ጌትነት ተስፋማርያም
በአነስተኛ መሬት ይዞታ ላይ በሚተገበር የከተማ ግብርና ያደጉት ሀገራት ሰፊ ልምድ አላቸው። በተለይ አውሮፓውያኑ በከተሞች ያለውን የግብርና ምርት ፍላጎትና አቅርቦት የተመጣጠነ ለማድረግ በአነስተኛ ቦታ በዋናነት በመኖሪያ አካባቢዎች የሚተከሉ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ምርቶች ላይ ማተኮር ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል።
የቤልጂየሟ ብራስልስ ከተማ ፈጥነው የሚደርሱ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች በማምረት እ.አ.አ. በ2035 ለምግብ ፍጆታዋን 30 በመቶ ከከተማ ግብርና ለመሸፈን አቅዳ እየሰራች
ነው፡፡ የኢትዮጵያ ከተሞችስ በዚህ ዘርፍ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን መቃኘት ከተቻለ አዲስ አበባ ላይ የተለያዩ ተሞክሮዎች መኖራቸውን እንታዘባለን። እኛም በከተማዋ ያለውን የከተማ ግብርና ዝግጅትና ሥራ፣ የድጋፍ ክንውኖች እና ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የሚደረጉ ድጋፎችን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ መሐመድ ልጋኒ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ የተቋቋመበት አላማ በዋናነት ምንን መሰረት ያደረገ ነው?
አቶ መሐመድ፡- ተቋሙ ከለውጡ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ተዋቅሮ ነው ሥራ የጀመረው። ኮሚሽኑ በዋናነት ሁለት ጉዳዮች ላይ መሰረት ያደረገ ሥራ አለው። በአንደኛው ዘርፍ ክንውኑ ከአርሶ አደሮች ጋር የተያያዘ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።
ከአዲስ አበባ የልማት ሥራዎች ጋር ተያይዞ በተለያዩ ወቅቶች በከተማዋ ዙሪያ የነበሩ ኑሯቸውን በእርሻ ሥራ ላይ ያደረጉ አርሶ አደሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከከተማዋ መስፋት ጋር ተያይዞ አርሶአደሮቹ መሬታቸውን በማጣታቸው የመፈናቀል ችግር አጋጥሟቸዋል።
ወቅቱን የጠበቀ የካሳ ክፍያ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራ ባለመሰራቱ ምክንያት አርሶአደሮቹ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች መጋለጣቸው ይታወሳል። ስለዚህ ኮሚሽኑ በተለያየ ሁኔታ የተፈናቀሉ አርሶአደሮችን መልሶ የማቋቋም ተግባርን የማከናወን ኃላፊነት ተጥሎበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከግብርና ጋር ተያይዞ የምናከናውናቸው ሰፊ የልማት ሥራዎች አሉ። ከገጠር ወደከተማ የሚፈልሰው የህዝብ ቁጥር እያየለ በመምጣቱ ለመዲናዋ የምግብ ፍላጎት የሚውል ምርት በሰፊው ማግኘት ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ ከሌሎች አማራጮች በተጓዳኝ የከተማ ግብርናን ማስፋፋት ይገባል በሚል ኮሚሽኑ ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሰራበት ይገኛል። በዚህ ሂደት ውስጥ ኮሚሽኑ የከተማ ግብርናን በማስፋፋት የሚስተዋለውን የምግብ እጦት ችግር ለመቀነስ አስተዋጽኦውን እያበረከተ ነው።
በከተማ ግብርና የሚሳተፉ ሰዎችንና ተጠቃሚዎችን በማብዛት የግብርና ምርት እንዲዘጋጅ የማድረግ ሥራውን እየተወጣ ይገኛል። በክረምት እና በበጋ ወቅቶች እንደአየር ንብረቱ አስፈላጊ የሆኑ ተክሎችን እናቀርባለን። በየጊዜው ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የምናከናውናቸው የልማት ሥራዎች ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
አዲስ ዘመን፡- በመዲናዋ በከተማ ግብር የሚሳተፉ ምን ያክል ዜጎች አሉ?
አቶ መሐመድ፡- በአንድ በኩል በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ አርሶአደሮች አሉ። አሁንም ኑሯቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በእርሻ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። አርሶ አደሮቹ ጤፍ እና የተለያዩ የምግብ እህሎችን በየዓመቱ ያመርታሉ። አርሶአደሮቹን በሙያም ሆነ በምርጥ ዘር እና በተለያዩ የግብርና ግብአቶች የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
በሌላ በኩል በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ እና በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ አትክልቶችን እና የፍራፍሬ ተክሎችን የሚያመርቱ ኗሪዎች አሉ። በመኖሪያ ቦታቸውም ሆነ በአካባቢያቸው የሚገኙ አነስተኛ ቦታዎች ላይ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን እንዲያመርቱ እንደየምርጫቸው ድጋፍ ይደረጋል። ኮሚሽኑ የስም ዝርዝራቸውን ይዞ በከተማ ግብርና ሥራ የተለያዩ ድጋፍ የሚያደርግላቸው 157 ሺህ ኗሪዎች አሉት።
ባለቻቸው አነስተኛ ስፍራም ቢሆን የተለያዩ የብረት እና የእንጨት እንዲሁም የፕላስቲክ እቃዎች በመጠቀም ሽቅብ ግብርና ስልት የሚጠቀሙ ዜጎች አሉ። አደራጅተንም ቢሆን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና የተለያዩ አነስተኛ መሬት ላይ እንዲሰሩ እድሉን ያመቻቸንላቸው ወጣቶች አሉ።
ከዚህ ባለፈ የሃይማኖታዊ ቦታዎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ወንዝ ዳርቻ ቦታዎች ላይ የከተማ ግብርና ሥራዎች የሚያከናውኑ ኗሪዎች አሉ። በአጠቃላይ በአርሶአደር ደረጃም ሆነ በከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎችን ባማከለ ሁኔታ የግብርና ማዳበሪያ፣ የሙያ ምክር እና ቦታ ዝግጅት ድጋፍ የመሳሰሉ ድጋፎች እየሰጠን ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚገኙ አርሶአደሮች ምን ያክል ድጋፍ አቅርባችኋል?
አቶ መሐመድ፡- በአዲስ አበባ ዙሪያ በርካታ የግብርና ምርምር እና ቴክኖሎጂ መሳሪያ ማምረቻዎች ቢኖሩም አርሶአደሮቹን ያማከለ ሥራ ግን አልነበረም። ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ በፊት በመጀመሪያ ምንም አይነት ድጋፍ የማያገኙ እና በመሰረታዊነት በግብርና ላይ የተሰማሩ አርሶአደሮች መኖራቸውን ለይተናል።
ይህን መነሻ በመያዝ ባለፈው ዓመት እንዳደረግነው ድጋፍ ሁሉ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ለአርሶአደሮች ከ16 ሺህ ኩንታል በላይ የዩሪያና ኤንፒኤስ የተሰኙ የማዳበሪያ አይነቶችን አቅርበናል።
ሰፊ መሬቶችን የማረስ ፍላጎት እያላቸው በአቅም ማነስ ምክንያት ሥራቸውን እንዳያስተጓጉሉ በሚል የማዳበሪያው ወጪ ሙሉ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ የተሸፈነ በመሆኑ ለአምራቾች በነጻ የቀረበ ነው። አርሶአደሮቹ በራሳቸው የሚገዙት ማዳበሪያም ስላለ ለከተማ ግብርናው የዋለው ማዳበሪያ ከፍተኛ ነው።
ከምርጥ ዘር ጋር ተያይዞ ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር ከሶስት ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ግዥ ተፈጽሞ ለአምራቾች ተከፋፍሏል። ከየአካባቢው አግሮ ኢኮሎጂ ጋር የሚሄዱ ዝርያዎች ተመርጠው ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። የጤፍ፣ የምስር እና የስንዴ ምርጥ ዘሮችም ከተከፋፈሉ ዘሮች መካከል ናቸው።
ከዚህ ውጪ በአዲስ አበባ ከተማ ክልል ውስጥ የሚገኝ ቦታ አንድም መሬት ጾሙን ማደር የለበትም በሚል መርህ ሰፋፊ መሬቶችን ለማረስ የሚያስችል ስድስት ትራክተሮችን ለስድስት ክፍለ ከተሞች አከፋፍሏል።
አቃቂ ቃሊቲ፣ የካ፣ ለሚኩራ፣ ቦሌ ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች በንጽጽር በርካታ አርሶአደሮች የሚገኙባቸው በመሆናቸው ትራክተሮቹን ተረክበዋል። አርሶአደሮች ሰፋፊ መሬቶችን በሙሉ አቅማቸው እንዲያርሱ ክፍለ ከተሞቹ እገዛ እያደረጉ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- በክረምቱ ወቅት በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ለሚከናወኑ የከተማ ግብርና ሥራዎች ለኗሪው ያቀረባችሁት ዘርና የችግኝ ብዜት ምን ያክል ነው?
አቶ መሐመድ፡- በመሃል ከተማ እና በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ በመደብ ላይም ይሁን በጓሮ ለሚከናወኑ የከተማ ግብርና ሥራዎች ዘር እና ችግኞች አቅርበናል። በአነስተኛ ቦታ ለሚከናወኑ ግብርና ሥራዎች ስድስት ኩንታል የተለያዩ ዘሮችን አዘጋጅተናል።
የሽንኩርት፣ጥቅል ጎመን እና የተለያዩ ዘሮችንም ህብረተሰቡ እየተጠቀመባቸው ይገኛል። በየክፍለ ከተሞቹም የውሃ ማጠጫ የእጅ መሳሪያዎች፣ ጄኔሬተሮች፣ መኮትኮቻዎች ቀርበዋል። በንብ ማነብ ለሚሰማሩ ደግሞ የንብ ቀፎዎችን እና ሌሎች ድጋፎችን አቅርበናል።
ለከተማ ግብርና እና ምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ አላቸው የተባሉ መሳሪያዎችን ግዥ በመፈጸም አምራቾችን የማበረታታት ሥራ እያከናወንን ይገኛል። ከከተማዋ የአየር ንብረት እና አፈር አይነቶች ጋር የሚዛመዱ የፍራፍሬ ዝርያዎችም ለኗሪው ቀርበዋል።
ከዚህ ባለፈ በኮሚሽን ደረጃ የሚተዳደር የችግኝ ብዜት ማዕከል አለ። ማዕከሉ ለከተማ አስተዳደሩ የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን ማፍላት ነው። የተለያዩ የአቮካዶ፣ አፕል፣ ካዝሚር እና የተለያዩ ግለሰቦች በግቢያቸው ውስጥ ሊተክሏቸው የሚችሏቸው ከ120 ሺህ በላይ ችግኞች በአዲስ አበባ ተዘጋጅተዋል።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ግለሰብ በአነስተኛ ቦታዬ ላይ የከተማ ግብርና መስራት እፈልጋለሁ ቢል የግብርና ግብአቶችን በአቅራቢያው ማግኘት የሚችልበት አማራጭ አለ?
አቶ መሐመድ፡- ከከተማዋ የመሬት ሁኔታ እና የቦታ ይዞታ ጋር ሊጣጣሙ የሚችሉ ዘሮችን በማሰራጨት ላይ ነን። በሁሉም ክፍለ ከተሞች 121 ወረዳዎች የዘር አቅርቦት አማራጭ አቅርበናል።
ስለዚህ እያንዳንዱ ቀበሌ ላይ ለከተማ ግብርና የሚሆኑ ዘሮችና ግብአቶችን ነጻ በሚባል ደረጃ ማግኘት ይቻላል። በወረዳ ደረጃ የአርሶአደር እና የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ተቋቁሟል። ጽህፈት ቤቶቹ ዘንድ በመሄድ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል።
በወረዳ ደረጃ የሚፈልጉት ግብአት ባይኖር እንኳን ወደ ክፍለከተማ በመሄድ የአርሶአደር እና ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት በመቅረብ መስተናገድ ይችላሉ። በጽህፈት ቤቶቹ ግብአት ብቻ ሳይሆን የባለሙያ እገዛ ካስፈለገም ድጋፍ ለማድረግ ባለሙያዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ዜጎች ቤታቸው ድረስ በመውሰድ ባለሙያዎች ስለግብርና ሥራቸው እንዲያማክሯቸው ማድረግ ይችላሉ። ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የከተማ ግብርናን ለመተግበር የሚያስችል የባለሙያዎች ቅጥርና ዝግጅት ተደርጓል። ስለዚህ ከኗሪው የሚጠበቀው አስፈላጊው የግብርና ዘር እና የሙያ ድጋፍ እንዲሰጠው በአቅራቢያው በሚገኙ የአስተዳደር ማዕከላት ሄዶ መጠየቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በክረምቱ ወቅት ምን ያክል መሬት በከተማ ግብርና ሥራ ይሸፈናል?
አቶ መሐመድ፡- ቀደም ባለው ጊዜ ለግንባታ እና ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በሚል የታጠሩ ሰፋፊ መሬቶች አሉ። እነዚያ መሬት ለሚፈለገው አላማ እስኪውሉ ድረስ ወጣቶችን በማደራጀትም ሆነ በሌሎች አማራጮች እንዲታረሱ እየተደረገ ነው።
አይሲቲ ፓርክ አካባቢ የሚገኙ ሰፋፊ የታጠሩ መሬቶች ጭምር ለከተማ ግብርና ሥራ እንዲውሉ ተደርጓል። በመንገድ አካፋይ ላይ የሚገኙ እና ለቀጣይ ሥራዎች ዝግጁ ሆነው የተቀመጡ ስፋት ያላቸው መሬቶች ጭምር ነው ለክረምቱ ሥራ ጥቅም ላይ የዋሉት።
እንደከዚህ ቀደሙ የመንገድ መሃል መሬቶች ጤፍ እና የተለያየ ሰብሎችን ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎባቸዋል። በቀጣይም የሚሰራባቸው የመንገድ ዳር ቦታዎች አሉ። በየመኖሪያ ቤት ጓሮ እና አነስተኛ ቦታዎች ላይ የተተከለውን ሳይጨምር 25 ሺህ ሄክታር መሬት በክረምቱ የከተማ ግብርና ይለማል ተብሎ ይጠበቃል።
አንድም ሳይታረስ የሚኖር ቦታ እንዳይኖር ነው ጥረት የምናደርገው። ምግባችን ከደጃችን በሚል መርህ የተለያዩ አይነት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ባለችው ቦታ ላይ እንዲያመርት ጥረት እያደረግን ነው።
ከዚህ ባለፈ ያለሥራ የተቀመጡ መሬቶች ለጊዜውም ቢሆን ውጤት እንዲያስገኙ እየታረሱ በተመሳሳይ ለሥራ እድል ፈጠራውም አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። ሰፋፊ መሬቱ በዚህ ክረምት ብንዘራበት ከሁለትና ሶስት ወራት በኋላ ቦታው ነጻ ይሆናል፤ ለሚፈለገው ዋና አላማ ቦታውን ማዋል ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በክረምቱ የከተማ ግብርና ሥራ በተቋማት ደረጃ ምን ያክል ተሳትፎ እየተደረገ ነው?
አቶ መሐመድ፡- የከተማን ግብርና ከማስፋፋት ጋር ተያይዞ የከተማ ግብርና ላይ የማይሳተፍ ተቋም መኖር የለበትም የሚል አቋም አለን። የትኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋም በከተማ ግብርና ላይ ቢሳተፍ ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም።
የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር ባላቸው ቦታ ላይ የከተማ ግብርናን ሊሰሩ ይችላሉ የሚል ሃሳብ አለን። በዚህ አግባብ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመነጋገር እየሰራን ነው። የተለያዩ ተቋማት ሃሳቡን በመደገፍ በምድረ ግቢያቸው የግብርና ሥራዎችን ማከናወን ጀምረዋል።
ከጊዜ ወደጊዜ የተሳታፊ ተቋማት ቁጥር ቢጨምርም ጎልተው የወጡ ተቋማት ደግሞ መኖራቸው እርግጥ ነው። የትምህርት ተቋማት ግን ሰፊ የከተማ ግብርና ሥራ እያከናወኑ ይገኛል። ከከንቲባ ቢሮ በተሰጠው መመሪያ መሰረት ከተማው ትምህርት ቢሮ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤቶች በከተማ ግብርና በስፋት እየተሳተፉ ይገኛል።
የተማሪ ምገባ ሁል ጊዜ ግብአት በመግዛት ላይ ብቻ መንጠልጠል እንደሌለበት እና እያንዳንዱ ትምህርት ቤት ላይ በሚመረት ምርት የተወሰነውን ወጪ መሸፈን ይገባል በሚል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ እድሜ ጠገብ ትምህርት ቤቶች ሰፋፊ መሬቶችን የያዙ በመሆናቸው የጓሮ አትክልቶችን እያለሙ ይገኛል።
ከስፖርት ሜዳ እና ለትምህርት አስፈላጊ ከሆኑ ቦታዎች ውጪ ያሉ መሬቶቻቸውን ለግብርና ሥራ እያዋሉ ነው። በትምህርት ቤቶች ውስጥ የከተማ ግብርናን ማስፋፋቱ በገቢ ደረጃ ከሚሰጠው ጥቅም ባለፈ ተማሪዎች ስለግብርና ተግባራዊ እውቀትና ልምድ እንዲያገኙ ያግዛል።
ተማሪዎቹም አሰራሩን በቤታቸው ወስደው እንዲተገብሩት የሚያነሳሳ በመሆኑ የትምህርት ተቋማቱ ሥራ ከጅምሩ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል። እኛም ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት የግብአትና የባለሙያ ድጋፍ እንዲያገኝ ጥረት እያደረግን ይገኛል።
ከዚህ ባለፈ አዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ሰፊ ጥረት እያደረጉ ነው። በተለይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲዎችም በከተማ ግብርና ላይ የሚከናወኑ ምርምሮችን በማድረግ የግንዛቤ ሥራዎች ላይ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። በከተማዋ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም ለከተማ ግብርና የሚውሉ ፈጠራዎችን እና ቀላል ቴክኖሎጂዎችን ሰርቶ በማስተዋወቅ ረገድ ጠቃሚ ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው።
ኮሌጆቹ ከዚህ በፊት ለኮንስትራክሽንና ለማምረቻ ፈጠራዎች ይሰጡ የነበረውን ትኩረት አይነት ለከተማ ግብርና እየሰጡ በመሆኑ በትንሽ ቦታዎች ላይ ብዙ ምርት የሚያስገኙ ዘዴዎችን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው። በአጠቃላይ ካየነው የትምህርት ተቋማት በከተማ ግብርና ደረጃ እያበረከቱት ያለው ሚና ትልቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከከተማ ግብርና ጋር ተያይዞ ከአትክልትና ሰብል ልማት ባለፈ ከእንስሳት ተዋጽኦ ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ ኗሪዎች እንዲሳተፉ ምን አይነት ጥረት አደረጋችሁ?
አቶ መሐመድ፡- ከከተማ ግብርና ክንውኖች መካከል የዶሮ እርባታ እና የእንስሳት እርባታ እንዲሁም የንብ ማነብ ሥራዎችም ተጠቃሽ ናቸው። ለንብ ማነቡ ቀፎዎችን እንዳቀረብን ሁሉ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመተባበር ደግሞ በአነስተኛ ቦታ ላይ በርካታ ዶሮዎችን ማርባት የሚያስችሉ ዘዴዎችን በማስተዋወቅ ላይ ነን።
አንድ ግለሰብ በግቢው ውስጥ በሚገኝ አራት ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ወደላይ በመገንባት እንዴት 50 አሊያም 100 ዶሮዎችን ማርባት ይችላል የሚለውን አሰራር በመለየት ላይ ነን። ጤናን በጠበቀ መልኩ በአነስተኛ ቦታ ላይ በርካታ ዶሮዎችን በመኖሪያ አካባቢ ለማርባት የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያመርቱ ጥረት እያደረግን ይገኛል።
ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመተባበር ለአንድ ሰው 100 ዶሮ በሚል መሪ ሃሳብ በትንሽ ቦታ ላይ ማርባት የሚያስችለውን ሥራ በተለይ በቀጣይ ዓመት በተጠናከረ ሁኔታ ለማከናወን ውጥን ይዘናል። ይህም በከተማዋ ያለውን የእንቁላል ዋጋ መናር እና የዶሮ ዋጋ ጭማሪ ለመቀነስ ይረዳል ተብሎ ይታመናል።
ከዚህ በተጓዳኝ ብዙ ወጪ የማይጠይቁና ትርፋማ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ለማምረት የሚያስችል ሙያዊና የግብአት ድጋፍ እናደርጋለን። አርሶአደሮችን በከብት ማርባት፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ዝግጅት ላይ ስልጠና በመስጠት በዘርፉ የተደራጀ ምርት እንዲያመርቱ እያገዝን ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- በክረምቱ የከተማ ግብርና ሥራ ምን ያክል ምርት እንጠብቅ?
አቶ መሐመድ፡- የከተማ ግብርና ምርቶቹ ዞሮ ዞሮ ለከተማዋ ነዋሪዎች ፍጆታ የሚውሉ በመሆናቸው ለመዲናዋ የምግብ ፍጆታ አቅርቦት ከማሳደግ አኳያ የእራሳቸው በጎ አስተዋጽኦ አላቸው።
የከተማ ግብርና ሥራው አንድ ዜጋ ሙሉ ለሙሉ የምግብ ፍጆታ ዋስትናውን ከክረምት ምርቱ ማረጋገጥ ባይችል እንኳን ቢያንስ መጠነኛ ፍላጎቱን ከከተማ ግብርና ማግኘት ይችላል የሚል እይታ አለው።
የከተማ ግብርና ምርት ከአዲስ አበባ ዓመታዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) አንጻር የአንድ ነጥብ ሶስት በመቶውን እንዲይዝ አቅደን ነው እየሰራን የምንገኘው። ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባለፈ አካባቢን አረንጓዴ ከማድረግ እና ጤንነቱ የተረጋገጠ ምርት ከማፍራት አኳያም የከተማ ግብርና ሥራው ሚናው ከፍተኛ ነው።
በመዲናዋ በክረምቱ ወቅት ከሚከናወኑ የከተማ ግብርና ሥራዎች 67 ሺህ ቶን ምርት ይገኛል ብለን እንጠብቃለን። የእቅድ መጠኑ በከተማ ውስጥ ለውጥ ቦታዎች ከሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች እና አጠቃላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶአደሮች ጨምሮ በአጠቃላይ በከተማ ግብርና ከሚሳተፉ 177 ሺህ በላይ አምራቾች የሚጠበቅ ነው።
ተገማቹ የምርት መጠን በሰብል ዘርፍ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበውን ያጠቃለለ ነው። ባለፈው ዓመት የከተማ ግብርና ሥራ 62 ሺህ ቶን ምርት ነው የተገኘው። ዘንድሮ አንጻር ካለፈው ዓመት ብልጫ ያለው ምርት ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- ካለፈው ዓመት የበለጠ ምርት ይገኛል ብላችሁ ግምት ያስቀመጣችሁት ከምን አንጻር መዝናችሁት ነው?
