የኢ.ፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙትን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አምባሳደር መሀመድ ሳሊም አልራሺዲ የሹመት ደብዳቤ ቅጂ ተቀብለዋል።
ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የኢትዮጵና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሃገሯ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እያደረጋች ያለውን ድጋፍ አመስግነዋል።
በሁለቱ አገራት የተመሰረተውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በንግድና በኢንቨስትመንት ለማጠናከር ሁለቱም አገራት የበለጠ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
አዲሱ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አምባሳደር መሀመድ ሳሊም አልራሺዲ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ አገራቸው እንደሚቆጥሩ ገልጸው፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ ኢንቨስትመንት እና ንግድ እንዲሳተፉ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የስራ ቆይታቸው በመንግስት በኩል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ለአምባሳደር መሀመድ ሳሊም አልራሺዲ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ሲሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተለያዩ ስራዎች ላይ እየሰሩ ይኖራሉ።
እንደ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅ/ቤት መረጃ ኢትዮጵያ በዱባይ የቆንስላ ጽ/ቤት በ1996 የከፈታች ሲሆን ከዚያም ኤምባሲዋን በ 2005 ዓ.ም በዋና ከተማዋ በአቡዳቢ ከፍታለች። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲዋን በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከፍታለች።