ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ ብቻ ሳይሆን ከተሞቿም በፍጥነት እያደጉ መሆኑ ይነገራል፡፡ የኢኮኖሚው እድገት የህዝቦችን ፍላጎት እንደማሳደጉ ሁሉ፤ የከተሞቿም እድገት የከተማ ነዋሪዎችን ቁጥር በማሳደግ የቤት ፍላጎት ጥያቄዎች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ በከተሞች የመኖሪያ ቤት ትልቅ ችግር እንዲሆን፤ ከተሞችም ለቤት ልማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አነሳስቷል፡፡ ለዚህም ነው የቤት ልማት ጉዳይ በተለያየ አጋጣሚ እየተነሳ፣ ችግሮቹም እየተለዩና መፍትሄ ይሆናሉ የሚባሉ አቅጣጫዎችም እየተቀመጡ መሄዳቸው የተለመደ ተግባር የሆነው፡፡ ስምንተኛውን የከተሞች ፎረም ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን እየተካሄዱ ካሉ የውይይት መድረኮችም አንዱ በከተማ ቤት ልማት ላይ ያተኮረው መድረክ አንዱ ነው፡፡ በዚህ መድረክ ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዶክተር ዘመንፈስ ገብረእግዚኣብሔር፣ “የከተማ ቤት ልማት በኢትዮጵያ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫ” በሚል ርዕስ የውይይት ጥናት አቅርበዋል፡፡
ጥናቱ ሰባት ከፍተኛ፣ ስድስት መካከለኛና ስድስት አነስተኛ ከተሞችን በናሙናነት በመውሰድ የኢትዮጵያን የቤት ልማት ስራ ከተደራሽነቱ ጎን ለጎን የነዋሪውን አቅም ባገናዘበና የከተሞችንም ገጽታ ባማከለ መልኩ እየተከናወነ ስለመሆኑ የፈተሸ ነበር፡፡ በጥናቱ እንደተመላከተው፤ በኢትዮጵያ ያለው የከተማ ቤት ልማት ፖሊሲ ከተሞች የቤት እጥረት እንዳይኖርባቸው የቤት ልማት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፤ የቤት ልማት ስትራተጂውም ለተግባሩ ውጤታማነት ጉልህ ሚና ያላቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል፡፡ በዚህ ልክ ባለመሰራቱ ግን በሚፈለገው መጠን መጓዝ አልተቻለም፡፡ ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ ተወስነው የቀሩት የ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንኳን ከማህበራዊ ትስስር ይልቅ የነዋሪዎችን አቅም መሰረት አድርገው የተገነቡ ናቸው፡፡
ከዚህ ባለፈ እ.አ.አ. ከ2004 እስከ 2015 ድረስ በየዓመቱ 250ሺ ቤቶችን በመገንባት 2ሚሊዮን 250ሺ 831 ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ ቢሆንም፤ በዚህ ልክ ባለመሰራቱ የነበሩት ጥያቄዎች በይደር እንዲቆዩና አዳዲስ ፍላጎቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ እስከ 2020 ድረስ4ሚሊዮን 630ሺ ተጨማሪ ቤት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታም የግለሰቦች ቤት ኪራይ እየናረ ከመሆኑም በላይ፤ ተከራዮች የሚከፍሉትን ገንዘብ የሚመጥን ቤት ውስጥ መኖር አልቻሉም፡፡ በመሆኑም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ፍላጎት ለማርካት መንግስትና የግሉ ዘርፍ ተቀናጅተው ሊሰሩ፤ የቤት ልማቱም ከመጠለያነት ባለፈ ዘመኑን ያማከለና ዋጋውም የህብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ ሊሆን፤ ለውጤታማነቱም ወቅቱን የሚመጥን ፖሊሲ ቀርጾ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡
በጥናቱ ውጤት ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡት የጥናቱ አቅራቢ ዶክተር ዘመንፈስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ የከተሞች ህዝብ ቁጥርም በፍጥነት እያደገ በመሆኑ የሚፈጠረውን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎችና የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፤ አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር አብሮ እየፈጠነ የሚሄድ ስላልሆነ በቤት ዘርፉ ያሉ ችግሮች ተፈትተዋል ለማለት አይቻልም፡፡ በከተማ ቤት ልማት ዙሪያ ያሉ ችግሮች ተብለው በዋናነት የሚገለጹ አሉ፡፡ አንዱ፣ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚሆን የለማ የከተማ ቦታ ማቅረብ ላይ በቂ አይደለም፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የከተማ ቤት ልማት በግለሰብ፣ በአልሚም ሆነ በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚጠ ይቅ እንደመሆኑ ለዚህ ተግባር የሚውል ፋይናንስን በቀላሉ የማመቻቸት ችግሮች ናቸው፡፡ ሦስተኛው የቤት ግንባታ ግብዓት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሄድ ሲሆን፤ የግብዓት ዋጋ በጨመረ ቁጥር ለቤት ግንባታ የሚወጣው ገንዘብ ከከተማ ነዋሪው የመክፈል አቅም በላይ ይሆንና ተደራሽነቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጠበበ የሚሄድበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
እንደ ዶክተር ዘመንፈስ ገለጻ፤ የሚጠበቀውን ያክል ውጤት ባያስገኙም እነዚህ ችግሮች ለማቃለል የተወሰዱ አማራጮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በተለይ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል፤ ብዙዎችንም የቤት ባለቤት አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ካለው ከህዝብ ቁጥር እድገትና ከመኖሪያ ቤት ፍላጎት አንጻር ሲታይ የፈቱት ችግር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ሪል ስቴቶችም ሆኑ ማህበራት ብዙም ችግሩን ፈትተዋል ሊያስብል የሚችል ሚናን አልተጫወቱም፡፡ ምናልባት ብዙ ትኩረት የማይሰጠውና የመኖሪያ ቤት ችግሩን እየፈታ ያለው ግን የግል ቤት ኪራይ ነው፡፡ በተለይ ሰፋ ባሉ ግቢዎች ውስጥ ሰርቪሶችን በመገንባትና በማከራየት የሚገለጸው ተግባር የቤት ችግሩን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ አማራጮች የሚደረገው እገዛ ከሁሉም ያነሰ በመሆኑ ሊደገፍ ይገባል፡፡ ድጋፉም ብድር በማመቻቸት፣ በቀላሉ የግንባታ ፈቃድ በመስጠት፣ ከተቻለም የቤት ችግሩን በመፍታት ረገድ ያላቸውን ሚና አገናዝቦ ከአከራይ ተከራይ የሚገኘውን ገቢ በመተው ሊሆን ይችላል፡፡ በአንጻሩ፣ በእነዚህ የግል ኪራይ ቤቶች ዙሪያ የሚስተዋሉና መፈታት ያለባቸው ችግሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ተገማች ያልሆነ (መቼ ምን ያህል ዋጋ እንደሚጨምሩ የማይታወቅበት) የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡ ፡ ይሄን ለማስተካከል ደግሞ ትልቁ መፍትሄ አቅርቦትና ፍላጎቱን ማጣጣም ሲሆን፤ ሁለተኛው ማበረታቻ በማድረግ የቤት አቅርቦቱን ማሳደግና በማበረታቻው የገነቧቸውን ቤቶች ፍትሃዊ በሆነ ዋጋ ለተከራዩ እንዲያቀርቡ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ በማድረግ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡
ዶክተር ዘመንፈስ እንደሚያብራሩት፤ የቤት ጥያቄን ከመመለስ አንጻር ከላይ በችግርነት የቀረቡትንም ሆነ ተያያዥነት ያላቸውን ማነቆዎች ለመፍታት አማራጭ ሀሳብ መፈለግ ይገባል፡ ፡ ለምሳሌ፣ አንዱ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ በቂ የሆነ የቦታ አቅርቦት ላይ መስራት፤ የቤት ግንባታ ሲታሰብ የፋይናንስ አማራጮችን በማየት የፋይናንስ አቅርቦት ተግዳሮቱ መፈታት፤ ግንባታዎች በታለመላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የግንባታ ግብዓት አቅርቦቱ ማሻሻል፤ የግንባታ ዘርፉንም መጠናከር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ጥረት ተጨምሮበት፣ የተቀመጡ አማራጮችም ተካትተውበት ከተሰራ የቤት አቅርቦት ችግሩ ሊቃለል ይችላል፡፡ ሆኖም በደንብ ታቅዶና በቅልጥፍና ወደተግባር ካልተገባ በቀላሉ የሚፈታ ችግር አይሆንም፡፡ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው እንዳሉት፤ አንድ የከተማ ህብረተሰብ የገቢውን 30 በመቶ በታች ለመኖሪያ ቤት አቅርቦት ማዋል ሲችል ብቻ የቤት አቅርቦቱ አስቻይ ይሆናል፡፡ ሆኖም በየትኛውም አገር የቤት አቅርቦቱ የዜጎችን አቅም ያላማከለና በቀላሉ ሊገዙት የማይችሉት መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያም ያለው ተመሳሳይ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሁኔታአቅርቦቱም ሆነ አስቻይነቱ (የነዋሪውን አቅም ያማከለ ከመሆን አኳያ) በከተሞች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ማድረግ በሚችልበት አግባብ እየቀረበ አይደለም፡፡ እናም እንዴት ሊኬድበት ይገባል የሚለውን መመለስ ተገቢ ነው፡፡
ከተሞች ሰፊ ነዋሪ ያለባቸው እንደመሆኑ፤ ከመንግስት ሰፊ ድጎማ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አኳያ መንግስት የመሬትም ሆነ የፋይናንስ አቅርቦቱ ምን መምሰል አለበት፤ ፖሊሲውስ እንዴት መሻሻል አለበት፤ የሚሉ ጉዳዮችም በትኩረት ታይተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያቤቱም መውሰድ የጀመራቸው እርምጃዎች አሉ፤ የቤት አልሚዎችን ለማሳተፍ የሚያስችሉ ወደ ሰባት የሚጠጉ የቤት አቅርቦት አሰራሮችንም ለመዘርጋት ታስቧል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የመንግስትና የግል ሴክተሩ አጋርነት በሚል ለዜጎች ቤት የሚቀርብበት አሰራር ሲሆን፤ በዚህ ሂደት መንግስት መሬትና መሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የግል ባለሃብቱ ደግሞ እውቀት፣ ገንዘብና ቴክኖሎጂ ይዞ በጋራ የሚሰሩበት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ በስተቀር ጥናቶች እንዳመላከቱትም የነበረውን ውዝፍ ፍላጎትና አዲስ የሚመጣውን ጥያቄ ለመመለስም ሆነ ዘመናዊ ከተማን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በታሰበው ልክ የሚሄድ አይሆንም፡፡
ይህ ፎረም ከተሞችን በአንድ ያሰባሰበ እንደመሆኑ በቀጣይ በምን መልኩ መኬድ እንዳለበት በጋራ መክሮ በመግባባት የፖሊሲ አቅጣጫ ጭምር ተቀምጦለት ወደ ተግባር የሚገባ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የከተማ እድገቱና የቤት ፍላጎቱ መበላለጥ እንዲሁም በይደር የቆዩ የቤት ጥያቄዎችን በፍጥነት እየመለሱ መሄድ አለመቻሉ በቀጣይ የቤት ጥያቄው ሊበረታ ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ መንግስትም ዋናውና ብቸኛው የቤት አቅራቢ መሆን ስለሌለበት መኖሪያ ቤት በግልና በማህበራት እንዲሁም በሪል ስቴት መልክ መሰራት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የሚቀርቡ ቤቶች አንድም የህብረተሰቡን አቅም ያማከሉ እንዲሆኑ፤ ሁለተኛም የከተማን ገጽታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይከናወናሉ፡፡ ከግል ኪራይ ቤት ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ የኪራይ ቤት የሕግ ማዕቀፍ የለም፡፡ ይህ በቀጣይ የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ተወስዶ ሊሰራበት ስለሚገባ፣ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ሥራ ለማከናወን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያሰበበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ነው አቶ ካሳሁን የተናገሩት፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2011
ወንድወሰን ሽመልስ