በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከበሩ መብቶች መካከል የዜጎች የመደራጀት መብት በዋነኝነት ይጠቀሳል። የአገሪቱ ህገመንግሥት አንቀጽ 31 የሚከተለውን ይደነግጋል። ‹‹ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማህበር የመደራጀት መብት አለው። ሆኖም አግባብ ያለውን ህግ በመጣስ ወይም ህገመንግሥታዊ ስርዓቱን በህገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ይሆናሉ።›› በመሆኑም ዜጎች ህገመንግሥቱ ያጎናፀፋቸውን የመደራጀት መብት በመጠቀም በበጎ አድራጎት ወይም በማህበር ሊደራጁ ይችላሉ።
ማኅበራዊ ህይወት ከውልደት እስከ ሞት የሚኖር እና ቀጣይነት ያለው ሂደት ሲሆን በትምህርት እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት የሚዳብር ነው።የሰው ልጅ ስለራሱ እና ስለሚኖርበት ማኅበረሰብ የሚኖረውን ዕውቀት በተለያየ መልኩ ማለትም የመግባቢያ ቋንቋ በመማር፤ አካባቢያዊ ሁኔታውን በመመልከት እንዲሁም ማኅበራዊ ክህሎቶችን በመማር እያሳደገ ይሄዳል። ይህ የማኅበራዊ ህይወት ክህሎት በአግባቡ መዳበር ለተሟላ ስብዕና እና ዕድገት ወሳኝነት አለው።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቱ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እያረገ ሲሆን አቅመ ደካማዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በሁሉም ቦታዎች እየተቀጣጠለ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ወጣቱ ግንባር ቀደም ነው። መንግሥትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቸገሩ በማብላትና ቤታቸውን በመጠገን ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ነው። ይህም እንቅስቃሴ በዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ነው። የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ በሁሉም ቦታዎች በጎ አድራጎት ማህበራት እየተበራከቱ ይገኛል። በተለይ የህብረተሰቡን ችግር ከስሩ ለመፍታት ውጤታማ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
በብዛት ወጣት ከሚገኝባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ ታድያ ወጣቱ ክፍል ከመስራትና አገርን ከማሳደግ ይልቅ ባልባሌ ትርክቶች ተጠምዶ እርስበርስ ሲጋጭ ማስተዋል ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል። በአገሪቱ የሚሰራ ስራ ጠፍቶ ሳይሆን አለመስማማቶች በመበራከታቸው የሚሰሩ እጆች ለጥፋት እየዋሉ ይገኛሉ። በመንግሥትም ደረጃ ጠንከር ያሉ ስራዎች ባለመከናወናቸው ዝርፍያና ቅምያ በከተሞች አካባቢ እየተስፋፋ ይገኛል። ይህን ጉዳይ ያለ ምክንያት አይደለም ያነሳሁት። ለጥፋት የሚውሉ እጆች እንዳሉ ሁሉ ለበጎ ተግባራት የሚሰነዘሩ እንዳሉ ለማሳየት ፈልጌ ነው። የተቸገሩ አረጋውያንንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚደግፉና አለንላችሁ የሚሉ በርካታ በወጣቶች የተመሰረቱ ማህበራት እንዳሉ በዚሁ አምዳችን አስቃኝተናችሁ ነበር። አብዛኛዎቹ ማህበራት እውቅናና ፈቃድ አግኝተው እርዳታ በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው።
የስብዕና ልህቀትና የአስተሳሰብ ለውጥን በመደበኛ ትምህርት ብቻ ማሳካት አይቻልም። ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በህብረተሰቡ አስተሳሰብ ለውጥ ላይ የሚሰሩ ማዕከላት እገዛ ያስፈልጋል። የጋራ ጥረት ለውጤት ያበቃል። በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የሚሰሩ ሥራዎች ተከታታይነት ከሌላቸው የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አያስችልም። ምክንያቱም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ መሆን ስላለበት ነው። ሃሳብ የመጀመሪያው የሃብት ምንጭና የአንድ ሀገር ዕድገት መለኪያ ሲሆን ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል። አሁን ባለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በማህበረሰብ ደረጃ ቀናና የበለጸገ አስተሳሰብ ማምጣት ለፍትሃዊ ዕድገት ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ በአስተሳሰብ ላይ ብዙ መስራትና የመወያያ መድረኮችን ማበራከት ያስፈልጋል። ወደ ግለሰብ፣ ቤተሰብና ማህበረሰብ በማውረድ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግም ይገባል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማህበረሰብ አገልግሎትን እንደ አንድ ስራ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን በዚህም በርካታ ውጤት አምጥተዋል። በተለይ ተቋሙ የሚገኝበትን አካባቢ ከማልማት ጀምሮ አርሷደሮችን በመደገፍና በምርምር የተገኙ የግብርና ግብዓቶችን እያቀረቡ ይገኛሉ። ይህንን ስራ ተማሪዎችም በመከተል በሰብል ስብሰባና በሌሎች ስራዎች እገዛ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል። ነገር ግን ተማሪዎች በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ተሰማርተው የተቸገሩትን እንዲደግፉ የተቀመጠ ነገር የለም።
ሰውን ለመርዳት ሀብታም ወይም የሚሰጥ ነገር መኖር የለበትም። ሰው ሰውን ለመርዳት ቅንነትና ፍላጎት በቂ ናቸው። የሚረዳቸው ሰው ያጡ አረጋውያን፣ ህፃናትና አካል ጉዳተኞች በየቦታ ወድቀው ይታያሉ። ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር የመረዳዳቱ ሁኔታ አነስተኛ በመሆኑ ነው። ነገር ግን የመረዳዳትም ሆነ በልክ የመኖር ባህሎች ዛሬም እንዳሉ የሚያሳዩ ተግባራት እንዳልጠፉ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በተለይ በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን።
በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማለት በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ በማድረግ ውስጣቸው ከሚሰማቸው ሰብአዊ አመለካከት ተነስተው ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ሰፊ የልማት አውታሮችን በመዘርጋት የዜግነት ኃላፊነትን የሚገነዘቡ ሃገራዊና ብሄራዊ ግዴታዎችን የሚያውቁበት በማህበራዊ ሚናዊች ስር ግንባር ቀደም የሚሆኑና የሃገርና የወገን ፍቅርን የሚያዳብሩበት ትልቅ ሚና ያለው ተግባር ነው። እነዚህ ወጣቶችም ባላቸው የእረፍት ጊዜያቸውን መስዋት አድርገው ልማትን ለማምጣትና ለአካባቢ ደህንነት ነጻ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ጉልበታቸው እና እውቀታቸዉን በተጨማሪም በጎ አመለካከትን የሚያውሉበት ስራ ሲሆን ሌሎችን ከመርዳት አኳያም በጎ ምኞትን ተላብሰው ከማህበረሰባቸው ጎን ሆነው የሚያውቁትን ሚያስተምሩበትና ከሌሎች አካላትም የህይወት ክህሎት የሚቀስሙበት ዋነኛ መንገድ ነው።
በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ረጂና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኞች በዘመቻ መልክ ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ከተሞች ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት በመሰባሰብ አካባቢያቸው የሚገኙ ሰዎችን እየደገፉ ይገኛሉ። ወጣት በጎ አድራጊዎቹ አረጋውያንን፣ ህፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን እየረዱና እየደገፉ ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ የሀይቅና የተሁለደሬ ወረዳ በጎ አድራጎት ማህበር ይጠቀሳል። ማህበሩ ከተመሠረተ ቅርብ ጊዜ ቢሆነውም ተማሪዎችን በመርዳትና ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ላይ ይገኛል። ስለ ማህበሩ የስራ እንቅስቃሴ ከቦርድ ሰብሳቢው አቶ ወንድወሰን ይመር ሰኢድ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
የማህበሩ አመሠራረትና ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ 2010 ዓ.ም ላይ በአካባቢው በሚገኙ በጎ ስራ በሚያከናውኑ ሰዎች ተመሰረተ። ቀደም ብሎ የድጋፍ ስራዎች በተናጥል ይደረጉ የነበረ ሲሆን የአረጋውያንን ቤት መጠገንና የተቸገሩ ተማሪዎችን መርዳት በግል ይከናወን ነበር። ይህን የተናጠል ስራ በጋራ ለማከናወን በመታሰቡ ውይይት ተደርጎ ማህበሩ ሊመሰረት ይችላል። ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ በሀይቅ ከተማና በዙሪያው አካባቢዎች ለሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና ዩኒፎርም እንዲሰጣቸው ተደርጓል። ይህም ስራ አሁንም ድረስ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተጨማሪም የአረጋውያንን ቤት መጠገን በተያዘው ክረምትም እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል። በተጨማሪም በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን እየረዳ ይገኛል።
ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ ዜጎች በዞን ደረጃ ቀደም ብለው የህፃናት ማሳደጊያ የነበሩ ቦታዎችን በመጠቀም ከመንግሥት ድጋፍ ጎን ለጎን የምግብና ሌሎች እርዳታዎች እየተደረጉ ናቸው። ማህበር ከተመሰረተ በኋላ በርካታ ቤቶች የታደሱ ሲሆን በተያዘው ክረምትም አራት ቤቶች የተዳሱ ሲሆን ፈርሰው መሰራት የነበረባቸውን ቤቶች እንደ አዲስ እንዲሰሩ ተደርጓል። በየቀበሌው መታደስ የሚገባቸው ቤቶች ተለይተው የተቀመጡ ሲሆን ከውጭ አገራት በሚደረጉ ድጋፎች ለመስራት እቅድ አለ።
ተማሪዎችን በመደገፍ ረገድ ትምህርት በሚጀመርባቸው ወቅቶች የሚሰጡ ሲሆን አሁን በዋናነት እየተሰራ የሚገኘው አንድ ሺ ስምንት መቶ ተፈናቃዮች በሀሐይቅ ጃሪ አካባቢ አንድ ሺ ሁለት መቶ ይገኛሉ። እንደገና መካነእየሱስ ስደስት መቶ ተፈናቃዮች ተጠልለው ይገኛሉ። ለተፈናቃዮቹ መንግሥት ከሚያደርግላቸው ድጋፍ በተጨማሪ ማህበሩ ህብረተሰቡን በማስተባበር ፍራሽ፣ ብርድልብስ፣ የቤት መገልገያ ቁሰቁሶች እንዲሁም ሌሎች ምግብ ነክ ነገሮች እየተሰጣቸው ይገኛል። በተጨማሪም ለአንዳንድ ወጪዎች ጥሬ ንዘብ ይሰጣቸዋል። ለሁሉም ተፈናቀዮች በነብስ ወከፍ በሁለት ዙር ተሰጥቷል። የኮሮና ወረርሽኝ ወደ አገሪቱ ከገባ በኋላ በየቤቱ ለሚገኙ ችግረኞች ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ በከተማው አስተዳደር በኩል በማሰባሰብ ማህበሩ የማስተባበር ስራ አከናውኗል።
የህብረተሰቡ አቀባበል
የህብረተሰቡ አቀባበል መጀመሪያ አካባቢ ላይ የተወሰኑ ጥርጣሬዎች ነበሩ። እንደሚታወቀው በጎ አድራጎት ስራ ሲባል የተወሰኑ ችግሮች ስለሚኖሩት ጥርጣሬዎች በስፋት ነበሩ። ነገር ግን በተሰሩት ስራዎች በተጨባጭ ህዝቡ ማየት በመቻሉ ማህበሩን ወደ ማመን መጥቷል። በየቀበሌው ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ በሚሰጥበት ወቅት የአካባቢው አስተዳደር የመኪና ትብብር ያደርግ ነበር። ከአካባቢው አስተዳደር ጋር መረጃ በመለዋወጥ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። የዞንና የክልል አስተዳደሩ ለማህበሩ እውቅና በመስጠታቸው በጋራ በመሰባሰብና የስራ ድርሻ በመከፋፈል ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።
በሀይቅ የሚገኙ ተፈናቃዮች ትውልዳቸው ሌላ ቦታ በመሆኑና በአቅራቢያ ዘመድ ስለሌላቸው እነሱን በመደገፍ ረገድ በጣም ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው። በበዓላት ወቅትም በሬ በመግዛት በደስታ እንዲውሉ ተደርጓል። አሁን ሁሉም ማለት በሚቻል መንገድ በጥሩ ሁኔታዎች ላይ ይገኛሉ። የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር የእንጀራ መጋሪያ ምጣዶች እንዲሰጧቸው ተደርጓል። በአልባሳት በኩል ደግሞ ከሁሉም ቦታዎች በማሰባሰብ ተሰጥቶ የተረፈውን ደግሞ አርጎባና አጣዬ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ተልኳል።
በውጭ የሚገኙ ዜጎች በሚያደርጉት ድጋፍ ዱቄትና ሌሎችም ምግብ ነክ ነገሮችን በመግዛት ለተፈናቃዮቹ እንዲሰጥ ተደርጓል። ተፈናቃዮቹ አሁን ያሉበት ሁኔታ ጥሩ ላይ ናቸው። የአካባቢው አስተዳደር አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮችን ከመደገፍ ባለፈ በራሱ ተነሳሽነት በጎ ስራዎችን ያከናውናል። የመኪና አቅርቦት፣ የፀጥታ ችግሮች ሲፈጠሩ የጥበቃና ሌሎች እገዛዎችን ያደርጋል።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ምንም አይነት እንቅፋት አልገጠመውም። በየጊዜው የህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚያድግ በመሆኑ ችግሮች የሉም። ለተረጂዎች የሚሰበሰበው ነገር በአግባቡ የሚደርስ በመሆኑ እንቅፋቶች እስካሁን የሉም። ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ገንዘብ ከውጭ አገራት ሲላኩ በአግባቡ የማዳረስ ስራ ይሰራል።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
በቀጣይ ማህበሩ በዋናነት አላማው የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ሲሆን ተማሪዎች በችግር ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ማድረግ ነው። ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን መደገፍ በቀጣይ ሊሰራበት ከተያዘው እቅድ ውስጥ ይካተታል። ቀደም ብሎ ጃሪ ህፃናት ማሳደጊያ የነበረው በአሁን ወቅት ምንም አይነት አገልግሎት የሚሰጥ ባለመሆኑ የክልሉ መንግሥት ፈቃድ ከሰጠ በድጋሚ ስራ ለማስጀመር እቅድ አለ። በማዕከሉ ውስጥ በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን የመንከባከብ አላማ ተይዞ እየተሰራ ነው። አረጋውያንን በመደገፍ የታሰበ ሲሆን ቤታቸውን በማደስና አቅም የሌላቸውን በሁሉም ነገር ለመደገፍ ታስቧል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013