
-ከአንድ ሺህ 83 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታና የጥገና ሥራዎች ተሠርተዋል
አዲስ አበባ፡– በ2017 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ በአጠቃላይ 44 ሺህ 389 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 17 የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራዎች መገንባት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ ባለፉት 9 ወራት ከአንድ ሺህ 83 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍን ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታ እና ጥገና ሥራዎች ማከናወኑን ጨምሮ ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰሎሞን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የከተማዋ የመንገድ ኔትወርክ እንዲጨናነቅ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ የሚገኘውን የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ በእዚህም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በአጠቃላይ 44 ሺህ 389 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 17 የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራዎችን በጥራት በመገንባት የከተማዋ የትራፊክ ፍሰት እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የአዲስ አበባ ከተማ ሁለንተናዊ እድገት እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ከሚገኙ የመሠረተ-ልማት አቅራቢ ዘርፎች አንዱ የመንገድ ሴክተር መሆኑን ገልጸው፤ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በአጠቃላይ 9 መቶ 75 ነጥብ 41 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች ለማከናወን አቅዶ፤ በድምሩ ከአንድ ሺህ 83 ኪሎ ሜትር በላይ ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታና የጥገና ሥራዎች በማከናወን ከእቅድ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
አፈጻጸሙም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ41 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንም ገልጸዋል።በእዚህም በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መካከል 10 የመንገድ እና ሁለት የድልድይ ፕሮጀክቶችን ግንባታ አጠናቆ ለምረቃ ዝግጁ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።
እንደ አቶ ኢያሱ ገለጻ፤ በአገልግሎት ላይ የሚገኙ የከተማዋ መንገዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ፣ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአጠቃላይ 835 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።በአጠቃላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑት የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች ከዕቅድ በላይ የተከናወኑ ናቸው።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሥራዎችን በፍጥነትና በጥራት ለመፈፀም የሚያስችለውን የአፈጻጸም ስልት ቀይሶ በተሟላ መልኩ መተግበር መቻሉ ሥራዎች ከዕቅድ በላይ እንዲፈጸሙ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል።
የግንባታና የጥገና ግብዓቶችና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን በቅንጅትና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉ፣ እንዲሁም ቀደም ሲልም ሲሠራበት የቆየውን የምሽት ክፍለ ጊዜ የሥራ ስምሪት ይበልጥ በማጎልበት፣ የ24/7 ትግበራን በማጠናከሩ እና በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ላይ ለአንድ ወር በዘለቀ የዘመቻ ሥራ ጉዳት የደረሰባቸውን የከተማዋን መንገዶች በስፋት መጠገን በመቻሉም ለተገኘው ስኬት ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።
በአፈጻጸም ወቅት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል፤ የወሰን ማስከበር ችግር ጎልቶ የሚጠቀስ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚከናወነው የመንገድ መሠረተ-ልማት ቀድሞ በተገነባ ከተማ ውስጥ የሚካሄድ በመሆኑ የወሰን ማስከበር ሥራ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም የሚያጓትት ቀዳሚ ችግር መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በመንገድ ወሰን ውስጥ የነበሩ 438 ቤቶች፣ 299 የመብራት እና 128 የኢትዮ ቴሌኮም ፖሎችን አስነስቷል።ለእዚህም ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ ፈፅሟል።አሁንም በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ያልተፈቱ የወሰን ማስከበር ቀሪ ሥራዎች መኖራቸው፤ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተፈለገው ልክ እንዳይራመድ ተፅእኖ ማሳደራቸውንም ገልጸዋል።
ደካማ የሥራ አፈጻጸም ባሳዩ አንዳንድ የሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ሳቢያ ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ፤ በውሉ መሠረት ጥብቅ ክትትል የማድረግና የእርምት ርምጃ መውሰድ ትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በቀጣዮቹ ወራት ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል፤ በመንገዶች ላይ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የተዘጋጀው የመንገድ ሀብት አጠቃቀም መመሪያ በፍጥነት ፀድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ይደረጋል። በምንዛሪ ምጣኔ ለውጥ ምክንያት በፕሮጀክቶች ላይ የሚመጣውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቋቋም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለመስጠት ይሠራል።በተጨማሪም ለምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና ስርፀት ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ከለውጡ በኋላ ባሉት ሰባት ዓመታት ከ35 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚችሉ 150 የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን እና 49 የአውቶቡስ እና የታክሲ ተርሚናሎች መገንባታቸውም ታውቋል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም