
አዲስ አበባ፡– በስፔስ ሳይንስ፣ በምድርና በከርሰ ምድር ላይ የተሟላ መረጃ ከሌለን ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጉብኝትን አስመልክተው ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በሰጡት ማብራሪያ፤ እንደሀገር በስፔስ ሳይንስ፣ በምድርና በከርሰ ምድር ላይ የተሟላ መረጃ ከሌለን ብልፅግናን ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትም ከከርሰ ምድር እስከ ስፔስ ያለውን ለልማት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን (ዳታዎች) የመለየት፣ መተንተንና ለውሳኔ በሚያመች መልኩ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
በእዚህ ደረጃ የደረጀ ተቋም የማየት ጉጉት ቢኖረንም በእዚህ ልክ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ተቋሙ በዘርፉ ትልቅ መሠረት መጣሉን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
በተቋሙ ያለንን የውሃ፣ የአረንጓዴ ሽፋንና የመሬት ሀብት መለየት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በከተሞች አካባቢ የከርሰ ምድር ውሃ ያለበትን ቦታ ለይተዋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ያሉ ሐይቆች ባለፉት አስር፣ አስራ አምስት ዓመታት የነበራቸውን መጠን እየጨመሩ ያሉትን፣ ባሉበት የቆሙትን ለምን እንደቆሙም ጭምር የመለየት ሥራ እየተሠራ እንደሆነም አመልክተዋል።
በተጨማሪም የት አካባቢ አረንጓዴ ቦታ እንዳለ ለእርሻ ምቹ የሆነ ምን ያህል መሬት እንደሆነና ያልተጠቀምንበትን ቦታ የመለየት ሥራ ይሠራል ብለዋል።
ከመሬት መረጃ ሥርዓት አንጻር ተቋሙ እያደገ ያለበት ደረጃ ካርታን ከማተምና ዲጂታላይዝ ከማድረግ አልፎ በመተግበሪያ በኩል እየሄደበት ያለው ርቀት ተስፋ ሰጪ መሆኑንም አስረድተዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሁለት ሳተላይቶችን ወደ ምህዋር መላኩን አስታውሰው፤በሚቀጥለው ዓመት ወይም ሁለት ዓመታት ውስጥ ሦስተኛውን ሳተላይት ለማምጠቅ የሚያስችል የምርምር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በሰው ሀብት ልማት ላይም ትልቅ ሥራ እየሠራ መሆኑን አስታውቀው፤ ተሰጥኦ ያላቸው ሕጻናትንም እያሰለጠ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት። ይህም በስፔስ ሳይንስ አካባቢ ላይ ቢዝነስ መሥራት ለሚፈልጉ አካላት ጭምር ግብዓት ሊሆን የሚችል ሥራ መሆኑን አመልክተዋል።
የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ አቅምን በማሳደግ መረጃዎችን ከሀገር ውስጥ አልፎ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችል አቅም መገንቱን ገልጸው፤ ከእዚህ ተቋም ሚወጣው መረጃ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተቀባይትና ተአማኒነት ያለው መሆኑን አንስተዋል።
ተቋሙ ሲቋቋም አስፈላጊነቱ ላይ ክርክሮች እንደነበሩ አስታውሰው፤ የተገኙ ውጤቶች ለትውልድ የሚሠሩ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግ ትልቅ ማሳያ እንደሆነ አብራርተዋል።
የተቋሙ ሠራተኞችም እየሠሩት ባለው ሥራ ከመኩራት አልፈው ለነገው ትውልድ መሠረት መጣልን ታሳቢ አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ለነገ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ መሠረት እየጣለች ያለችበት መንገድ ለልጆቻችን የተሻለ ዓለም እየተፈጠረ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። የዛሬ ችግርና ጉድለት የተሻለ ነገ መፍጠሪያ መሆኑን እያሰብን ተግተን መሥራት ይኖርብናል። በእዚህም ለልጆቻችን ከሌላው ዓለም ጋር መነጋገር የሚያስችል አቅም ያላት ሀገር ማስረከብ ይገባናል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከምድር እስከ ህዋ ድረስ የሚገኙ መረጃዎችን በመተንተን የምርምር ሥራዎችን የሚያከናውን ተቋም መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም