በሀገራችን የፍቅረኞች ቀን (ቫላንታይን ደይ) የሚከበርበት መንገድ የብዙዎች መነጋገሪያ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም “ምነው ይህ ነገር ቢቀርብን ” ይላሉ፡፡ ፓኪስታን ይህ ቀን በሀገሯ እንዳይከበር በይፋ አግዳለች። ባለስልጣናቱ “ለምን?” ተብለው ሲጠየቁ፤ “ለህዝባችን የሚሰጠው ጥቅም ስላልታየን”፤ በማለት አጭር መልስ ይሰጣሉ። በጉዳዩ ላይ ያመረሩ ጥቂቶች ደግሞ፤ የቀኑን መጠሪያ ቀይረው “የወሲብ ቀን” ብለው እስከመጥራት ደርሰዋል፡፡ ለምሳሌ፤ አንዱ በፌስቡክ ገጹ የለጠፈውን ላስነብባችሁ፡፡
“ዛሬ የተነሳሁበትን የወሲብ ቀንንም በተመለከተ ከአንድ ወር በፊት ሀገሪቷ ውስጥ የሚነገር ነገር የጠፋ እስኪመስል፤ በተለይ በኤፍ ኤም ራዲዮኖቻችን በኩል የተለየ ቅስቀሳ ሲደረግ ሰንብቷል። ቅስቀሳው በግልጽ ነው። ሆቴሎቹ አልጋ አንጥፈው ሽቶ አርከፍክፈው ዝሙቱን እና ድሪያውን በባንድ ሙዚቃና በታዋቂ ዘፋኞች አጅበው እንደሚጠብቋቸው ሲለፍፉ ያልሰማ የለም። ይህን የሰሙ ጨቅላ ህፃናት ሳይቀሩ ወደ ዝሙት ካምፑ ይጎርፋሉ። በዚያም የሚሆነው ሁሉ ይሆናል። ይህ ሁሉ ሲሆን በቤተ መንግሥትም፤ በቤተክህነትም፤ በቤተ መስጊድም ያሉ መሪዎች በደንብ ይሰማሉ፤ ያያሉም። ነገር ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዚህ ጉዳይ አንዳችም ነገር አይናገሩም ሆደ ሰፊም ናቸው”
በሀሳቡ ተስማማችሁ? እኔ ግን ቢያንስ መቆርቆሩንና ትዝብቱን ለማካፈል መድፈሩ ያስመሰግነዋል እላለሁ፡፡ የፍቅረኞች ቀን አቀጣጣይ ቤንዚን/አልኮል ነው፡፡ በፍቅረኞች ቀን እንደጉድ ይጠጣል፡፡ እውነት ፓርላማችን በቅርቡ መጠጥ ላይ መጨከኑ አበጀ የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ፤ የአልኮል መጠጥን በብሮድካስት ሚዲያ አማካይነት ለማስተዋወቅ የሚቻለው ከምሽቱ 5 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ብቻ እንዲሆን ተደንግጎ ቢቀርብም፤ አብዛኞቹ እንደራሴዎች ሙሉ በሙሉ የአልኮል መጠጥ በነዚህ የሚዲያ አውታሮች መተዋወቅ የለበትም የሚል ሐሳብ አቅርበው በሬድዮና በቴሌቪዥን የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎችን ማስነገር ተከልክሏል፡፡ እዚች ላይ ግን በፓርላማው ውስጥ የመጠጥ ነገር የማይሆንላቸው፤ አሊያም በቢራ ፋብሪካዎች ውስጥ አክሲዮን ያላቸው ባለወንበሮች ጠፍተው ነው በሙሉ ድምጽ የጸደቀው? ወይስ የምር ለትውልድ ማሰብ ጀምረው? ማን ያውቃል? ምናልባትም “ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” አሁንም አለሞተ ይሆናል፡፡
ስለ ፓርላማ ሳነሳ ሰሞኑን ቢቢሲ ያስነበበው ዘገባ ትዝ አለኝ፡፡ ጃክሊን ንጎንያኒ የታንዛኒያ ፓርላማ አባል ናት፡፡ ንጎንያኒ ታዲያ ወንድ የፓርላማ አባላትን በተመለከተ ያነሳችው ሐሳብ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የፓርላማ አባሏ ወንድ የታንዛንያ ፓርላማ አባላት መገረዝ አለመገረዛቸው ይረጋገጥልኝ፤ ካልተገረዙም እንዲገረዙ መደረግ አለበት ብላለች፡፡ የቢቢሲ ዘገባ እንደሚለው ከታንዛንያ ወንዶች 70 ከመቶ ያህሉ የተገረዙ ናቸው፡፡ የወንዶች መገረዝ በኤች አይ ቪ ቫይረስ የመያዝን እድል በ60 ከመቶ ያህል ይቀንሳል፡፡ ለአቅመ አዳም ከደረሱ ታንዛንያውያን 5 ከመቶ ያህሉ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር ነው የሚኖሩት፡፡ በኤች አይ ቪ ስርጭትም ከዓለማችን ሐገራት በ13ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የፓርላማ አባሏ ታዲያ “…ለመሆኑ የፓርላማ ባልደረቦቼ ወንዶች ምን ያህሎቻችሁ ይሆን የተገረዛችሁት ይሄ ይረጋገጥልኝ – ያልተገረዛችሁ ካላችሁም ለሕዝቡ ምሳሌ ለመሆን መገረዝ አለባችሁ” ብላለች፡፡
ወደቀደመ ጉዳዬ ልመለስና የፍቅረኞች ቀን ማድመቂያው መጠጥ ነው፡፡ የዕለቱ ሽር ጉድ ፍጻሜውን የሚያገኘው በመጠጥ የመዝጊያ ንግግር ነው፡፡ በፍቅረኞች ቀን ልጃ ገረዶች ቀይ ለብሰው፤ ቀይ አበባ ይዘው ፤ በቀይ ምንጣፍ ላይ ተራምደው፤ ቀይ ወይን ሲጠጡ አምሽተው ቀይ መስመር ያልፋሉ፡፡
ለዚህ ነው በመጠጥ ላይ መጨከኑ አበጃችሁ የሚያሰኝ ተግባር ነው ያልኩት፤ ሌላው ዓለም በዚህ ረገድ ጥሎን ሄዷል፡፡ ለምሳሌ፤ ሲኤንኤ በዚህ ሳምንት ዘገባው፤ የአሜሪካዋ ሐዋይ ግዛት እ.አ.አ እስከ 2024 ድረስ እድሜያቸው ከ100 ዓመት በታች ያሉ ዜጎች ሲጋራ እንዳይገዙ የሚያስገድድ ረቂቅ ህግ ማውጣቷን አስነብቧል፡፡ ዘገባው የአሜሪካዋ ሀዋይ ግዛት ከሌሎቹ ግዛቶች በተለየ ከ21 ዓመት እድሜ በታች ያሉ ወጣቶች ሲጋራ ማጨስን የሚከለክል ህግም እንዳላት በዚህም ግዛቷ ሲጋራ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳትና ሞት ለማስቀረት ማቀዷ ተገልጿል፡፡
እኛ ሀገር ግን በተገላቢጦሽ ልጁ ሲጋራ እንዲገዛለት ሱቅ የሚልክ አባት ጥቂት አይደለም። ተራማጁ ዓለም ደግሞ ከመቶ ዓመት በታች ዕድሜ ያለው ሰው ሲጋራ መግዛት እንዳይችል የሚከለክል ህግ ያወጣል፡፡
በሬድዮና በቴሌቪዥን የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎችን ማስነገር በከለከለው አዋጅ ውስጥ በመንደር ውስጥ የሚሸጥ ጠላ መኖሩን ለማመላከት በጠላ ቤቱ ደጅ መጠነኛ ዘንግ ላይ የሚሰቀል ጣሳ ወይም ኩባያ ተካትቶ ይሆን? ተራ ማስታወቂያ እንዳይመስላችሁ፡፡ ጠላ ሲኖር ጣሳው (ኩባያው) ይሰቀላል፤ ጠላው ሲያልቅ ደግሞ ይወርዳል፡፡ አንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ ውብሸት ወርቃለማው በአንድ ወቅት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በዚህች ጠላ መኖሩን ለመግለጽ በምትሰቀል ጣሳ ተወዳድሮ አሸንፏል፡፡
በአንድ የሬዲዮ ፕሮግራም ደግሞ የመጠጥ ማስታወቂያ ሙሉ ለሙሉ በሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዳይተላለፍ መከልከሉ ተገቢ አለመሆኑን ለማስረዳት የቢራ ፋብሪካዎች በተለያየ መንገድ እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ ሲገልጽ ሰምቻለሁ፡፡ አጋጣሚ ሰምታችሁት ከሆነ ድምጸቱን እንደኔ ሳትታዘቡት አትቀሩም፡፡ ቁጣ የተናነቀው ነው የሚመስለው፤ እንዲያውም ሳዳምጠው አንድ ቀልድ አስታወሰኝ፡፡ የምርጫ ሰሞን ነበር፣ አንድ የቅንጅት ደጋፊ “ቅንጅት ያሸንፋል ኢህአዴግ ይወድቃል!” እያለ ሲጮህ አንድ ፌዴራል ፖሊስ ይይዘውና “ምንድነው አንተ የምትለው! ኢህአዴግ ት/ቤት አልሰራም፤ መንገድ አልሰራም፤ ሆስፒታል አልሰራም?” ብሎ ሲያፈጥበት “ልክ ነህ ሰርቷል ” ይላል ልጁ፤ “ታዲያ ምንድነው የምትለው” ብሎ ፌዴራሉ ሲጠይቀው ልጁ ደንግጦ “አይ ደክሞታል ይረፍ ነው ያልኩት” አለው ይባላል፡፡
ለአንዱ መርገምት የሆነው ለሌላው በረከት ይሆናል፡፡ እንደኔ በአጋጣሚው የእግር ኳስ ቡድኖችና ጋዜጦች የአልኮል መጠጦችን ለማስተዋወቅ ይበልጥ ተመራጭ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ እነዚህ ፈርጣማ አቅም ያላቸው የቢራ ፈብሪካዎች ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ፊታቸውን ወደ በጎ አድራጎት ሥራ ማዞር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
የአልኮል ማስታወቂያ በብሮድካስት ሚዲያዎች እንዳይተላለፍ መደረጉ የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ ክፉኛ ሳይጎዳው አይቀርም፡፡ በዘመናችን አሉ የተባሉ ተዋንያን ፣ ዳይሬክተሮች ፣ሙዚቀኞችና የገጽ ቅብ ባለሞያዎች ተሳትፈውበት ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት የሚሰራው ፊልም ሳይሆን የ1 ደቂቃ የቢራ ማስታወቂያ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አርቲስቶቻችን በመደበኛ ስራቸው ላይ የሚያውሉት በቂ ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡
እንደኔ እንዲያውም የመጠጥ ፋብሪካዎች ፊታቸውን ከተዋንያን ወደ ቀልደኞች መልሰው አሪፍ አሪፍ ቀልዶችን እያስነገሩ ህዝቡን ጦሽ በማድረግ ምርታቸውን የማስተዋወቅ ስልት ቢቀይሱ ያዋጣቸዋል፡፡ ናሳ እንኳን የእነዚህን ቀልድ አዋቂዎች ምትሀታዊ ኃይል ተረድቶ ሊጠቀምባቸው ጉድ ጉድ እያለ ነው፡፡ ከሰሞኑ ዴይሊ ሜል እንደዘገበው የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ድርጅት (ናሳ) ቀልደኛ እና አዝናኝ ሰዎችን በጠፈርተኝነት ለመቅጠር እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ጠፈርተኞች በተለምዶ ቁም ነገረኞች እና ቁጥቦች፤ እንዲሁም በቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ መሣሪያዎችን የሚያበርሩ፤ ከፍተኛ ኃላፊነት ተሸካሚዎች ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ቀልድ አዋቂ እና አዝናኝ ግለሰቦችን መቅጠር ረዥም እና አሰልች የጠፈር ጉዞዎችን አዝናኝ እና አስደሳች ለማድረግ እንደሚረዳ በጥናት አረጋግጫለሁ ብሎ ነው ናሳ ቀልድ አዋቂዎችንና አዝናኞችን መቅጠር የፈለገው፡፡ ምጥን ቀልድ እና ጨዋታ የማንኛውንም የሥራ ቡድን ውጤታማ ያደርጋል በማለት በቀጣዩ 2030 (እ.አ.አ) ለሚደረገው የማርስ ተልዕኮ ከሚጓዙ ጠፈርተኞች ጋር ቀልድ አዋቂዎች አብረው እንደሚጓዙ አሳውቋል፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፤ እዚህም እዛም ስል ረፈደብኝ፡፡ ህግ መውጣቱ ብቻውን መፍትሄ አይደለምና ተፈጻሚነቱን በማረጋገጥ በየዕለቱና በተለይም በፍቅረኞች ቀን በመጠጥ ገፋፊነት የሚቀጠፉ አበባዎችን ሕይወት ለመታደግ ዓመቱን ሙሉ የሚተላለፉ ምራቅ የሚያስውጡ የመጠጥ ማስታወቂያዎች ዘመን እንዲያበቃ እንስራ እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
የትናየት ፈሩ