የቱንም ያህል በኢንዱስትሪው ዘርፍ ጫፍ የደረሰ እድገት መታየት ቢችልም ግብርና አይቀሬ የሆነና ለኢንዱስትሪውም ጭምር የጀርባ አጥንት ስለመሆኑ ይነገራል። ግብርና በተለይ ለታዳጊ አገሮች ሁሉ ነገር ነው ማለት ይቻላል። ምንም እንኳ መምጫ መንገዱ በኢንዱስትሪ ውስጥ ይሁን እንጂ በበለጸጉ አገሮችም ቢሆን የምግብ ጠረጴዛቸው ላይ ተትረፍርፎ የሚታየው ምግብ መነሻው የግብርና ውጤት ስለመሆኑ አይዘነጋም። ታዲያ ግብርናው ለሰው ልጆች የዚህን ያህል ላቅ ያለ ጥቅም ያለው በመሆኑ የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር በዚህ የመኸር ሰብል ወቅት እየተንቀሳቀሰበት ስላለው አካሄዱና በተለይ ደግሞ መንግስት ከውጭ አገር በውጭ ምንዛሬ የሚመጣን የስንዴን ምርት አገር ውስጥ በማምረት ለመተካት እቅድ ይዞ እየሰራ ስላለው ስራ አዲስ ዘመን በግብርና ሚኒስቴር የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ተወካይ አቶ ገርማሜ ጋሩማ ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አሰናድቶታል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡– ዘንድሮ የመኸር ሰብል ዝግጅት ምን ይመስላል? ምን ያህልስ መሬት በሰብል ተሸፍኖ ምን ያህል ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል?
አቶ ገርማሜ፡– በ2013/14 የምርት ዘመን በአጠቃላይ ወደ 13 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማረስ 375 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት እቅድ ተይዟል። ይህንን እቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተዋል። ከእነዚህም መካከል አንዱ የግብዓት አቅርቦት ነው። ለምሳሌ የማዳበሪያ አቅርቦቱን ከባለፈው ዓመት አራት ሚሊዮን ጭማሪ በማድረግ 18 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አገር ውስጥ ማስገባት ተችሏል። አሁን በመጓጓዝ ላይ ያለው ጥቂት ያህል ማዳበሪያ ብቻ ነው።
750 ሺህ ኩንታል የምርጥ ዘር ዝግጅት ተደርጓል። ይህም ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል ላይ ይገኛል። እንዲሁም ለሚቀጥለው ዓመት የሚበቃ የሰብል ጥበቃ የአግሮኬሚካል እንዲሁ በግል ባለሀብቱ ማለትም በነጋዴ የሚመጣው ነው። በዚህ በኩል ድጋፍ ሰጥተን ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።
በአጠቃላይ በዓመቱ ትኩረት ከሚሰጣቸው ሰብሎች አንዱ ስንዴ ነው። በቆሎ፣ ጤፍ፣ ገብስ በዋናነት የምግብ ሰብሎች ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው። ስለሆነም በእነዚህ ሰብሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶባቸው የሚሰሩ ናቸው። ከ13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታሩ ጤፍ ነው። ከ1 ነጥብ 8 እስከ 2 ሚሊዮን የሚጠጋው ደግሞ ስንዴ ነው። ወደ 1 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ በቆሎ ነው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ማሽላም አንዱ የምግብ ሰብል ውስጥ የሚካተት በመሆኑ ነው።
ስለዚህ እነዚህ አምስት ሰብሎች በዋናነት ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰራባቸው ናቸው። በዋናነት ለእነዚህ የሚሆን በተለይ ለስንዴ፣ በቆሎ እና ጤፍ አብዛኛው የግብዓት ዝግጅት ተደርጎ ወደስራ ተገብቷል። እስካሁን ባለው ሂደት ማለትም ከሳምንት አስቀድሞ ወደ 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሷል። ወደ አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ደግሞ በዘር ተሸፍኗል።
በዚህ ዙሪያ ትኩረት ተደርጎ ስራው እየተሰራ ነው። አጠቃላይ ያለው የአየር ሁኔታ በጣም ምቹ ነው። በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራም ሆነ በአንዳንድ ቦታዎች በተወሰኑ ኪስ አካባቢዎች የዝናብ መዘግየት ታይቶ ነበር። በአሁኑ ሰዓት በሁሉም አካባቢ በቂና መደበኛ እንዲሁም ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እየጣለ ነው። አርሶ አደሩ የማሳ ዘዝግጅቱን በማድረጉ ዘር ጀምሯል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለአርሶ አደሩ የሚቲዮሮሎጂ መረጃ እንዲደርሰው ይደረጋል።
በየአስር ቀኑ የሚወጣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሪፖርት አለን። ይህንንም ሪፖርት ለክልሎች እንልካለን ፤ ክልሎች ደግሞ በተዋረድ መረጃውን ያደርሳሉ። ዝናቡ በምን ያህል ሁኔታ ነው የሚቀጥለው፤ ጎርፍስ የት የት አካባቢ ነው የሚያጠቃው የሚሉና መሰል መረጃዎችን ለአርሶ አደሩ ያደርሳሉ። የተባይም ክስተት ካለ እንዲሁ መረጃው ይሰጣል።
አዲስ ዘመን፡– በስንዴ ራስን የመቻል ሂደቱ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ሲነገር የቆየ ነውና ጉዞው ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ገርማሜ፡– አዎ! በጣም ስኬታማ ነው ማለት እንችላለን። እንደሚታወሰው ስንዴ የማልማትን ተግባር የጀመርነው በበረሃማው አካባቢ ነበር። በመቀጠልም ዘንድሮ በወይናደጋውም በደጋውም መስራት ጀምረን ውጤታማነቱን እያየን ነው። በዚህም ከዝናብ ከምናገኘው መኸር በተሻለ ምርታማነቱን ስናስተውል በመስኖ ያገኘነው ተሽሎ አግኝተነዋል።
ስለዚህ አሁን እሱ ስራ ተጠናቋል፤ በመሆኑም ጉዟችን ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ወደመኸር ነው። መኸርም ላይ እንዲሁ ትኩረት ተሰጥቷል። አንደኛ ከስንዴ ምርት በዚህ መኸር እስከ ስልሳ ሚሊዮን ኩንታል ይጠበቃል። የአገራችን ፍጆታ ደግሞ በየዓመቱ የሚያስፈልገን ከ60 እስከ 65 ሚሊዮን ኩንታል ነው። ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልሽ ለዚህ ግብ ስኬት አስፈላጊው ምርጥ ዘር ተሰራጭቷል። በተመሳሳይም ማዳበሪያ ተሰራጭቷል። እንዲሁም የአሲዳማነት ችግር ያለባቸወ አካባቢዎች እንዲሁ በተመሳሳይ መሬቱን ማከሚያ የሚሆን ኖራ ተሰራጭቷል። በየክልሉ ደግሞ የኖራ መፍጫ ወፍጮዎች አሉ።
በተለይ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ እነዚህ ሶስቱ ክልሎች ናቸው ከፍተኛ የመሬት አሲዳማነት ችግር ያለባቸው። እነዚህ ክልሎችም ኖራውን ለአርሶ አደሩ አሰራጭተዋል። ስለዚህ በቀጣዩ ዓመት በመኸር የእርሻ ሰብል ይገኛል ብለን ያቀድነው የስንዴ ምርት ከተሳካ እና ይህንኑ ምርት ከፍ ለማድረግ በበጋ ስንጨምርበት ምናልባት 90 እና 95 መቶ የአገር ውስጥ ፍጆታችንን እናሟላለን ብለን እንጠበቃለን።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ተፋሰስን በመጠቀም ወደ ስንዴ ምርቱ ለማግባት ዝግጅቱ እንዳለ ጠቅሰዋል፤ በቅርቡ የተመረቁ እንደ ርብ አይነት ፕሮጀክቶች ምን ያህል ውጤት እያስገኙ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ገርማሜ፡- በመሰረቱ የተፋሰሱም ዝግጅት ለራሱ ለአርሶ አደሩ ነው፤ አንዱ እያንዳንዱ አርሶ አደር መሬት አለው፤ የተለያዩ ዝርያዎችን አትክልቱንም ሆነ ሰብሉን እንዲሁም ፍራፍሬውን ያመርታል። እኛ እነዚህን ሁሉ ማምረት በሚያስችለው አቅም ልክ እንዲመርት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ነው የምንሰራው።
በተለይ አርሶ አደሩ ምን ምን ቢያመርት ነው ውጤታማ መሆን የሚችለው የሚለውን በመግለጽ ያለውን ጠቀሜታ እንነግረዋለን። እኛ የአገሪቷ ፍላጎት በአሁኑ ወቅት ስንዴ በመሆኑ ስንዴ እንዲያመርት እና ወደዛም ምርት እንዲገባ ነው ለአርሶ አደሩ የምንነግረው። ሁሉም አርሶ አደር ወደዚህ ወደስንዴ የማምረቱ ተግባር እንዲገቡ ይደረጋል፤ ፍላጎት ያለው ወደ ስንዴ ማምረቱ ይገባል። ነገር ግን አርሶ አደሩ ለራሱ የሚበጀውን መርጦ የእኔ ፍላጎት ሽንኩርት ማምረት ነውና የምገባው ወደ ሽንኩርት ማምረቱ ነው ካለ መብቱ ነውና ወደዚያው መግባት ይችላል።
በእርግጥ ባሉን ትልልቅ መስኖዎች በሙሉ በስንዴ ይሸፈናል ተብሎ አይገመትም። አንዳንዱ የሚወስነው ራሱ አርሶ አደሩ ነው። በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን ዘርም ሆነ አስፈላጊውን ግብዓት አዘጋጅተን በዚህ በዚህ ሁኔታ የምትሰሩ ከሆነ በሄክታር ይህን ያህል ኩንታል ምርት ታገኛላችሁ። በሽንኩርት ከምታባክኑት ጉልበት በዚህ የተሻለ ውጤት ታገኛላችሁና ወደዚህኛው ምርት ግቡ በሚል ምክር እንሰጣለን። ያለውን ጥቅምና ጉዳት በአግባቡ ሰርተን ነው የምናሳያቸው።
በዚህ በምንሰጣቸው ምክር የሚስማሙ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ የኦሮሚያም የአማራም አርሶ አደሮች በተነቃቃ ፍላጎት ነው የሰሩት። ስለዚህ ርብም ሆነ ሌሎችም በደቡብ ክልልም እንዲሁም አንድ ትልቅ የጊዳቦ ግድብም ለመስኖ ስራው ይገባል። ዘንድሮ ግማሽ ያህሉ የገባ ቢሆንም በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ብቻ ሳይሆን በወንዝ ዳርቻዎች ልክ አምና እንደሰራነው ፓምፕ በመጠቀም በየወንዝ ዳርቻዎች ያሉ ማሳዎችን ሁሉ በዚህ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ የበለጠ ይደረጋል። ይህን የምናደርገው ዘመናዊ መስኖን ተጠቅመን ሳይሆን ወንዞቻችንና ጉድጓዶችን በመጠቀም ነው። ከዚህ በተጨማሪ አዋሽ ተፋሰስ አለ፤ ባለሀብቱ ፈቃደኛ ከሆነ በሰፊው በዛ ላይም መስራት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ ግብዓቱ መዳረሱን ነው የጠቀሱልን፤ ነገር ግን አንዳንድ ክልል ባሉ ዞኖች ውስጥ ግብዓቱ ከሚፈለገው በላይ ሲሆን፣ ሌሎቹ ዘንድ ደግሞ የማይዳረስበት ሁኔታ አለና ይህ የማመጣጠኑ ስራ እንዴት ይታያል? የማስ ኃላፊነት ነው?
አቶ ገርማሜ፡– ክልሎች በበጀታቸው ኳላራተራል ይገቡና ግብርና ሚኒስቴር ከብሄራዊ ባንክ እስከ 30 ቢሊዮን ብር ይበደርና ማዳበሪያ ይገዛል። በእንዲህ አይነት መልኩ ለእያንዳንዱ ክልል ለምሳሌ ኦሮሚያ የ10 ቢሊዮን ብር ማዳበሪያ ገዝቶ ከሆነ የ10 ቢሊዮን ብሩ ማዳበሪያ ለኦሮሚያ እንደሚሰራጭለት ይነገረውና ወደ ክልሉ ማዳበሪያ እንዲሄድ ይደረጋል።
ክልሎቹ እንዳልኩሽ ከብሄራዊ ባንክ ተበድረው የገዙትን ማዳበሪያ የት የት ይራገፍላቸው የሚለውን በመረዳት ልክ ማዳበሪያው ከጅቡቲ እንደተነሳ ወይ ወለጋ ወይም ደግሞ ጂማ ሊሄድ ይችላል። ይህም ማለት ማዕከላዊ መጋዘኖች ባለበት ይራገፋል። ከዚህ ቀጥሎ ወደየመሰረታዊ ማህበር የሚሄድ ሲሆን፣ መሰረታዊ ማህበሩ ደግሞ ለየአርሶ አደሩ ያሰራጭ። ለሁሉም ክልሎች በዚህ መልኩ ነው የሚሄዱት።
አንድ ወረዳ ላይ ትርፍ አለ፤ በሌላ ወረዳ ደግሞ ጎዶሎ ነው የሚለው የእነርሱ ስራ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ማዳበሪያን የገዙት በራሳቸው በጀት ሲሆን፣ የት ዘንድ ክፍት አለ የሚለውን ማረጋገጥና ማከፋፈል የሚጠበቅባቸው ራሳቸው ናቸው።
ከፌዴራል መንግስት ለየትኛውም ክልል ከራሱ ገንዘብ ውጪ የሚላክለት ተጨማሪ ነገር የለም። የ10 ቢሊዮን ብር ማዳበሪያ ነው የምፈልገው ላለው ክልል እንዳልኩሽ የሚላክለት ያው የ10 ቢሊዮን ብር ማዳበሪያ እንጂ የ11 ቢሊዮን ብር ማዳበሪያ ሊላክለት አይችልም። ምክንያቱም የማን ብር ነው ሊላክለት የሚችለው። ስለዚህ እያንዳንዱ ክልል የዚህን ያህል ብር ማዳበሪያ ይላክልኝ ባለው መጠን ብቻ ነው የሚላክለት። ከዚያ በኋላ የዚህ ቀበሌ ማዳበሪያ በዝቷል፤ ወይም አንሷል የሚለው የራሳቸው የየክልሎቹ ስራ ነው ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– እንደሚታወቀው አረንጓዴ አሻራ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ቆይቷል፤ አረንጓዴ አሻራና የሰብል ልማት ያላቸው ትስስር እንዴት ይገለጻል?
አቶ ገርማሜ፡– አረንጓዴ አሻራ ከሰውም ከእንስሳትም እንዲሁም ከሰብልም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ነው ያለው። አገራችንን በረሃማነት እያጠቃው ሲሄድ የዝናብ ሁኔታ እየተቆራረጠ በወቅቱ የማይወጣና በወቅቱ የማይመጣ፤ ሲፈልግ በጎርፍ አጥለቅልቆ አገር ምድሩን የሚገለባብጥ፤ ሲሻው ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ድርቅ እንዲሆን በማድረግ በኩል ተጽዕኖው የመበርታቱ ዋናው ምክንያት አካባቢያችን በእጽዋት ያለመሸፈኑ ጉዳይ ነው።
በዕጽዋት የተሸፈኑ ቦታዎች ሲታዩ ዝናቡ በተገቢው መንገድ ይዘንባል። ስለዚህ የአርንጓዴ አሻራ ዋና የሰብል ምርትና ምርታማነትን በማሳደጉ በኩል ትልቅ አስተዋጽዖ ያለው ነው። ምክንያቱም ትልቁ ግብዓት ዝናብ ነው፤ ውሃ ነው። አዲስ አበባ እና ካፋ እኩል አይደሉም። እንዲሁም አዲስ አበባ እና ኢሉ አባቦር እኩል አይደሉም። ካፋና ኢሉ አባቦር በደን የተሸፈኑ ናቸው። በአካባቢው ዝናብ በወቅቱ እንዲሁም በሚፈለገው መጠን ይዘንባል።
ወደ አፋር ብንሄድ ወይ ይዘንባል፤ ወይም ደግሞ አይዘንብም። ቦረናም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። የአረንጓዴ አሻራ ሳያሰልስ የሚከናወን ከሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ይበለጽጋል። ዝናብ ሳይስተጓጉል በወቅቱ መዝነብ ይችላል። ስለዚህ እኛ በሁሉም ስፍራ አረንጓዴ አሻራችንን የምናኖር ከሆነ ለሰብል ልማት ትልቁን አስተዋጽኦ አበረከትን ማለት ነው። ለሰብል ልማት ውሃ ዋና ጉዳይ ነውና።
ስለዚህም አረንጓዴ አሻራን ማሳረፍ ለሁሉም ነገር መፍትሄ እንደማበጀት ይቆጠራል። ለሰው ቀለብ፤ ለእንስሳቱ መኖ ለሁሉም ነገር መላ የሚያመጣ ነው ማለት ይቻላል። ደን ባለበት ቦታ ድህነት የለም። ሌላው ቀርቶ ዘር ባንዘራ እንኳ ድህነት አይኖርም። ደን ካለ ማር አለ፤ ቅመማቅመሙ አለ፤ ሌላው ቢቀር ዛፉን ሸጦ መብላት ይቻላል። ድህነት ሊባል የሚችለው ዛፍ ሳይኖር ሲቀር ነው።
በ1990ዎቹ አካባቢ ድሬዳዋ በጎርፍ ስትጠቃ የመጨረሻዋ ዛፍ ተቆርጣ ነው መባሉን አስታውሳለሁ። እንደሚታወሰው የድሬዳዋ ጎርፍ የመጣውም አሳቻ በሆነ በውድቅት ሌሊት ነበር። ለዛ ሁሉ አደጋ የመጋለጣችን ምክንያት ዛፍ ባለመኖሩ ነው። የዛፍ መኖር ለግብርናው ለሰብል ልማት ትልቅ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡– ግብርና ሲታሰብ ዘርቶ ለማጨድም ሰላም በእጅጉ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን በትግራይ ክልል ያለው የግጭት ሁኔታ በተፈለገው ልክ ማምረት የማያስችል እንዲሁም አምናም አስቸጋሪ ጊዜ እንደሆነ ይገመታልና እንዴት እያስኬዳችሁት ነው?