አቶ መሐመድ፡- ለክረምት የከተማ ግብርና የግብአት ድጋፍ ብንመለከት ካለፈው ዓመት የተሻለ ነው ዘንድሮ ያቀረብነው። ከተደረገው ዝግጅት እና የዝናብ ሁኔታ አንጻር ስንመዝነው የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ገምተናል።
ለአብነት ባለፈው ዓመት አርሶአደሩ ያቀረብነው ማዳበሪያ ስምንት ሺህ ኩንታል ነበር፤ አሁን ፍላጎትም በማደጉ በእጥፍ አቅርበናል። ይህን ያክልም አቅርበን አሁንም በተጨማሪነት አርሶአደሩ ጋር ያለው ፍላጎት እያየለ በመምጣቱ በገንዘባቸው ጭምር ገዝተው መጠቀም ለሚፈልጉትም እድሉን እያመቻቸን ነው።
በምርጥ ዘር አቅርቦት ብናይ ያለፈው ዓመት አንድ ሺህ ኩንታል ነው ለከተማ ግብርና ተጠቃሚዎች ያቀረብነው፤ ዘንድሮ ግን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ነው እየሰራን የምንገኘው። በተጨማሪ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች በመጠኑም በማቅረባችን የተሻለ ምርት እንድናገኝ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ከግብርና ሥራዎች የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ በሚኖሩ ሥራዎች ላይ በህብረት የአርሶአደሩን ሰብል የመሰብሰብ እና በአግባቡ እንዲከማች ማድረግንም ያጠቃለለ የድጋፍ ክንውን ታሳቢ ሲደረግ የታቀደውን ያክል ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ምርት ሊገኝ እንደሚችል ይጠበቃል።
አርሶ አደሩም ሆነ የከተማው ነዋሪም በግብርና ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ነው። ከየወረዳዎችም ሆነ ከገበያ ገዝቶ የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን በመትከል እያለማ ይገኛል። ባለችው ጠባብ ቦታም ቢሆን የእራሱን ጥረት የሚያደርገው አዛውንትና ወጣት ቁጥሩ ቀላል አይደለም።
ይህን እንቅስቃሴውን ደግሞ በመጠኑም ቢሆን መደገፍ ስንችል በየዓመቱ በመኖሪያ አካባቢው ማልማት የሚፈልገው ኗሪ ቁጥር እየጨመረ ይመጣል። ይህ ሲሆን እንደአደጉት ሀገራት ምርጥ ከተሞች ሁሉ ንጹህ አካባቢን በመፍጠር የምግብ ፍጆታን መሸፈን የሚያስችል አማራጭ መፍጠር ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ከከተማ ግብርና ሥራዎች ጋር በተያያዘ የመሬት መቀራመት ችግር እንዳይፈጠር ምን ያክል ጥንቃቄ አድርጋችኋል?
አቶ መሐመድ፡-የከተማ ግብርናን በማስፋፋት ተግባር ጠንካራ የህብረተሰብ ተሳትፎ እየታየ እንዳለ ሁሉ ችግሮችም የተስተዋሉበት ነበር። ከዚህ ቀደም በተመለከትነው መሰረት የከተማ ግብርናን እሰራበታለሁ በሚል የተለያዩ ቦታዎችን በመያዝ በኋላ በዘላቂነት በይዞታነት ለማረጋገጥ የመፈለግ ሁኔታዎች መኖራቸውን አይተናል።
የከተማ ግብርና የሚሰሩበትን ክፍት ቦታ የእኔ ነው ብሎ ህጋዊ የመሬት ማስረጃ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አግባብ አይደለም። ከክፍለ ከተማና ወረዳ የመሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ቀርበው ጥያቄ ያቀረቡም ነበሩ። ይህ አካሄድ ግን ስህተት መሆኑን አስረግጠን እየገለጽን ነው።
ችግሩን ለመቅረፍ በመጀመሪያ ደረጃ እያደረግን ያለው የግንዛቤ ትምህርት መስጠት ነው። ‹‹ምግባችን ከደጃችን›› በሚል መሪ ቃል የመኸር እርሻ ሥራ የማስጀመር ሰፊ የከተማ ግብርና ንቅናቄ መድረክ በተካሄደባቸው ሳምንታትም ከከተማ ግብርና ጋር ተያይዞ የመሬት መቀራመት ህገወጥነት ላይ እንዳይሳተፍ ለህብረተሰቡ መልዕክት ተላልፏል።
ህጋዊ ሆኖ የመንግሥት የመሬት ምዝገባ እና ቁጥጥር አካል እስካላወቀው እና ፍቃድ እስካልሰጠበት ድረስ ለከተማ ግብርና ብሎ መሬትን ለሌላ አላማ ማዋል እንደማይቻል ሁልጊዜ መልዕክት እያስተላለፍን ነው።
