የካቲት 7ቀን 2011 ዓ.ም የተከበረው የመከላከያ ሰራዊት ቀን ያዘጋጀው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በመተባባር ነው። በአዳማው አባገዳ አዳራሽ በዋዜማው በተካሄደው የውይይት መድረክ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጋባዥ እንግዶችና የተለያዩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ታድመዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ መከላከያ እንዲሁም አየር ኃይል ለሀገራቸው ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ በኢፌዴሪ ሠራዊት አባልነትና መሪነት ሲያገለግሉ የነበሩና በጡረታ የተሰናበቱ ባለውለታዎችን በክብር ጋብዘው በዓሉን እንዲሳተፉ በማድረጋቸው፣ ከወትሮው በተለየ መልኩም የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከፍተኛ ጀነራል መኮንኖች መጋበዛቸው በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ሲሆኑ፣ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን ‹‹መከላከያ ሰራዊት በለውጥ ሂደት›› እንዲሁም የአየር ኃይል አዛዥ ብርጋድየር ጀነራል ይልማ መርዳሳ‹‹የኢትዮጵያ አየር ሃይል ታሪካዊ ጉዞ ከትናንት እስከ ዛሬ›› በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፎችን አቅርበዋል።
ጀነራል ሰዓረ መኮንን እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገር እንጂ ብሄር የለውም። ሀገሩ የሚጠብቃትና ሕይወቱን የሚሰጥላት ኢትዮጵያ ነች። የሰራዊት አባል የኢትዮጵያ የሰላም፣ የአንድነቷና የሉዓላዊነቷ ጠባቂ፣ ጥቃት ተከላካይ መከታና ጋሻዋ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወደ ኋላ ስናይ ተከስተው የነበሩት ትርምሶችና ግጭቶች እየተስፋፉ የመሄዳቸውን ያህል ሀገር መከላከያ ሠራዊት በየቦታው እየገባ የተቀጣጠለውን እሳት ባያበርድ ኖሮ ኢትዮጵያ በምንም መልኩ እንደ ሀገር መቀጠል አትችልም ነበር።
በውይይቱ ከአንድ ተሳታፊ የተነሳው የባሕር በር ሳይኖረን ባሕር ኃይል ለምን ያስፈልገናል? የሚልና በሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ አቶ ለማ መገርሳ ምላሽ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ባህር ሃይልን በተመለከተ
የባሕር በር ሳይኖረን ባሕር ኃይል መፍጠሩ አስፈላጊ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ተነስቷል። ይሄ ጥያቄ ለመከላከያ መቅረብ ያለበት ጥያቄ አይመስለኝም። በአንድ በኩል የባሕር በር ጉዳይ ከባድ የሆነ የፖለቲካ አጀንዳ ነው። በአንድ ወገን የመከላከያ ሠራዊታችን ከፖለቲካ መራቅ አለበት ከፖለቲካ ነጻ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኢትዮጵያን ማገልገል አለበት እያልን በጎን ደግሞ እንዲህ አይነት የፖለቲካ አጀንዳ ለመከላከያ መስጠቱ ብዙም ጥቅም የለውም።
ሀገራዊ አጀንዳ መሆን ያለበት የፖለቲካ መሪዎች መመለስ ያለባቸው ጉዳይ ነው።
የባሕር ኃይል ባሕር ሳይኖረን ምን ያደርግልናል የሚለው ባሕር ባይኖረንም ሀይቆች አሉን። የባሕር ኃይል እንዲኖረን የባሕር በር የግድ አይደለም። በዓለማችን ላይ የምናያቸው ብዙ ሀገራት የባሕር በር የሌላቸውም በጠነከረ ሁኔታ የባሕር ኃይል እያደራጁ ነው ያሉት። ባህር የግድ አይደለም። ቢኖረን ቢያድለን ጥሩ ነው። ማን ያውቃል ወደፊት ሊኖረን ይችላል። የባሕር ኃይል እጅግ በጣም ያስፈልገናል። በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች።
አንደኛ በአጠቃላይ የዓለምን ጉዞ በወታደራዊው መስክ ያሉትን እድገቶች ስናያቸው የባሕር በር የሌላቸውም ሀገራት በጠነከረ ሁኔታ የባሕር ኃይል እያደራጁ ነው ያሉት። ሁለተኛ ከአለንበት ቀጣና አንጻር ብናይ የአፍሪካ ቀንድ የሁሉም ዓለም መሰብሰቢያ ቀጣና ነው የሆነው። ዛሬ ዛሬ ስናይ የየቀጣናው አለን ባዮች፣ሌሎችም የዓለም ኃያላን ነን የሚሉ ሀገሮች በቀጣናችን አካባቢ የባሕር ኃይል መንደር ምስረታ እየመሰረቱ ነው። በዚህ ቀጣና ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊነኩ የሚችሉ የኢኮኖሚ መሰረታችን የሆነው አፍሪካ ቀንድ ባህር ላይ ብዙ ሰፈራዎችን እናያለን።
እነዚህ ነገሮች ለክፋት የሚደረጉ ናቸው ብለን ባንልም ሁልግዜ በጎ ናቸው ብሎ ማሰብ ደግሞ ሞኝነት ነው። ባሕር ኃይልን ለመጠቀም በተለይም ለሀገር ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በርካታ ዲፕሎማቲክ ስራዎችን በመስራት ብዙ የምንገለገልባቸው በርካታ ነገሮች ስላሉ ለእኛ እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ያስፈልገናል። ለሀገራዊ ደሕንነታችን ለሀገራዊ ጥቅማችን በጣም አስፈላጊ ስለሆነ በዚህ መልኩ ቢታይ ጥሩ ነው።
የመከላከያ ሪፎርሞች
ሌላው በመከላከያ ውስጥ በርካታ ሪፎርሞች እየተካሄዱ ነው። ቀደም ሲል የነበሩ ሪፎርሞችም አሉ። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ ሀገራዊ ለውጡን ሊመስል፣ ሀገራዊ ለውጡን ሊያጠናክር የሚችል በተለይም የሀገራችንን ሕዝቦች ፍላጎት በተረዳ መልኩ በመከላከያ ውስጥ ለውጥ እየተካሄደ ነው። በአደረጃጀቱ በአጠቃላይ ቁመናው በሳምንታትና በወራት ውስጥ ሳይሆን በየቀኑ ሪፎርም ውስጥ ነው ያለው። በምን ደረጃ የሚለው በሂደት የሚታይ ይሆናል። ነገር ግን መከላከያ ውስጥ ሪፎርም ለመኖሩ የምናረጋግጥባቸው ጥሩ ውጤቶች አሉ።
አጠቃላይ መከላከያ ሠራዊታችን በሚሰራቸው ስራዎች ላይ በሚያስመዘግባቸው ድሎችና ውጤቶች መመዘን ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ብዙ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። መከላከያችን በጣም ከፍተኛ በሆነ ሪፎርም ውስጥ መሆኑን መገንዘቡ በዚህ ደረጃ አስፈላጊ ነው።
የደምብ ልብስ
ለአንድ ሠራዊት የደምብ ልብሱ መለያው ነው። ክብሩ ነው። የአንድ ሠራዊት መለያ ክብሩ የሆነው የደምብ ልብሱ በማንም ሸማቂ በማንም የሰፈር ወንበዴ መጠቀሚያ ሲሆን ይህ የሠራዊታችንን አጠቃላይ ሁኔታ የሚያጎድፍ ከስነምግባሩ ጋርም የማይሄድ ትልቅ ጉዳት ሊያመጣም የሚችል ስለሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባና መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው።
የመከላከያ ሠራዊት የደምብ ልብስ የመከላከያ ሠራዊት እንጂ የማንም የደምብ ልብስ ሊሆን አይችልም። ሊሆን አይገባም። ሊታሰብበት የሚገባው ለመከላከያ ኃይል ወይንም ለመከላከያ ሚኒስቴር ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም። ዞሮ ዞሮ የመከላከያ ኃይል የሀገሪቷ ኃይል እስከሆነ ድረስ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በግል በጋራም ሁላችንም ይሄን መከላከልና ማውገዝ መቻል አለብን። ሕግ ሊወጣለት ይገባል። ይሄን የሚያደርጉ አካላትም ሊጠየቁ ይገባል። ጉዳቱ የጋራችንና የሀገር ጉዳት ስለሆነ ሁላችንም መከላከል አለብን።
የመከላከያ ኃይላችን ኩራታችን
በአጠቃላይ የመከላከያ ኃይላችን ኩራታችን መሆኑን ማየት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ለእያንዳንዳችን ኢትዮጵያውያኖች መከላከያ ኃይል የእኛው የራሳችን ነው። የማንም ኃይል አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጅ፣ የኢትዮጵያ ክንድና ኃይል ነው።
የመከላከያ ኃይላችን የሀገራችንን ክብር የሚጠብቅ የሚያስጠብቅ ኃይል መሆኑን ዝም ብለን ለማወደስ የምንናገረው ጉዳይ ሳይሆን በተግባር ሞቶ በተግባር ዋጋ ከፍሎ ያሳየ ያረጋገጠ ኃይል ነው። ስንወረር ሕይወቱን ገብሮ በዱር በየሸንተረሩ ኖሮ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አስከብሯል። እያስከበረም ነው ያለው። መከላከያ ኃይላችን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ድንበሯን ከመጠበቅ ከማስከበር ከመጠበቅ አልፎ የአፍሪካ አለኝታ መከታም እየሆነ ነው ያለው።
ሁላችንም እንደምናውቀው በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ችግር ሲፈጠር ከማንም በላይ ግንባር ቀደም ኃይል ሆኖ ማንነቱን ለአፍሪካም ለዓለምም ኃይሎች ማንነቱን አስመስክሯል። በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ሰላምን ማስከበሩ በዚያ ሀገር ላይ ሰላምን ማስፈኑ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ደረጃ ከፍ በማድረግ ጥቅሟ በሌላው ዓለም ላይ እንዲከበር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የነበረና ዛሬም ጭምር እየሰራ ያለ ኃይል ነው።
የመከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ ነው። ይህ ማናችንም የምንክደው ጉዳይ አይደለም። መከላከያ ሠራዊታችን ቆራጥ ጀግና ሠራዊት ነው። ተግባሩና ውጤቱ የሚያሳየው ይሄንን ነው። መከላከያ ሠራዊታችን ጀብደኛ እብሪተኛ ሳይሆን ዓላማውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ለዓላማው ስኬት በትልቅ ወኔና ጥበብ የሚሰራ ኃይል ነው። በሚሰጡት ግዳጆች ሁሉ ሀገሩን ያኮራ ያስከበረ እንጂ ያስወቀሰ ሠራዊትና ኃይል አይደለም። ይሄንን ሁላችንም በጋራ የምናውቀው ነው።
ሉዓላዊነታችንና ሰራዊታችን
ኢትዮጵያ በታሪኳም ቢሆን በተለይም ስኬቷን በዚህ ረገድ ካየን እንዲህ በተደራጀ መልኩም ባይሆን ሉአላዊነቷን በማስከበር ረገድ ጠንካራና ቆራጥ ኃይል በመገንባት ጥሩ ታሪክ ያላት ሀገር ነች። ከሕዝብ የተፈጠረ ከሕዝብ የተቀዳ ሠራዊት ስለሆነ ከኢጣሊያን ወረራ ዘመን በፊትም በኋላም ጥሩ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ዛሬ ዛሬ ዓለም ስለኢትዮጵያ ሠራዊት ብቃት መመስከርን በተመለከተ እጅግ በጣም በርካታ ምስክርነቶች የተሰጡ ቢሆንም በተለይም የኢጣሊያን ወራሪ ሃይል በኢትዮጵያዊያን የደረሰበት ታሪካዊ ሽንፈት ስለሚያሳፍራቸው ለመናገር በጣም ይቸገሩበታል። ያን ያህል የተደራጀ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ በዘመናዊ አደረጃጀት የተዋቀረ ወራሪውን የኢጣሊያ ሠራዊት በኋላ ቀር መሳሪያ የመከተ ያዋረደ ጀግና ነው- የኢትዮጵያ ሠራዊት።
ወታደርነት ክብርና ኩራት ነው
ለአንድ ሠራዊት ጥንካሬ ለአንድ ሠራዊት ጀግንነት መሰረቱ ትጥቁ ብቻ አይደለም። መሰረቱ ወታደራዊ ብቃቱና ክህሎቱ ብቻ አይደለም። መሰረቱ የሕዝብ ወገንተኝነቱ የሕዝብ ልጅነቱ ነው። የሕዝብ ድጋፍ ያለው ሲሆን ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ወታደርነት ክብርና ኩራት ነው። እንዲህ አይነት ባሕል ያለን ሕዝቦች ስለሆንን ኋላ ቀር መሳሪያ ይዘን ዘመናዊ ነኝ የሚለውን ሠራዊት ማሸነፍ እንደምንችል ኢትዮጵያዊያኖች ለዓለም አስመስክረናል። በዚህ ረገድ የጎደፈ ታሪክ ያለን ሀገርና ሕዝቦች አይደለንም። ይሄ ዛሬም ጭምር ባሕላችን ሆኖ የዛሬው ትውልድ የመከላከያ ሠራዊታችን ያንኑ ታሪክ እየደገመ ነው ያለው። ይሄ ወደፊትም መጠናከር አለበት።
ጠንካራ አጥራችን
አንድ ሀገር ጠንካራና ደካማ መሆኗ በሌሎች ዓይን የሚለካው ሀገሪቷ ያላት ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ዋናና ትልቁ መመዘኛ ነው። ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት የሌላት ሀገር እንደ ድሀ አጥር ነው የሚቆጠረው። የድሀ አጥር ማለት ሌባውም ውሻውም እንዳሻው ሲገባና ሲወጣበት ክብር የሌለው ማለት ነው። ጠንካራ አጥር ያለውን ማንም አይደፍረውም። መከላከያ ሠራዊታችንም ጠንካራ አጥራችን ነው።
እንዳለመታደል ሆኖ የፖለቲካ መድረካችን እሾህ የበዛበት ሆኖ እንጂ በየግዜው ክፉም ይሁን ደግ የነበሩት መንግሥታት በዚህ ረገድ ለኢትዮጵያ ሲባል ጠንካሮች ነበሩ። ለኢትዮጵያ ጠንካራ ሠራዊት በመገንባት ረገድ የዋዛዎች አልነበሩም። በእርግጥ ፖለቲካችን ብዙ አበላሽቶብናል። አፍርሰን መገንባት እንደ አዲስ ባህላችን ስለሆነ ነው እንጂ ከዚህም የበለጠ ጉልበት አቅም ሊኖረን እንደሚችል ምንም ጥያቄ የለውም። ወደፊትም ትልቅ ትምህርት ሊሆነን የሚችለው ይሄ ነው።
ተቋም በአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን በሂደት የሚገነባ ግን ደግሞ ዘመን ተሻጋሪ ነው። ተቋምን አስቦ መገንባቱ ለእኛ ለዛሬዎቹ ትውልዶች ትልቅ ትምህርት ይሆነናል ሲሉ አቶ ለማ መገርሳ ሰፊና መሳጭ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ወንድወሰን መኮንን