አብዛኛውን እድሜያቸውን ያሳለፉት በፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ረዘም ላለ ዓመታት በማገልገል ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ከአርባ ዓመታት በፊት ኦነግን ከመመስረት እስከ መምራት ድረስ ያገለገሉም ናቸው። በሽግግሩ ወቅትም በሚኒስትሮች ምክርቤት አባልና የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። በተመሳሳይ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ያማክራሉ። አሁን ደግሞ በግላቸው ተወዳድረው ፓርላማ በመግባት አገራቸውን ለማገልገል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በኢኮኖሚው መስክም ቢሆን የኢትዮጵያ ገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ምክርቤት አባል ናቸው። ከአገር ወጣ ሲባል እንደ ኦክስፎርድ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በምርምር ተሳትፈዋል። ስለሆነም የዘንድሮን ምርጫንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣመር እንዲያነሱልን ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ዲማ ነገዎ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አጠናቅረናል፤ መልካም ንባብ ተመኘን።
አዲስ ዘመን፡– መንግሥት ምርጫውን አስመልክቶ ፍትሀዊና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን ብዙ እንደለፋ አስታውቋል። እውነት ሂደቱ ባለው ደረጃ ተከናውኗል፤ እንዴት አገኙትስ?
ዶክተር ዲማ፡– ምርጫው በብዙ መልኩ እንደተባለው እንደሆነ በተወዳደርኩበት ቦታ ላይ ማየት ችያለው። ይሁን እንጂ ከብልጽግና ፓርቲ የተለየ ተወዳዳሪ ስለሌለበት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። ከምርጫ ቦርድ አንጻር ሲታይ ግን ባየኋቸው አካባቢዎች ጥሩ መስተንግዶ ነበረበት። ሁኔታውን በደንብ ያደራጀና ምርጫው በተአማኒነት እንዲከናወን ያደረገም ነው። በተመሳሳይ በመንግሥት በኩልም ከጥበቃ ጀምሮ ህዝቡ በሰላም መርጦ እንዲገባ በማድረጉ ዙሪያ የተለየ ተሳትፎ ነበረው።
የአየኋቸው አካባቢዎች ብዙ ተወዳዳሪ የነበረበት አልነበረም። ስለዚህም በመራጩ ህዝብ ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ ሲደረግ አላየሁም። ስለዚህም በአጠቃላይ ካለፉት የምርጫ ሂደቶች ይህ የተሻለና ወደፊትም ብዙ እድሎችን የሚሰጥ እንደሆነ እገምታለሁ። በተለይ የውድድር ሜዳውን ክፍትና ገለልተኛ ተቋማትን እየፈጠርን ከሄድን የሚቀጥለው ምርጫ ከዚህ የበለጠ ፍትሀዊና ተአማኒ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገርም መሰናክሎች አይኖሩብንም። ይልቁንም ጅማሮው ጥሩ መስመር ያሲዘናል።
አዲስ ዘመን፡– የዘንድሮ ምርጫን በተመለከተ ምን ጥንካሬና ምን ደካማ ጎኖች ነበሩት ይላሉ? በተለይ ይዘናቸው ብንጓዝ ከነበረን ስህተት እንማርባቸዋለን የሚሉትስ የትኞቹን ነው?
ዶክተር ዲማ፡– ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ እንጂ ብቸኛው አይደለም። ምክንያቱም የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫዎች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ የመጻፍ ነጻነትና የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው። በምርጫ ሲመጣ ደግሞ እንደፈለገው የመወዳደር መብትና ሙሉ ግልጋሎት የማግኘት ነጻነት ይጠቀሳል። ስለዚህም ምርጫ አገርን ለተወሰነ ጊዜ የሚያስተዳድሩ ሰዎች የምንመርጥበት ሂደት ነውና ይህንን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማድረግ ከተቻለ አንዱ ተሰራ ልንል እንችል ይሆናል። እንደሚታወቀው በአገራችን ብዙ ጊዜ ምርጫ ተካሂዷል። ነገር ግን የተካሄዱ ምርጫዎች ምን ያህል ዴሞክራሲያዊ ነበሩ? ምን ያህልስ የሕዝቡን ፍላጎት አንጸባርቀዋል? ብለን ከጠየቅን ብዙ የሚጎድላቸው ነገሮች ነበራቸው። የአሁኑ ምርጫ ግን ቀደም ሲል ከነበሩት ምርጫዎች የተሻለ እንደሆነ ማየት የቻልኩባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚያሳየው ምርጫ የውድድር መድረክ መሆኑን ነው፤ ከተወዳዳሪዎቹ ውስጥ ህዝቡ የእኔን ችግር ሊፈታ ይችላል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ የሚመርጡበት ሂደት ነው። ምን ያህል ፓርቲዎች አሉ? ምን ያህሉስ ለዚህ ተዘጋጅተዋል? ምን ያህልስ አማራጭ ለህዝቡ አቅርበዋል? ብለን ከጠየቅን ብዙ አይደለም የሚል ምላሽ ነው ያለኝ።
ሆኖም ባለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ የሽግግር ሂደት ውስጥ ነበረች ማለት እፈልጋለሁ። በተለይ ለረጅም ጊዜ አገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው አመራር ተለውጦ ሌላ አመራር ተተክቷል። እናም የተተካው አመራር ቅቡልነት ለማግኘት ወደህዝቡ መሄዱ አጠያያቂ ነገር አይደለም።
እንደእኔ አስተሳሰብ ግን ኢትዮጵያ ብዙ ውስብስብ ችግር ያለባት አገር ናት። ምርጫ ደግሞ ብቻውን እነዚህን ሁሉ የኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮች ይፈታል ብዬም አልገምትም። ምርጫ ሊፈታ የሚችለው ማን አገሪቱን ለተወሰነ ጊዜ ያስተዳድር የሚለውን ብቻ ነው። እናም በዚህ ደረጃ በአገራችን ከመንግሥት ውጪ፣ ከአስተዳደሩ ውጪ እንዲሁም ከዚያም በላይ ብዙ ውስብስብ ችግሮች አሉ። የአገረ መንግስቱ ቅቡልነት በራሱ ጥያቄ ውስጥ ያለባት አገር ናት። ይህንን ችግር ለመፍታት ግን የተወሰኑ ጅማሮዎች እንዳሉ በምርጫው በተወሰነ ደረጃ ያየን ይመስለኛል። ይህም ቢሆን በአገራዊ ውይይት መፈታት አለባቸው ብዬ የማስባቸው ጉዳዮች አሉ።
አሁን አሁን በአካባቢ ስም ሁሉ ስንጨቃጨቅ ነው የምንታየው። ለሰንደቅ ዓላማችን ሳይቀር የተለያየ ትርጉም ስንሰጥ ነው የምንስተዋለው። እነዚህ ሁሉ ችግሮች በጣም በርካታ በመሆናቸው ሰፊ የሆነ አገራዊ ውይይት ይፈልጋሉ። ውይይት ተደርጎም ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ ከተጓዝን የተፈጠሩት ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ከምርጫው በፊት የነበረው ሥራ እንዳለ ሆኖ ከዚያ የቀሩትን ምርጫው በሰላም መደረጉ ትንሽም ቢሆን መስመር ያሲዘዋል የሚል እምነት አለኝ።
በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ብዙ አይነት መሰረታዊ የሆኑ ሂደቶች አሉ። ህዝቡ በሰላም ገብቶ መውጣት መቻል፣ ኑሮውን በተደላደለ መልኩ ማሳለጥ፣ በአገር ውስጥ በነጻነት መኖር መቻልን በዋናነት ያካትታል። ለዚህ ደግሞ ምርጫ አንዱ እንጂ ብቸኛው አይደለም። እናም ከምርጫው ጋር ተያይዞ የፍትህ ስርዓቱ፣ የጸጥታ ሁኔታው፣ የጸጥታ አስከባሪዎች ሥራን በአግባቡ መስራት፣ ባለሥልጣናቱ ህግን ማክበርና ማስከበር ላይ ቁርጠኛ መሆን መቻልም ይኖርባቸዋል። በተለይም የህግ የበላይነት በሁሉም ላይ መስራት እስካልቻለ ድረስ ምርጫ ብቻውን ዲሞክራሲን ሊያረጋግጥ አይችልም። ስለሆነም ለዚህ ተግባራዊነት ሁሉም መስራት አለበት።
የአገሪቱ ዋና ዋና ተቋማት የጸጥታና የፍትህ ስርዓቱን አስፈጻሚ አካላት ወዘተ ለሁሉም ነጻና ገለልተኛ ህዝብንና አገርን የሚያገለግሉ ሆነው መዋቀር ይኖርባቸዋል። የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች መሆን የለባቸውም። ወገንተኝነታቸውን ማሳየት ያለባቸው ለህዝብ ብቻ ነው። በዚህ በኩል ደግሞ ብዙ እንደተሰራ የሚታዩ ነገሮች አሉ። ሁኔታው ሂደታዊ በመሆኑም የሥራውን ግንባታም በጊዜ ሂደት እናገኘዋለን። በሌላ በኩል ከአካሄዱ እንዳስተዋልኩት ነጻ ነው፤ ህዝቡም ምን ያህል ምርጫውን እንደፈለገው ያሳየበት ነው። በነጻነት የፈለገውን ሰው ያለምንም ተጽዕኖ መምረጥ የቻለበትም እንደነበር በነበርኩበት ሁኔታ አይቻለሁ። እንደ በፊቱ ምርጫው ብዙ ተጽዕኖ ያረፈበትም እንዳልነበር መመልከት ችያለሁ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ማስፈራራትም ብዙ አልነበረም። በብዙ መጠን ቀንሷል ብዬ አምናለሁ። ገለልተኛ ተቋማት ተቋቁመው መስራት መጀመራቸውና መሰል ነገሮቹ ሊጠናከሩ ይገባል ባይ ነኝ።
ማንኛውንም የዲሞክራሲ ስርዓት ስኬታማ ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸው ወሳኝ ሚና አላቸው። በዚህም በዘንድሮ ምርጫ ጠንካራ የሆኑ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢያስፈልጉም ብዙም አይደሉም። ለህዝቡ አማራጭ የሚሆኑ ፓርቲዎች መሆን ነበረባቸው፤ ግን አገራዊነት ስለሚጎላቸው አማራጭ ሆነዋል ለማለት ያስቸግራል። ነገ ሥልጣን ላይ ያለው አካል ከወረደ እርሱን ተክተው መንግሥት መሆን የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ይገባቸዋል። በዚህ ደረጃ ግን አሉ ሊባሉ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገና በሂደት ላይ ናቸው። የዘንድሮን ምርጫ በኢትዮጵያ ይካሄዱ ከነበሩት ለየት ቢያደርገውም በጠንካራ ፓርቲዎች ደረጃ ግን ድክመት ያለበት እንደነበር መውሰድ ይቻላል።
ሌላው በገዢው ፓርቲና በመንግሥት መዋቅር መካከል ምንም አይነት ድንበር አለመኖሩም እንዲሁ። ስለሆነም መንግሥት እንደ መንግሥት የሁሉም ሆኖ መቀጠል ይገበዋል። ለራሱ የሚያደላበትን ማቆም የመጀመሪያ ተግባሩ መሆን አለበት። ፓርቲም ቢሆን የተበጀተለትን ብቻ ነው እንደማንኛውም ፓርቲ መጠቀም ያለበት። ይህ ችግር በቀጣይ ይቀረፋል የሚል እምነትም አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በዘንድሮ ፓርቲ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ አላየሁም ያሉበት ምክንያት ምንድነው?
ዶክተር ዲማ፡- በእርግጥ አባባሉ ጥናት ይፈልጋል። ሆኖም በሚታየው ነገር ህዝባዊነትንና አገራዊነትን አጀንዳ አድርገው መንቀሳቀስ ላይ ከፍተኛ ክፍተት አለባቸው። አብዛኛውንም ህዝብ ያቀፉ አይደሉም። ከዚያ ይልቅ ለአካባቢያቸው ብቻ ለመስራት የተወዳደሩ ናቸው። ይህ ደግሞ ለአብዛኛው ህዝብ ጥቅም ለመስራት ይቸገራሉ። ምክንያቱም አብዛኛውን ህዝብ አባል አድርገው አልተንቀሳቀሱም። ታችኛውን ህዝብም ያዩ ናቸው ለማለት ያስቸግራል።
ይህ የሆነው በሁለት ምክንያት ሲሆን፤ የመጀመሪያው አላማ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከአሰራር አንጻር ያዳበሩት ነው። እናም አላማቸውን የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ማድረጋቸውና አስተሳሰብና ጥቅሙም ለእነዚህ ህዝቦች ብቻ እንዲሆን መፈለጋቸው ሁሉም ህዝብ በእኩል ደረጃ እንዳይመርጣቸው፤ እንዳያምንባቸውና ነገ መንግሥት ሆነው እንዲቀጥሉ እንዳይሽታቸው ሆነዋል። በተጨማሪ ጉልበትና አቅምም ለራሳቸው ጭምር እንዳይሆኑ ውስንነት ያለባቸው መሆኑ ጠንካራ አይደሉም አስብሏቸዋል። በእርግጥ በአገሪቱ በሙሉ ለመደራጀትና ለማደራጀት ኢኮኖሚያዊ አቅም ግድ ነው። በመሆኑም አብዛኞቹ ይህንን ስለሌላቸውም ጥንካሬያቸው ተፈትኗል ብዬ አስባለሁ።
የእኛ አገር ፓርቲዎች በግለሰቦች አካባቢ የተደራጁም ናቸው። በአላማና በፕሮግራም ተወዳጅተው ውስን በመሆናቸው ሰፊውን ህዝብ አይተው እንዳያሳትፉት አድርጓቸዋል። እናም ይህም ተጽዕኖ ፈጥሮባቸው ነው ጥንካሬያቸው የተቀማው። በእርግጥ እነዚህ ችግሮች በትክክል መጠናትና እልባት ማግኘት ይኖርባቸዋል። የፓርቲዎች ችግር ይህ ነው የሚለውም በጥናት መመለስ አለበት። ከዚያ በቀጣይ መንግሥት የሚሆነው አካል ይህንን አስቦ የሚገዳደረው ፓርቲ መፍጠር ላይ ለመስራት ይችላል። ምክንያቱም ይህ ምላሽ ጠንካራ ፓርቲን ያፈራለታል። ጠንካራ ፓርቲ ሲኖር ደግሞ ጠንካራ አገርን፣ ጠንካራ መንግሥትን መመስረት ቀላል ነው። በተመሳሳይ የመንግሥትን ችግር ፈልፍሎ ለማውጣትና አቅም ለመሆን ያግዛል። ስለዚህም የፓርቲዎች ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ ከኦነግ ፓርቲ መውጣትዎ እንደተናገሩት ሆኖ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለምን በጋራ ለመሳተፍ አልፈለጉም? የእኔን ሀሳብ የሚመጥን ፓርቲ የለም ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዲማ፡– አዎ። አሁን ባለው ሁኔታ መቼም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጠውና መኖር ያለበት አገር ነው። ለዚህ ደግሞ የሚመራ መንግሥት መኖር አለበት። ስለዚህም ከብልጽግና ውጪ ሌሎቹ ፓርቲዎች ላይ በአብዛኛው በሚባል ደረጃ እንደአገር የተወዳደረ የለም። በእርግጥ በአሁኑ ሰዓት አገሪቱን ሊያስተዳድር የሚችለው ብልጽግና ፓርቲ ነው ብዬ አምናለሁ። ሆኖም ብልጽግናን ደግሞ በአሁኑ ሰዓት መደገፍም፣ አባል መሆንም አልፈልግም። ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያቶች አሉኝ። ለአብነትም ከኢህአዴግ የወረሳቸው ጸባዮች ያሉት፣ የተደራረቡበትና ቀስ በቀስ በአሠራር ሊፈቱትም ላይፈቱትም የሚችሉት ችግር ያለበት በመሆኑ ፓርቲ ውስጥ ተካትቼ ስራዎችን ለመስራት አልፈለኩም።
ብዙ ማረም ያለበት ችግሮች ስላሉም ለእኔ በሚስማማኝ ደረጃ ላይ ስላልተቀመጠ ከእርሱ ጋር ለመስራት ፍላጎቱ የለኝም። ወደፊት ለእኔ በሚመችና አሰራሩን ካሻሻለ ልቀላቀል እችል ይሆናል። በተለይ ከህዝቡ ጋር ያለውን ቁርኝት ካጠናከረ ፣ በቀበሌ፣ በወረዳ ታችኛው ክፍል ድረስ ደርሶ ህዝብን በእኩል ደረጃ የሚያስጠቅም ከሆነና ከድሮው የተለየ ሥራ ሰርቶ የሚያሳይ ሆኖ ካገኘሁት የእኔም አስተሳሰብ ነውና ልቀላቀለው እችላለሁ። ግን ብዙ ሂደቶች ይኖሩታልና በሂደት የምናየውም ይሆናል። እስከዚያ ግን በግል የማበረክተው እንደሚበልጥ ስላመንኩ በግሌ ለመወዳደር ወስኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በግል ተወዳድሮ ፓርላማ መግባት ምን ያህል ተሰሚነትን ያላብሰኛል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ዲማ፡– በግል የሚሰራ ሥራ የመንግሥትን ያህል ለማበርከት እንደማይቻል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም እንደሚባለው በአስተሳሰብ ብለይም ለአገር ጥቅም የቻልኩትን በማድረግ አምናለሁና በፓርላማም ሆነ በአካባቢዬ እንዲሁም በአገራዊ ሥራዎች ላይ በተጠራሁበት ሁሉ አግዛለሁ። እኔን በሚመጥኑ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍም የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ። አሁን መንግሥት የሚመሰርተው አካል ብልጽግና እንደሆነ ይታወቃል። ከእርሱ ጋር በመሆን ለአገር የሚበጀውን ለማድረግም ዝግጁ ነኝ። ከመንገድ ወጥቷል ብዬ ሳስብ ደግሞ ሂስ በማድረግ ለማረም መሞከሬንም እቀጥላለሁ። በተለይም የሚቀጥለው አምስት ዓመት ብዙ ፈተናዎችን የምንጋፈጥበት ጊዜ ነውና ያንን ለማለፍ የሚያስችሉ ነገሮችን ሁሉ ለማድረግም ተዘጋጅቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ በግል ተወዳድሬ ፓርላማ ከገባሁ ለአገሬ ምን አበረክታለሁ ብለው አስበዋል?
ዶክተር ዲማ፡– ፓርላማው የተለያዩ ፓርቲዎችን የሚያካትት በመሆኑ ብዙ ፍጭትና አዲስ ሀሳቦች ይመጣበታል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ደግሞ ሆነ ማለት አምስት ዓመቱ የዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማምጣትና ወደዚያ የሚደረገውን ጉዞ ያጠናክረዋል። በተጨማሪ በሀሳብ የማያሳምን ሰውም የሚናገርበት መድረክ አይሆንም ብዬ አምናለሁ። አቅጣጫችንም ቢሆን የሚወሰነው በዚህ ጊዜ ላይ ነው። ስለሆነም በተሰጠኝ ጊዜ የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግም ነው የተዘጋጀሁት።
እኔ ጋር ብዙ እውቀት አለ፤ በፖለቲካው አለምም ብዙ ልምድ አካብቻለሁ። ስለዚህም ይህንን ለማጋራትም ነው በግል የተወዳደርኩትና ሳልሰስት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለኝን ለመስጠት የተነሳሁት። በእርግጥ ይህንን አበረክታለሁ የምለው ነገር የለም። ምክንያቱም ተግባር ከወሬ ይቀድማል። እናም እኔ ወደፊት በምሰራው ሥራ አገሬ እንዲያየኝ ነው የምፈልገው። የኢትዮጵያን የፓርላማ አሰራርም በደንብ ስለማላውቀው ብዙ ነገር ማየትና አዲሱ የሚገባውን የፓርላማ መድረክ መዋሀድ ያስፈልገኛል። እኔ የሰራሁት የሽግግሩ መንግሥት ምክር ቤት ውስጥ ነው። ያ ደግሞ ከዚህኛው በብዙ መንገድ የሚለይ ይመስለኛል። ምክንያቱም በህዝብ የተመረጠ አይደለም። በፖለቲከኛና በተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አማካኝነት የሆነ ነው። እናም ወደፊት የመጀመሪያ ሥራዬ የሚሆነው አሰራሩን መልመድ ነው።
