የለንደን እና ሪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች የ800ሜትር ባለ ድል፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሶስት ጊዜ ሻምፒዮን እንዲሁም የ1ሺ500ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ችላለች። ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሰመኒያ፡፡ በርቀቱ ስኬታማ አትሌት ትሁን እንጂ፤ ሁሌም በውድድሮች ካሸነፈች በኋላ መነጋገሪያ ርዕስ መሆኗ ግን አይቀሬ ነው። ምክንያቱ ኮስታራው ፊቷ እና ፈርጣማው ተክለ ሰውነቷ ሲሆን፤ በርካቶችም የጾታዋ ጉዳይ ግራ አጋቢ መሆኑን ይገልጻሉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ አትሌቷና ያልተለመደው ክስተት የተስተዋለው እአአ በ2009 የበርሊን አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ800 ሜትር ውድድር ላይ ነበር። የአጭርና መካከለኛ ርዝመት አትሌቷ ሰመኒያ፤ በውድድሩ ላይ ከተሳተፉት አትሌቶች ሁሉ የወንድ በሚመስለው ተክለ ቁመናዋ የተለየች ነበረች። ውድድሩንም በከፍተኛ ልዩነትና ብቃት ነበር ያሸነፈችው። ነገሩ አወዛጋቢ በመሆኑም ወጣቷ አትሌት ጾታዋን እስከ መመርመር በደረሰ ሂደት ለማለፍ ተገደደች።
የአትሌቷ ጾታ ተረጋግጦ ወደ ውድድር ከተመለሰችም በኋላ እርሷ እና መሰሎቿ ከሌሎች አትሌቶች አንጻር የሚታየው ልዩነት ለበርካታ ጊዜያት በስፖርቱ ዘንድ ቅሬታ ሲያስነሱ ቆይተዋል። ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበርም በምክር ቤቱ ካጸደቀ በኋላ፤ በስድስት ወራት ውስጥ በስራ ላይ እንደሚያውለው አስታውቆ ነበር።
ደንቡ ሴቶችን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፤ የ400፣ 400 መሰናክል፣ 800፣ 1ሺ500 ሜትር እንዲሁም የአንድ ማይል ርቀት ተወዳዳሪ አትሌቶች ላይ የሚተገበር ነው። ይኸውም በሰውነታቸው ያለው «ቴስቴስትሮን» የተባለ ንጥረ ነገር መጠን ከፍተኛ የሆኑ ሴት አትሌቶችን ብቻ ይመለከታል።
በወቅቱም አብዛኛዎቹ ሴት አትሌቶች (0.12 – 1.79 nmol/L) በሆነ ዝቅተኛ የ«ቴስቴስትሮን» መጠን ሮጠው አሸናፊ እንደሚሆኑ መረጃው አመልክቷል። በአንጻሩ በወንዶች ሰውነት ውስጥ በመደበኛነት (7.7 – 29.4 nmol/L) የሚለካ መጠን ያለው ቴስቴስትሮን ይገኛል። (5 nmol/L) እና ከዚያ በላይ መጠን ያለው ንጥረ ነገር በሰውነታቸው የሚገኝ ሴት አትሌቶችም ወደ ወንዶቹ የሚጠጋጋ አቅም ያላቸው ናቸው። ማህበሩም እነዚህ አትሌቶች በሴቶች ምድብ መወዳደራቸውን ትክክል ሆኖ እንዳላገኘውና የአሸናፊነት ዕድሉም ወደ እነዚሁ አትሌቶች ያደላ በመሆኑ ደንቡን ለማውጣት እንደተገደደ ገልጾ ነበር።
በዚህ መጠን ንጥረ ነገሩ በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኙ ሴት አትሌቶችም ሁለት አማራጭ የቀረበላቸው ሲሆን የመጀመሪያው ነገር የሚወዳደሩበትን ርቀት በመቀየር ወደ ረጅም ርቀቶች እንዲገቡ ማድረግ ነው። ሌላኛው ደግሞ በህክምና ማለትም በቀዶ ጥገና አሊያም በመድሃኒት (እስከ ስድስት ወር በሚወስድ ጊዜ) የንጥረ ነገሩን መጠን ከሰውነታቸው መቀነስ ነው። ይህ ደንብ ደግሞ እንደ ሰመኒያ ያሉ አትሌቶችን በተለይ የሚመለከት በመሆኑ ተቃውሞ እንዳላትና ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነም ነገሩን ወደ ህግ እንደምትወስደው አስታውቃ ነበር።
አትሌቷ ከወራት በፊት ማህበሩን በደንቡ ዙሪያ ለመታገል ማቀዷን ዘ ጋርዲያን አስነብቦ ነበር። በአስተያየቷም ላይ «ይህ ትክክል አይደለም፤ እኔ የምሮጠው በተወለድኩበትና ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ነው። እኔ ካስተር ሰመኒያ ሴት ነኝ፤ ደግሞም በጣም ፈጣን» ስትልም ነበር የገለጸችው።
ከሁለት ወራት በፊት ደንቡ ወደ ትግበራ መገባቱን ተከትሎም አትሌቷ እንዳለችውም ጉዳዩን ወደ ስፖርት ገላጋዩ ፍርድ ቤት ማቅረቧን ነው ቢቢሲ በድረ ገጹ ያስነበበው። ጠበቃ አቁማ በመከራከር ላይ የምትገኘው አትሌቷ በደቡብ አፍሪካዊያን እና በሃገሪቷ የአትሌቲክስ ማህበር ዘንድ ድጋፍ ያገኘች ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በምርመራ ሴት መሆኗ መረጋገጡንም ነው የምታነሳው። ከዚህ ባሻገር ይህን ዓይነት ኃይል በሰውነቷ እንዲኖር ያደረገው ተፈጥሮ እንጂ በሰው ሰራሽ መንገድ አለመሆኑን በመጥቀስ ልትገደብ እንደማይገባም ነው እየተከራከረች ያለችው።
አራት አባላት ያሉት የአትሌቷ ጠበቆች ቡድንም ዓለም አቀፉ የአትሌቶች ማህበር ያረጋገጠውን የአትሌቷን ጉዳይ አሁን መልሶ መጣሱ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል። የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሎርድ ኮ በበኩላቸው «ህጉ የወጣው ሴት አትሌቶችን ለማበረታታት በማሰብ ነው። በእኩልነት ላይ የተመሰረተ እና ግልጽ የሆነ ውድድር ለማካሄድም» በሚል ደንቡ መውጣቱን ነው የገለጹት። ጠበቆቹ ግን እኩልነት ላይ የተመሰረተውን ጉዳይ ይዘው ወደ ፍርድ ቤት በማቅናት እንደሚከራከሩ አሳውቀዋል።
በስፖርት የሚነሱ ቅሬታዎችንና አለመግባባቶችን ለመዳኘት የተሰየመው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ከያዘው ሳምንት የሆነው ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ይህንን ያህል የቆየ ጉዳይ አልታየም። ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድቤት ዋና ጸሃፊ ማቲው ሬብ ጉዳዩ በሶስት ዳኞች እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል። ቆይታውን በተመለከተም «ያልተጠበቀና ከዚህ በፊትም ያላጋጠመ አዲስ ክስተት» በመሆኑ ውሳኔውንም አስተማማኝ ለማድረግ እንደሆነ ማስረዳታቸውን ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
ዳንኤል ዘነበ