የፍትሕ ተቋማት በሕግ ዝግጅት ሂደት የሕዝብን ተሳትፎ ለማረጋገጥ መሥራት ይገባቸዋል

አዲስ አበባ:- የፍትሕ ተቋማት በሕግ ዝግጅት ሂደት የሕዝብንና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ መሥራት ይገባቸዋል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ። የፍትሕ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ የምክክር ሥርዓት (E-consultation portal) ሥራ አስጀመረ።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የፍትሕ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ የምክክር ሥርዓት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ፤ በተለያዩ ጉዳዮች ሕጎችን የሚያዘጋጁ የመንግሥት ተቋማት በተዘጋጀው ሥርዓት አማካኝነት በረቂቅ ሕጎች ላይ ዜጎችና ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ረቂቅ አዋጆች ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ከደረሱ በኋላ በረቂቆቹ ላይ ከኅብረተሰቡ ግብአት የሚሰበሰብበት ሥርዓት ተዘርግቶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፤ዜጎች የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ በመጠቀም ግብዓት በመስጠት የሕጎችን ጥራትና ተፈፃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ውጤት የሚያስከትሉ በአስተዳደር ተቋማት የሚዘጋጁ መመሪያዎች ላይም የሕዝብንና ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማረጋገጥ ፈርጀ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ይህም ግልፅነትና ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

በተለይ የፍትሕ ተቋማት በሕግ ዝግጅት ሂደት የሕዝብንና ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ መሥራት ይገባቸዋል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ይህም የመንግሥትን አሠራር ግልፅነትና ተጠያቂነት አንዱ ማሳያ እና የሕገ መንግሥት መርሆችን ተግባራዊ ማድረጊያ መንገድ አንዱ አካል ነው ብለዋል።

በሀገራችን የሕግ አወጣጥ ሂደት የሕዝብ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሕግ ማሕቀፎች እና አሠራሮች ተዘርግተው መተግበራቸውን ጠቅሰው፤በሕግ አመንጪ ተቋማት ረቂቅ ሕጎችን ለአስተያየት ክፍት የሚያደርጉበት ኅብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት በረቂቅ ሕጎቹ ላይ አስተያየት የሚሰጡበት እንዲሁም አርቃቂው አካል ግብአቶቹን ሰብስቦ ረቂቅ ሕጎችን የሚያዳብርበት የድጅታል ሥርዓት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርአያ ስላሴ በበኩላቸው፤ባለፉት ዓመታት ሕጎች ሲወጡ ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሂደት የነበረ ቢሆንም፤ በተደራጀ መንገድ ሁሉን አቀፍ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ እንደ ውስንነት ሲስተዋል ቆይቷል።

ይህን ክፍተት ለመሙላት የፍትሕ ሚኒስቴር “በሕግ ማውጣት ሂደት የሕዝብ እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማንዋል” አዘጋጅቶ ከጥቅምት 2016 ዓ.ም መተግበር መጀመሩን አውስተው፤ በሕግ ማርቀቅ ሂደት የሕዝብ እና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማሳደግም የኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለትግበራ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ብለዋል።

ሥርዓቱ ሰፊ ተደራሽነት ለመፍጠር የሚያስችል ፈጣንና በአነስተኛ ወጪ የሚከናወን ሥርዓት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በክልል ደረጃ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉ የመንግሥት ሥራን በዲጂታል ሥርዓት ለመደገፍ እየተተገበረ ያለው ኢ ገቨርናንስ  ( e-gevernance) አንዱ መገለጫ መሆኑን አመልክተዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You