በኮሚቴነት የሚቀመጡት አካላት የአስፈጻሚውን አካል መመርመር ነው። እናም በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ለማገልገልም ፍላጎቱ አለኝ። ከዚያም በላይ የሚሰጠኝ ነገር ካለ ለመስራት ዝግጁ ነኝ። ዋናው አላማዬም ህዝብንና አገርን ማገልገል በመሆኑ ለእርሱ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ እከፍላለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ከተሸናፊው አካል ምን ይጠበቃል፤ ምንስ ማድረግ አለባቸው ይላሉ?
ዶክተር ዲማ፡– መሸነፍ ጥሩ እድል ይሰጣል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ቀጣይ ድክመታቸው ላይ የሚሰሩበትን እድል ያቀዳጃል። በተወሰነ ደረጃም ያሸነፉ ቢሆኑ እንዲሁ ሙሉ ለምን አላሸነፍንም የሚለውን ወደኋላ ተመልሰው እንዲያዩ ጥሩ በር የሚከፍት ነው። ምን ብናሻሽል ጠንካራ ፓርቲ እንሆናለን የሚለውን እንዲያዩም መንገድ ይጠርግላቸዋል። ለሚቀጥለው ምርጫም ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ያግዛቸዋል። መዋሀድ ካለባቸውም ተዋህደው ለአገር ማገልገል ምን እንደሆነ እንዲረዱም ያደርጋቸዋልና ይህንን በሚገባ ማመን አለባቸው። ይህ የዝግጅት ጊዜ እንደሆነም መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ የኢትዮጵያ ገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ምክርቤት አባል ነዎትና ይህ ምክር ቤት አሁን ላይ ምን አይነት ቁመና ላይ እንዳለ ትንሽ ቢሉን?
ዶክተር ዲማ፡– ገለልተኛ ምክርቤቱ ልዩ ልዩ አገሮች ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች የተውጣጡ ናቸው። ምጥጥኑ ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያንንም ያካትታል። እናም እስከ አሁን ብዙ ስብሰባዎችን አድርጓል። በእነዚህ ስብሰባዎችም የኢኮኖሚ አማካሪ መዋቅሩን ለኢትዮጵያ በሚመች መልኩ እያዘጋጀ ይገኛል። ውስጠ ደንቡን፣ አመራሩንና የመሳሰሉትን የማደራጀት ሥራ ላይም ነው። በዚህም ገና ወደዋና ስራው አልገባም።
ይህ ምክርቤት በውጪው አለም የተለመደና ብዙዎችን ከችግር ያላቀቀ ነው። በተለይም የመንግስትን አቅጣጫ በመምራት በኩል ከፍተኛ ሚና አለው። ዋና ጥቅሙም ለመንግሥት ገለልተኛ የሆነ አስተያየትና ምክረሀሳብ መስጠት ነው። ገለልተኛ የሆነ ፖሊሲ፣ እቅድና አማራጮችን የሚሰጥም ነው። ስለዚህም ምክርቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመ በመሆኑ ለኢኮኖሚው ግንባታ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። ይህ የሚሆነው ግን መንግሥት በትክክል