በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የፍትሁ ዘርፍ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ይጠቀሳል። በተለይም በመዘግየት በኩል ያለው ችግር ተደጋግሞ ሲገለጽ ይሰማል። ህግን ከማክበርና ከማስከበርም አኳያም እንዲሁ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት ይነሳል። ሆኖም ከለውጡ በኋላ ግን የተለያዩ መሻሻሎች እንዳሉ ይጠቆማል። ለመሆኑ ይህ መስክ ምን ያህል መሻሻሎች አምጥቷል፤ ምንስ ያህሉ በውጤት የተደገፈ ነውና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት በፍትሁ ዘርፍ ከረዳት ጠበቃ እስከ ምክትል ጠቅላይ አቃቢህግነት ለረጅም ዓመታት ከሰሩት ምክትል ጠቅላይ አቃቢህግ አቶ ፈቃዱ ጸጋዬ ጋር ቆይታን አድርገናል። እርሳቸው የሰጡንን ማብራሪያም እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡– በአገራችን ከለውጡ ወዲህ በፍትህ አካላት ላይ የተደረገው ሪፎርም ምን ደረጃ ላይ ይገኛል፤ እስካሁንስ ምን ውጤት ተገኝቶበታል?
አቶ ፈቃዱ፡– ከለውጡ በኋላም ሆነ ከለውጡ በፊት በዚህ ቤት ስለነበርኩኝ ሁለቱንም አነጻጽሮ ለመናገር እድሉ አለኝ። በዚህም ከፍትህ አንጻር የተለየ ለውጥ መጥቷል ተብሎ የሚታሰበው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በዜጋው የዕለት ተዕለት ህይወቱ ላይ ትልልቅ ተጽዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ የህግ መሻሻሎች መከናወናቸው አንዱ ነው። በዚህም እንደ አገር ሲያሶቅሰን የነበረው ያለፈው ስርዓት ዜጎችን ለማፈን ሲጠቀምባቸው የነበሩ ህጎች ተሻሽለዋል። ለአብነት የሲቪል ማህበረሰብ ህግን ብንወስድ ተደራጅቶ ህዝቡን አንቅቶ ለመብቱ ተሟጋች እንዳይሆን የተለያዩ ገደቦች የነበሩበት ነበር። አዋጅ ቁጥር 6/ 21። ስለዚህም ይህ ተሻሽሎ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል።
የጸረ ሽብር አዋጁንም ብንወስድ እንዲሁ ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ የተለያየ መድሎ እንዲደረግበትና በሰበብ አስባቡ ለከባድ ቅጣት ጭምር እንዲዳረግ ይጋብዛል። በፈጸመው ወንጀል ልክ ቅጣቱ አይበየንበትምም። ስለሆነም ይህንን ማሻሻል መቻሉም በጣም ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ የፈቀደ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። የአስተዳደር ሥነስርዓት ህግ የወጣውም በዚህ ጊዜ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ በተለይም ችግራችን የመልካም አስተዳደር ችግር ነው የሚባለውን ቋሚ የረጅም ዓመታት ንግግር ከመፍታት አኳያ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። ባላወቅነው መመሪያ መመሪያ አይፈቅድልንም የሚባል ነገር እንዳይኖርም መሰረት የጣለ ህግ ነው። በተመሳሳይ አንድ አስተዳደር የሚሰጠው ውሳኔ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይግባኝ የማይጠበቅበት እንዳይሆንም እስከ ፍርድቤት ድረስ ተሄዶ ይግባኝ የሚጠየቅበት ህጎች ጭምር የወጡበት ነው።
በአይነቱ ብዙ ማስተዋወቅን የሚጠይቅ ብዙ መፍትሄዎችን የሚሰጥ ህግ ከለውጡ በኋላ ወጥቷል። የመንግስት ሃላፊዎች፣ ተቋማት ተጠያቂነትን በደንብ አውቀው እንዲሰሩ የሚያደርግ የዜጎችን የእርካታ ደረጃ ከፍ ሊያደርግ የሚችል በመንግስት ጠቅላላ አገልግሎትም ጥራት ያለው አሰራርን ለመፍጠር የሚያስችልም ህግ ነው የወጣው። ስለዚህም ይህ ጊዜ ለ50ና 60 ዓመት ያህል የተጠቀምንበትን ህግ በሚተካ መልኩ ሁለተኛ አብዮት የተፈጠረበት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
