ያለ እድሜ ጋብቻ በተጋቢዎች ዘንድ በተለይም በሴቶች ላይ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ፤ ስነልቦናዊና፤ አካላዊ ችግሮችን የሚያስከትል ነው። እነዚህ ችግሮች ደግሞ አንዳንድ ጊዜ እስከህይወት ፍጻሜ አብረው የሚዘልቁ እስከመሆን ይደርሳሉ። የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ካለ እድሜያቸው የሚዳሩትን ልጆች ለመከላከል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት የሀይማኖት ተቋማትም ጨምሮ የተሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም ድረስ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ለማለት የሚያስደፍር ሥራ አልተሰራም። ለመሆኑ በያለእድሜ ጋብቻ የሚጣሱ መብቶች ምንድን ናቸው የሚፈጥሩትስ ችግር እንዲሁም እንዴት ልንከላከላቸው ይገባል ስንል የአማራ ክልልን እንደ መነሻ በማድረግ ከክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት የፍትሐብሄር አቃቤ ህግ የሆኑትን አቶ አማረ ሲሳይን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አቶ አማረ እንደሚያብራሩት ጋብቻ የአንድ ሀገር መሰረት ነው። ይህም በመሆኑ ማህበረሰቡ የሚመራባቸው የሃይማኖት መጻሕፍት ጋብቻ ክቡር፣ መኝታውም ቅዱስ እንደ ሆነ ያስተምራሉ:: ከዚህም ሌላ ጋብቻ የህብረተሰብ ተፈጥሯዊ መነሻ የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረትበት በመሆኑ ከመንግሥትና ከህብረተሰብ ያላሰለሰ የህግ ጥበቃና ክትትል የሚያስፈልገው ነው:: ይህም ጉዳይ በበርካታ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ብሄራዊ ህጎች እውቅና አግኝቷል፡፡
ይሁንና የጋብቻው ክቡርነትም ይሁን የመኝታው ቅዱስነት የሚረጋገጠው እንዲሁም መንግሥትና ህብረተሰብ ህጋዊ ጥበቃ የሚያደርጉለትን ቤተሰብ ለመመስረት ብቁነት የሚኖረው ጋብቻው በህግ መሰረት የተፈጸመ ሲሆን ነው:: ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው በአማራ ክልል ከሚመሰረቱ ትዳሮች መሀከል አብዛኛዎቹ ያለ እድሜ ጋብቻ የሚፈጸምባቸው ናቸው:: ይህም የችግሩን ስፋትና አሳሳቢነት የሚያመላክት ነው።
በመሆኑም ይህንን አካሄድ በመቀየር የችግሩን ስፋት ለመቀነስ ያለ እድሜ ጋብቻን ምንነትና በህግ አግባብ የሚኖረውን ምላሽ ማወቅ ይገባል። ለዚህም፤ ያለ እድሜ ጋብቻን ምንነት፣ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ስለ ያለ እድሜ ጋብቻ ያላቸውን አቋምና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እናያለን። በመቀጠልም በያለ እድሜ ጋብቻ የሚጣሱ መብቶችንና ያለ እድሜ ጋብቻ መፈጸም የሚያስከትለውን የህግ ተጠያቂነት አቃቤ ህግ አቶ አማረ ሲሳይ እንደሚከተለው በዝርዝር ገልጸውታል።
ያለ እድሜ ጋብቻ ምንነትና የሰብአዊ መብት ስምምነቶች አቋም
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ140 በላይ የሚሆኑ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ይገኛሉ:: ከእነዚህ አንዱና ዋናው ደግሞ ያለ እድሜ ጋብቻ ነው:: በዚህ ያለ እድሜ ጋብቻ የአማራ ክልል በሀገር ደረጃ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ሲሆን ይሄው ድርጊቱ ከገጠሩ የክልሉ ክፍሎች አልፎ በከተሞች አካባቢም ይፈጸማል፡፡
ያለ እድሜ ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ከተጋቢዎቹ ጥንዶች ሴቷ፣ ወንዱ ወይም ሁለቱም ከ18 ዓመት በታች ሲሆኑ ነው:: ይህ ደግሞ በአፍሪካ የህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ 21 (2) ስር በግልጽ ተደንግጓል:: በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሏዊ ልዩነት ለማስወገድ በተደረገው ስምምነት አንቀጽ 16 (2) መሰረትም አንድ ሰው ለጋብቻ የሚበቃበት አነስተኛ እድሜ መወሰን ይኖርበታል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በኢ.ፌ.ዲ.ሪም ሆነ በአማራ ክልል ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 34 (1) ላይ እንደተጠቀሰው በሕግ ከተወሰነው የጋብቻ እድሜ ላይ የደረሱ ወንዶችም ሴቶች የማግባትና ቤተሰብ የመመስረት መብት አላቸው:: ነገር ግን በስምምነቱም ይሁን በሕገ-መንግሥቶቹ በሕግ መወሰን ያለበት እድሜ ስንት እንደሆነ ተለይቶ አልተቀመጠም፡፡
በመሆኑም ለጋብቻ የሚያበቃን አነስተኛ እድሜ ለማወቅ ህጻን ማን ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያሻል:: ምላሹም በአፍሪካ የህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ 2 ላይ ተጠቅሷል:: ይሄው አንቀጽ “ህጻን ማለት እድሜው ከ18ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ነው” በማለት ሲተረጉም የህጻናት መብቶች ስምምነትም በአንቀጽ 1 ህጻን ለሚለው ቃል ተመሳሳይ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡
በዚሁም መሰረት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 7 (1) እና በአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 18 (1) “ወንዱም ሆነ ሴቷ አሥራ ስምንት ዓመት ሣይሞላቸው ጋብቻ መፈጸም አይችሉም” በማለት ተደንግጓል:: ሆኖም ግን በእነዚህ አንቀጾች ንኡስ አንቀጽ (2) መሰረት የተለየ ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ተጋቢዎቹ በራሣቸው ወይም ከተጋቢዎቹ በአንዳቸው ወላጆች ወይም በአሣዳሪዎቻቸው በሚቀርብ ጥያቄ የፍትሕ ሚኒስትሩና የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ይህንኑ እድሜ በሁለት ዓመት ዝቅ አድርገው ወደ 16 ዓመት ሊያወርዱት ይችላሉ፡፡
ከፍ ሲል የተጠቀሱት ሕጎች ሕጋዊ ጋብቻ ለመፈፀም ወንዶችና ሴቶች ዕድሜያቸው 18 ዓመት መድረስ እንዳለበት ቢደነግጉም ህጉ ወጥነት ባለው ሁኔታ ተግባራዊ አልተደረገም:: እንዲያውም በገጠር የሚገኙ አብዛኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ህጉ ስለመኖሩ ግንዛቤው የላቸውም፡ ስለሆነም በዕድሜ የገፉ ወንዶች ለአካለ-መጠን ያልደረሱ ሴቶችን የማግባት ባህላቸው ስር የሰደደ ሊሆን ችሏል፡፡
ያለእድሜ ጋብቻ ገፈት ቀማሾች ብዙን ጊዜ ሴት ህጻናት ሲሆኑ ወንዶች ልጆችም አልፎ አልፎ በድርጊቱ ሲጠቁ ይስተዋላል:: ያለዕድሜ ጋብቻ ለመፈጸም ባህላዊ ምክንያቶቹ ጾታዊ ተፅዕኖ፣ ከጋብቻ በፊት የሚፈፀም ወሲብንና እርግዝናን መከላከል፣ ወገን ከወገን ማገናኘት ወዘተ የሚሉ ሲሆኑ ቁሳዊ ምክንያቶቹ ደግሞ ድህነት፣ አለመማር፣ የልጅ ልጅ ለማየት መፈለግ የመሳሰሉት ናቸው:: ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምን ያለ እድሜ ጋብቻ በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸም ከፍተኛ በደል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚያጋጥሙ ችግሮች
ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚያጋጥሙ ችግሮች በርካታ ናቸው:: እነዚህም ችግሮች ከአካባቢ አካባቢ፣ ከባህል ባህልና ከሃይማኖት ሃይማኖት ይለያያሉ:: በዚህ ረገድ በእየለቱ ሥራ ላይ በተግባር ከሚያጋጥሙትና ለአብነት መነሳት ካለባቸው ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ለአካለ መጠን ያልደረሰችውን ወይም 18 ዓመት ያልሞላችውን ለመዳር ዕድሜዋ ለጋብቻ የደረሰ ሌላ ሴት ልጅ ወደ ቅድመ-ጋብቻ የእድሜ ምርመራ ልኮ ማስመርመር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ችግር ነው:: ለምሳሌ፡- በእድሜዋ ለጋብቻ ያልደረሰችውን ህጻን ለመዳር ወይም ለማግባት አስበው ለዕድሜ ምርመራው ከ18 እስከ 20 ዓመት የምትገመት ሌላ ልጅ ልከው ሲያስመረምሩ በህብረተሰቡ እየተጋለጡ ጋብቻው ሳይፈጸም የሚቀርባቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
2. ከእድሜ የህክምና ማስረጃ ጋር በተያያዘ የህክምና ባለሙያዎች ከዚህ እስከዚህ የሚል ማለትም ከ16-18 ወይም ከ17-18 ዕድሜ የሚል ማስረጃ ስለሚሰጡ የተጋቢዋ ወላጆችና አግቢዋ 18 ዓመት ያልሞላትን ልጅ 18 ዓመት ሞልቷታል በማለት ጋብቻው እንዲፈጸም ያደርጋሉ:: ፍርድ ቤቶችም ለሴት ህጻናቱ የተሻለ ጥቅም ከመወገን ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ማስረጃ ስለሚቀበሉ ጋብቻውን በፍትሐብሔር ከሶ ለማስፈረስና በወንጀል ለመክሰስ አስቸጋሪ ሆኗል:: ይህም ሁኔታ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ላይ ይገኛል፡፡
3. ከእድሜ የህክምና ማስረጃው ባሻገር ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስፈረስ የሠው ማስረጃም ለፍርድ ቤት ሊቀርብ ይችላል:: ሆኖም ያለ እድሜ ጋብቻው ሲፈፀም ያዩ ሰዎች የተጋቢዎቹ ቤተሰቦች ስለሚሆኑ ፍርድ ቤት ቀርበው ለመመስከር ፈቃደኛ አይሆኑም:: በመሆኑም እንዲህ አይነት ሰዎች ባሉበት አካባቢ ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚደረገውን ሂደት ፈታኝ ያደርገዋል፡፡
4. ዕድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሰ ሴት ልጆች በተለይ በገጠር አካባቢ ለመምህራን፣ ለጤናና ለግብርና ሰራተኞች በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ሲሰሩ በዚያው ወደ ጋብቻ ይገባሉ:: ይህም ጉዳይ ያለዕድሜ ጋብቻን ለመከላከል ከሚያጋጥሙ እንቅፋቶች አንዱ ሆኖ ይታያል፡፡
5. ከህክምና ተቋማት ርቀው የሚገኙ ሴት ልጆች ዕድሜያቸውን ለማስመርመር ብዙ ብዙ ይቸገራሉ:: ስለዚህ ወደ ህክምና ተቋማቱ የመሄጃና መመለሻ ገንዘብ እጦት ስለሚያጋጥማቸው የእድሜ ምርመራ ሳያደርጉ ለማግባት ይገደዳሉ:: ስለሆነም የህክምና ተቋማት ርቀትና ድህነት ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቆም ከሚያጋጥሙ ችግሮች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡
6. ህብረተሰቡ የሴት ህጻናት ልጆቹን እድሜ ለማስመርመር ፈቃደኛ ካለመሆኑ ባለፈ ያለዕድሜ ጋብቻ ተፈፅሞ ሲገኝ አያጋልጥም:: ሰርጉንም የሚፈጽመው በማህበር፣ በሰደቃ፣ በደቦና በሌሎች ተመሳሳይ ድግሶች አመካኝቶ ነው:: ይህም ያለዕድሜ ጋብቻን ቁጥጥር አስቸጋሪ ሊያደርገው ችሏል፡፡
7. አንድ ወንድ እድሜዋ ለጋብቻ ያልደረሰችን ሴት ሊያገባት ሲፈልግ ለቤተሰቦቿ በገበሬነት ተቀጥሮ ይሰራል:: ከዚያ በኋላም ቀስ ቀስ እያለ ህጻን ልጃቸውን ያገባል:: እንዲህ አይነቱ ድርጊትም ከላይ እንዳየናቸው ችግሮች ሁሉ ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ያለእድሜ ጋብቻን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ህብረተሰቡ ነው:: ይሁን እንጂ ከፍ ሲል ከተመለከቱት ችግሮች አብዛኞቹ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በራሱ በህብረተሰቡ የሚፈጸሙ ናቸው:: በእነዚህና ሌሎች መሰል ምክንያቶች ለማስቆም ባልተቻለው ያለእድሜ ጋብቻ በርካታ የህጻናት መብቶች ይጣሳሉ:: እነዚህ መብቶች ምን ምን ናቸው ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ይቻል ዘንድም ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ተዳሰዋል፡፡
ሀ. በህይወት የመኖር መብት
ሁሉም ዓለማቀፋዊና አህጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ያለ ምንም ልዩነት ጥበቃ የሚያደርጉለት መብት ቢኖር በህይወት የመኖር መብት ነው:: የኢ.ፌ.ዲ.ሪና የአማራ ክልል ሕገ-መንግስቶችም በተመሳሳይ በአንቀጽ 15 ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብት አለው በማለት ደንግገዋል:: ይሁንና ይሄው የመብቶች ሁሉ እናት የሆነው መብት በተለያዩ ምክንያቶች ይጣሳል:: ከምክንያቶቹም ግንባር ቀደሙ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊትነት የተፈረጀው ያለእድሜ ጋብቻ ነው፡፡
ያለእድሜ ጋብቻ እድሜያቸው ሳይደርስ የሚያገቡ ሴት ህጻናትን ጤንነትና ደህንነት አደጋ ላይ የመጣል ቀጥተኛ ውጤት አለው:: ከዚህም አልፎ በውስብስብ እርግዝናና በልጅነት ወሊድ ሳቢያ አያሌ ህጻናትን ለሞት ይዳርጋል:: ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ10 እስከ 14 ዓመታቸው ያገቡ ህጻናት በወሊድ ምክንያት የመሞት እድላቸው ለጋብቻ እድሜ ከደረሱት ከ5 እስከ 7 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን እድሜያቸው ከ15 እስከ 19 የሚሆኑት ደግሞ እድሜያቸው 20ና ከዚያ በላይ ከሆኑት በወሊድ የመሞት እድላቸው በእጥፍ ይበልጣል፡፡
በመሆኑም ያለእድሜ ጋብቻ የህጻናት እናቶችን ህይወት በመቅጠፍ የመሪነት ደረጃ ይዟል:: ከዚህም ባሻገር 18 ዓመት ካልሞላቸው እናቶች የሚወለዱ ልጆች የመሞት እድላቸው 19 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ እናቶች ከሚወልዷቸው ህጻናት 60 ጊዜ ይበልጣል:: ስለዚህ ያለእድሜ ጋብቻ የህጻናት እናቶችን ብቻ ሳይሆን በልጅነት አቅማቸው የወለዷቸውን ህይወት ጭምር የሚቀጥፍ አስከፊና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን ማንኛውም ሰው ሊገነዘበው ይገባል፡፡
ለ. የትዳር ጓደኛን የመምረጥ መብት
የልጃቸውን ባል ወይም ሚስት መምረጥ ለብዙ ወላጆች የተለመደ ጉዳይ ነው:: በዚህም የተነሳ እድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ልጆች ያለፈቃዳቸው እንዲያገቡ ይገደዳሉ:: ይህም ድርጊት ያለእድሜ ጋብቻ እንዲፈጸም ያስችላል፡፡
በተግባር እየሆነ ያለው ከፍ ሲል የተገለጸው ቢሆንም ጋብቻ ያለተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፈቃድ መመስረት እንደሌለበት የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ሁሉ ያውጃሉ:: በዚሁም መሰረት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ዓለምአቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 10 (1) ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ጋብቻ በተጋቢዎች ፈቃድ የሚመሰረት ይሆናል፡፡
በሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለምአቀፍ ቃልኪዳን መሰረትም ያለተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፈቃድ ጋብቻ መመስረት የለበትም:: በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሏዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ስምምነትም እንዲሁ በአንቀጽ 16 (1) /ለ/ የትዳር ጓደኛን የመምረጥና ጋብቻን በውዴታና በነጻ ፍላጎት የመፈጸም መብት ለተጋቢዎች ብቻ የተሰጠ መሆኑን ይደነግጋል፡፡
ከእነዚህ ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ የኢ.ፌ.ዲ.ሪና የአማራ ክልል ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 34 (2) ጋብቻ በተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፈቃድ ላይ ብቻ እንደሚመሰረት ይገልጻል:: ይሄው ድንጋጌ በኢ.ፌ.ዴ.ሪና በአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 6ና 17 እንደቅደም ተከተላቸው ቃል በቃል ሊባል በሚያስችል መልኩ የሚጸና ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነጻና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ ነው በሚል ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ነገር ግን ከላይ በተብራሩት የሰብአዊ መብት ስምምነቶችም ሆነ በብሄራዊ ሕጎች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የትዳር ጓደኛን በነጻና ሙሉ ፈቃድ የመምረጥ መብት ለተጋቢዎች ወላጆች የተሰጠ ያህል በመብቱ ሲጠቀሙ የሚስተዋሉት እነሱ እንጂ ተጋቢዎቹ አይደሉም:: ስለሆነም መብቱ ከሚከበርበት ይልቅ የሚጣስበት ጊዜ ይበልጣል:: በዚህም ምክንያት ሁለቱ ተጋቢዎች ተመራርጠው፣ ወደውና ፈቅደው የሚጋቡበት እድል በጣም ጠባብ ከመሆኑም ባለፈ የወደፊት እጣፋንታቸውንም ለመወሰን እንቅፋት ሆኗል፡፡
ቀጣዩን ክፍል በሚቀጥለው እትም ይዘን እንቀርባለን
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም