብቻ ማሰብ ጀመረ። ታሪክን ማጋነንና በተሳሳተ መንገድ መተርጎም እንዲሁም የታሪክ ሽሚያ መፍጠርም ይስተዋላል። ለምሳሌ የአድዋ ድል ሁሉም የኢትየጵያ ህዝብ በጸሎትም ይሁን በጦርነት ተዋግቶ ያመጣው ድል ነው። ይህ ሆኖ እያለ ‹‹የድሉ ባለቤት እኛ ነን፤ እገሌ ባይኖር ድል አይገኝም ነበር›› በማለት ከፖለቲካው ጫና የተነሳ የተዛባ ትርጉም የሚሰጡት አሉ። ከዚህም አልፎ ታሪክን አዛብቶ መተርጎምም ይታያል። ‹‹የሰሜኑ አካባቢ የደኸየው የመሃል አገር ሰራዊት እየመጣ በጦርነትና ሌሎች ምክንያት ባላገሩን በመበዝበዙና በመጨቆኑ ነው›› በማለት የማይሆን ነገርና ምንም ምንጭ የሌለው በፖለቲካ ብቻ የተቃኘ የታሪክ አተረጓጎም መጥፎ ነው። ከዚህ አልፎ የሀሰት ታሪኮችም ይፈጠራሉ። ልክ እንደ አኖሌ ያሉ ታሪኮች ማለት ነው። አኖሌን ከዛ በፊት ለምን አልሰማንም?፣ ለምንስ አልተቀነቀነም? ምኒልክ ወደ አርሲ ሲዘምት የሸዋውንም የሰላሌውንም ጦር በራስ ዳርጌ ሥር አድርጎ ነው ይዞ የሄደው። የራስ ጎበና ጦርም ነበር። ከጉራጌ አካባቢ የሄደም ብዙ ሰራዊት ነበር። የለም የአማራ ሰራዊት ነው የመጣው ተብሎ ለምን ተወሰደ? በውጊያው ጊዜ አርሲ በቀላሉ እጅ አልሰጠም ከሁለቱም ወገን ሰው አለቀ። በኋላ የተማረከውን ባሪያ አታድርጉት ፍቱት ልቀቁት ብለው አስለቅቀውታል። ጡት ተቆረጠ የሚባለው ከዬት መጥቶ ነው? ለግዳይ ተብሎ ወንድ ልጅን መስለብ ጨምሮ እጅና እግርን መቁረጥ የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ታሪክ እንስት ላይ እንዲህ የሚጨክን ማኅበረሰብ አልነበረም። በፖለቲካው የሀሰትና ፈጠራ ታሪኮች ሆን ተብለው እንዲሰራጩ ይደረጋል። ለአገር የሞቱ ጀግኖችን ከፋፍሎ የኔ ነው ማለት። ይህ ሁሉ በታሪክ አረዳድ በተለይ በአዲሱ ትውልድ ላይ ትልቅ ውዥንብር የፈጠረ ነው። ይህንን ያመጣው የአገሪቱ የፖለቲካ ቅኝት ነው። ፖለቲካው ከታሪክ እጁን መሰብሰብ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የተደበላለ ቀና ታሪክን የዘነጋ አካሄድ ከምን የመነጨ ነው?
ረ/ፕሮፌሰር አበባው፡- ይህ የሆነው ከግብዝነት የተነሳ ነው። ታሪክ ሊተውና ሊቀየር የማይችል ነገር ነው። ከ1983ዓ.ም ጀምሮ የመጣንበት የፖለቲካ መፍጨርጨርና ፖለቲካውን ሲመራው የነበረውን ቡድን ስንመለከተው አዲስ ኢትዮጵያ በአዲስ ፖለቲካ በአዲስ የታሪክ ትርክት መፍጠር ነው የፈለገው። ለዚህ ደግሞ ትልቅ መሰናክል የሚሆንበት ያለፈው ታሪክ ነው። ‹‹የማስከብረው የብሄር ብሄረሰብን መብት ነው›› ብሎ ተነሳ። ይህንን ሲል ደግሞ የብሄርን ታሪክ ሊፈጥር ነው። ይህ ከዚያ በፊት የነበረውም የብሄር ብሄረሰብ ታሪክ ነው እንጂ ኢትዮጵያዊያን መስተጋብር አልነበራቸውም የሚል አንድምታ ነው ያለው። ከዚህ በኋላ ታሪክን እንደመጥፎ ነገር መቁጠር መጣ። ያለፈ ታሪክ ከሆነ እንዴት ነው በአዲስ የምንተካው ሲባል፤ ልክ እንደፖለቲካው እየመነዘሩ ታሪክን ከፋፍሎ መስጠትና አንድ መስተጋብር እንዳልነበረ ማድረግ ነው። ታሪክን ከተፈጥሮ መነጠል አይቻልም። አንድ ፈላስፋ ስለ ታሪክ ሲናገሩ፤ ‹‹ታሪክን እንደ ሻንጣ ወርውረህ ባቡር ተሳፍረህ ጥለኸው የምትሄደው አይደለም›› ብለዋል። ስለዚህ ታሪክን መላቀቅ ስለማይገባ በትክክለኛው መንገድ ማስኬድ ነው። ታሪክ በፖለቲካ መነጽር የምናነበው አይደለም። ካለፈ በኋላም አይጣልም። ካለፈው ጋር ሲጣላ ነው ፖለቲካውም እየተበ ላሸ የሚሄደው። ስለዚህ ፖለቲከኞች በተለይ የታሪክን ጉዳይ ትተው ፖለቲካው ላይ ቢያተኩሩ ይሻላል። ሁለቱ የተለያዩ ናቸውና። ታሪክን እንደማሳመኛና ህዝብ ማስተባበሪያ መጠቀም አይገባም። በመሠረቱ የፖለቲካ ትኩረት አሁንና ወደ ፊት የሚለው ነው። በእርግጥ ከታሪክ አንዳንድ ነገሮችን መውሰድ ይችላል። ታሪክ ደግሞ ያለፈን ድርጊት በማለፉ ምንም ሳይዛባ ምንጩና መረጃው በሚያስችለው መሠረት በትክክል መዘገብ አለበት። ስለዚህ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ታሪክንና ፖለቲካን በተሳሳተ መንገድ ማገናኘት ነው። እንደ ልምድ እንኳን የተወሰደው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲቋቋሙ ‹‹በዚህ ጊዜ እንዲህ ሆኜ ነበር›› የሚል ሀሳብ ያንጻባርቃሉ። ፖለቲካና ታሪክ በቅን ልቡና ካልሆነ በስቀር ሊጣጣሙ አይችሉም። የተደረጉትን ጦርነቶች መርሳት አንችልም፤ ነገር ግን በቅን ልቡና ማየት ነው። ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ‹‹የሰገሌ ጦርነት ላይ ተጎድቻለሁና የሸዋ ፓርቲ አቋቁማለሁ›› የሚል ምክንያት አይሰራም። ታሪክ እውቀቱ የሚውለው ለበጎ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- የታሪክ አረዳድ የተስተካከለ ያለመሆኑ ያስከተላቸው ውጤቶች ምንድናቸው?
ረ/ፕሮፌሰር አበባው፡- ይህ ሁሉ ውዥንብር በወጣቱ ትውልድ ላይ የመጣ ነው። አዲሱ ትውልድ መጽሔት ላይ የሚያነበውና ክፍል ውስጥ የሚማረው የተለያዩ ሆነውበታል። ማንን ማመን እንዳለበት ግራ ተጋብቷል። የሚያኮራ ታሪክ አለን እያልን እንደገና ‹‹የትኛው ታሪክ ነው›› የሚል ጥያቄ ውስጥ ነው የገባነው። በዚህ ወቅት አንድም የሚገላገል አካል የለም። የታሪክ ትምህርት ክፍሎቻችን ብዙ ጫና ስለነበረባቸው ደክመዋል። የታሪክ መጻህፍት እንዳሻቸው ይታተማሉ። ነገሮች መረን ሲለቅቁ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ሥራ አልሰራም። ላለፉት 27ዓመታት የታሪክ ትምህርት ክፍሎች አልተፈለጉም ነበር። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ክፍል እንኳን ብዙ ጫና ነበረበት። ታሪክን የሚያቀነቅንና ለኢትዮጵያ ታሪክ የጎላ ቦታ ሚሰጠው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም እንዲዳከም ተደርጓል። በዚህ ተቋም ይሰሩ የነበሩትም ታላላቅ ምሁራን ሳይቀሩ ተገፍተዋል።
አዲስ ዘመን፡ የአረዳድ ህጸጾች እንዴት ይቃኑ? ታሪክን የመዘንጋት አካሄድን ለማስ ተካከል ከማን ምን ይጠበቃል?
ረ/ፕሮፌሰር አበባው፡- የታሪክ ትም ህርት ክፍሎች የጋራ ፎረም ኖሯቸው ታሪክ ላይ መምከር አለባቸው። በመሆኑም በየዩኒቨ ርሲቲው ያሉትን የታሪክ ትምህርት ክፍሎችን ማጠናከር ነው። ብቁ የታሪክ ምሁር ማፍራት። ይህ ሲባል ጅማ ያለው የታሪክ ትምህርት ክፍል የራሱን ብቻ የሚያስተምር፤ አዲስ አበባ ያለውም እንዲሁ የራሱን ሌሎችም የየራሳቸውን የሚያስተምሩ መሆን የለባቸውም። የታሪክ አስተማሪ ማለት ትውልድን ቀራጭ ነው። የሀገርን ሀብት የሚሰጥ ነው። በሌላ በኩል አሁን ላይ እየተለመደ የመጣው ነገር ሁሉም ሰው ታሪክ ጸሐፊ እየሆነ ነው። ማኅበረሰቡም ታሪክን የሚፈልገው ፖለቲካ ቀመስ ሲሆንለት ነው። አንዱ ይነሳና ‹‹የእገሌ ህዝብ ታሪክ›› ብሎ ይጽፋል። ለብቻ ከማተኮር ይልቅ ሰፋ አድርጎ መጻፉ ይሻላል። ብሄር እየተባለ ለብቻ እየተነጠለ የሚጻፍ ነገር ታሪክ ከማሳወቅ ይልቅ ሰውን ወደ ፖለቲካ አዝማሚያ የሚገፋ አካሄድ ነው። በዚህ ረገድ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ተቋቁሞ የማይሆን መጽሐፍ ሲታተምና የሀሰት ትርክት ሲመጣ መቆጣጠር መቻል አለበት። ከዚህ ባሻገር ታሪክን በማሳወቅ የክፍል ትምህርት በቂ አይደለም። በርካታ ህዝብን መድረስ የሚችሉ ሚዲያዎችም ሚናቸውን መወጣት አለባቸው። ነገር ግን ሚዲያዎች ታሪክ ነክ በሆኑ ዘገባዎች ላይ መጠንቀቅ አለባቸው። ምክንያቱም በአንድ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ሰዎች ዘንድ ይደርሳሉ። ዘገባዎችን በግልቡ ከማቅረብ አጥንተው ወይም ባለሙያዎችን በሚገባ ጠይቀው እውነተኛ የሆነ ነገር ማቅረብ ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም በማያልቅ የታሪክ መስተጋብር ውስጥ ስላለ የታሪክ ነክ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀትና የሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ መስተጋብር የሚያሳይ ታሪክ ማቅረብ አለባቸው። በተ ለይ ከዚህ በፊት ለፖለቲካ ተልዕኮ ተብሎ የመንግስት ሚዲያው ነበር ታሪክን ሲያበላሽ የነበረው። ታሪክ ሙያ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ደግሞ ትልቅ ሀብት ነው። ‹‹ጣሊያንን አሸንፈናል›› ብለን ስናወራ ታሪክ በራሱ የጦር መሳሪያ መሆኑን ማወቅ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ለሠጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሠግናለሁ።
ረ/ፕሮፌሰር አበባው፡- እኔም አመሠግ ናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
አዲሱ ገረመው