በህግ ደረጃ በ1960 ዎቹ ነው በኢትዮጵያ ትልልቅ መሻሻሎችና አገር ሊፈውሱ የሚችሉ ህጎች የወጡት። ለአብነትም እንደ ንግድ ህግ፣ የወንጀል ስነስርዓት ህግ፣ የፍትሐብሔር ህግ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ህግና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ከዚያ በኋላ ግን ይህ ሳይታይ ቆይቷል። አሁን በሦስት ዓመታት ውስጥ ነው ዳግም የህግ አቢዮት የፈነዳው። ይህ ሲሆን ደግሞ የመንግስት አካል ስለፈለገው፣ የለውጥ ሀይሉ እንዲሁም ፖለቲከኛው ስላሰበው የተደረገ ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ እኔ በማውቀው ያገባናል የሚሉ አካላት ተሳታፊነት የተከናወነ ነው። በፈረንጅ የወጣልን ሳይሆን በራሳችን ባለሙያዎች ተፈትሾ የመንግስት አዳዲስ አስተሳሰቦችን የመቀበል ተነሳሽነት ተጨምሮበት እውን መሆን የቻለ ነው። ስለዚህም ይህ ወቅት ህግና ህጋዊነትን በመለወጥ ደረጃ ብዙ መሻሻሎች የታዩበት ማንሳት ይቻላል።
በእርግጥ የህግ ጋጋታ ብቻ ምንም ውጤት አይደለም። ማሳወቅ ላይ መስራት ያስፈልጋል። ዜጋውም ለማወቅ ራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት። በተመሳሳይ መንግስት ለስራው እውን መሆን ትክክለኛ አሰራር መዘርጋትና ተግባራዊነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል። እንደ ህግ አውጪው አካልም በደንብ ህጉን ማሳወቅና ለተግባራዊነቱ ታማኝ መሆን ላይ ከአሁኑ መዘጋጀትና መስራት ይጠበቅበታል። የሚቀረውም ይህ በመሆኑ ለዚህ መዘጋጀት ታላቁን ድል ያጎናጽፋል።
አዲስ ዘመን፡– በሃገራችን ከፍትህ ስርዓት ጋር ተያይዞ የፍትህ መዘግየት እንደ መሰረታዊ ችግር ይታያል፤ ምክንያቱ ምንድነው? ከዚህ አንጻር የነበሩ ክፍተቶችን ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ፈቃዱ፡– ከፍትህ መዘግየት ጋር በተያያዘ ሁለት ነገሮችን በዋናነት ማንሳት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። አንዳንዴ እውነትም የሚዘገዩ ፍትሆች አሉ። አንዳንዴ ደግሞ ከተሳሳተ ምልከታ አንጻር ፍትህ ይዘገያል ይባላል። በተለይ የወንጀል ፍትህን ስንወስድ በእርግጥ ፍትሀብሔርም ቢሆን ሁለት ተከራካሪዎች ያሉበት ነው። ግን የወንጀሉን ብቻ ነጥለን ብናይ መርማሪ ፖሊስ ከአቃቢህግ ጋር በመሆን ይመረምራል። አቃቤህ ከፊል የዳኝነት ስልጣን በሚመስል ሁኔታ ያስከስሳል አያስከስስም የሚለውን ይመረምራል። ከዚያም የሚያስከስስ ከሆነ ነው ወደ ክሱ የሚገባው። ስለዚህም መመርመሩ የሚወስደው ጊዜ መኖሩን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።
መመርመር እንዳደጉት አገሮች በቴክኖሎጂ ጥረት አድርገን ፤ እያንዳንዱን ዱካ አሻራ አንስተን አይደለም ሂደቱን የምናከናውነው። ሰውና ሰውን ብቻ መሰረት ባደረገ ሁኔታ ነው። ሰነድም ቢሆን ለማሰባሰብ ብቻ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ተደክሞ ነው። ይህ ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዘ በመረጃ ስለማይያዝበት አንድ ሰው ለማግኘት በመታወቂያ ብቻ ብዙ ልፋትን ይጠይቃል። ብዙ መታወቂያ ይዞ ስለሚንቀሳቀስ። በዚያ ላይ ምስክር ማግኘቱና ከመሰከሩ በኋላ የሚመጣው አላልኩም ሀሳብና ክህደት ሌላው ችግር ነው። ስለዚህም ረጅም ጊዜ ለምርመራ መውሰድ ግዴታም ጭምር ይሆናል።
ከክስ በኋላም ቢሆን እንዲሁ ሲገል ታይቶ ጭምር አልገደልኩም ብሎ መከራከር መብቱ ነው። በማስረጃ ማረጋገጥ ደግሞ ግዴታ ይሆናል። ክርክር ሂደት ነው። ይህ ክስ አልገባኝም ከማለት ጀምሮ ክሱ ይሻሻልልኝ እስከማለት የሚጓዝም ነው። በሁለተኛ ደረጃ ፍትህ ዘገየ ብሎ ቅሬታ የሚያነሳው አብዛኛው አካል በራሱ በኩል ያለውን ብቻ ስለሚያይና መንግስት ይህ ተደርጎብኝ ይህን አላደረገልኝም ይላል። ይህ ደግሞ ጤነኝነትም ነው። ነገር ግን ከዚያ ጀርባ ያለው አይታይም። ምን ያህል መዝገብን በምን ያህል የሰው አቅም እየተሰራ እንደሆነ አይረዳም። ጉዳዩም ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ከሚቀርቡት ኬዞች ብዛትና ከምርመራ ጊዜው አንጻር እንጂ በቸልታ የታለፉ አይደሉም።
ከአገራዊ ግጭቶች ጋር በተገናኘ ብቻ እንኳን ብናይ ብዙ ኬዞች ወዲያው ውሳኔ አላገኙም በሚል ይተቻል። ሆኖም ብዙዎቹ ውሳኔ ላይ የደረሱ ነበሩ። በዚያው ልክ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የዘገዩ ጉዳዮች አሉ። ለዚህም በፕሬዚዳንቱ የሚመራው የእነአብዲ ኢሌ ጉዳይን ብቻ ማየት በቂ ነው። ይህ ጉዳይ ጥር 2011 ዓ.ም አካባቢ ክሱ ተጀምሯል። ሆኖም አሁንም ድረስ ከምስክሮች ጥበቃ ጋርና መሰል ነገሮች ጋር ተያይዞ መጠናቀቅ አልቻለም። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ዘገየ ለማለት የማያስችልበት ሁኔታ አለ።
ቦስተን ውስጥ በነበረ የቦንብ ጥቃት በጣም ሰለጠኑ በሚባሉት ጭምር ከሁለት ዓመት በላይ ምርመራውን ብቻ ለማካሄድ ጊዜ ወስዶባቸዋል። እኛ ጋር ግን የሰኔ 16ቱን ብናነሳ ምንም ቴክኖሎጂ በሌለበት ሁኔታ በሁለት ዓመት ነው እልባት እንዲያገኝ ያደረግነው። ስለዚህም ምክንያት አለ፣ መዘግየት አንጻራዊ ነው ተብሎ ቢወሰድ መልካም ነው። በተዘዋዋሪ ችሎት ጭምር እንዲታይ ብዙ የተጣረበት ነው።
በአዋጁ መሰረት ከፍተኛ የፌደራል ፍርድቤት በክልሎች የተዘዋዋሪ ችሎት ውክልና ቢሰጥም በአምስት ክልሎች ላይ ውክልናውን አንስቷል። በወቅቱ ፍርድቤቶችን ባለማደራጀቱ መጓተቶች እንደተስተዋሉ አይካድም። እስከዛሬም ሀዋሳ ላይ ብቻ ለማደራጀት ተሞክሯል እንጂ ሌሎቹ ይህንን እድል አላገኙም። ስለሆነም በእነዚህ ምክንያት ክፍተቶች እንደነበሩ ሊወሰድ ይገባል። ከዚህ በተጓዳኝ ከአቃቢህ አለያም ከፖሊስ ቸልታ አንጻር የሚከሰቱ መዘግየቶች አይኖሩም ተብሎ ሊወሰድ አይችልም። የሰው ሀይል እጥረትም እንዲሁ ለመጓተቱ መንስኤ ነበር። 40 ዳኞች ከተቀጠሩ በኋላ ነው ወደመፍትሄው የተገባው። ግን በእነዚህ ምክንያቶች የሚከሰቱ መዘግየቶች በጣም በጣም ጥቂት ነውና በብዛት መዘግየቱ የሚመጣው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች እንደሆነ ሊወሰድ ይገባል። ይህ ነገር በቋሚነት መፍትሄ እንዲያገኝም ማህበረሰቡ ለፍትሁ ምን ያህል አግዤያለሁ ማለት አለበት። ፍርድቤቶችም ያለባቸውን ክፍተት ሊደፍኑ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ከለውጡ ወዲህ በሃገራችን በተጨባጭ ከፍተኛ ሃገራዊ ቀውስ ያስከተሉ ወንጀሎች ሲፈፀሙ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ለፍርድ ቀርበዋል፤ ለምሳሌ በአማራ ክልል፤ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ፣በአዲስ አበባ፣ ወዘተ ነገር ግን ወደፍርድ የማቅረቡና ተገቢው ቅጣት እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች እንዳሉ ይገለፃል፤ ከዚህ አንጻር ያለው ችግር ምንድነው፤ ይህንን እንዴት ያብራሩታል?
አቶ ፈቃዱ፡– ከለውጡ ወዲህ በርካታ ግጭቶች ተከስተው በርካታ ተጠርጣሪዎች ወደ ህግ ቀርበዋል። ብዙዎቹም ውሳኔዎችን በፍጥነት አግኝተዋል። ይሁንና ወንጀሉ ሲፈጸምና በሂደት ባለው ዘገባ መካከል ብዙ ልዩነቶች ስላሉ ዜጋው ይህንን እንዳያውቅ ሆኗል። በተመሳሳይ ፍርድቤቶች ባላቸው ዌብሳይት ማሳወቅ አለመቻላቸውና እንዲዘግብ መንገዶችን አለማመቻቸታቸው ሁኔታውን ማህበረሰቡ እንዳይረዳ አድርጓል። ለዚህም ማሳያው ላይ የኦነግ አመራሮች ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ቡራዮና አዲስ አበባ በተፈጸሙ ወንጀሎች በቡራዮ ብቻ 108 ተከሳሾች ላይ ክስ ተመስርቶ ሁሉም ውሳኔ አግኝተዋል። አዲስ አበባ ላይም ከ60 በላይ ተከሳሾች ነበሩ። ሁሉም ውሳኔ ያገኙ ኬዞች ናቸው።
ከለውጡ በኋላ በተገናኘ አገራዊ ግጭት ላይ ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት የአርቲስት ሀጫሉ
ሁንዴሳ ጉዳይ ሳይቀር በዓመት ውስጥ ብዙ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች አሉ። ወደ 3375 ተከሳሾች ተይዘው በ17 መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው ሁሉም የአቃቢ ህግና የመከላከያ ምስክር ተሰምቶባቸዋል። ሻሸመኔ ላይ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ለፍርድ ከመቀጠር በስተቀር ሁሉም መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋልም። ከሰኔ 16 በኋላም ቢሆን እንዲሁ ቤኒሻንጉል ላይ 26 ሰዎች የሞቱበት በጣም አስከፊ ወንጀልም ተጠርጣሪዎቹ ሊያውም በተዘዋዋሪ ችሎት ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል። መስቃንና ማረቆ የነበሩ መዝገቦችም እንዲሁ ከአራቱ ሦስቱ ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል። ይህ የሆነው ደግሞ ይህንን ሥራ የሚሰራ ብቻ ችሎት የኦሮሚያ ፍርድቤት በማቋቋሙና ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት ከ30 የሚበልጡ አቃቢ ህጎችን በመመደብ መስራቱ ነው። ይሁን እንጂ ወንጀል በተፈጸመ ጊዜ ያለው ዘገባና በፍርድቤት ሂደቶች የሚሰጠው ዘገባ ተመጣጣኝ ባለመሆናቸው ጉዳዩን ማህበረሰቡ እንዳያየው ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡– በሃገራችን አንዳንድ ጊዜ ፍርድ ቤት ነጻ ካለ በኋላ ተጠርጣሪውን ያለመልቀቅ ሁኔታ እንደነበርና ይህ ደግሞ የፍትህን የበላይነት እንደሚቃረን ብዙዎች ይገልጻሉ። ይህ እንዴት ይታያል?
አቶ ፈቃዱ፡– በፌዴራል መንግስት የምርመራና አቃቢህግ ደረጃ እንዲህ አይነት ነገር አልገጠመንም። አልተከሰተምም። የፍርድቤት ትዕዛዞች ያለመከበር ጉዳይ እውነት ለመናገር በዚህ ተቋም አላየሁም። እንደውም ትዕዛዞች በተሻለ ሁኔታ ይፈጸማሉ። ነገር ግን ፍርድቤቶች በሚሰጧቸው ውሳኔዎች የማንረካበት፣ በጣም የማይዋጡ ውሳኔዎች የሚጠላለፉበት ጊዜ ብዙ ነው። ነገር ግን እስከ ስህተቱ እያከበርነው እንሄዳለን። ምክንያቱም ህግ ለማስከበር ብለን ሌላ ህግ አንጥስም።
የይግባኝ ስርዓቱን ተከትለን እናስፈጽማለን እንጂ በቀጣዩ እንዲታገድ የቻልነውን ከማድረግ ውጪ ትዕዛዛ አናፈርስም። ፍርድቤት የለቀቃቸውንም ለማሰር የምናደርገው ነገር የለም። አንዳንድ ቦታ የተነሱትን በተመለከተ እኛም እንደማንኛውም ሰው እንሰማለን። ስህተት እንደሆነም በቻልነው መጠን ኢንተርቪው አድርጎ ጭምር ለመስራት የተሞከረበት ሁኔታ አለ። ለማስረዳት እንሞክራለን። ይሁን እንጂ ሥራው ጥልቅ በመሆኑና በአንድ ጊዜ ለማረም የማይቻል በመሆኑ በሂደት ለማረምም የምንሰራ ይሆናል። ምክንያቱም ይህ ነገር የበቀለና አዕምሮ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የተተከለ አሰራር ነው። ስለዚህም ሂደቶች እያስተካከሉት ካልመጡ መፍትሄ የሚሆን ነገር አይኖርም።
ሰዎች በእውቀትም ፣ በአመለካከትም ፣ የዜጋንና የመንግስትን መብት የምናስከብረው በህግና በህግ ብቻ ነው ተብሎ እስካልታመነ ድረስ እነዚህ ስህተቶች ስህተት ሆነው መቀጠላቸው አይቀርም። ህዝቡም ቢሆን መረዳት ያለበት አንድ ነገር አለ። የመንግስት መዋቅር ውስጥ ይህ መንግስት እንዲቀጥል ፣ እንዳይረጋጋ የሚሰራ እንዳለ የሚሰራ ሀይል እንዳለ ማወቅ ነው። እኔ ሙሉ ለሙሉ ትዕዛዝ እየተከበረ አይደለም ብሎ የሚያነሳውን ለመንግስት ከሚያስብ ወገን ነው ብዬ ስለማልወስድ ነው።
የመሰወርና የፍርድ ትዕዛዝ አለማክበር ስርዓት ከማስከበር ጋር ብቻ የሚወሰድ አይደለም። ሆን ብሎ ህዝብንና መንግስትን ከማቃረን አኳያም የሚታይ ነው። መንግስትንና ህዝብን በአንድ መንፈስ፣ በአንድ ሀሳብ ለመምራት ከሆነ የተፈለገው እዚህ ውስጥ ይገባል ተብሎ አይታመንም። ስለዚህም ከስርዓት ማክበሩም ሌላ ጎን ማየት ያስፈልጋል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- የአቃቤ ህግም ሆነ ፖሊስ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ከማክበርም ሆነ ለህግ ከመገዛት አንጻር ያሉበት ቁመና እንዴት ይገለፃል? ተቀናጅቶ መስራት ላይስ ምን ያህል ናችሁ?
አቶ ፈቃዱ፡- ተቀናጅቶ የመስራቱ ሁኔታ ቡራቡሬ መልክ ያለው ነው። ቅድም እንዳልኩት በአገራችን ያለው ሁኔታ አንድ አይነት መልክ አይታይበትም። በዜናና መሰል ነገሮች እንደምንሰማውም ይህ ሁኔታ በስፋት ይታያል። አንዱ ጋር የተሻለ ሲሰራ ሌላው ጋር ስህተቶች የገዘፉበት ይሆናል። በዚህም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እየሰማናቸው ያለነው ጥሩ ያልሆኑ ዝንባሌዎች አሉ። ይህ ደግሞ ግማሹን ለአቃቢ ህግ ግማሹን ለፖሊስ የምንከፋፍለውም አይደለም። ምክንያቱም ህዝቡ ፍርድቤት ነው ያጠፋው ፖሊስ ነው የሚለውን አይለይም። ሁሉንም አጠቃሎ የመንግስት ችግር ነው ብሎ ነው የሚያነሳው።
ፍርድቤቶችም ሆኑ ፖሊሶች እንደመንግስት ተጠቅልለው መታየታቸው ደግሞ ችግሩን ለይቶ እልባት ለመስጠት አዳጋች ነው። ስለሆነም መፍትሄ መሰጠት ያለበትም ተሰብስቦ ነው። በፌደራል ደረጃ ከለውጡ በኋላ ማንም ሰው ሊመሰክር በሚችልበት ሁኔታ የፌደራል ፖሊስን ጨምሮ ከቃል አቀባበል፣ ከእስረኞች አያያዝና ከግቢው ሁኔታ አንስቶ እስከ ውሳኔ ድረስ ብዙ ለውጦች የታዩበት ነው። በችግር ደረጃ የሚነሳም አለ ለማለት እቸገራለሁ።
ፌዴራል ተቋሙ በደንብ አድርጎ እንደውም አሁን እየተነሳ ያለው ችግር መርማሪውና አቃቢ ህጉ ተሸነፉ። በተሸናፊነት ስሜት ነው ከተከሳሹ አንጻር ችሎት ላይ እየቀረቡ ያሉት ነው የሚባለው። የመንግስትና የህዝብን ጥቅም የማስከበር የቆመ አካሂድ ሳይሆን የሚመስለው ከመብት መስጠትም በላይ ሆናችኋል ይባላል። ስለዚህም የፍርድቤትነም ትዕዛዝ ከማክበር አንጻር በጣም ዝቅ ብለው እየሰሩ እንደሆነም መወሰድ አለበት። ችግር ሲከሰትም ወዲያው የመፍታት ሁኔታም አለ።
አዲስ ዘመን፡– በሃገራችን ከወንጀሎች መበራከት ጋር ተያይዞ ተጠርጣሪዎችን ወደፍርድ ለማቅረብና ወንጀሎች ተደብቀው እንዳይቀሩ ከማድረግ አንጻር አቃቤ ህግና ፖሊስ ምን ያህል ተቀናጅተው ይሰራሉ፤ አቅማቸውንስ ከማጠናከር አንጻር ምን አዲስ ሥራ አለ፤ ምንስ እየሰተራ ነው?
አቶ ፈቃዱ፡– ወንጀል መከላከል፣ ወንጀለኛን ለፍርድ ማቅረብ የፖሊስና አቃቢህግ ሥራ ብቻ አይደለም። የእነርሱ ሥራ መመርመርና ለክስ ማቅረብ ብቻ ሊሆን ይችላልም። ከዚያ በፊት ግን ወንጀለኛውን አጋልጦ መስጠት የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው። በተለይም የህዝቡ አስተዋዕጾ ከፍተኛ ነው። በየደረጃው ያለው የፖለቲካ አመራርም እንዲሁ። በተለይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ፣ የደረሰውን መፈናቀልና ነፍስ መጥፋት ተገቢ አለመሆኑን በሚዲያ ሲገልጽ የነበረው ሄዶ ተጠርጣሪ ሲፈልግ መሳተፍ አይፈልግም። ሌላ ሰው ሆኖ ታገኝዋለሽም። ወንጀል መፈጸሙ እየታወቀም ምስክሮች ተደራጅተውበት ነው እንጂ እርሱ አልሰራም ይባላልም። ጠበቃ ለወንጀለኛው ጭምር ይበዛልም። ስለዚህም የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ወደታች ሲወረድ ያለው አመራርም ፈቃደኛ መሆን አለበት። የፌደራል ፖሊስ ወረዳ ላይ ወርዶ ተጠርጣሪን ፈልጎ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ማሰብም አይችልም። ስለሆነም መንግስት ለዚያ አካባቢ ብሎ ያደራጀው አካል እስካለ ድረስ የእዚያ አካባቢ ፖሊስና አመራሩ ፈቃደኛ ካልሆነ ምንም የሚሳካ ነገር አይኖርም።
አገራዊ ለውጡን አስመልክቶ የተከሰቱ እያንዳንዳቸው ግጭቶች ማነው ያነሳሳው፣ እነማን ናቸው የተሳተፉት፣ ማነው ከመነሳሳቱ ጀምሮ ክብሪቱን ጭሮ ያቃጠለው፣ የገደለው፣ የተኮሰው የሚለው ማስረጃዎች ከሞላ ጎደል መሰብሰብ ተችሏል። ተጠርጣሪዎቹ መያዝ ጋር ሲኬድ ግን አካባቢው የፖለቲካ መዋቅር ማህበረሰብ ካልተባበረ ምንም የሚሳካ ነገር አይኖርም። ማሕበረሰቡ ወንጀል የፈጸመን ሰው ምንም ይሁን ምን አይጠቅመውም። እኔን አይወክልም የሚል አስተሳሰብ ማምጣትም አለበት።
መስረቅ ወንጀል መሆኑን በህግ ትምህርትቤት ልንማረው የምንችለው አይደለም። የተፈጥሮ ህግ ነው። ማንም ሰው የእርሱ ያልሆነ ነገርን መውሰድ እንደሌለበት ማንም ያውቃልም። ስለዚህ የግንዛቤ ችግር አይደለም ያለው። ከመስረቅ ፣ ማቃጠል ጥፋት መሆኑን ከዚህም በላይ ሀጢያት መሆኑን ማንም ይረዳል። ምክንየቱም ከ98 በመቶ በላይ አማኝ በሆነበት አገር ውስጥ ይህንን አያምንም ተብሎም አይታሰብም። ግን ወደ ወንጀል ፍለጋ ሲገባ ተቃራኒ ነገር ነው የሚገኘው። ኮታ ይፈልጋሉ። ማለት በተመረመረው ልክ ሳይሆን እነገሌ ስለጠሉት ነው፣ የእነገሌ ወገን ስላልሆነ ነው፣ ከእነዚያ ወገን ስንት ታሰረ እየተባለም ስሜት የማይሰጥ ነገር ይቀመጣል። ስለዚህም የፖሊስና የአቃቢህግ መቀናጀት በተለይ በፌደራል ደረጃ መመርመር ላይ አንድም ችግር ገጥሞን አያውቁም። ችግሩ ከታች ካልመጣ በስተቀር።
አቅምን ከማጠናከር አኳያ የአቅም ውስንነት ሁሉም ዘንድ ስላለ ይህንን ማድረግ ግድ ነው። በተለይም ከተደራሽነት አንጻር ሁሉም ቦታ አለ። ስለዚህም በተቻለ መጠን የአቅም ውስንነቶቹ እየታዩ እየተሰራ ነው። ብዙ ለውጦችም መጥተዋል። ብቻውን መለወት ግን ምንም ፋይዳ የለውም። ታችኛው ማህበረሰብ ድረስ የዘለቀ ስራ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በትግራይ እየተካሄደ ባለው ህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የአውሮፓ ሃገራት ጣልቃ ሲገቡ ይስተዋላል፤ ይህ ጣልቃገብነት ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል፤ ምንስ መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ፈቃዱ፡– ፖለቲካዊ ችግር ሆኖ ነው። አለምአቀፍ ህግ ስለጠፋቸው አይደለም። ስለትግራይ ከሌላው በበለጠ ስለሚቆረቆሩ እንዳልሆነም ግልጽ ነው። ስለሰው መብት ከሆነ የሚቆረቆሩት ሁሉንም በእኩል ሂሳብ ባያዩም የተቀራረበው እንደ ማይካድራውም አይነቶቹ በትግራይ ልክ ሊያሳስባቸውና ሊያሳዝናቸው ይገባል። ፍልስጤም አከባቢ የቦንብ ናዳ ሲወርድ አንድ ኣረፍተነገር የማያወጣ አካል በእኛ አገር ጉዳይ ላይ የሌለ ያለውን አውጥቶ ጫና ለመፍጠር መስራት መሞከር እውነት የአገር ጉዳይ አሳስቧቸው ነወይ ብሎ እንዲጠይቅ ማንንም ያደርጋል። ይህንን የሚያደርጉበት የአለምአቀፍ ህግም አልፈቀደላቸውም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሉአላዊት አገር ነች። ሁሉም የራሱ የሆነ አመለካከትና የራሳቸው የመከላከያ አካሂድም አላቸው። እኛ ላይ ያደረጉት ነገር በእነርሱ ላይ ቢሆን ኖሮ የማይቋቋሙት እንደሆነም ግልጽ ነው። እንደ እኔ እምነት ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ከህግ ማስከበሩ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው ብዬ አላምንም። ህዳሴ ግድቡን ለማስተጓጎል በማሰባቸው ያደረጉት ነው።
ለማንም አገር ቢሆን የማይካድራን ጉዳይ ለአለም ህዝብ ያሳወቅን እኛ ነን። እንደ ተቋምም ሆነ እንደመንግስት ይህ አልተሸሸገም። ለፖለቲካ ፍጆታ ቢሆን ኖሮ ከአንድ ሺህ በላይ ሲባል የነበረውን ምርመራችንም ያው ነው ብሎ ያልፈው ነበር። ሆኖም ሳይንሳዊ በሆነ ደረጃ ምርመራው ታቶ በልኩ ተቀምጧል። የማይካድራው የማያስጮኸው ሰው ካላዘነ የተፈጠረው ችግር ያነገበገበው አይደለም። ከጀርባ ያነገበው ሌላ ነገር አለ። ወይም የቀድሞ ወዳጅነቱ ፣ የጥቅም ፈላጊዎች የተዛባ ዘገባ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ለሁሉም ያዝናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደአገር የመልማት ፍላጎታችንን ለማደናቀፍ ካልተፈለገ ሁሉም እኩል መታየት ነበረበት ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን– የመጨረሻ መልዕክት ካልዎት ቢያስተላልፉ
አቶ ፈቃዱ፡– ማህበረሰቡ መንግስት ህግን አላስከበረም ብሎ ጣቱን ከመቀሰሩ በፊት ራሱን ቢመለከት። እያንዳንዱ መንግስታዊ አመራርም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና አደረጃጀቶች የህግ የበላይነትን ከማስከበርና ከማክበር አንጻር እኔ ያለብኝን ሀላፊነት ተወጥቻለሁ ወይ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። ሌላው ለፍተን ባላገኘነውና እኛ ባልሰራነው ላይ የማንጣላ መሆን አለብን። ብሔር የሚገኘው ጎበዝ ስለሆንን ወይም ሰነፍ ስለሆንን አይደለም። መርጠንም የሆነው አይደለም። በመወለድ ብቻ ያገኘነው ነው። ፈልገን የምንተወውም አይደለም። ስለዚህም የሚያዋጣን አንድና አንድ ሲሆን፤ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በእኛ የተፈጠሩ አይደሉምና ማቆም።
እኛ አገር ካለው በላይ ሌሎች አገሮች ላይ በርካታ ልዩነቶች አሉ። ግን ስለተከባበሩና አብሮነትን ስለመረጡ አብረው ይኖራሉ። ስለሆነም የሚለየንን ነገር ከማጎልበትና እዚያ ለይ ጊዜ ከማጥፋት የሚያስተባብረንን ብንፈልግ ለዛሬ ችግሮቻችን መፍትሄ እናገኛለን። ሰው መሆናችን ያስተሳስረናልና ይህንን እናጉላው። በተጨማሪ የምንለውን ሆነን እንገኝ። ካለመዋደድ እንቅልፍ ማጣት ይመጣል፤ አዕምሮ እረፍት ያጣል። ስለዚህም ለአዕምሮ እረፍታችን ስንል ፍቅራችንን እናጠንክር።
ኢትዮጵያን የምንወድ ከሆነ ኢትዮጵያ ተራራ አይደለችምና ህዝቦቻቸውን ስለሆኑ እነርሱን እንውደድ። በማንነት ዜጎቿን እያሳደድን ኢትዮጵያን እንወዳታለን ማለት ሞኝነት ነውና ከዚህ እሳቤያችን እንውጣ። ከውስጥ እያፈረሱ ከውጪ መታደግ የለምና ውስጥን በውስጥ ፈውስ አጠንክረን ውጪውን በትብብር እንመክት።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን።
አቶ ፈቃዱ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2013