ከተጠቀመበት ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ፈታኝ ነው። በተለይም ምዕራባውያን የሚያደርጉት ጫና ከፍተኛ ሆኗል። ከዚህ ለመውጣት ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ዶክተር ዲማ፡– የውጪውን ፈተና ለመቋቋም የቤት ሥራችንን መጨረስ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ከውስጥ ያለውን መፍታትና የውስጥ ጥንካሬን መጎናጸፍ ወሳኝ ነው። ምክንያቱም የውስጥ ጥንካሬ የውጪውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ወሳኝ የሆነ ሚና አለው። ስለዚህም ውስጣችንን ለማጠናከር ቆርጠን መነሳት አለብን። የጋራ ቤታችንን በጋራ ማጽዳትም ያስፈልገናል። የውስጥ ችግሮችን በጊዜው መፍትሄ መስጠትም ይገባል። የውጪ ተጽዕኖ የሚመጣው የውስጥ ቀዳዳ ሲያገኝ በመሆኑ የከፈትነውን ቀዳዳ መድፈን ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲያርፍ እየሰሩ ናቸው። አሁን ደግሞ ሁለተኛ ዙር ሙሌቱ ተጀምሯል። ይህንን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ዲማ፡– ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብቷ በዓለማቀፍ ህግ ጭምር የተረጋገጠ ነው። እስከአሁን አቅሙ ስለሌላትም አላደረገችውም እንጂ መብቱ እንደነበራት ማንም ይረዳል። አሁን ደግሞ በህዝባችን አቅም እየገነባን በመሆኑ ቶሎ ለማለቁ መፋጠኑና በተያዘለት ጊዜ የፈለግነውን ማድረግ መብታችን ነው። እንደውም እስካሁን መቆየቱ ለዚህ ሁሉ ተጽዕኖ አጋልጦናል። እንደተጀመረ ወዲያው ቢያልቅ ኖሮ ጉዳያችን ሌላ ይሆን ነበር። አዲስ ስራና አዲስ ተስፋ። ስለሆነም አሁንም ቢሆን ከመጨረስና ግድቡን ከመሙላት የሚያግደን ማንም ሀይል ሊኖር አይገባም።
እኛ እየሰራን ያለነው የታችኛዎቹን ተፋሰስ አገሮች በሚጎዳ መልኩ አይደለም። ዓለም አቀፉ ህግ ከሚፈቅደው በላይ በእኛ ገንዘብ ለምቶ በጋራ እንጠቀም በሚል ነው። ይህንን ደግሞ ማንም የሚቃወመው ሳይሆን ይበልጥ የሚጨበጨብለትና የሚደግፈው ሊሆን ይገባዋል። በተለይ የግብጽ ምልከታ እጅግ የሚያስገርምና እኔ ብቻ ነኝ በዓባይ ላይ ሥልጣን ያለኝ፣ ያለኔ ፈቃድ የመጠቀም ምንም መብት የላቸውም፤ ምንም ነገር ከፈቃዴ ውጪ መስራት የለባቸውም ባይነት የሞላበት ነው። የዓለም አቀፍ ህግ እንኳን በማይደግፈው ሁኔታ መንቀሳቀስ ደግሞ የሚያዋጣ አይደለም። ድሮ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ጊዜ የተከፋፈለ የውሃ መጠን እንድትነጠቅ ስለማትፈልግም ነው ችግር እየፈጠረች ያለችው። ይሁንና የዚህን ጊዜ ሌላውን ያላካተተችበት ስለነበር ደግሞ ፍትሀዊ ነው ሊባል አይችልም። ስለሆነም የማያዋጣውን ያዋጣል ብላ መንቀሳቀሷን ብታቆም ይበጃታል።