ለልማት የታጠሩ ቦታዎች ላይ ለከተማ ግብርና የተሰማሩ የተደራጁ ወጣቶችም ከከተማ አስተዳደሩ በሚገቡት ውል መሰረት ነው የሚሰሩት። ሥራው ሲጠናቀቅ በውሉ መሰረት መሬቱ ለታለመለት የግንባታም ሆነ ሌላ ልማት ሥራ ይውላል። ከዚህ ውጪ በማንኛውም መንገድ በከተማ ግብርና ሰበብ የሚደረግ የመሬት ወረራ ተቀባይነት የለውም።
በየአካባቢው የሚገኙ የጸጥታ አካላት ለከተማ ግብርና በሚል የመሬት ወረራ የሚያካሂዱ ካሉ የህግ እርምጃ እንደሚወስዱ ተነጋግረናል። ስለዚህ እስካሁን ጥቃቅን ችግሮችን አይተን ለማስተካከል ሞክረናል፣ አስጊ የመሬት ወረራ የሚመስል ችግር ካለ ግን አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ማወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ከከተማ ግብርና ሥራዎች ባለፈ ለልማት ተነሺ አርሶአደሮችን በምን መልኩ ድጋፍ እያደረጋችሁ ነው?
አቶ መሐመድ፡- የልማት ተነሺ አርሶአደሮችን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ላይ ነው አተኩረን እየሰራን የምንገኘው። የተለያዩ ማዕከላትን ገንብተን የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ እና ለአርሶአደሮቹም ሆነ ለልጆቻቸው የሚሆኑ እንደትምህርት ቤት ያሉ የአገልግሎት መስጫዎችን ለተጠቃሚዎች እናቀርባለን።
በቅርቡም የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል። ከነዚህም መካከል የጎበና ቡታ፣ የአቤቤ ቱፋ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና የመጀመሪያው ምዕራፍ የአርሶአደሮች መልሶ ማቋቋም የእንስሳት እርባታ እና ተዋጽኦ ማዕከልን ተጠቃሽ ናቸው።
በከተማው አስተዳደር ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል የተገነባው የጎበና ቡታ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 49 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ የሆነበት ሲሆን በ561 ነጥብ 3 ካሬሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው። የአቤቤ ቱፋ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ51ሚሊዮን ብር ወጪ ሁለት ዘመናዊ ባለ4 ወለል ህንጻዎች የመማሪያ ክፍሎች ፣ የመመገቢያ አዳራሾች አሉት። .
የአርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ የእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ ማዕከል በ14 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን በርካታ አርሶአደሮችን የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችል ዘመናዊ ማዕከል ነው። የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችም በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ዋነኛ ተጠቃሚ ናቸው።
በተጨማሪ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል። በከተማዋ ያሉ አርሶአደሮችን ከዚህ ቀደም ከገጠማቸው ከፍተኛ ማህበራዊ ችግር ለመታደግ እና መልሶ ለማቋቋም በዘላቂነትም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
የልማት ተነሺ አርሶአደሮች በየክፍለከተማው በማነጋገር ችግሮቻቸውን እና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ውይይት በማድረግ ላይ ነን። አርሶአደሮቹን በከብት ማድለብ ፣ በወተት ላም እርባታ፣ በዶሮ እርባታና በንግድ ሥራ ላይ ስልጠና እየሰጠን ይገኛል። ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ መሐመድ፡- እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም