ወዳጆቼ! እንደምን ከረማችሁ? ክረምቱ እንዴት ይዟችኃል? የዘንድሮ ክረምት ከዝናብና ከብርዱ በተጨማሪ ይዞት የመጣው ነገር ጉድ ያሰኛል። ታዲያ ‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› ማለት ይሄኔ ነው። ይህ ለሰሚው ግራ የሚያገባ ነገር አንድ ታሪክ አስታወሰኝና ላወጋቸሁ ተመኘሁ።
ድሮ ድሮ ነው አሉ። በአንድ በረት ውስጥ በርካታ ከብቶች ይኖሩ ነበር። ከብቶቹ በመልክ ፣ በባህሪይ እና በተግባራቸው ሁሉም የሚለያዩ ነበሩ። በበረቱ አብሮ የመኖርና የመቻቻል ህግ በአንድ ጥላ ሥር እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። አንድን በረት በመጋራት ፣ ለበረቱ ምቹነት በጋራ እንዲተጉ የሚያስገድድ ነበር። ይህ በአንድነትና በመተባበር መሠረት ላይ የታነፀ አብሮነት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ፤ የውጭ ጠላት በአንድነትና በጋራ በመመከት የደመቀ ታሪክ የተጻፈበት ነበር አሉ። እንግዲህ አሉ ነው።
ለበረቱም ጠባቂ እረኛ ያስፈልገዋል። ለበረቱ የሚስማማ፤ የእረኛ መመሪያና ህግ የሚያሟላ እረኛ ይሾምለት ነበር። እረኛው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በረቱን በአግባቡ በመጠበቅ፤ ያስተዳድራል። ይህ በእንዲህ ቀጥሎ አንዱ አንዱን እየተካ በርካታ አመታት ታለፈ። ከአስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ያለቦታው የእረኛነቱን መንበር የተቆናጠጠው እረኛ ግን ባህሪው ለየት ያለ ነበር። የእረኝነቱን ሥራ በአግባቡ የማይወጣ፣ በከብቶቹ መካከል መከፋፈልና ልዩነት ለመፍጠር የሚያሴር ‹‹ተንኮል ቀለቡ›› የሚባል አይነት ነበር።
እረኛው ስግብግብና ለሆዱ ብቻ ያደረ ፣ የበረቱ ደህንነት እና ምቹነት የማያሳስበው ራስ ወዳድ ሆኖ ተገኘ። ለከብቶቹ ለብዙ ዓመታት የሚያገለግለውን መኖ እየዘረፈ ለራሱ ምቾትና መንደላቀቂያ ሲያሻው ፍራሽ ሲያሰኘው እየሸጠ አልጋ ይገዛ ነበር። ለሚፈልገው አጋሩም አሳልፎ የሚሰጥ ነበር። ለዚህ እንዲያመቸው ሴራውና ተንኮሉን በመጎንጎን ሀሳቡን የማይከተሉትን ከበረታቸው እንዲወጡ ይገፋ ነበር። በከብቶቹ መካከል ልዩነትን በመፍጠር እንዳይግባቡና አንድነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ከአንዱ ጋር በመሆን ለአንዱ ያደላ በማስመሰል ለመከፋፈል ጥረት ያደርግ ነበር። ከብቶቹም የእረኛቸው ጠባይ በጣም ግራ ያጋባቸው ነበር። በዚህ ግራ መጋባት ውስጥ እርስ በእርስ ሲተያዩ ቆይተዋል።
‹‹ከስንዴ መካከል እንክርዳድ አይጠፋምና›› እንዲሉ አበው ከከብቶቹ መካከል የእረኛው ደጋፊዎችና ተከታዮች ነን ባዮች አልጠፉም። እረኛው እረኛ መሆኑ ቀርቶ ጠብ ጫሪ፣ ተንኳሽና መሰሪነት ተልዕኮውን በመፈጸሙ ምክንያት በረቱ ተተራመሰ። ነጋ ጠባ በከብቶቹ መካከል ጠብ እና ንትርክ ሆነ። በረቱ መተራመሱና መታወኩ ቀጠለ። እረኛው በከብቶቹ መካከል መቃቃርና ጠብን በመጫር ፤እርስ በርስ ማጋጨት እና በበረቱ ውስጥ እሳት በማቀጣጠል እራሱን ከሰቀለበት የከፍታ ማማ ላይ ሆኖ ትዕይንቱን መመልከቱን ቀጠለ።
ውሎ እያደር ከዕለት ወደ ዕለት የበረቱ ሰላም የበለጠ ተናጋ፤ ትርምሱ አየለ። የሰላማዊው በረት ህይወት ጋሬጣ የበዛበት ኡኡታና ጩኸቱ የበረከተበት ሆነ። በየቦታው ሰላም ጠፋ፤ ከከብቶቹ መካከል አንገዛም የሚል ኃይል እያየለ መጣ ። ከውጭ ሆነው የበረቱን ትርምስ እና መታወክ የሚያዩ ሰዎች ግን ምንም ለማለት አልፈለጉም። ጩኸቱን እያሰሙ ፤ትርምሱን እያዩ ዝምታን መረጡ። የሰዎቹ ድርጊት ከብቶች በእጅጉ አስገረመ።
ከብቶቹም በየጊዜው የሚደርስባቸውን በደልና ግፍ እንዲሁም የበረቱን መፍረስ አደጋ ለሰዎች በማስረዳት እንዲተባበሯቸው ለማድረግ ሞክረው ነበር። ሆኖም ሰሚ ጆሮ አጡ፤ ሰዎቹ እንዳልሰማ ዝምታ መረጡ። ከብቶቹም መፍትሔ ለማምጣት አንድነታቸውን አጠናክረው ተነሱ። በአንድነት ‹‹ሆ›› ብለው በመነሳት እረኛው ሳይገባው ከተቀመጠበት መንበር ላይ በውድ ሳይሆን በተባበረ ጽምፅ አማራጭ አሳጥተው በግድ እንዲነሳ አደረጉት። በቦታው ሌላ አዲስ እረኛ እንዲተካ ተደረገ።
ስልጣን ያልጠገበውና ከተደላደለበት ምቾት ከብቶቹን እንደፈለገው አድርጎ የሚያግደው እረኛ ከመንበሩ ሳይፈልግ መልቀቁ አንገበገበው፤ እንቅልፍ ነሳው። በንዴት የበገነው እረኛ አንድ ጥግ በመያዝ በረቱን እንደገና ማመስ እና ማፍረስ የሚችልበት ስትራቴጂ ነደፈ። ተበድያለሁ፤ ከእረኝነቴ የተነሳሁበት መንገድ ትክክል አይደለም። የበረቱ ሰላም ካለእኔ እረኝነት ፈጽሞ መቀጠል አይችልም፤ በረቱ እንዳልነበር ሆኖ ፈርሶ ከብቶቹም ይበታተናሉ። እኔ የበረቱ ምርጥ እረኛ ነበርኩ እያለ አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓችነቱን እያሳየ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱን ቀጠለ።
አዲሱ የበረቱ እረኛም ያለፈው አልፏልና በረቱን በጋራ ለመገንባት ተባብረን መስራት ይጠበቅብናል አለ። አመጸኛው እረኛ ግን በከብቶቹ በይቅርታ እንዲታለፈ አልፈለገም፤ አመጸኛው እረኛ ምቾች አልተሰማውም። የተፈጠረው ለተንኮል ነውና የመሰሪነቱና የተንኳሽነት ባህሪውን ቀጥሎ ከተደበቀበት አንድ የበረት ጥግ ላይ ሆኖ በረቱን እንዲፈርስ ለማድረግ ከጠላት እንዲጠብቁ በተመረጡት ጠባቂዎች ላይ ጨለማን ተገን አድርጎ ዘግናኝ ግፍና በደል ፈጸመ። ለበረቱ ሰላምና ከብቶች ደህንነት በማሰብ በትዕግስት የቆየው አዲሱ እረኛ ህግ የማስከበር ግዳጅ አለበትና ህግ ለማስከበር ሥራ ሲጀምር የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማት ጀመረ። ‹‹ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል ›› እንዲሉት አይነት።
ወዳጆቼ! ጉድና ጅራት ወደኋላ የሚባለው ይሄኔ ነው። ታዲያ ከብቶቹን ያስረገማቸው በዝምታ የሚመለከቱት ሰዎች ጉዳይ ነው። ከውጭ ሆነው የበረቱን መታመስ በአንክሮ ሲከታተሉ ቢቆዩም ዝምታ የመረጡት ሰዎች በርካታ ነበሩ። ማስታረቁ እንኳን ባይሆንላቸው አመጸኛው እረኛ አደብ እንዲይዝ ለማድረግ ሞከረው አያውቅም። ለብዙኃኑ እሮሮ ምላሽ አልባ ሆነው ሳለ፤ አሁን ደግሞ የቀድሞው እረኛ ተጎድቷል፤ በደልና ግፍ ደርሶበታል እያሉ የእረኛውን ጽምፅ ሆነው መቅረባቸው፤ የከብቶቹን በረት ጣልቃ ለመግባት ማለማቸው ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ሆነ። ለከብቶቹም እነዚህን ሰዎች በትዝብት መነጽር አይተው አንቅረው ተፍተዋቸው፤ ወደ በረታቸው ተመለሱ ይባላል።
ልክ እንደቀደሞ እረኛ ሁሉ ከኔ በቀር እረኛ ለአሳር ባዩ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በሀገርና በህዝብ ላይ ከሚሰራው ሴራና ተንኮል በተጨማሪ የሀገር ዳር ድንበር ጠባቂ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ሳይቀር ዘግናኝ እና አሰቃቂ በደል በመፈጸም ተወዳዳሪ የለሽ ነበር። በትግስት የቆየው መንግሥት የሀገር ዳር ድንበር ጠባቂዎች ላይ የደረሰው በደል ትግስቱን ተፈታትኖት ህግ እንዲከበር ለማድረግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል።
መሰሪው እና ተንኮለኛው ቡድን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ወደ ሞት ተሸኝቷል። ከሞቱ የተረፉቱ ቀሪ ርዝራዦች ግን ከተደበቁበት የቀበሮ ጉድጓድ አፈር ልሰው ብቅ ብለዋል። ከሞት አፋፍ የተረፈችው የአሸባሪው ነፍሱ ግን በደሏ እንዲሻር ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ በበደል ላይ በደል ለመፈጸም አልዘገየችም። ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንደሚባለው ከቀድሞ ተግባሩ ይልቅ ወደ ባሰ የከፋ ድርጊቱ መሻገሩን ከሰሞኑ አይተናል።
መንግሥት የተኩስ አቁም እርምጃ በመውሰድ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት መከላከያ ሥራዊትን ከክልሉ ባወጣበት ቅጽበት መንግሥትን በማሸነፍ መቀሌ መቆጣጠሩን በጀሌዎቹ በኩል አስተጋብቷል። አፍታ እንኳን ሳይቆይ የተንኳሽነቱ ባህሪው አለቅ ብሎት ወደ አዋሳኙ አማራ ክልል ህጻናት ሳይቀር በጦርነት እያሰለፈ በግልጽ በዓለም እንዲታይለት በማድረግ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ወደለየለት አረመኔያዊ ድርጊት ገብቷል። ምን ይሄ ብቻ! ከተደበቀበት ሆኖ የትግራይ ህዝብ ተርቧል፤ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ይድረስልኝ እያለ ሲወተውት ቆይቷል። ‹‹አንቺ ታመጪው አንቺው ታሮጪው›› እንዲሉ የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ እርዳታ እንኳን ለህዝቡ እንዳይደርስ ለማድረግ የተከዜን ግድብ በማፈራረስ እኩይ ተግባር ፈጽሟል፤ ቆሜለታለሁ የሚለውን ህዝብ መከራና ሰቆቃ እያበዛ ቀጥሏል።
እናንተዬ ! ከሁሉም እጅግ ግርም የሚለው ደግሞ ቀደም ሲል በዝምታ ተመልካች የነበሩት ምዕራባዊያን ጉዳይ ነው። መንግሥት የህግ ማስከበር እርምጃን ሲወስድ የምዕራቡ አለም ቅጥ ያጣ ማስጠንቀቂያ ማጉረፉን ተያይዞት ነበር። የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ሳይቀር የትግራይ ህዝብ ተርቦ ፣ሰብዓዊ መብት ጥሰት ደርሷል ሲሉ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባና ክስ ሲያሰሙ ቆይተዋል። የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት (አምነስቲን ኢንተርናሽናል) ሳይቀር በአክሱም በርካታ ሰዎች መሞታቸውን አገኘሁት ባለው ለአንድ ወገን ያደላ፤ ያልተረጋገጠ መረጃ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይነት ሪፖርት አይተን ታዝበናል።
አሁን ላይ የምዕራቡ አለም ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጫና ለመፍጠር የሚያሴሩት ሴራ አይጣል አያድርስ የሚያሰኝ ሆኗል። እንደ አሜሪካ የለየለት ደግሞ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ በመጣል ያላቸውን ፍላጎት ምን እንደሆነ በግልጽ አሳይተዋል። እንደ ኒዮርክ ታይምስና አሶሼትድ ፕሬስ ያሉ ሚዲያዎቹም አሸባሪው የህወሓት የጥፋት ቡድን እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረስ ህጻናት ሳይቀር ለውትድርና መጠቀሙን በማሞካሸት የህዝብ ድጋፍ እንዳለው አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል። እነኝህ ሚዲያዎች ይህንን ዘገባ ሲሰሩ እውን ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ወንጀል ሆኖ መደንገጉ ጠፍቷቸው ነው? ወይስ ለምን? የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል።
ወዳጆቼ! ጠርጥር ገንፎ ውስጥም ይኖራል ስንጥር አለ የሀገሬ ሰው። መጠርጠር አይከፋም። ይቺ ጎንበስ ጎንበስ ያለምክንያት አይደለችም በእነዚህ ሚዲያዎች ሙገሳና ውዳሴ የተቸረው አሸባሪው የህወሓት በመከላከያ ሠራዊትና በማይካድራ በዜጎች ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት ባልሰማና ባላየ መታለፉ ለምን? እውን ሚዲያዎቹ ከጀርባቸው ሌላ አሻጥርና ተንኮል ባይኖር ኖሮ ሚዛናዊ ዘገባን ለህዝብ አይንና ጆሮ ለማድረስ የታመኑ ይሆኑ ነበር። በዚያን ጊዜ ለምን ዝምታን መረጡ? በጥልቀት መመርመር ይገባል።
ለሰብዓዊ መብት መከበር ቆሜያለሁ የሚለው አምነስቲን ኢንተርናሽናል በበኩሉ በቲውተር ገጽ የኢትዮጵያን ስም ማጠልሸቱን ተያይዞታል። የትግራይ ተወላጆች እየተዋከቡ በማለት የሀሰት ክሱን በማቅረብ ዱባ እና ቅል ለየቅል አይነት ተግባሩ የተጋለጠበት መንገድ በፎቶው ባለቤት ጋዜጠኛ አማኑኤል ስለሺ ማጋለጡን ሰምተናል።
እናንተዬ ! ኧረ ጉድ ነው። ታዲያ በምን እሳቤና ስልት ከዚህ አሸባሪ ጎን ለመቆም የደፈሩት ? ይህ ሊመለስ የሚገባው ጉዳይ ነው። ለአንድ አሸባሪ ቡድን ይህንን አይነት ወገንተኝነት የጤና ነው ብላችሁ ነው? አይመስለኝም። ይህማ ባይሆን ኖሮ መንግሥት ያደረገው ይህንን ቡድን ለመታገስ የከፈለውን መስዋዕትነት ይናገሩ ነበር።
ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ አሉ እማማ! ምነው መንግስት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ ለስምንት ወራት ያለአንዳች አጋዥ ያከናወነውን ተግባር ለመናገር ሆነ ለመስማት ጊዜ አልፈለጉ። መንግሥት በክልሉ ለሰብዓዊ ድጋፍ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ውጪ ማድረጉን ለመናገር ምነው ተናነቃቸው?
በእውር ድንብር ፈረስ በመጋለብ ለአንድ ወገን ከመቆም በመመርመር እውነታ ፍለጋ ላይ ለምን አልደከሙም። መመስገን የሚገባን ለመወቀስ፤ መወቀስ የሚገባን ለማመስገን የምንችልበት የዓለም ህግና ሥርዓት አልተቀየረ። እነሱን በተመቻቸው መንገድ ብቻ የሚፈስበት መንገድ ላይ ያለን እውነት እየደመሰሱ መሄድ ያዋጣ ይሆን?
የጊዜ ጉዳይ እንጂ ምንም ነገር ተድበስብሶ የሚቀር ጉዳይ የለም። እውነትና ንጋት ፈክቶ ሲታይ ዛሬ በአደባባይ በቅጥፈት የቆሙ ነገ መግቢያ ይጠፋቸዋል። ሌላው ቢቀር የሚመሰገነውን ማመስገን እንኳን ቢቀር የሚወቀሰውን መውቀስ ግን የህሊና ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም ባይ ነኝ። ሰላም!
እየሩስ አበራ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2013