በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ዴሞክራሲ ግንባታውን ለማሳለጥ የሚያግዙ ገለልተኛ ተቋማት ተመስርተዋል። እነዚህ ተቋማት ደግሞ በተለይም ለዘንድሮው የምርጫ ሂደት እጅግ አጋዥና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያደረጉ ተቋማት እንደሆኑ በተግባር አረጋግጠዋል። ከእነዚህ መካከልም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት አንዱ ነው። የአስተሳሰብ ልዕልናን በማምጣትና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የጋራ ውይይት በማዳበር ሁነኛ መፍትሔ የሰጠም እንደሆነ ይገለጻል። ለመሆኑ ይህ ምክርቤት በዘንድሮው ምርጫና አገራዊ ጉዳይ ላይ ምን አስተዋፅኦ ነበረው፤ በቀጣይስ ምን ያደርጋልና መሰል ወቅታዊ ጉዳዮችን በማንሳት ከምክርቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባቴ ጋር ቆይታን አድርገናል። የሰጡንን ምላሽም እንደሚከተለው አቅርበነዋልና መልካም ንባብ ተመኘን።
አዲስ ዘመን፡– የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከመጀመርያው ጀምሮ ሲያከናውናቸው የነበሩ ጥረቶች እንዴት ይገለጻሉ?
ዶክተር ራሄል፡– የጋራ ምክርቤቱ ከተቋቋመበት ጀምሮ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም የተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድነት ላይ ብዙ ለውጥ የሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ሠርቷል። ብዙ የተሳኩለት ጉዳዮችም አሉ። ለአብነት ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ አንዱ የሥራው ውጤት ነው። የሦስት ዓመት ሥራ ባይሆን ኖሮ ይህ አስተሳሰብ ዳብሮ ለሰላማዊ ምርጫ ፍጻሜ ባልተደረሰ ነበር። እናም ለውጡን ተከትለን ለውጥ የሚያመጡ የተግባቦት ሥራዎችን አከናውነናል። በተለይም በውይይት ላይ መሰረት ያደረጉ መድረኮች መካሄዳቸው ብዙ ዕድል የሰጠና ለውጡን ለውጥ ያሰኘ እንዲሁም አገርን ያስከበረ ምርጫ እንዲከናወን ሆኗል።
በምክርቤቱ ሥራ ፓርቲዎች በጋራ መሰባሰብ እንዲችሉ ሆነዋል፤ አገራዊም ሆነ የፓርቲ ችግሮች ሲኖሩም በጋራ ለመፍታት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከሁሉም በላይ በቀደመ አስተሳሰብ መሄድ እንደማያዋጣ ለማየት ያስቻለ ነበር። ማለትም ገዢው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአንድነት ተቀምጠው እንዲወያዩና ችግሮቻቸውን እንዲያስታውሉ ዕድል ሰጥቷል። በአቻነት የሚወዳደሩበት መድረክ እንዳለም ለማየት የቻሉበት ነው። ምክንያቱም እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ መቼም ታይተው አያውቁም። አሁን ግን ምክርቤቱ በመቋቋሙ ይህ ሁኔታ በስፋት እንዲዳሰስና ከሞላ ጎደል ችግሮቹ መፍትሔ እንዲያገኙ ሆኗል። ተሰሚነታቸው እንዲጨምርም አድርጓል።
አንዱ ስለሌላው የማወቅንና የመደማመጥን ባህል ያዳበሩበት መድረክ እንዲሰፋም ያደረገ ነው። ሌላኛው ጫማ ውስጥ ጭምር ገብቶ የማየት ዕድል የሰጠ ሥራ በምክርቤቱ በመሠራቱ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስችሏል።
አዲስ ዘመን፡– የጋራ ምክር ቤቱ ሁሉንም በሚባል ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ያካተተ እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ አንጻር የተለያየ አስተሳሰብ፣ ፍላጎትና እንቅስቃሴ ያላቸው በመሆኑ እነዚህን ለማስታረቅ የምክር ቤቱ አስተዋፅኦ ምን ነበር?
ዶክተር ራሄል፡– በልዩነት ውስጥ አንድነት ይመጣል ተብሎ ስለታመነም ነው ፓርቲው በመሰረታዊነት እንዲቋቋም የተደረገው። የተለያዩ አስተሳሰቦች ለጠንካራ አገርና ዴሞክራሲ ግንባታም አስፈላጊ ናቸው። እናም ግድ ስምምነት ብቻን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች አይከናወኑም። ሆኖም የጋራ መሆን ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ግን በብዙ መንገድ ወደ አንድ ሃሳብ እንዲመጡ የማድረግ ተግባር ይከናወናል። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የውይይት መድረክ መፍጠር ሲሆን፤ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሽሩ ይደረጋል። ለመተማመንም ይሞከራል። ነገር ግን አላምንም፤ ሃሳቡን አልቀበልም ያለውን ልናስገድድ የምንችልበት ሁኔታ የለም። ምክንያቱም ምክርቤቱ በሃሳብ የበላይነት አገር ትሻገራለች ብሎ ያምናል። ስለዚህም በአብላጫው ሃሳብ በመስማማት አልቀበልም ያለውንም ባለበት በመተው ለማለፍ ይሞከራል። ይህም የሚጠበቅ ነው።
በልዩነት የተመሰረተ አንድነታችን ያሳድገናል። ስለዚህም የተለያየ ሃሳብ ይዞ በአንድ ላይ መሰባሰቡ አዲስ ሃሳብን፣ አዲስ መልክንና አዲስ ቅኝትን ይሰጠናል። በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ የራሱ ፕሮግራም አለውና ያንን ከማስቀጠል አኳያ ብዙ ነገር ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን በመተማመን ማለፍን በማስቀደም ወደ አንድ ሃሳብ የምንመጣበትን መንገድ በመፈለግ ነው የሚሠራው። ባለመግባባታችን ጭምር ተስማምተንም የምንሄድበት ጊዜ ብዙ ነው። ይህ ደግሞ በብዙ ነገር ውጤታማ አድርጎናል።
አዲስ ዘመን፡– ምክር ቤቱ በሚያወጣቸው አንዳንድ መግለጫዎች አንዳንድ ፓርቲዎች እንዲህ አላልንም የሚል ተቃርኖ ያነሳሉ። ምክንያቱ ምንድነው? ሁሉም አባላት በጋራ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ላይ የማይደርሱት በግል ሃሳብ ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?
ዶክተር ራሄል፡– በመርህ ደረጃ አስተሳሰቡ ትክክል አይደለም። ተቀባይነት የለውምም። ምክንያቱም የጋራ ምክርቤቱ አባል ሲኮን የጋራ ምክርቤቱ የሚያወጣው ማንኛውም መረጃና መግለጫ የፓርቲው አካልና ሃሳብ እንደሆነ መውሰድ ይገበዋል። ባለቤቱ እኔ ነኝ፤ ይመለከተኛልም ማለት ይገበዋል። እማይስማማበትና ያላመነበት ጉዳይ እንኳን ቢኖር በውስጥ ሃሳቡን አቅርቦ መፍታት እንጂ እንዲህ ዓይነት ተግባር መከወን አልነበረበትም።
ይመራኛል፣ ይወክለኛል ብለው ካሰቡ ከእርሱ ውጪ የሆኑ ተግባራትን መከወንም ተገቢነት የለውም። ተጠያቂም ያደርጋል። ነገር ግን ሲባልና ሲነገር ተሰምቷል። ይህ ደግሞ በሁለቱም መልኩ ሊከናወን ይችላል። በፓርቲም በግለሰቦች አስተሳሰብም። ግን ወጥቶ ፈትኖናል የምንለው ጉዳይ ብዙም አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡– ከምክር ቤቱ የጋራ ደምብና መመሪያ የሚያፈነግጡ ፓርቲዎች ሲኖሩ ችግሩን ለመፍታት የምትሄዱበት መንገድ ምን ይመስላል፤ እስከአሁንስ ከዚህ አንጻር ያጋጠማችሁ ችግርና የፈታችሁት ነገር ካለ ቢገልጹልን?
ዶክተር ራሄል፡– ይህም እንደ ላይኛው ነው። ምክንያቱም ምክርቤቱ ያለ ውይይት የሚፈታ ነገር አለ ብሎ አያምንም። ለሁሉ ነገር ማሰሪያውም መፍቻውም ውይይት እንደሆነ አበክሮ ያምናል። ስለሆነም መመሪያውም ሆነ ደንቡ ይህንን መሰረት ያደረገ ሥራ እንዲከናወን ነው የሚያዘው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህን ያህል ችግር አጋጠመ የምንለው ጉዳይ የለም። የህወሓት ጉዳይ ነበር እርሱም ቢሆን በራሱ ጊዜ ህወሓት አጠናቆልናል። መጀመሪያ ስብሰባ ላይ ባለመገኘት ከዚያ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ራሱን በማግለል ስለወጣ ዕርምጃውን ለማስፈጸም እኛን የጠየቀን ሥራ የለም።
የምክርቤቱ አባል ለመሆን ህጋዊ እውቅና ማግኘት የመጀመሪያ ግዴታ ነው። ህወሓት ደግሞ የፓርቲ ህጋዊ እውቅናው በምርጫ ቦርድ ተነጥቋል። ስለሆነም አባል ሆኖ መቀጠል እንደማይችል ግልጽ ነውና እኔ ወደሥራ ከገባሁ ይህ ዓይነት ሁኔታ አላጋጠመም። ሆኖም ቢያጋጥመን መጀመሪያ የሚደረገው ውይይት ነው። ከዚያ ካለፈ ደግሞ በኢትዮጵያ ህገመንግሥት መሰረት ወደመፍትሔው የሚመጣ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– አሁን በሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላማዊ የትግል ስልት የጀመሩት መንገድ ከኛም አልፎ ለሌሎች የአፍሪካና የዓለም ህዝብ ምን መልዕክት ያስተላልፋል?
ዶክተር ራሄል፡– ለፓርቲዎችም ለዜጎችም ኢትዮጵያ ከማንም በላይ እንደሆነች የተናገሩበትና አለምም በአገሩ የሚደራደር ማንም ዜጋም ሆነ ፓርቲ እንደሌለ እንዲያውቁ ያደረገ ነው። ምንም ዓይነት ችግርና ጦርነት እንዲሁም መሰናክሎች ቢበረቱም ለአገር ማሸነፍ ሁሉም እንደሚረባረብም ያሳየ ነው። ምክንያቱም ውጪዎች አገሪቱ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች ምርጫውን ማካሄድ የለባትም ሲሉ ነበር። ሆኖም በአገር ማሸነፍ ኃይል ተነስተው አሳይተው አረጋግጠው ሁሉንም ዝም አስብለዋል።
ይህ ምርጫ ከአገር ሰላም በኋላ ሌላው ነገር ይሟላልን የሚለውን ያሳየም ነው። ምንም ነገር የኢትዮጵያዊ አንድነትን እንደማይንደውም ያሳየና አለሙን ጭምር ያስተማረም ነው። በዚህ ምርጫ ይህንን ማንም አልጠበቀም ነበር። አሰፍስፈውም እኛን ለማጥቃት እየጠበቁ ነበር። ነገር ግን በዚህ ያፈሩና ከእኛ ጭምር ተሞክሮ የሚወስዱ ይመስለኛል። ወደፊትም በዚህ ጥንካሬዋ እንደምትቀጥል የተረዱበት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡– አሸናፊነት በፖለቲካ ፓርቲዎች እሳቤ አሁንና ቀደም ሲል የተለየ መልክ እንዳለው ይታያል። አገር አሸንፋለች ወደሚለውም መጥቷል። ይህ እንዴት ሆነ፤ መንስኤውስ ምንድነው ይላሉ?
ዶክተር ራሄል፡– በፖለቲካ ፓርቲዎች እሳቤ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ የጦርነት ታሪክ ፤አንዱ ከሌላው ጋር የመቃቃር ታሪክ ነበር የነበራት። በዘንድሮ ምርጫ ግን ወንድማማቾች እዚያው ተነጋገርው ችግሮቻቸውን መፍታት እንዳለባቸው የተማማሩበት ነው። አገር ስታሸንፍ ነው እኛ የምናሸንፈው ወደሚለው ገብተዋልም። የከረረ ጸብ ውስጥ መግባት ለራስም አለመሆንን የተገነዘቡበት በመሆኑ አሸናፊነት እሳቤው እንዲቀየር መንገድ ጠርጓል። ሰላማዊ ምርጫ ብለን ስናወራ ፣ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ስንል ዝም ብለን የምናወራው አይደለም። በተግባር በብዙ ድካም የሚመጣና የሚታይ ነው። ለዚህ ደግሞ የእኛ ኢትዮጵያውያን መረዳት ወሳኙን ስፍራ ይይዛል።
የትግራይን ችግር እንኳን ብንመለከት ሰላም በመጥፋቱ አሸናፊ ማን እንደሆነ ግራ ተገብቷል። ምክንያቱም በወንድምና ወንድም መካከል መሸናነፍ የለም። የትግራይ ችግር የአገር ችግር እንደሆነ ሰላም የተነሳውን ህዝብ ብቻ በማየት መናገር ይቻላል። ስለዚህም የአንድ አካባቢ ችግር ለሌላውም እንደሚተርፍ መገንዘብ ያስፈልገናል። የአካባቢያችን ሰው አልሞተም ብንል እንኳን ከአገር ሀብት ላይ ተቀንሶ ለዚህ ችግር መፍቻነት የምንጠቀመው ገንዘብ ቀላል አይደለም። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ብሎም ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሚያመጣ ግልጽ ነው። ለሌላ የምናውለውን በእጥፍ ይወስድብንና ተጠቃሚነታችን በእጥፍ ይቀንሰዋልም። እናም ሰላም ማጣት የሁሉንም ቤት የሚያንኳኳ በመሆኑ አሸናፊነት ከአገር ውጪ መሆን እንደሌለበት ሁሉም ፓርቲ እንዲያይ ሆኗል። ተግብሮትም ህዝቡን ብቻ ሳይሆን ዓለምን አስደምሟል።
አሸናፊነት በእስከዛሬው ልምድ አብሮ የመኖርን ባህል ያጠፋል፤ ያነካክሳልም። ከዚህ አልፎ ያገዳድል ነበር። ለዚህ ደግሞ መንስኤው የተማረው ኃይልና የፓርቲዎች አለመስማማት ነው። ለአብነት የህወሓት መከላከያን መምታትና ጸባ ጫሪነት የፌዴራል መንግሥት የሄደው ዕርምጃ ዴሞክራሲያዊ መፍትሔን ማምጣት አለመቻሉ ዛሬ ድረስ የተረጋጋ ማህበረሰብ በትግራይ ውስጥ እንዳይኖር አድርጓል። ስለዚህም ሰላማዊነት ግለሰቦችን ወይም ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን አገርንም እንድታሸንፍ እንደምታደርግ በዚህ ምርጫ አረጋግጠናል። በምርጫው ችግር ሳይኖር ቀርቶ አይደለም አገር አሸነፈች የተባለው። ሁሉም ሰላምን፣ አገርን አስበልጦ ማየቱና ያለምንም ግጭት መጓዙ ለሰላማዊ ድል አብቅቶናልም። ልጆቿን በነብስም በስጋም አቆይታቸዋለችም። በዚህም አገር አሸንፋለች ብለናል።
አገር ታሸንፋለች ማለት አገሪቱን እንደአገር ህዝቧን እንደ ህዝብ ወዶ በሰላም ማሻገር መቻል ማለት ነው። በዚህ ምርጫ አገር ስላሸነፈች ሁላችንም ሰላም ሆነናል። ወጥተን መግባት ብቻ ሳይሆን ወደ ልማት መጓዙንም ተያይዘነዋል። ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ አንዱ በአንዱ ጫንቃ ላይ ሆኖ ለማሸነፍና ፍላጎቱን ለማሟላት ብዙ ነገር አድርጓል። በዚህም የፖለቲካ እሳቤው ከገዢው ውጪ አያሸንፍም በሰው አዕምሮ ውስጥ ተቀምቷል። ግለሰቦች እንጂ አገር እንደማትጠቀምም ማንም ይገምታል። ይህ ምርጫ ግን ይህንን ሁሉ በአገር አሸናፊነት ስላሳየ የዴሞክራሲ ጅማሮን በሚገባ አሳይቷል። ገዢውፓርቲ ብቻ አሸናፊ የሚለውንም አመለካከት የቀነሰ ነው።
ህወሓት የያዘው አመለካከት ወደ ህዝቡ ባይገባ ኖሮ ፓርቲዎች ባላቸው ችግር ራሳቸው ቢፈቱት ዛሬ ድረስ ዋጋ አንከፍልም ነበር። ስለዚህም የፓርቲ አባላትና የተማረው ኃይል አላግባብ መጓዝ አገር እንዳታሸንፍ አድርጓታል። ሆኖም አሁን በነበረው ምርጫ ግን ህዝቡም ሆነ ፓርቲዎች እንዲሁም የተማረው ኃይል የራሱን ውሳኔ በነፃነት መወሰን መቻሉ ከዚያም አልፎ ችግሩን ለአገሩ ሲል በመቻል ማለፉ አገር አሸንፋ ህዝብ ሰላም እንዲሆን ዕድል ሰጥቷል።
የተማረው መልካም ሃሳብና የተፎካካሪ ፓርቲዎች አገር ወዳድነት ወደ ህዝቡ ልብ ስለዘለቀ አገር ማሸነፍ ችላለች። ስህተቶች ነገ ይታረማሉ ብለው በመተዋቸው፤ ተናበው ለአገር ሲሉ ችግሩን በማለፋቸው እንዲሁ ጠላት ድል ተመቷል። በፓርቲ ደረጃ ብዙ ፓርቲ ተሸንፎ ሊሆን ይችላል። በእርሱ ላይ አድሏዊ አሠራሮች ተፈጽሞባቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ለአገሩ ማሸነፍ ሲል ያደረገው ስለሆነ የሚቆጨው አይደለም።
በቀደመው ስርዓት ውስጥ ያለፍን በመሆናችን የነበረው ስርዓት በሰው ልጅ አዕምሮ ላይ ያስቀመጠው ብዙ ነገር ነበር። ከዚያ ውጪ አይሆንም የሚል አስተሳሰብ በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፉ ይታሰብ ነበር። ሆኖም በሚያስደንቅ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ ከተሠራበት ስርዓትና አመለካከት ወጥቶ ምርጫውን ለአገር አሸናፊነት ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን፡– አሸናፊው ፓርቲ ለሌሎች ፓርቲዎች በመንግሥት የሥራ ቦታ ውስጥ ተካተው እንዲሠሩና እንዲያግዙት እንደሚያደርግም ቃል ገብቷል። ይህ እንደ ምክርቤት እንዴት ይታያል፤ እሳቤውስ ምንን ያመለክታል?
ዶክተር ራሄል፡– እንደእኔ በመንግሥት በኩል ያለው አካሂድ በጣም ጥሩ ጅማሮ ነው። በመሪ ደረጃ ስለተነገረ ነው እንጂ ይህ አስተሳሰብ መኖር የነበረበት ቀደም ሲልም ነበር። ምክንያቱም ያለን አንድ አገር እንጂ ብዙ አይደለም። በአገር መደራደር፣ በአገር መባላት ለማንም አይጠቅምም። እናም አሁን መንግሥት የወሰደው ዕርምጃና የገባው ቃልኪዳን አገርን በዴሞክራሲው መስክ አንድ ዕርምጃ የሚያሻግር ነው የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን እስከዛሬ በነበርንበት ስርዓት ውስጥ ይህ ምልከታ አልነበረም። እንደውም ተፎካካሪ ከሆነ ብዙ የሚነጠቀው መብት አለ። ከእነዚህ ውስጥም የትምህርት ዕድል አለማግኘት፣ እድገት አለመስጠት፣ ከሥራ የመባረር ፣ እንዳይቀጠር ማድረግ፣ ቤት ሲከራይ ጭምር የሰዎች መልካም ፍቃድ ብቻ እንዲሆን ማዕቀብ ይጣልበት ነበር። ታስሮ ከመደብደቡም በላይ በህይወት የመኖር መብቱ ጭምር ሲነጠቅ ቆይቷል። በዚህም ከሥራ አጥነት እስከ ዝቅተኛ የሥራ ደረጃ ላይ ተቀምጠው በትንሽ ደሞዝ የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው። የሰው እጅ የሚጠብቁም እንዲሁ ጥቂት አይደሉም። አሁን ግን ይህ ሁሉ በስፋት የተቀረፈበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል። ምክንያቱም ከመሪ ጀምሮ እስከታችኛው ክፍል ድረስ ያለው የመንግሥት አስተዳደር ሁሉን አቃፊ እንዲሆን እየተደረገ ነው።
በሦስት ዓመት ውስጥ ሲሠራ የቆየውም የአስተዳደር ችግሩን መፍታት ላይ ነው። ስለሆነም አብዛኛው ጥቃት የደረሰባቸው ቀበሌ ላይና ወረዳ ላይ እንዲሁም ዞን ላይ በመሆኑ እዚያ ላይ በመጠኑ መሠራቱ የዛሬውን ተስፋ እንድናይ አድርጎናል። አሁንም ግን ብዙ ያልጠሩ መኖራቸውን ማየት ያስፈልጋል። ቃሉ እውን የሚሆነው ከቀደመው አመለካከታቸው ያልተፋቱ ብዙ የብልጽግና አባላት ሊኖሩ ይችላሉና እነርሱን መከታተልም ተገቢ ነው።
መንግሥት ይህንን ያለበት እሳቤ በአንድነት የመሥራትን ኃያልነት ማሳየት ነው። የሃሳብ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለመም ነው። ይህንን አገር በጋራ ካልሆነ በስተቀር በተናጠል ወይም በአንድ ፓርቲ የበላይነት የምናልመው ቦታ ላይ ልናደርሳት አንችልም። ሁሉም ፓርቲ ተረዳድቶና ተመጋግቦ መሥራት ሲችል ብቻ ነው አገር የምትሻገረው። ስለሆነም የመንግሥት እሳቤም ይህንን ያለመ ነው። ይህ መደረጉ ደግሞ ድልም የሚገባንም ነው። ምክንያቱም የተሠራብን የጥላቻ ግንብ በመቶ ዓመትም የሚፈወስ አልነበረም። ሆኖም መንግሥት ይህንን ዕድል መስጠቱ ቅሬታዎች እንዲጠቡና ጥላቻው ከሞላ ጎደል እንዲቀል ያስችላል።
አዲስ ዘመን፡– ብልጽግና የማሸነፉ ምክንያት የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎቹም ሥራ እንደሆነ እውቅና ሰጥቷል፣ አመስግኗልም። ይህንንስ እርስዎ እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ራሄል፡– ብልጽግና ተወዳድሮ እንዲያሸንፍ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ይህ የሚታየውም ከሁለት በኩል ነው። የመጀመሪያው ከራሱ ከብልጽግና አመራሮች ጋር ተፋጭተውና ተጋግመው ጫናውን ከአገር ማሸነፍ ጋር አስተሳስረው ማለፋቸው ነው። ሁለተኛው ስርዓቱ በጣም የሠራው በብልጽግና ካድሬዎች ላይ ነው። ስለዚህም ካድሬዎቹ ለመለወጥና ለውጡን ለመቀላቀል ብዙ ጊዜ ይወስድባቸዋል። በተለይ ወደታች በወረድን ቁጥር ያለው አመለካከት ገና ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ ነው። ስለሆነም እንደነበሩ የመጡትን የብልጽግና ካድሬዎች ኢትዮጵያ ትበልጥብናለች በሚል ተሸክመው የተከፈለውን ያህል ዋጋ ከፍለው ወደ ምርጫ መግባታቸውምና ተወዳዳሪ ፓርቲን ማብዛታቸው ህዝብ የሚወደውን እንዲመርጥ ዕድል ሰጥተዋል። ስለዚህም በዋናነት በእነዚህ ሥራቸው ብቻ ምስጋና ሲያንስባቸው ነው።
መንግሥት እንደመንግሥት ያወረደውን ስርዓት እኩል አገልግሎት ሰጥተው ይህንን ጫና ተጭነው ማለፍ የነበረባቸው የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ነበሩ። ሆኖም በተቃራኒው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን ተሸክመው ለአገርና ለህዝብ መስዋእት ጭምር ሆነው ብልጽግና የአሸናፊነትን ካባ እንዲከናነብ አድርገውታል። ስለዚህም ሊያመሰግናቸው ግድ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በዘንድሮው ምርጫ መመሰጋገኖች በስፋት ታይተዋል። ይህ ባህል እንዲዳብር ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር ራሄል፡– መመሰጋገን ውዴታ አይደለም ግዴታም ጭምር ነው። ምክንያቱም ዋጋ አለበት፤ ክፍያም ይፈልጋል። እናም አሁን ጀምረነዋል መቀጠሉ አጠያያቂ መሆን የለበትም። በማመስገን ውስጥ ብዙ የሚመጡ፣ ብዙ የሚለወጡ፣ ብዙ የሚሰጡ ነገሮች አሉ። ለዚህ ደግሞ ይህ ባህል መዳበር አለበት። እናም ፖለቲከኛው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ነው ይህንን መልካም ሃሳብ ሊያዳብረው የሚገባም። ምክንያቱም መልካሙን የማይፈልግ ዲያቢሎስ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ከራስ የጀመረ ሥራ እንደሚያስፈልግ ሁሉም መገንዘብ አለበት።
ሰው ራሱን ሲለውጥ ቤተሰቡን ከዚያም አካባቢውን እያለ ለአገር ይደርሳል። ስለዚህም መልካሙን ብቻ ማሰብ ከግለሰብ መጀመር ይኖርበታልና ለዚህ ሁሉም ቃል መግባት አለበት።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይ ተሸናፊውም ሆነ አሸናፊው ፓርቲ ለአገር ብዙ መሥራት እንዳለበት ይታወቃል። በዋናነት ሁለቱም አካላት ምን ምን ተግባራትን ማከናወን አለባቸው ይላሉ?
ዶክተር ራሄል፡– በዋናነት መሥራት ያለበት ሁለቱም አካል የዴሞክራሲ ግንባታው ተጀምሯል እርሱን ማጠናከር ነው። ቅድሚያ ለአገር የሚለውም ጉዳይ በስፋት የተማመንበት በመሆኑ እርሱንም እያስቀጠሉ መጓዙ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። ከዚህ በተጓዳኝ አገራዊና ክልላዊ ምርጫው በመጠናቀቁ በዚህ ሂደት ከተማርንባቸው ስህተቶች ልምድን ቀምረን በቀጣይ እንዳይደገሙ ማድረግ ላይ መሥራትም ይገባል። በተለይም ከዚህ ምርጫ በኋላ የዞንና የወረዳ እንዲሁም የቀበሌ አደረጃጀቶች ላይ ሰፊ ሥራ ተሠርቶ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ ካልተሠራ ምርጫውን ዋጋ ያሳጠዋልና በምርጫው ልክ በተጓዝንበት ሁኔታ እዚህም ላይ ጥሩ የሚባል አገራዊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።
ከምንም በላይ ህዝቡ ያሳየውን ጽናት ተገን አድርገን መሥራት ይኖርብናል። በተለይም ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መንግሥት አደራ ተቀባይ፣ ድምፃቸውን አክባሪ ሊሆኑ ይገባል። ምክንያቱም በህዝብ መደገፍ ከምንም በላይ ማሸነፍም አገር ማቆምም ነው። በቀጣይም ነፃና በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ምርጫ ህዝቡ እንዲከናወን ከአሁን የጀመረ ሥራ መሥራትም ይኖርበታል።
በተሸናፊው በኩል በተለይ ለመሸነፌ ምክንያቱ ምንድነው ብሎ ማየት ለነገ የሚሰጥ የቤት ሥራ መሆን የለበትም። ያንን መርምሮ ለቀጣይ ምርጫ ራስን ማዘጋጀትና የተሻለ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ብዙ ዕድሎች ተመቻችተዋልና ያንን መጠቀም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ያለው የውጪ ጫናን በተመለከተ ጋራ ምክርቤቱ ምን እየሠራ ነው፤ በቀጣይስ ምን ለመሥራት አቅዷል?
ዶክተር ራሄል፡– የውጪ ጫናው አሁን የመጣ ብቻ አይደለም። ቀደም ሲልም በብዙ ነገሮች ይደረግ ነበር። ሆኖም መቼም ቢሆን የማትበገር አገር ውስጥ ስላለን እንደምንረታቸው አምናለሁ። ለዚህ ደግሞ ሁሉም በአንድ ሃሳብ ውስጥ እንደሚቆም ይሰማኛል። ምክንያቱም ምንም እንኳን እርስ በእርሳችን ብንጣላም በአገራችን ግን ማንም ወደ መደራደሩ ይገባል የሚል እምነት የለኝም። ስለሆነም መፍትሔው በአንድ ሆኖ መሥራት ነውና ሁሉም ዛሬን በጋራ መሻገር አለበት።
እንደ ምክርቤት መንግሥት የሚሰጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ለአገር የሚበጀውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም መግለጫ ሰጥቶ ከእነርሱ ጋር እስከመነጋገር የሚያደርሱ ሥራዎችን ከመንግሥት ጎን በመሆን ሲሠራም ነበር። አሁንም ቢሆን ይህንኑ ሥራውን የሚቀጥል ይሆናል። በተለይም ከሌላው በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃይል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነውና በአንድ ሃሳብ፣ በአንድ አቋም እንዲናገሩና ስለ አገራቸው እንዲያሳስቡ ማድረግ ላይ በስፋት ሠርቷልም ወደፊትም ይሠራል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ፈቃደኝነቱን ሲያሳይ እንደነበር በብዙ መልኩ አይተነዋል። አሁንም ያንን እንዲያደርግ የምናበረታታና የምንሠራ ይሆናል።
የጋራ ምክርቤቱ ሲጀምር ኢትዮጵያን የሚወክል አካል ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ጉዳይ ከመንግሥት ቀጥሎ የሚመለከተው ነው። እናም በዚህ ደረጃም ነው እየሠራ የሚገኘው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካው ጉዳይ ላይ የሚሰጡት ሃሳብ ደግሞ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ማንም ይረዳልና ይህንን ከማድረግ አንጻር የሚሠራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይስ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር ራሄል፡– የትግራይን ጉዳይ ሳስብ በጣም አዝናለሁ። እንደ ወንድማማች ልንተሳሰብ፣ አብረን ልንቆም ሲገባን ወደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ መግባታችን እጅግ ልብን የሚሰብርም ነው። በተለይም አገር በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች እንዲህ ዓይነት ውጥንቅጥ ውስጥ መሆናችን እንደ አገር አንድ የቀነሰብን ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ወታደራዊ ዕርምጃዎች ከህግ ውጪ አይወሰዱም፣ በዚህም መንግሥት የሄደበት ርቀት ትክክልና ተገቢውን ሰዓት የጠበቀ ነው። ከሰላማዊው ህዝብ የተለየ ለማድረግም ብዙ ጥሯል የሚል እምነት አለኝ። ይሁን እንጂ በህወሓት አለመስማማት አሁን ላይ ይህ እንዳይቻል አድርጎታል። መጀመሪያ ላይ ጦርነቱ ባይጀመር የኢትዮጵያ ሠራዊት ባይነካ አገር ብዙ ዋጋ ባልከፈለች ነበር።
የህወሓት ሥራ ያልተገባ ተግባር ነው። ህወሓትና ህዝብንም የነጠለ ነው ለማለት ይቸግራል። ምክንያቱም አስተሳሰቡ ህዝቡ ውስጥ ገብቶ አሸባሪውንና ንጹሑን የለየ አይደለም። በዚህም ንጹሐኑን ለማዳን ሲባል መከላከያ ወጣ። ይህ ደግሞ አጠቃላይ ትግራይ ሰላሟን እንድታጣ አደረገ። ህወሓት ሲቪልም ወታደርም ሆኖ እየተዋጋ ባለበት መከላከያን አይውጣ ብሎ መወሰን ንጹሐንን መጨረስ ነው። ለዚህ ደግሞ መከላከያ እጁም ህጉም አይፈቅድለትም። መንግሥትም ቢሆን ንጹሐን ዜጋ መግደል አይፈልግምና ህንን ለማዳን መንግሥት ግን አፋጣኝ ግዳጅ መፍትሔ ወስዷል።
አሁን ባለው የትግራይ ሁኔታ ላይ በተለይ የትግራይ ህዝብ የተሰጠውን የጽሞና ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ ብዙ የሚያመልጠው ነገር ይኖራል የሚል ግምት አለኝ። ምክንያቱም ሲያድነውና ሲታደገው የኖረውን ሌላውን አካሉን በህወሓት እንዲነጠቅ ሆኗል። መንግሥትም ቢሆን ንጹሐኑን ከወታደሩ መለየት ተስኖታልና ማገዙ በሚፈልገው ልክ እንዳይሆንለት ሆኗል። እናም የሚበጀውን መምረጥና ኢትዮጵያዊነቱን ማረጋገጥ ላይ በስፋት መሥራት አለበት። እንደ ትግራይም ሆነ እንደ አገር የትኛው ነው የተሻለው፤ የትኛው ነው የሚያተርፈን የሚለውንም በደንብ ማመዛዘን ይገባቸዋል።
ይህ የጽሞና ጊዜ የትግራዊያን ብቻ አይደለም። ሌላው የኢትዮጵያዊም የሚያስብበት፣ መፍትሔ የሚፈልግበት ጊዜ ነው። የችግሩ እልባት ከእኛ ውጪ አይሻገርምና ለእኛ እኛ እንዴት እንሁን የሚለውን በሚገባ ማየት ላይ ልንረባረብ የምንችልበት ጊዜ ነውና እንጠቀምበት።
አዲስ ዘመን፡– አሸባሪው የህወሓት ቡድን ንጹሐን ዜጎችን በአመለካከታቸው ምክንያት እየገደለ ነው። የክልሉ ነዋሪዎችም ቢሆኑ እየተሰደዱ እንደሆነ ይገለጻል። እናወራርዳለን የሚል የጦርነት ዝግጅት እያደረገ እነደሆነና ወጣት አዛውንቱን ሳይቀር ለግጭት እያዘጋጀ መሆኑም ይነገራል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ ?
ዶክተር ራሄል፡– መረጋጋት ያስፈልጋል ነው የምለው። ምክንያቱም ብዙ ያልተተገበሩ ፣ ያልታዩ፣ ያልተረጋገጡ ወሬዎች በብዛት ይወጣሉ። ስለዚህም ከማንኛውም አንደበት የሚወጡ ሃሳቦች ጥንቃቄ የተሞላባቸው ሊሆኑ ይገባል። በተለይም ከአመራሮች። ከዚያ ውጪ ሚዲያዎችም ሲዘግቡ አገርን የሚያድን እንጂ ሰውን ከሰው የሚያጋጭ ፣ የበለጠ ጦርነት ውስጥ የሚከት ሃሳብን በመያዝ መሆን የለበትም። በእያንዳንዱ ዘገባቸው መረጃና ማረጋገጫን መያዝ ክምንም በላይ አስፈላጊ ነው። ገለልተኛ መሆንን ለአገርና ለህዝብ ብለው ቢላበሱ መልካም ነው።
ከዚያም ከዚህም የሚሞተው ኢትዮጵያዊ ወገናችን እንደሆነ ማመን አለብን። የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በእርሱ መታረቅን ያውቅበታልና ሰከን ብሎ ጊዜውን ይጠቀምበት ማለት እፈልጋለሁ። መሪዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የተሳሳተ መንገድ ውስጥ ሊከቱን ይችላሉ። ስለሆነም ያንን መመዘኑ የእያንዳንዱ ዜጋ መሆን አለበት። ከችግሩ ስፋት አንጻር ለምን አልሞትም የሚያስብሉ ነገሮች ተፈጥረው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ዛሬን ችሎ ማለፍን የመሰለ ነገር የለምና ደጋግሞ ማሰብ፣ ወገናዊነትን ማለም፣ የነገ ተስፋዎቻችንን በብርሃን ጭላንጭል ማየት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆንም ነው ነገን በተድላና ደስታ የምንኖረው። ስለዚህ ሌላም መንገድ እንዳለ ማሰብ ከምንም በላይ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፋንታ በእርስዎ እይታ ምን ይመስላል፤ ምንስ ሊሆን ይችላል?
ዶክተር ራሄል፡– ብዙ ተስፋ ነገሮች ይታዩኛል። መከራዋን እየጨረሰች ያለች አገር ነች ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ብዙ የተቸገረቻቸው ነገሮች አሉ። አሁን ደግሞ እንደ ህዝብ ይቅር መባባልንና ችሎ መተውን ካነገብን ላንሻገረው የምንችለው ነገር ይኖራል ብዬ አልገምትም። ሞታችን ውስጥ ቆመን ደም መፋሰሶችንን ከማሰብ ይልቅ ተስፋውን ማለም ከቻልን ነገ ብርሃን የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚ አለ። የኋላ ነገራችን ዳግም የምናሻሽለው የምናተርፈው አይደለምና በእርሱ ከመቆዘም መውጣት ከቻልን ብሩህ ተስፋችን የሚለመልምበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ዛሬ ላይ ቆመን ነጋችንን እናትርፍ ዋና ተስፋችን ነው። የልጆቻችን የወደፊት ዕጣ ፋንታ መወሰኛና ማረጋገጫም ነው። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ማሸነፍ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አጠቃላይ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያስተላልፉት ካለ ?
ዶክተር ራሄል፡- ከዚህ በኋላ ያለውን የኢትዮጵያ ተስፋ እንደ ባላደራ ትውልድ የተረከብን ነንና እልሀችንን ትተን ሰላምን አስቀድመን አገራችንን ወደተከበረችበት ማንነቷ መመለስ ያስፈልጋል። በተለይም ይህ ትውልድ የዕድል አጋጣሚ ፈጣሪ በእጁ ላይ የተወለት ትልቅ እዳ አለበት። ይህም አባቶቹ የደም ዋጋ ከፍለው ክብር ሰጥተውታል። ሉአላዊነቷ የማይደፈር አግርን አስረክበውታል። ስለሆነም እርሱም የደም ሳይሆን ጊዜው የሚጠይቀው የአስተሳሰብ ለውጥ በመሆኑ በአስተሳሰብ ባለጸጋ ሆኖ በደም የተረከበውን በአስተሳሰብ አልቆ ማሻገርና ለተተኪው ማስረከብ የውዴታ ግዴታው እንደሆነ ማመንና ወደ ሥራ መግባት አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ሃሳብ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
ዶክተር ራሄል፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2013