
አዲስ አበባ፦ በቅርቡ የፀደቀውን የአረንጓዴ ዐሻራና የተጎዱ መሬቶች ማገገሚያ ልዩ ፈንድ (1361/2017) አዋጅ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለመተግበር የሚያስችል የዝግጅት ሥራ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራና ሰው ሰራሽ ደን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበሩ ጠና ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ወደ ሥራ ለመግባት የአምስት ዓመት የአሠራር ፕሮግራም ማሕቀፍ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ማሕቀፉ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊከናወኑ የሚገባቸው ዝርዝር ነገሮችን የያዘ ነው ብለዋል፡፡
በዝርዝር የአሠራር ማሕቀፍ ውስጥ፤ የሚሠራው ሥራ የተጎዳ መሬት እንዲያገግም የሚከናወነው ሥራ ምን ያህል ችግኝ በምን ያህል ሄክታር፣ የሥራ እድል ፈጠራ ከሆነ ለምን ያህል ሰዎች የሚለውን ያካተተ መሆኑን ለአብነት የጠቀሱት አቶ አበሩ፤ ክልሎችም የፌዴራሉ የአሠራር ፕሮግራም ማሕቀፉን መሰረት በማድረግ የራሳቸውን የአሠራር ፕሮግራም ማሕቀፍ በማዘጋጅት ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ለልዩ ፈንዱ ተጓዳኝ በጀት በየዓመቱ እንደሚመድቡ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ አበሩ ገለጻ፤ ክልሎቹ በልዩ ፈንዱ የሚለሙ ቦታዎችን ይመርጣሉ፤ ያዘጋጃሉ፤ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ይሰጣሉ፤ በልዩ ፈንዱ በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ የሚሆኑ ማህበረሰቦችን በተለይም ሴቶችና ወጣቶችን ያደራጃሉ፣ ሕጋዊ ዕውቅና ይሰጣሉ፤ በልዩ ፈንዱ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ፅንሰ ሃሳብና የፕሮጀክት ሰነድ አዘጋጅተው ያቀርባሉ፣ ሲጸድቅም ይተገብራሉ፣ አፈጻጸማቸውን ይከታተላሉ፣ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራና የተጎዱ መሬቶች ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማውጣት ያስፈለገበትንም አቶ አበሩ እንዳብራሩት፤ የተጎሳቆለ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደኖችን በመጠበቅና በመንከባከብ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የሥነ- ምህዳር ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም ለአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች ቋሚና ተቋማዊ ሥርዓት ያለው የፋይናንስ አቅም እንዲኖር ማስቻል፣ በተጨማሪም በዘላቂነት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም እና ከአየር ንብረት ብክለት የፀዳ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተያዘው ሀገራዊ ራዕይ እንዲሳካ አስተዋፅኦ ማድረግ በማስፈለጉ የሚሉት በዋናነት ጠቅሰዋል።
የአዋጁ ዋና ዓላማ፤ የተጎሳቆለ መሬት በተፈጥሮና በመልሶ ማልማት መርህ በመታገዝ እንዲያገግም በማድረግ የደን ልማት እና የደን መልሶ ማልማትን መደገፍ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እና በዜጎች ተሳትፎ የተተከሉ ችግኞች እና ያገገሙ መሬቶች ውጤታማ እንዲሆኑና ዘለቄታ እንዲኖራቸው መደገፍ
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም