የኢትዮጵያ ህክምና ማህበርና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት 4 ኛው የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር ‹‹ለደኅንነታችን እንሩጥ›› በሚል መሪ ቃል እሁድ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ይካሄዳል። የውድድሩ ቅድመ ዝግጅትን በተመለከተ በትናንትናው ዕለት በፌደሬሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተሰጠው መግለጫ ወቅት የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ፤ማህበሩ መርሀ ግብሩን ላለፉት ሶስት ዓመታት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር እና ከዓመታዊ ሀክምና ጉባኤው ጋር በማቀናጀት ሲያዘጋጅ ቆይቷል። በዘንድሮው ዓመትም ይህንን መርሀ ግብር ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማካሄድ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ዘንድሮ ለ4ተኛ ጊዜ‹‹ለደህንነታችን እንሩጥ››የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር ይካሄዳል ብለዋል ።
የህብረተሰቡን ጤና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዋነኛ ዘዴዎች መካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማጎልበት ጤናን መጠበቅ መሆኑን ማሳወቅ፤ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በሰፊው በመስራት ለአትሌቲክሱ እድገት ድርሻ ማበርከት የውድድሩ አላማ መሆኑን አስረድተዋል።« በውድድሩ 2ሺ ስድስት መቶ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩ የገለጹት ዶክተር ገመቺስ፤ከእነዚህ ውስጥ ከአስር ክለቦች የተውጣጡ 100 ሴትና ወንድ አትሌቶች እንዲሁም 2ሺ 500 የህክምና ባለሙያዎች ናቸው» ሲሉ አስረድተዋል።
በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ እንደየ አሸናፊነታቸው የተዘጋጀ የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት ይኖራል። በሁሉም ጮታ ካታጎሪ ለሚሳተፍ በክለብ ተመዝግበው ለሚወዳደሩ አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለሚወጡ የሜዳሊያ ሽልማት ተዘጋጅቷል። እንዲሁም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ለሚወጡት ከ15 ሺ እስከ 1ሺ ብር በየደረጃው የገንዘብ ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል። በሁሉም የጾታ ካታጎሪ ለሚሳተፍ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለሚወጡትም የወርቅ፣ብርና ነሀስ ሜዳሊያ እንደሚበረከትላቸው በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር መነሻውና መድረሻው መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ በማድረግ እሁድ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. በድምቀት የሚካሄድ ይሆናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
ዳንኤል ዘነበ