ግብጽ የተለያዩ አገራት መንግሥታት አጠገቧ እንዲቆሙ የተለያየ ተግባር ስትፈጽም ቆይታለች። በተለይ ደግሞ ያለውን እውነት በማዛባት ታቀርባለች። ኢትዮጵያ ግብጽ ውሃ እንዳታገኝ አድርጋለች በሚልም ጭምር ነው እውነትን አዛብታ የምታቀርበው። እንደሚታወቀው ግብጽ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ከእኛ የተሻለ ሰዎች አላት። ስለሆነም የፖለቲካውን ተጽዕኖና በእኛ በኩል የመጣባትን ችግር ለመፍታት የቻለችውን ሁሉ እንድታደርግ ሆናለች። ነገር ግን የቱንም ያህል ከምዕራባውያን አገራት የተሳሰረች ቢመስልም የትኛውም የዓለም አቀፍ ህግ ግን የአባይን ውሃ ለግብጽ ነው የሚል የለም። ስለሆነም ግብጽና ሱዳን የቱንም ያህል ተጽዕኖ ለመፍጠር ቢጥሩም ኢትዮጵያን በሀብቷ እንዳትጠቀም ለማድረግ አይቻላቸውም። ይህን ለማድረግ መብትም ችሎታም የላቸውም።
እንዲህም አይነት ውጣ ውረድ ሊመጣ የቻለው በኢትዮጵያ በኩል መሰራት የተገባው ስራ ባለመሰራቱ ነው። ከእርሷ ጎን ናቸው በሚባሉ አገራት ላይ እንኳን እውነታውን በመግለጽ ተጽዕኖ ማሳደር ስንችል ስራ ግን አልተሰራም። ስለዚህም በኢትዮጵያ በኩል አንዳንድ ድክመቶች መኖራቸው አይካድም። ከዚህም አንዱ በውጭ ግንኙነት ላይ ብዙ ያልተሰራ ስራ መኖሩ ነው። በመሆኑም እሱ ላይ ጠንከር ያለ ስራ መስራት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ በውጭ አገር የተሰማሩ ዲፕሎማቶቻችን ዋና ስራቸው የአገራችንን ጥቅም ማስጠበቅ ነውና በዚህ ላይ በአግባቡ መስራት ያስፈልጋል።
ከሱዳን ጋር በተያያዘ ግን ጊዜያዊ ክስተት ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ለረጅም ጊዜ ግድቡን ስትደግፍ ቆይታለች። ግድቡ ከኢትዮጵያም በላይ ለሱዳን እንደሚጠቅማት ትረዳለችም። ከጎርፍ አደጋ፣ ከመስኖ ችግር የሚታደጋትም ይህ ግድብ እንደሆነ ታምናለች። እናም ይህንን መመለስ የምንችለው የውስጣችንን ቀዳዳ በመድፈንና ኃይላችንን በማጠናከር ስለሆነ ሁላችንም ለዚህ መረባረብ ያስፈልገናል። በዲፕሎማሲያዊ በኩል የምናደርገውን እንቅስቃሴም ማጠናከር ይገባል። በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሚሰሩ ሥራዎችንም ለይቶ ማከናወን ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በአጠቃላይ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ትንሽ ቢሉን ?
ዶክተር ዲማ፡– በአገራችን ያለው ሁኔታ አሳሳቢ የሆኑ ነገሮች የሚታዩበት ነው። ለዚህ ደግሞ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። በተለይም የገነገነ ብሔርተኝነትን ከአገር ማጥፋቱ ላይ መረባረብ የግድ ይለናል። ብሔርተኝነት እየተስፋፋ ባለበት ጊዜ ውስጥ ህዝብ ከህዝብ ጋር እንዳይጋጭ ብዙ ሥራዎች ያስፈልጉናል። ህዝብም ቢሆን መተሳሰብ በአንድ በኩል ተቻችሎ መኖር ይጠበቅበታል። ሁላችንም ተመሳሳይ የሆነ ፍላጎት፣ አቋም ሊኖረን አይገባም። ግን ተመሳሳይ አገር አለንና ተቻችለን ችግሮቻችንን መተራረም ይገባናል። እንኳን አገር ቤተሰብም ተቻችሎ ካልኖረ ኑሮውን በሰላማዊ መንገድ ሊመራ አይችልም። በዚያ ውስጥ ደግሞ መተሳሰብንም ሊጨምርበት ይገባል። ምክንያቱም መቻቻል ብቻውን ቁርሾንም ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም መቻቻል በመተሳሰብ ሲደገፍ ቤተሰብንም፣ አገርንም ይታደጋል፤ ቀጥ ብሎ ለመቆምም ያስችላል። ስለሆነም ይህንን ልምድ ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናሁ።
ዶክተር ዲማ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013