ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ አለሙ ይባላሉ። በአካባቢ ልማትና የትምህርት ጥራትና በእጽዋት በሽታ ላይ የሚሰሩ ናቸው። በኢትዮጵያ ደረጃ ባለስልጣን በደረጃ መዳቢዎች ኮሚቴነትና በኢትዮጵያ ባዮሎጂካል ሳይንስ ሶሳይቲ በፀሐፊነት ሰርተዋል። እንዲሁም በኢትዮጵያ ማይክሮ ባዮሎጂ ሶሳይቲ በፕሬዚዳንትነት እየሰሩ ይገኛሉ። ከሁሉም በላይ በቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴርና በተለወጠው ስሙ በቡናና ሻይ ባለስልጣን በስራ በነበሩበት ወቅትም በቡና በሽታዎች ላይ በአገር ደረጃ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን በመስራት አሻራቸውን አሳርፈዋል። በዚህም የቡና ምርትና ምርታማነትን ሊጨምር የሚችልበትን ሁኔታ የሚያመቻች አዲስ ፕሮጀክት ነድፈው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ለውጤቱ እየሰሩ ይገኛሉ። ፕሮጀክቱ በተለይም የቡና በሽታ መከላከያ ዘዴዎች ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ የአገራችንን ገበሬ በብዙ መንገድ እንደሚታደገውም ነግረውናል።
ፕሮጀክቱ በስነህይወታዊ የበሽታ መከላከያ ዘዴ የቡና ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችል ሲሆን፤ ይህንን የፕሮጀክት ውጤት ፋብሪካ በመክፈት ገበሬው ጋር ለማድረስና አገርን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ አጫውተውናል። በአሁኑ ወቅት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰና ጥቅሙ በምን ደረጃ ይገለጻል ለሚለው ጥያቄያችንም ሰፊ ምላሽ የሰጡን ሲሆን፤ ይህንንም እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡– ተፈጥሮ ኢትዮጵያን ብዙ አድላታለች ቢባልም የመጠቀሙ ሁኔታ አናሳ ነው። በዋናነት ችግሩ ምንድነው ይላሉ?
ዶክተር ተስፋዬ፡– የሚባል ብቻ ሳይሆን በተግባር ያለም ነው። ለአብነት በእንጉዳይ ብቻ በዓለምና በኢትዮጵያ ውስጥ ከ12ሺህ በላይ ዝርያዎች ይገኛሉ። ሆኖም በኢትዮጵያ ተጠንተው ወደ ምግብነትና በገበያ መግባት የቻሉትም ጥቂቶች ናቸው። ሁሉንም ማየት ብንችል ግን ብዝሀ ሕይወት ለሰው ልጆች በቀጥታው ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ተቋዳሽ እንሆን ነበር። ለምሳሌ ከሚሰጠው አገልግሎት አንጻር ስናነሳ ለምግብነት ፤ ለመድሃኒት፤ ለጥሬ እቃ አቅራቢነት፤ ለሀይል ምንጭነት፤ ለግንባታ ለልብስ ወዘተ መጠቀም የምንችለው ነው። በተጨማሪም ቆሻሻን ለማፅዳት፤ የአየር ሚዛንን ለመጠበቅ ፤ኦክስጂንና እርጥበትን ለማመንጨት፤ የንጥረ ነገሮች የውሃ ኡደትን ለማቃጠል፤ የአፈር ለምነትን ለማስጠበቅና በአጠቃላይ ህይወት በዓለም ላይ እንዲቀጥል ለማድረግ ከተፈጥሮ ውጪ አማራጭ የለም። ግን በእጅ የያዙት ወርቅ ሆነና ጊዜያዊ እንጂ ዘለቀታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ባለመረዳታችን ያለንን እያጣነው ነው። ይህ ሲባል ግን አሁን መነሳሳት የለም ለማለት አይደለም። ዘመኑን የዋጁ በርካታ ተፈጥሮን የመመለስ ሥራ እየተከናወኑ ናቸው። ከእነዚህ መካከል የችግኝ ተከላ መርሃግብሩ አንዱ ነው። እናም ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።
የተፈጥሮ ብዘሃ ሕይወት ለሰው ልጆች ተገልጸው የማያልቁ ጥቅሞችን የሚያበረክቱ እንደሆኑ መናገር ለቀባሪው አረዱት ነው። እናም የእነሱ መጥፋት የምድራችንን ቀጣይ እድል ማኮሰስ እንደሆነ አምኖ መስራት ያስፈልጋል። በተለይም እንደ እኛ አይነት የተፈጥሮ የበላይነት ያየለበት አገር ይህ ሀብቱን ተንከባክቦ ለሌሎች ማትረፍ ካልቻለ እራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይዞ ይጠፋል። እናም የአለን የብዝሀ ሕይወት ብዛት በነበረን ሳይሆን በአለን መልክ መታየት መቻል አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ተፈጥሮን መንከባከብ የሁልጊዜ ተግባራችን ማድረግ ይኖርብናል። በዘላቄታዊነትም ውጤታቸውን እያዩ መሄድ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ባህላዊ የችግኝ አተካከል ምን ጥቅም አለው?
ዶክተር ተስፋዬ፡– በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተለያዩ ባህላዊ የችግኝ አተካከል ስልቶች አሉ። እንክብካቤያቸው ጭምርም ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ይለያያል። ባህሉ የዳበረና በትክክል ስነህይወታዊ ዘዴን የተከተለ ነው። ነገር ግን በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ በመሆኑ እንደኋላ ቀር ተቆጥሮ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲተው ሆኗል። በማይመስልና ለአየር ንብረቱም ሆነ ለመልከአምድሩ ምቹ ያልሆነ አዲስ ሥራና ቴክኖሎጂ መጥቶ ተጠቀሙት ይባላል። ይህ ደግሞ አሁን ያለንበትን የማምረት ሁኔታ አምጥቷል።
ጥራት ያለውና ስፋት ያለው ምርት እንዳናመርትም የሆነው በባህሉም ሆነ በመልከአምድሩ የተሻለው የትኛው ቴክኖሎጂ ነው የሚለውን በአግባቡ መርምረን አለመተግበራችን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የሚጣል ስነህይወታዊ የበሽታ መከላከል ባህል የለም። ሁሉንም በአግባቡና ባህሉን ባልለቀቀ መልኩ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ ብቻ በማከል ብንጠቀመው ባህላችን ይበልጥ ያገነናል እንጂ አይጥለንም። ወደ ልመና የምንሰማራበት ሁኔታንም አይፈጥርም። ለዚህም የጤፍ የአመራረት ዘዴን በአብነት ብቻ ብናይ በቂ ነው። ከበሽታው ብንነሳ በባህላዊ መንገድ ተመርቶ የመጣ ጤፍ ተፈጥሯዊ ነገሩን በምንም መልኩ አይቀንስም።
መሬቱም ቢሆን ለዓመታት የተደላደለ ነው። ቴክኖሎጂውን አምጥተን የተለያዩ ኬሚካሎችን ረጭተን የምናመርተው ምርት ግን ምን እንደሆነ እያየነው ስላለን መናገር አያስፈልገንም። እናም አሁን መንቃት ያስፈልጋል። የትኛው መሬት በየትኛው ቴክኖሎጂ አመጣሽ አሰራር መከናወን አለበት የሚለውን መለየትና መተግበር ተገቢ ነው። ባህልን እርግፍ አድርጎ ከመተው ይልቅ መኖሩን አምኖ መሻሻል ያለበትን ብቻ እየመረጡ ማሻሻል ብዙ ነገሮቻችንን ይጨምርልናል። በተጨማሪም ባህላዊ የችግኝ አተካከልና እንክብካቤን በተመለከተ ማስተማርና ለሁሉም ማሳወቅም ይገባል። ምክንያቱም ቴክኖሎጂ ብቻ ሲሆን አሰራሩን በፍጥነት ቢያቀለውም ብዙ ይዞት የሚመጣ ችግር ግን አለ። ለምሳሌ የመሬት ለምነትና የአየር ንብረት እንዲሁም የመልከአምድር ሁኔታን በብዙ መልኩ ያዛባዋል። በተለይ ደግሞ ባህላዊ አሰራሮችን ሙሉ ለሙሉ መቀነሱ አይቀሬ ነው። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ በባህል የተመራው ኑሯችንና ህይወታችን ይዛባል።
ባህል ኑሮም፣ ህይወትም ነው። አገር ወዳድነትንም ያላብሳል። ሥራዎች ሁሉ ተወደው እንዲከናወኑ ያደርጋል። ነገር ግን ቴክኖሎጂው ከሚያመርተው እስከ ሚሰራው ተግባር ድረስ ስለሚያራርቀን ይህ ነገራችን ልክ ያጣል። እናም ቴክኖሎጂው ከባህላችን እንዲበልጥ ማድረግ አይገባም። ከዚያ ይልቅ ባህላችን ቴክኖሎጂውን መርቶት የተሻለ ላይ እንዲያደርሰን ማድረግ ለሁሉም ነገር ይበጃል። የአለም ሀገራት ቴክኖሎጂውን በሚፈልጉት ላይ ብቻ ነው የሚጠቀሙት። እኛ ጋ ያለው ሁኔታ ግን ተቀበል አይነት ስለሆነ ጥንቃቄም አሰራርም ይጎለናል። ይህ ደግሞ እድገታችንን ይጎትተዋል። ባህላችንንም ፈትኖት ሊያጠፋው ይችላል። ስለሆነም እንደበለጸጉት ለመሆን ባህል እንጂ ቴክኖሎጂ እንዲያሸንፍ አናድረግው። ለቴክኖሎጂው የሚሰጠው ቦታ በሚጠቅመን ልክ ብቻ መሆን አለበት። ይህም ሚዛን ላይ አስቀምጠን ተፈጥሮን በማይረብሽ መልኩ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከድህነት ለመውጣት ታዳጊ አገሮች ምን ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ?
ዶክተር ተስፋዬ፡- ከድህነት ለመውጣት መጀመሪያ መልካም እድሎቻቸውን ማየት ያስፈልጋል። ተፈጥሮ የሰጣቸውንና እነርሱ ምን ያህል መጠቀም እንደሚችሉ መገንዘብና በሥራ መተርጎም ይኖርባቸዋል። ከዚያ በተፈጥሮ ብቻ የሚመልሱት ብዙ ነገር ይኖራቸዋል። የሌላቸውን ብቻ መማር ቢኖርባቸውም ያለን ሳያዩ ከሆነ ግን ዋጋው የከፋ ይሆናል። ምክንያቱም ተፈጥሮ በሰው ሰራሽ ነገር በብዙ መንገድ ይበከላል። ቴክኖሎጂውም በራሱ የሚያመጣቸው ጉዳቶችም እንዲሁ ቀላል አይደሉም። በተለይም አካባቢውን ሳይረዱ የተማሩትን ብቻ ለመተርጎም መሞከር አደጋው የከፋ ነው። እናም ድህነትን ለመቀነስ ከድህነት አስተሳሰብ መውጣት ያስፈልጋል። መጀመሪያ ለአገር የሚበጀውን መምረጥና በዚያ ላይ መመራመር ያስፈልጋል። ምርምሮች ደግሞ በጠረጴዛ ላይ የሚቀሩ መሆን የለባቸውም። ለዚህም ደግሞ ራሱ ተመራማሪውም መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ከተንቀሳቀስን ደግሞ በተግባር ውጤታማ መሆን እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡– ወደ ፕሮጀክት ሥራው ከመግባታችን በፊት የፈንገስን ጉዳት ከፈንገሶች ጥቅም አንጻር በመዘርዘር እስኪ ያንሱልን?
ዶክተር ተስፋዬ፡– የፈንገስ ተመራማሪዎች ስላሉ እነርሱ ቢያስረዱ መልካም ነበር። ሆኖም እናንሳ ከተባለ ከፕሮጀክቱ ጋር የሚያገናኘው ብዙ ነገር ስላለ ጥቂት ልበል። አገራችን ከሌሎች የአለም አገራት በርካታ ዝርያዎችና አቅም ያላቸው ፈንገሶች ይገኙባታል። አቅም ያላቸው ፈንገሶች ደግሞ መርዛማ ነገሮችን ለማምከን ወሳኝ ናቸው። ከዚያ ባሻገር ለባዮ ቴክኖሎጂ፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና መሰል ግብዓቶች የሚውሉና ጥቅማቸው በገንዘብ የማይተመንም ነው። ስለዚህም በርካታ የፈንገስ ዝርያዎችን ለማግኘት አመቺ የሆነች አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናትና ይህንን አውቆ መጠቀም ያስፈልጋል።
የስነ ረቂቅ ተዋህስያን ሳይንስ ግንዛቤው በአገራችን በብዙ መንገድ ስላላደገ እንጂ ጥቅማቸው ተዘርዝሮ አያልቅም። ለአብነት ጸረ ፈንገሶችን በዕጽዋት ላይ ስንረጭ ርጭቱን ብቻ ስለምናይ ችግሩን አናውቀውም። ነገር ግን አፈር ውስጥ ከገባ በኋላ ብክነትን ያስከትላል። ከዚህ በተጓዳኝ ምርትን ለማሻሻል ተብለው ከውጪ የሚገቡ የግብርና ግብዓቶችም እንዲሁ አፈር ውስጥ ያለውን ስነህይወታዊ እንቅስቃሴ በማዛባት ምርትን በመቀነስ ብቻ ሳይሆን አካባቢ በመበከል፣ በሰው፣ በእንስሳትና በእጽዋት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።
ፈንገሶች ጸረ ፈንገሶች ውስጥ ያለውን መርዛማ ነገሮችን ከአካባቢው ያስወግዳሉ። በዚህም ይህንን እየተጨናነቅንበት ያለውን የመበከል ሁኔታ በማጥፋት የማይተካ ሚና አላቸው። ነባር የተፈጥሮ መልከአ ምድርን ዳግም በማምጣት የማይተካ ሚና አላቸው። ምክንያቱም መርዛማ ነገሮች ሲወገዱ በመሬት ላይ መደላደል ይፈጠራል። ጤናማ የተፈጥሮ እድገትም ይኖራል። ስለሆነም የጸረ ፈንገሶች ጥቅም በዚህ ደረጃ ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ሳይንሱ በትክክል ሲተገበር የሚመጣ ነው። ለሳይንሱ ተግባራዊ መሆን ደግሞ ባህላዊ እውቀቶች ወሳኝ ናቸው። እነርሱ አቅጣጫ ካልጠቆሙና ተጠብቀው እውቅና ተሰጥቷቸው መተግበር ካልቻሉ ሳይንስ የሚባል ነገር አይኖርም። እናም በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ በርካታ ባህላዊ እውቀቶች ለሳይንሱ መሪ መሆን መቻል እንዳለባቸው አምኖ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ አሁን እየሰሩበት ያለው መስክ ምን መጻኢ እድሎችን ይዞ ይመጣል፤ ለምንስ በዚህ ላይ ለመስራት ወሰኑ?
ዶክተር ተስፋዬ፡– እዚህ ላይ ለመግባት ያበረታታኝና ጫና ያሳረፈብኝ ሦስተኛ ዲግሪዬን ስሰራ ያማክረኝ የነበረው ፕሮፌሰር ነው። ይህም አገርህን የምትወድ ከሆነ በእጽዋት በሽታዎች ላይ ስራ በሚል የማጠናውን የትምህርት መስክ መረጠልኝ። በዚህም በስነህይወታዊ የበሽታ መከላከል ዘዴ ላይ ምርምሬን አድርጌያለሁ። ይህ
ደግሞ የቡና በሽታ የሚያሰቃያትን አገሬን በብዙ መንገድ እንታደጋት አግዞኛል። ወደፊትም የተሻሉ እድሎችን እንድፈጥርበት መንገድ ጠርጎልኛል። ለኢትዮጵያ የቡና ጉዳይ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊም ሆነ ፖቲካዊውን የሚይዝ ነው። ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ በዚህ ልክ ይወሰናል። እናም በዚህ ላይ በመስራቴ ይህንን ሁሉ እንዳደረኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።
መጀመሪያ ምርምር የጀመርኩት በአካባቢው በሚገኝ በትራይኮዳርማ ዝርያ ውስጥ ባለ የስነህይወታዊ በሽታ መከላከል ዘዴ ዙሪያ ነው። ትምህርቱ ጠቃሚ ፈንገሶችን በመጠቀም በእጽዋት ላይ በሽታ አምጪ ፈንገሶችን፣ ባክቴሪያዎችንና መሰል ማይክሮ ኦርጋኒዝሞችን ማጥናት ሲሆን፤ እንዴት በእጽዋት ላይ ችግር ይሆናሉ የሚለውን መመርመር የቻልኩበት ነው። ከዚያ መፍትሄውን ማመላከትና በተግባር እንዲተረጎም ማድረግ ነው። ማይክሮ ኦርጋኒዝሞች በአግባቡ ከተጠቀሙባቸው ከጉዳታቸው ይልቅ ጥቅማቸው ይጎላል። በእጽዋት ላይ በሽታ የሆኑ ፈንገሶች እንኳን መድሀኒት መሆን የሚችሉ ናቸው። ሆኖም በሚገባ ጥቅም ላይ መዋልና ክትትልን እንዲሁም የምርመራ ውጤትን ይጠይቃሉ። ከዚያ ውጪ ራሳቸው በራሳቸው ለተፈጥሮ መፍትሄ የሚሆኑ ናቸው።
ያጠናሁት ‹‹ቦተራይተስ›› የተባለው ፈንገስ ‹‹ግላዶለስ›› የሚባለውን አበባ ማዕከል ያደረገ ሲሆን፤ በዓለም ላይ ትልቅ የገበያ እድል ያለውና ተፈላጊ የአበባ ዝርያ ነው። እናም ይህንን አበባ የሚያመርቱ ገበሬዎች ጋር በመሆን በፕሮጀክት ምርምሬን ጀመርኩ። የአበባውን መበስበስ፣ መጠውለግና ሲጓጓዝ ችግር የሚፈጥረውን በመለየት ጥናቱን ማካሄዱንም ቀጠልኩ። ዘጠኝ ጠቃሚ> የትራይኮዳርማ ዝርያዎችንም በመውሰድ ነበር ሙከራ ያደረግነው። ከበሽታው ጋር እንዴት ተደርጎ መጠቀም እንደሚቻልም ተተነተነ፣ በተግባርም ተፈተነ፤ ውጤቱ ደግሞ አመርቂ ሆነ። በዚህም በመድሃኒት መልክ ወደ መቀመሙ ተገባ። ከዚያም አልፎ ሌሎቹ ላይ ጭምር ወደ መሞከርም ተቻለ።
በአገራችን የውጪ ምንዛሬን ከሚያመጡ ምርቶች ቡና የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል። ይሁን እንጂ የቡና በሽታው የአገሪቱን ገበሬዎች በእጅጉ እየጎዳቸው ይገኛል። እናም ይህንን ስሰማም ነው በአበባ ላይ ስሰራበት የነበረውን ምርምር ውጤት በቡና ላይ ወደ መሞከሩ የገባሁት። በሌሎች ላይ ሙከራ ሲደረግ መጀመሪያ ምን ያህል ፈንገስ አለ የሚለው ይለያል። ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ቡና አብቃይ አካባቢዎች የትራይኮዳርማ የፈንገስ ዝርያዎችን ማጥናት ጀመርን። ውጤቱም የቡና ተክል ግንድ አድራቂ በሽታ ፈንገስ መከላከያ እንድናገኝ አደረገን።
በሽታ አምጭውን ከንጹሁ በመለየት በሽታውን ለብቻው ንጹሁን ለብቻው ከአደረግን በኋላም ሁለቱንም በመከተብ ያለውን ለውጥ መዘንን። በዚህም መሰረት የትራይኮዳርማ የፈንገስ ዝርያዎችን የቡና ተክል ግንድ አድራቂ በሽታ መድሀኒት መሆኑን ተመለከትን። ይህ ደግሞ የተሻለ አማራጭ እንደሚያመጣ ስለተረዳን በአጭሩ ፎርሙላ አውጥተን ለቡና አምራች ገበሬዎች የሚጠቀሙበትን እድል አመቻቸን። በተለይም ቡና አምራቾች በብዙ መንገድ ውጤታማ መሆናቸውን አይተንበታል። በቤተሙከራ ብዙ ከተለፋበት በኋላ በጥራት፣ በምርታማነትና በገበያ ተወዳዳሪነት የተሻለ አቅም እንዲያገኙ ሆነዋል።
በዓለም 120 ሚሊዬን በአገራችን ደረጃ ደግሞ 25 ሚሊዬን የሚሆን ህዝብ በቡና ማምረትና ንግድ ውስጥ ይሳተፋል። ስለዚህም የቡና ተክል ግንድ አድራቂ በሽታ መፍትሄው በእኛ እጅ እንደሆነ ስለተረዳንም ወደ ስራው ገባን። በ2004 ተጀምሮ 2020 ተጠናቆ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ለባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ፕሮጀክቶችን በማግኘት 175 የትራይኮዳርማ የፈንገስ ዝርያዎችን የቡና ተክል ግንድ አድራቂ በሽታ የቡና ዝርያዎችን ለየን። ከፈንገሱ ጋርም በተለያየ መንገድ ስንሞክራቸው 24ቱ የተሻሉ መሆናቸውን አወቅን። እንደውም በዓለም ላይ ጭምር የማይገኙና የተሻሉ መሆናቸውንም ለማየት ተችሏል። በጣም ሲወርድ ደግሞ 16ቱ የበለጠ የተሻሉ እንደሆኑ ታውቋል። በዚህም ዝምድናቸው ፣ ስማቸውና ሌሎች መስፈርቶችን እያወጣን ደረጃ ሰጠናቸው። ይህ ደግሞ ለእያንዳንዱ በሽታ የትኛው በምን መጠን ይሰጣል የሚለውን ለመለየት አግዟል።
የቡና በሽታ የሆነው ፈንገስ መጀመሪያ በስራቸው ጋር በመግባት ተክሉን ያጠወልጋል። ከዚያም እንዲደርቁ ያደርጋቸዋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ምርት እንዳይሰጡ ሰፊ እንቅፋት ሆኗቸዋል። እናም ይህ ፈንገስ በመድሃኒትነት ተቀምሞ ታሽጎ የሚሸጥበት ሁኔታ ከተፈጠረ በአፍሪካ አምራች የምንሆንበት አጋጣሚ አለ። ምክንያቱም ከዓለም አገራት ነው እየገዙ የሚጠቀሙት። ሊያውም በውድ ዋጋ።
አሁን በተሰራው ሥራ በኢትዮጵያ እስካሁን ሪፖርት ያልተደረጉ 10 አÇዲስ የትራይኮዳርማ የፈንገስ ዝርያዎችን ማግኘት ተችሏል። እነዚህ ዝርያዎች ደግሞ በማንኛውም የጥራጥሬ ንፋስና የእህል ገለባዎች እንዲሁም በከተማ ላይ ከሚጣሉ ቆሻሻዎች ላይ የሚያድጉ ሲሆን፤ በሰው ልጅ ላይ ምንም አይነት መርዛማነት የሌላውና ጉዳት የማያደርሱ ናቸው። በዚያ ላይ በማሳ ላይ ያለውን የበሽታውን ስርጭት ሰባ በመቶ መቀነስ የሚችሉ ሲሆን፤ የምርት ይዘቱን የሚቀንሰውን በሽታ ደግሞ እስከ 32 በመቶ የመቀነስ አቅም እንዳላቸው ማወቅ ተቻለ። በተመሳሳይ 45 የሚሆኑ የፈንገስ ዝርያዎች ላይ ጥቅም የሚሰጡና መከላከል የሚችሉ መሆኑም ተለይቷል። ስለዚህም ተግባራቸውን በትክክል ለመረዳት ትልቅ ቴክኖሎጂን ይጠይቃልና ወደ ጀርመን አገር የትራይኮዳርማው ዝርያ ተልኳል።
ስሙ ሲመጣ ቀጥታ በኢንዱስትሪ ደረጃ ተመርቶ ወደ ሥራ ይገባበታል። ለዚህ ደግሞ እንደ ብዝሀህይወት ኢንስቲቲዩትና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂና ግብርና ዘርፉ በመሆን በጥምረት ለመስራት እየተነጋገርን እንገኛለን። ከብዙዎቹ ጋርም ስምምነት ላይ ተደርሷል። እንደውም ከቀድሞ የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአሁኑ ከኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ለባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ለምርመራ ስራውን ተመልክቶ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ሰጥቶን ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።
በፕሮጀክቱ ከአፍሪካ አገራት ጋር ተወዳድረን በማሸነፋችን ከባዮ ኢኖቬት አፍሪካ ለሁለት ዓመት ወደ 20 ሺህ ዶላር እንደሚያግዙን ቃል ተገብቶልናል። ደብዳቤ ተሰጥቶናልም። ባለሙያዎቹም መጥተው የምንፈራረም ይሆናል። አዲስ አበባ ባወጣው የዩኒቨርስቲና የኢንዱስትሪ ትስስርና ለሽግግር በወጣው ፕሮጀክት ላይም አሸናፊ ሆነን ዩኒቨርስቲው ለሦስት ዓመት የኢንዱስትሪ የመፈልፈያ ማዕከሉን እንድንጠቀምበት ፈቅዷል። የምንጠቀምበት መሳሪያ በሙሉ እንደሚገዛልንም ቃል ገብቶልናል። በዚህም ቤተሙከራውንና በመስኩ መጨረሻ የትራይኮዳርማ ምርምራችንን ለገበሬውና ለሌሎች ተጠቃሚዎች በስፋት ለማሰራጨት የሚያስችለንን ሥራ እንድናከናውን እየረዳን ነው።
አዲስ ዘመን፡– የቡና ምርታችን ጉዳይ ከብዙ አኳያ ለእኛ ለኢትዮጵያን ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው። የእናንተ ፕሮጀክት ይህንን ከመስራት አንጻር ምን ተግባር ከወነ?
ዶክተር ተስፋዬ፡– የእጽዋት በሽታን በስነህይወታዊ ዘዴ ማከም ተፈጥሮን ማከም ነው። በዚህም ብዙ ለውጦችን ያመጣና ብዙ መሻሻሎች የታዩበት ሥራን ማከናወን እንድንችል አድርጎናል። የመጀመሪያው ምርታማነትን መጨመር ሲሆን፤ ሌላው የበሽታ መከላከል ሥራው ይገኝበታል። ለዚህ ደግሞ ጣዕማቸው የተለየ፣ የአረቢካ ቡና ዝርያዎች ያሉባት ብቸኛ አገር መሆኗ ብዙ አግዞናል። ይህ ስራችን ከሥራ እድል ፈጠራው በላይ የውጪ ምንዛሬውን በማሳደጉ ዘርፍ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። ምክንያቱም የሚቀርበው ቡና በጥራትም ሆነ በመጠን እንዲሁም በጣዕም ተመራጭ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው።
አዲስ ዘመን፡– መድሀኒቱ ምን ምን ጥቅም አለው?
ዶክተር ተስፋዬ፡– አስተሳሰቡ የመነጨበት ዋና ነገር በስነህይወታዊ መንገድ በሽታን የመቆጣጠርና የመከላከል ዘዴ ነው። በዘጠኝ የእህል ዝርያዎች ላይም ያሉትን የእጽዋት በሽታዎችን የመከላከል አገልግሎት ይሰጣል። ለምሳሌ በጤፍ፣ በዘንጋዳ፣ በባቄላ ፣ በስንዴ፣ በሽንብራና በሌሎችም ላይ የተደረጉ ሙከራዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ስለዚህም መድሃኒቱ በተለያየ መልኩ ይሰጥና በሽታውን ማከምና መከላከል ይቻላል። ለአብነት በርጭት፣ በመከተብ፣ ከአፈር ጋር በመቀላቀል፣ ስሩን በመንከርና በመዝራት ወዘተ ተሰጥቶ በሽታው እንዳያጠቃቸው የሚያደርግም ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ ጥሩውንም በሽታውንም በመከተብ ነው።
የመድሃኒቱ ውጤታማነት የሚለካው የእህሉን በሽታ በመከላከል ብቃት ሲሆን፤ ጥሩው ደግሞ በሽታው ያጠቃውን፣ እንዲያገግምና ምርታማነቱን እንዲያሳይ ለማድረግ ነው። በእነዚህ መንገዶችም ጅማ፣ ጌራና ቴፒ የግብርና ምርምር ማዕከሎች ላይ ተሞክሮ አርሶአደሩ በውጤቱ ተደስቶባቸዋል። አሁንም በኢትዮጵያ ለ4ነጥብ 2 ሚሊዬን ቡና አምራች ገበሬዎችም ለመድረስ የምንሰራ ይሆናል። አሁን ያገኘነውና በእጃችን ላይ ያሉት መድሃኒቶች ባሉት ነገሮች ስናሰላው አንዷ ኪሎግራም የምትሸጠው እስከ ሦስት መቶ ብር ነው። አንድ ጸረ-ፈንገስ ልግዛ ቢል ግን ከ1200 እስከ 1500 ብር ያወጣል። ይህ ደግሞ ምን ያህል እንደሚቀንስለት በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
በሌላ በኩል ጸረ ፈንገሱን ገዝቶ ቢጠቀም ተጓዳኝ በሽታዎችን በሰዎች፣ በእንስሳትና በወንዞች በአጠቃላይ አካባቢው የመበከል ዝንባሌም ያለበት ነው። ምክንያቱም ከውጪ የሚመጡ ሁሉ በእኛ ነባራዊ ሁኔታ የተመረቱ ስለማይሆኑ የጎንዮሽ ጉዳታቸው የሰፋ ነው። ስለዚህም ከዋጋቸው በላይ የሚያደርሱት ዘላቂ ጉዳት የከፋ በመሆኑ ይህ መድሃኒት ብዙ ችግሮችን ይፈታል። ከዚህ ጎን ለጎን ለሥራ እድል ፈጠራም ቢሆን የማይተካ ሚና ይኖረዋል። በኢንዱስትሪ ሲመሰረት መቼም በጥቂት ሀይል መስራት የሚታሰብ አይደለም። ስለዚህም ሰፋ ያለ የሥራ እድል ለወጣቱ ይሰጣል። በተመሳሳይ ብዙ ነጋዴዎች በየአካባቢው እንዲኖሩም ያደርጋል።
የውጪ ምንዛሬም ቢሆን እንደዛሬው የሚሆንበት መንገድ አይፈጠርም። ምክንያቱም ሁለት ነው። የመጀመሪያው በጥራትና በብዛት የቡና ምርት ማቅረባችን ሲሆን፤ ሁለተኛው ለአፍሪካ አገራት ምቹ የሆንን እኛ በመሆናችን መድሃኒቱን በቅርብ ለማቅረብ ምቹ እድል ይሰጠናል። በዋጋም ቢሆን ተወዳዳሪ የምንሆንበትን መንገድ ስለምንቀይስ ብልጫ ማግኘታችን አይቀሬ ነው። ስለዚህም መድሀኒቱ ብዙ እድሎችን ለአገራችን ያመጣል የሚል እምነት አለኝ።
በአካባቢው፣ በእጽዋት፣ በእንስሳትና በሰው ላይ የጤና ችግር የሆኑ ነገሮችንም ከማስወገድ አኳያ የማይተካ ሚና አለው። ምክንያቱም ይህ መድሃኒት ተፈጥሮን የሚንከባከብና የነበረ ምቹነቷን የሚሰጥ ነው። ከዚያም አልፎ ምርታማነታቸውን የሚጨምር ነው። ጣዕም ጭምር የሚጨምር በመሆኑ ተመራጭነቱ ላይ ትልቅ አቅም ይሰጣል። በዚያ ላይ አሰራሩም ቢሆን ቀላልና የሚወድቁ ነገሮችን በመጠቀም የሚሰሩ ናቸው። ስለዚህም ቆሻሻን ለማስወገድም ፍቱን መድሃኒት ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሁን የተሰራው ፕሮጀክት ምርቱ ገበሬው ጋር መች ይደርሳል፤ እስካሁን የተሰሩት ሥራዎችስ ምን ይመስላሉ?
ዶክተር ተስፋዬ፡– ከምርቱ ጋር በተያያዘ መቶ በመቶ ተጠናቋል። የት የት ቦታ ምርታችን መሸጥ እንዳለበትና ሳይቶች በምን መልኩ መስተካከል እንዳለባቸው እንዲሁም ማን ያከፋፍል የሚሉት ጉዳዮችም ቢሆኑ በደንብ ዝግጅት የተደረገባቸው ናቸው። ምክንያቱም በአፍሪካ ቡና አብቃይ አገሮች ደረጃ ምንም አይነት የዚህን አይነት ሥራ ተሰርቶ በፋብሪካና በኢንዱስትሪ ደረጃ ለማምረት ዝግጅት ያደረገ አካል የለም። ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ የመሳሰሉ ቡና አብቃይ አገራትም በውድ ዋጋ ከውጪ እያስመጡም ነው የሚገለገሉት። ይህ ደግሞ የገበያ አማራጫችንን ስለሚያሰፋው ይህንን እድልም ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን። ነገር ግን በስፋት ከማምረትና ከማሰራጨት ጋር ተያይዞ ከውጪ የሚገዙ መሳሪያዎች ያስፈልጋሉና እነርሱን በመጠባበቅ ላይ ነን።
ሽያጩ በስፋት ያለው በአውሮፓ፣ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በኢስያ ነው። ከፍተኛ ገቢም ከዚህ ያገኛሉ። ስለዚህም እኛም በመጀመሪያ ደረጃ ምርታችን ወደ 2ነጥብ 5 ሚሊዬን ዩኤስ ዶላር ለማግኘትም አቅደናል። ቀጥለን ደግሞ 17 ነጥብ 5 ሚሊዬን ዩኤስ ዶላር ለማግኘትም እቅድ ተይዟል። ምክንያቱም በየጊዜው ካላሳደግነው ገቢያችንም በዚያው ልክ ያሽቆለቁላል፤ ተቀናቃኝም ሊፈጠርብን ይችላል። ስለሆነም በየጊዜው ፋብሪካዎችን ጭምር እያሰፋን ሥራውን ለመስራት ነው ያሰብነው።
ባለሀብቶችንም በዘርፉ ገብተው እንዲሰሩ እየጋበዝን እንገኛለን። በተለይ ከአገር ውስጥ ባለሀብት ባሻገር የምስራቅ አፍሪካ ባለሀብቶች ጭምር ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው። ሆኖም በብዛት ለማምረት የእቃዎች ግዢና መሰል የዝግጅት ጊዜያት ያስፈልጋሉና ይህ ዓመት በዚህ ያልፋል። ቀጣዩ ዓመት ግን የሥራና ምርቱን የማከፋፈሉ ተግባር ውስጥ ይገባል ብለን እናምናለን። ገበሬውም ሆነ አገር የምትደሰትበት ሥራ ለመስራትም እየጣርን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም ምርታማነትም ሆነ በሽታ መከላከሉ ላይ ምን ሰርታችኋል፤ ምርምራችን ለውጤት አብቅቷል የምትሉት ምን ምን ላይ ነው ? ከዚህ ትይዩ የሆኑ ሥራዎችስ አሉዋችሁ?
ዶክተር ተስፋዬ፡– ከዚህ ቀደም ዝንጅብል እጅግ ውድና በቀላሉ ለማግኘት የሚያስቸግር ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የዝንጅብል በሽታ ገብቶ ገበሬውና ተጠቃሚው በሚፈልገው ልክ ማምረት ባለመቻሉ የተከሰተ ነው። ስለዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማይክሮቢያል ሴሉላር፣ ሞለኪውላር ባይሎጂ ትምህርት ክፍል፤ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት/ ከአረካና ከቴፒምርምር ማዕከላት/ እና ከኢትዮጵያ ቅመማቅመም ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንዲሁም ከ ኢንታግ/ኔዘርላንድ መንግስት/ በተሰጠው ድጋፍ አማካኝነት የዝንጅብል በሽታ መከላከሉ ላይ በስፋት ሰርቶ አሁን አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ በሚባል ደረጃ ምርቱ እንዲቀርብና በተመጣጣኝ ዋጋ ጭምር እንዲገኝ ያደረገው አንዱ ሥራ ነው።
እንደ ቡናው ሁሉ ከዚህ ትይዩ የሆኑም ሥራዎች አሉን። ለሁሉም ምርት የሚያገለግል ብዙ ችግሮቻችንን የሚቀንስልን ተግባር ለማከናወን አቅደናል። ይህም የትራይኮዳርማ የፈንገስ ዝርያዎችን በመጠቀም የተፈጠሮ (ባዮፈልትራይዘር) ማዳበሪያ ማምረትና ገበሬው ጋር እንዲደርስ ማድረግ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ማዳበሪያ ከውጪ የማይመጣበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከወዲሁ ምርምሮችን እያካሄድን እንገኛለን። አሁን ባጠናነው ብቻ ለማወቅ እንደተቻለው ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ምርት የመጨመር ባህሪው በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ታይቷል። ስለዚህም ይዘታቸውን በመለየት ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው የሚጣል ቆሻሻን ሰብስበን ሥራውን ለመስራት እቅድ አለን። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ቆሻሻ ሁሉ ለምርት አስፈላጊና ምርታመነትን የሚሰጥ ነው። እናም አዕምሯችንን ለስራ አነሳስተን ወደ ተግባር ከገባንበት መፍትሄውም ውጤቱም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሚመጡ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ሀሳብ እናመሰግናለን።
ዶክተር ተስፋዬ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2013