አዲስ አበባ (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ።የነቀምት ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝና ተጠባባቂ ግብ ጠባቂውም ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
ኮሚቴው ውሳኔውን ያስተላለፈው ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ስታዲየም አርባ ምንጭ ከተማ ከነቀምት ከተማ ባደረጉት የአንደኛው ዙር 9ኛ ሳምንት የከፍተኛ ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ በታየው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።
በእለቱ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ነቀምት ከተማ 2 ለ 1 የሚሆንበትን ግብ ባስቆጠረበት ወቅት የአርባ ምንጭ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ድንጋይ በመወርወራቸው ጨዋታው ለ15 ደቂቃ ተቋርጧል።
በ89ኛው ደቂቃ ላይ የአርባ ምንጭ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ አቶ መሳይ ተፈሪ የቴክኒክ ክልሉን በመልቀቅ ወደ ሜዳ በመግባት የዳኛ ውሳኔ ተቃውሟል።
ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የነቀምት ከተማ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አቶ ቾንቤ ገብረሕይወት የጸጥታ ሃይሎችን በቃል እና በእጅ ምልክት አፀያፊ ስድብ ተሳድቧልም ተብሏል።
የነቀምት ከተማ ቡድን ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ኢብሳ አበበ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በፈጠረው ችግር ዳኞች ለ30 ደቂቃ ከስታዲየሙ እንዳይወጡ መታገታቸውን ኮሚቴው ከጨዋታ አመራሮች ከቀረበው ሪፖርት መረዳት መቻሉን ገልጿል።
በዚሁ መሰረት ኮሚቴው የጨዋታ አመራሮች ሪፖርት በመመርመር የአርባ ምንጭ ከተማ ቡድን 50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትና አንድ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ እንዲጫወት ተወስኖበታል።
የገለልተኛ የውድድሩን ሜዳ በተመለከተ የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ እንዲወስን እንደተመራለትም ተገልጿል።
የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች እያንዳንዳቸው በአራት ጨዋታዎች ላይ ቡድኖቻቸውን እንዳይመሩ እና አምስት ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተወስኗል።
የነቀምት ከተማው ተጠባባቂ ግብ ጠባቂም በሦስት ጨዋታ ላይ እንዳይሰለፍ እና የሦስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖበታል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲስኘሊን መመሪያ ክፍል ምዕራፍ 2 በአንቀጽ 80 በንዑስ አንቀፅ 16 መሰረት የአርባ ምንጭ ከተማ ስፖርት ክለብ ለደጋፊዎቻቸው ስለ ስፖርታዊ ጨዋነትና የስፖርት ህጐች ግንዛቤ እንዲያገኙ በ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ አስተምረው ለፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በጽሑፍ ሪፖርት እንዲያቀርቡም ተወስኗል።
የከፍተኛ ሊግ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመቀጠል የሚገኝ የእግር ኳስ ውድድር ነው።
በሌላ ዜና ነገ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ በጅማ ስታዲየም የአምናው የሊጉ አሸናፊ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት መከላከያን ያስተናግዳል።
ጅማ አባ ጅፋርና መከላከያ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በተመሳሳይ 17 ነጥብ ባላቸው የግብ እዳ ተበላልጠው በቅደም ተከተል 10ኛ እና 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የጨዋታው አሸናፊ ሆኖ ሦስት ነጥብ የሚያገኘው ቡድን ወራጅ ቀጠና ከሚገኙ ክለቦች በነጥብ ለመራቅ ያግዘዋል።
ጅማ ከነገው መርሐ ግብር በተጨማሪ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011