አቶ ገርማሜ፡– ክልሉ አምና አምርቷል፤ ነገር ግን ህዝቡ ያመረቱትን መሰብሰብ አለመቻላቸው ነበር ችግሩ። አምና እንደሚታወቀው አርሰው፣ ዘርተው፣ አጭደውና ከምረው ባለበት ጊዜ ነው ግጭቱ የተከሰተው። በእርግጥ የከመሩትን ወቅተው መብላት አልቻሉም።
በአሁን ሰዓትም ቢሆን በተለይ ግብዓትን በተመለከተ የሚቆጣጠር አካል አለ፤ ማዳበሪያም ሆነ ምርጥ ዘር ወደ ክልሉ ገብቷል። የተወሰነ ነበር የቀረው። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ ማቆሙን ተከትሎ ሰራዊቱ ከመቀሌ ስለወጣ ወደዛ መግባት አልተቻለም። ከዛ ውጪ ግን ከስልሳ አራት ወረዳዎች ውስጥ ወደ 50 ያህል ወረዳዎች ስራ ጀምረው ነበር። አሁን ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ብዙም አላወቅኩም። ይሁንና የትግራይን ክልል የሚቆጣጠር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንድ ብሄራዊ ኮሚቴ መኖሩን አውቃለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በ2013/2014 የመኸር ምርት ዘመን እናሳካዋለን ብላችሁ ለያዛችሁት እቅድ በትግራይ ክልል የተፈጠረው ችግር እቅዱን አያስተጓጉልም ይላሉ?
አቶ ገርማሜ፡– የትግራይ ክልል ምርት መስተጓጎል እንደ አገር ለተያዘው እቅድ የሚያመጣው ምንም ችግር የለም። የትግራይ ክልል የሚያመርተው ምርት ለራሱ እንኳ አይበቃውም። ሁሌም የሚሄደው ከማዕከል ነው። ስለዚህ ካለው ችግር የተነሳ መዝራትም መሰብሰብም ባይችሉም እዚህ ማዕከል ላይ ጥሩ ስራ መስራት ከቻልን እነርሱ ዘንድ ስጋት አይኖረንም። ምክንያቱም እነርሱን መቀለብ ይቻላልና ነው።
አዲስ ዘመን፡– የአገሪቱ ግብርና ዛሬም ድረስ የሚንጠለጠለው በተፈጥሮ ላይ ነው፤ በቀጣይ የሰብል ምርቱን ለማዘመን ምን ታስቧል? በዚህ ዙሪያ የተያዙ እቅዶች ይኖሩ ይሆን?
አቶ ገርማሜ፡– ዘመናዊ ስንል መታወቅ ያለበት አንድ ነገር ለምሳሌ ቻይናም ብትሄጂ በመስኖ የሚያመርቱት 20 በመቶ ብቻ ነው። 80 በመቶ ያህሉ የሚለማው በዝናብ ነው፤ ወደ አሜሪካም ብትሄጂ 30 በመቶ ያህሉ በመስኖ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ያለው በዝናብ ነው።
በመሰረቱ መስኖ የራሱ ችግር ያለበት ነው። ምክንያት ብትይኝ በተፈጥሮ የምንቸረው የእግዚአብሄር በረከት የሆነው ዝናብ ከተቋረጠ ነው በመስኖ መልኩም ልናገኘው የምንችለው። ከዚህ በተጨማሪ ምንም አይነት እንከን የሌለበት፤ ጨዋማነት የሌለበት፤ አፈሩ ላይ ጉዳት የማያስከትል ነገር ቢኖር የዝናብ ውሃ ነው።
እኛ ዋና ምርታችንን የምናመርተው በመኸር ነው። አሁን አስተማማኝ ዝናብ አለን ማለት ይቻላል። ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ደግሞ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ፤ ዝናብ በሚበዛበት አካባቢ ትርፍ ውሃ ከማሳ የማስወጣት ስራ የተለመደ ስራ በመሆኑ አሁንም አለ። ሰብልንም ሆነ አፈርን በማይጎዳ ሁኔታ ትርፍ ውሃን ከማሳ የማስወጣት ስራ ይሰራል። በዚህ ረገድ የተለያየ ቴክኒክ አለ፤ አንደኛ ትርፍ ውሃ ወደማሳ እንዳይገባ ማድረግ ነው፤ አልፎ የሚገባ ከሆነና ማሳው ከተጥለቀለቀ ውሃውን ማስወጣት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ዝናብ አጠር የሆኑ አካባቢዎች ምን ይሁኑ ለሚለው ደግሞ ዝናብ በደንብ የሚዘንብበት አካባቢ ስላለ ውሃውን አጠራቅሞ እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜ ወደ ማሳው መልቀቅ ነው የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል። እነዚህ ስራዎች ባለፉት ሶስት፣ አራትና አምስት ዓመታትም ስንተገብረው ነው የመጣነው፤ አሁንም እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ። ከዛ ውጪ ለመስኖ ምቹ አካባቢ ከሆነ በመስኖ ይደገፋል። ስለዚህም ዝናብ በሚቋረጥበት ጊዜ በመስኖ የመደገፉ ጉዳይ አለ።
ከዚህ ውጭ የመኸር ሰብል እንዳይጎዳ ለአርሶ አደሩ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ጠቃሚ የሆነ መረጃ እንዲደርሰው ይደረጋል። ምን ማድረግ፤ ምን አለማድረግ እንዳለባቸው ምክር ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ በትንበያ መሰረት የዝናብ ሁኔታ ወደፊት መግፋት አሊያም ቀድሞ መጀመር አይነት ነገር የሚታይበት ከሆነ መቼ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከወዲህ መረጃ የማቀበል ስራ ይሰራል። ተባይ የሚኖርም ከሆነ ምን አይነት ዝግጅት እንደሚያደርጉና የቱን አይነት ኬሚካል እንደሚጠቀሙም እናሳውቃለን።
አዲስ ዘመን፡– የኩታ ገጠም እርሻ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ምንም እንኳ በቅርቡ ቢሆንም እንደ አገር ውጤታማነቱ እንዴት ይለካል?
አቶ ገርማሜ፡– ኩታ ገጠም ሲባል ተመሳሳይ የሆኑ ሰብሎችን ወጥ አድርጎ በተመሳሳይ ጊዜ መዝራት፤ ተመሳሳይ እንክብካቤ ማድረግ ማለት ነው። ለምሳሌ ስንዴ የሚዘሩ ሰዎችን ሁሉም በአንድ አካባቢ ባለው በየማሳቸው ስንዴውን እንዲዘሩ ማድረግ ነው።
አሁን ኩታ ገጠም ሲባል መሬቱን ብቻ የማገጣጠም ተግባር አይደለም። የመጀመሪያው ጉዳይ ምክሩ ነው። መሬታቸው የተገጣጠመ አርሶ አደሮች በመጀመሪያ መዝራት ስለሚፈልጉት እና መቼ መዝራት እንደሚኖርባቸው ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል።
ሁሉም አርሶ አደር አንድ አይነት አይደለም። ትጉህ የሆነ አርሶ አደር የመኖሩን ያህል በጣም ኋላቀር የሆነ አርሶ አደርም ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ኋላቀር የሆኑት አርሶ አደሮች የጎበዙን አርሶ አደር አርዓያ እንዲከተሉ በማድረግ እርሻውን ሲያርሱ፣ ዘር ሲዘሩም ሆነ አረሙን ሲያርሙ በአንድ ጊዜ እንዲሆንና ምርቱንም ሲሰበስቡ ሆነ የገበያ ትስስሩን ሲፈጥሩ በአንድ ላይ ማድረግ አዋጭ ስለሚሆን በዚህ ጉዳይ መተባበር ነው። በዚህ ስራ እንደ አገር በጣም ውጤት ማግኘት የተቻለበት ነው።
ባለፈው ዓመት ወደ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ነው በኩታ ገጠም ለመሸፈን የቻልነው። ዘንድሮ ደግሞ ከአጠቃላይ ማሳችን ወደ 6 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ማለትም ከ13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ግማሽ ያህሉን በኩታ ገጠም ለማልበስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ ገርማሜ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013