በአማራ ክልል ከ23ሺህ 558 ኪሎ ግራም በላይ የጌጣጌጥ ማዕድናት ተመረቱ

አዲስ አበባ፡– የአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት በአስር ወራት 23ሺህ 558 ነጥብ ስምንት ኪሎ ግራም የጌጣጌጥ ማዕድናት ለውጭ ገበያ በመላክ ከዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ደረጃ የሕዝብና ሚዲያ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዝናው አበበ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት አስር ወራት 18 ሺህ 779 ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም የጌጣጌጥ ማዕድናት ለማምረት ታቅዶ፤ 23ሺ 558 ነጥብ ስምንት ኪሎ ግራም ማምረት ተችሏል።

ከተመረተው የጌጣጌጥ ማዕድናት ምርት 8ሺህ 768 ኪሎ ግራም በላይ ወደ ውጭ በመላክ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጸው፤ አፈጻጸሙም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 44 ነጥብ5 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም አመላክተዋል።

በክልሉ ወርቅም እየተመረተ መሆኑን ገልጸው፤ በአስር ወራት 75 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማስገባቱ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።ይህም አፈጻጸሙም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።

በክልሉ በማዕድን ዘርፉ ከሮያሊቲ ክፍያ፣ ከአዳዲስ ፍቃድና እድሳት፣ ከመሬት ኪራይና መሰል ሌሎች ክፍያዎች ገቢ የሚሰበሰብ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በተያዘው በጀት አስር ወራት 68ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ  መሰብሰቡን ገልጸዋል።ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ34 ነጥብ3 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተናግረዋል።

በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል ያሉት ኃላፊው፤ በከፍተኛ፣ በአነስተኛና በባሕላዊ በተሰጡ ፍቃዶች እና በማዕድን ነክ ፋብሪካዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፈጠሩን አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ አስር ወራት በማዕድን ዘርፉ በተሰማሩ ባለሀብቶች፣ ኩባንያዎች እና ኢንተርፕራይዞች ለ42ሺህ 136 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በቋሚነት የሥራ እድል የተፈጠረላቸው መካከል 82 ነጥብ7 በመቶዎቹ ወጣቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህም አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር 12 ነጥብ3 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ገልጸዋል።

የማዕድን ዘርፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከተሰጠው ዘርፍ አንዱ ነው ያሉት ኃላፊ፤ ይህም ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ ከመቅረፅ አንስቶ ዘርፉ ላቅ ባለ ደረጃ የሚለማበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር የቻለ መሆኑን አንስተዋል።

በክልሉ እስካሁን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ከ40 በላይ ማዕድናት (ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት፣ ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን የሚውሉ ግብዓቶች፤ የከበሩ ጌጣጌጥ፣ የኢነርጂ እንዲሁም የማዕድን ውሃ እና ጂኦተርማል ማዕድናት ) ክምችት እንዳሉ ተረጋግጧል ያሉት ኃላፊው፤ ተጨማሪ ማዕድን ሀብቶችን በጥናት ለመለየት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You