ለኗሪዎች ምቹ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ የአንድን ከተማ ግንባታዎችና የልማት ስራዎችን በፕላንና በእቅድ ተመርቶ መስራት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል። ያደጉት ሀገራት ከተሞች ከጥንስሳቸው ጀምሮ በፕላንና በእቅድ የተገነቡ በመሆናቸው የውሃ ፍሳሾቻቸውም ሆነ የኤሌክትሪክ መስመሮቻቸው እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት መገልገያዎቻቸው ለአይን በሚማርኩ እና እንቅስቃሴን በማይገድብ መልኩ ውብ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው።
ጉዳዩ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲመጣ አብዛኛዎች መንደሮች ከፕላንና እቅድ ውጪ የተገነቡ እና የመሰረተ ልማት ቅንጅት ችግር የሚታይባቸው እንደሆኑ መታዘብ ይቻላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህን ችግር ለመቅረፍ የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማዋ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ይገልጻል። እኛም በመዲናዋ ስለሚከናወኑ የፕላን ስራዎች፣ የመሰረተ ልማት ቅንጅት ስራዎች፣ ስለቀጣይ ውጥኖች እና ተቋሙ ላይ ስላሉ ችግሮች አንስተን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር መስከረም ምትኩ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡– በመዲናዋ በሚከናወኑ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ያለው የግንባታ ክትትል በተመለከተ ስራዎቹ በአመራር ደረጃ ምን ያክል ትኩረት እየተ ሰጣቸው ነው?
ዶክተር መስከረም፡– ከለውጡ በኋላ ቀድሞ ከነበሩ እሳቤዎች በተለየ ሁኔታ የከተማዋ ፕሮጀክቶች ተሻሽለው ነው መሰራት የጀመሩት። ከተማዋ ላይ የምናያቸውና በአጭር ጊዜያት ውስጥ የተጠናቀቁ ሜጋ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ጥናት ተሰርቶላቸው እንዲገነቡ ማድረግ ተችሏል።
ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ለአብነት የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት፣ የምገባ መርሃ ግብር፣ ከተማዋን የማስዋብ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች በቢሊዮኖች ወጪ የተደረገባቸው ግንባታዎች ሲከናወኑ የአመራሩ ክትትል ከፍተኛ ነው። እያንዳንዱ ስራ ሲከናወን ከፕላኑ ጀምሮ፣ ሂደቱ እና ጥራቱን በተመለከተ በየጊዜው ክትትልና ግምገማ ይካሄዳል።
በከተማዋ ልማትን ለሚያቀላጥፉ ሜጋ ፕሮጀክቶች እና የተለያዩ ስራዎች የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ በየሳምንቱም ይሁንን በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀናት በአመራር ደረጃም ቢሆን የከተማዋ ከንቲባ ጭምር የሚሳተፉበት ውይይት ይደረጋል።
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የአካል ጉብኝት በማድረግ ባለሙያዎችን የማበረታታትና አፈጻጸሞችን የመከታተል ሁኔታ አስደሳች ነው። በከተማዋ ተገንብተው ወደአገልግሎት የገቡትንም ሆነ በቀጣይ ወደአገልግሎት የሚገቡ ፕሮጀክቶችን ማየት ከተቻለ በፍጥነት እና በጥራት ለመሰራታቸው አንዱ ምክንያት ለፕሮጀክቶቹ የሚሰጠው ትክክለኛ ትኩረት መኖሩ ነው።
ከለውጥ በፊት ተጀምረው የሚረሱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ይታወቃል በአሁኑ ወቅት ግን የተጀመረ ፕሮጀክት ሁሉ በጊዜው እንዲያልቅ የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ማየት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወኑ የሜጋ ፕሮጀክቶች የታችኛው ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ህብረተሰብ ከማማከል አንጻር ምን ያክል ዜጋ ተኮር ናቸው?
ዶክተር መስከረም፡– የከተማ አስተዳደሩ የሚያከናውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ምን ያክል ዜጋ ተኮር ናቸው የምንለው በተግባር ውጤቱን በማየት ነው። ፕሮጀክቶች ለታይታ ሳይሆን በተጨባጭ ህብረተሰቡ ላይ ምን አይነት በጎ ተጽእኖ ያሳድራሉ የሚለውንም አጥንተን ነው ወደስራ የምንገባው።
ለአብነት ከማዘጋጃ ቤት እስከ ለገሃር ያለውን የመንገድ ዳር ማስዋብ እና አካባቢውን አረንጓዴ የማልበስ ፕሮጀክት እንዲሁም የመስቀል አደባባዩን ግዙፍ ፕሮጀክት ብናይ በየፕሮጀክቶቹ ስር ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል።
በከተማው እየተሰሩ ካሉት የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ መካከል አንዱ የሆነው የህዝብ ቤተ-መጽሐፍት ፕሮጀክት ግንባታ ማየት ብንችል አላማው ዜጋ ተኮር ነው። የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ የከተማው ነዋሪ በተለይ ወጣቱ ትውልድ በንባብ እራሱን እንዲያበለፅግ፣ በአስተሳሰብ እንዲቀየርና ከአልባሌ ቦታዎች እንዲርቅ ሁሉን አቀፍ መሰረተ ልማት ያለውና እጅግ ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ነው።
ማህበረሰቡን ያማከለ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በከተማ አስተዳደሩ ስር የሪፈራል አገልግሎት ጭምር የሚሰጡ ሆስፒታሎች ግንባታ እንዳለ ይታወቃል፤ ሆስፒታሎቹ ለዜጎች የጤና አገልግሎቶችን ለማዳረስ እና በህክምናው ዘርፍ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር የሚያግዙ ናቸው።
የታችኛው ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ዜጋ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ታሳቢ ተደርጎ የሚገነባ ነው። ከዚህ ባለፈ የአድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየም ፕሮጀክት፣ የዘመናዊ ገበያ ማዕከላት ግንባታ እና ሌሎችንም ፕሮጀክቶች ማየት ከተቻለ ህዝብ በብዛት የሚገለገልባቸው እና ለህብረተሰቡ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር የሚያግዙ ናቸው።
በአጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩ እየሰራቸው የሚገኙም ሆነ በእቅድ የያዛቸው የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ያማከሉ መሆናቸውን በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በመዲናዋ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን ፍላጎት ያሟሉ ስለመሆናቸው የምታረጋግጡት በምን መልኩ ነው?
ዶክተር መስከረም፡– የፕላን ኮሚሽን ልማቱ ህዝቡን ተጠቃሚ አድርጓል ማለት የሚችለው የሴክተሮችን አፈጻጸም በመከታተል ነው። ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ግብአቶችን ከተጠቃሚው ህብረተሰብ እንሰበስባለን። የደንበኛ እርካታ መመዝገቢያ መረጃዎችን እንሰበስባለን፤ በዚህ መልኩ የተወሰነውን የህዝብ ግብረ መልስ እንከታተላለን።
በዋናነት ግን ኮሚሽኑ ሰፊ የጥናት ክፍል አለው። በከተማዋ ምን ያክል የድህነት ምጣኔ አለ ምን ያህሉ ተቀርፏል?፤ ምን ያክል የመሰረተ ልማት ችግሮችን መፍታት ተችሏል?፤ ምን ያህሉንስ ተማሪ ወደትምህርት ገበታ መመለስ ተችሏል? በሚሉ ጥያቄዎች ላይ የተመሰረቱ ጥናቶች አሉን።
የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በተመለከተ የህብረተሰብ የእርካታ መጠን በሰፊው የሚያጠና የተደራጀ ክፍል አለን። ከኮሚሽኑ አጥኚ ባለሙያዎች በተጨማሪ የተለያዩ አማካሪ ድርጅቶችን በመቅጠር በከተማዋ የተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የህብረተሰብን ፍላጎት ከማሟላት አኳያ ምን ይቀራቸዋል? ምን አሳክተዋል? የሚለውን በማየት ማስተካከያ ይደረጋል።
ለአብነት ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ቤት በከተማ አስተዳደሩ ስር ሲከናወን የቆየው መንገዶችን የማስፋትና የማስዋብ ስራ ምን ያክል ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያን እና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹ መሆን አለበት የሚለውን በየግንባታዎቸ አፈጻጸም መሃል ላይ ጭምር በማየት ማስተካከያ ማድረግ ተችሏል።
ከግንባታ በኋላ ህዝብን የሚያስደስት ስራ መታየቱን ከሚመጡ ግብአቶች መረዳት ተችሏል። በአጠቃላይ ጥናትን፣ የግብአት መቀበያ ስርዓትን እና ሙያዊ እይታን በመጠቀም እንዲሁም ከየሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚመጡ መረጃዎችን በመተንተን የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡– በከተማ አስተዳደሩ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ምን አይነት ጥረት ታደርጋላችሁ?
ዶክተር መስከረም፡– ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ ፕሮጀክቶችን ብናከናውንም ዋነኛው ትኩረታችን ከጥራቱ ባልተናነሰ በጊዜያቸው መጠናቀቅ አለባቸው የሚለው ላይ ነው። አገራችን በዘርፈ ብዙ ችግሮች ተይዛ ባለበት እንዲሁም ኮቪድ በሽታ ባለበት ወቅት እንኳን ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የተደረገው ጥረት ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው።
የምገባ ፕሮጀክቶችን ብናይ ለዓመታት ታቅደው የተተገበሩ ሳይሆን ለአብነት በወራት እድሜ ታቅደው የተፈጸሙ ናቸው። ነባራዊ ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ የተከናወኑ የትምህርት ቤት ግንባታ እና እድሳቶች፣ የመስቀል አደባባዩ ግንባታ እና ሌሎችም የስራ ባህላችንን በመለወጥ ረገድ የረዱ ፈጣን ፕሮጀክቶች መካከል ናቸው። የመሳሰሉት ላይ የሚከናወኑ ስራዎችን የእቅድ አፈጻጸም ከላይ ክትትል ይደረጋል።
ፕላንና ልማት ኮሚሽኑ በበላይነት በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ተቋማት እንዲያቅዱ እና እቅዳቸው ምን ያክል አንዱ ከአንዱ ጋር የተናበበ ነው የሚለውን እናያለን። በዚህ አኳኋን ካየን አንድ የጤና ቢሮ ግንባታ ለማከናወን የያዘው እቅድ ከመሬት አቅርቦት ጋር ካለው እቅድ ጋር ምን ያክል የተጣጣመ ነው የሚለውን መልስ ሳያገኝ ዓመታዊ እቅዱም ወደተግባር አያመራም።
ለአምስት ዓመት የተለያዩ ተቋማት ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚውል ይሄን ያክል መሬት ተዘጋጅቷል ከተባለ የትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የወጣቶችና ስፖርት ማዘውተሪያ እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች በአምስት ዓመት ምን ያክል ለመስራት አቅደዋል የሚለውን በማየት የመሬት ይዘቱ እንዲያድግ ወይም ከእቅዱ ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ግብአት ይሰጣል።
በዚህ የትስስር ሂደት ነው በከተማዋ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በመናበብ እየተሰሩ የሚገኘው። ፕላን ኮሚሽን ያለተቋማት እቅድ የሚሰራ አይደለም፣ ያለ ፕላን ኮሚሽን ተሳትፎም የተቋማትም ስራ ቀልጣፋና እና ውጤታማ ሊሆን አይችልም።
በዚህ የጋራ እይታ ነው የስፓሻል ስራዎች ክንውን የሚደረገው። ፕሮጀክቶቹ በፕላናቸው መሰረት ስለመ ሰራታቸው እና አፈጻጸማቸውን በተመለከተ ክትትል በማድረግ ሊስተካከሉ የሚገባቸውን ከየተቋማቱ ጋር በጋራ እናስተካክላለን።
በየሩብ ዓመቱ የማህበራዊ ዘርፎችን ስራ እንገመግማለን፤ ከመሬት ልማት ማኔጅመንት ተቋም ጋር፣ ከመንገድ፣ ከውሃና ፍሳሽ ቢሮ እንዲሁም በተለያየ ፕሮጀክቶች ላይ ከሚሳተፉ ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡– ከተማዋን በፕላን የምትመራ ለማድረግ አዳዲስ ሰፈሮች ሲመሰረቱ በፕላንና በዲዛይን እንዲሰሩ ምን አይነት ስራ ታከናውናላችሁ?
ዶክተር መስከረም፡– የአዲስ አበባ ፕላንና ልማት ኮሚሽንን ከፌዴራል አቻ ተቋም ጋር የሚለየን ዋና ምክንያት እኛ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንንም ሚና በከተማ ደረጃ መወጣታችን ነው።
ግንባታ ፈቃድ በፕላኑ መሰረት ነው የሚሰጠው፤ ስለዚህ ፈቃዶቹ ከእኛ መስራት ይችላሉ የሚል ማረጋገጫ ሳያገኙ አይሰሩም። ከዚህ ባሻገር የአካባቢ ልማት ፕላኖችን እንሰራለን። የማስተር ፕላን ማስተግበሪያ ወይም የመዋቅራዊ ፕላን ማስተግበሪያ የምንላቸውን በየቦታው እቅዳቸውን መሰረት አድርገው እንዲፈጸሙ እንከታተላለን።
ሌሎች ተቋማት ቤትም ሆነ መንገድ አሊያም ሌላ መሰረተ ልማት እኛ ዲዛይን ያደረግነውን ነው የሚተገብሩት። ስለዚህ አዳዲስ መንደሮችም በሚመሰረቱበት ወቅት ከዋናው ፕላን ጋር ተጣጥመው እና ለእይታም ሆነ ለኑሮ በማይረብሽ መልኩ እንዲገነቡ ሰፊ ጥረት እናደርጋለን።
መንገዶች ምን ያህል ስፋት ይኖራቸዋል፤ የአረንጓዴ ስፍራዎች እና የመዝናኛ ቦታዎች እንዴት ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ተጣጥመው መቀመጥ አለባቸው የሚሉ እና ሌሎች በርካታ የፕላን ክንውኖች በባለሙያዎቻችን እናሰራለን።
የከተማዋን እና ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚተገበሩ እቅዶች በአዳዲስ ሰፈሮች ላይም ተግባራዊ እንዲሆን በየጊዜው ጥረት ይደረጋል። አዳዲስ የኮንዶሚኒየም መኖሪያ መንደሮችም ለዚህ አብነት ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– በከተማ አስተዳደሩ በፕላንና ልማት ኮሚሽን እቅድ መሰረት የተገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለታለመላቸው አገልግሎት ከመዋላቸው ባለፈ ምን አይነት ጥቅም እየሰጡ ነው?
ዶክተር መስከረም፡– በእውኑ ዓለም አንድ ሰው ያማረ ልብስ ለብሶ መድረክ ላይ ሲቀርብ የሚኖረው ተቀባይነትና ተጎሳቁሎ ሲታይ የሚሰጠው ግምት ይለያያል። አዲስ አበባ የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ መዲና ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የሚሰሩ የልማት ስራዎች ገጽታችንን ከመቀየር አኳያ የሚሰጡት ጥቅም አለ።
ከዚህ አንጻር የልማት ስራዎቹ በእራሳቸው ከሚሰጡት አገልግሎት ባለፈ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፍ ትኩረት ለመሳብ ይረዳሉ። ድሃ ሀገር ከመሆናችን ጋር ተያይዞ ሊሰጠን የሚችለውን ግምት በማስተካከል ረገድ በጎ ተጽእኖ ታይቶባቸዋል።
በከተማዋ የተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት እና የማስዋብ ስራዎች እንዲሁም የተለያዩ ዘመናዊ ይዘት ያላቸው ፕሮጀክቶች በውጭ ሀገራት ዘንድ ስለእኛ ያለውን አመለካከት በማስተካከል ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው።
በሌላ በኩል የቱሪዝም ገቢን ለመሳብ የሚሰጡት ሰፊ ጥቅም እንዳለ ሁሉ በከተማዋ የተለያዩ የሆቴል ዘርፎች ላይ ባለሃብቶች እንዲሰማሩ መነሳሳትን መፍጠራቸው ተረጋግጧል። ከዚህ ቀደም ሰዎች ለመዝናናት ወደዱባይ እና ሌሎች ቅርብ አገራት ለመሄድ ነው ምርጫቸው የነበረው፤ አሁን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በቂ የመዝናኛ አማራጮች መኖራቸውን በመረዳት ቱሪዝሙ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አይተናል።
ፕሮጀክቶቹ በዋናነት ደግሞ ከሚሰጡት የኢኮኖሚ ጥቅም ባለፈ የህብረተሰባችን አኗኗርና የዕለት ውሎ በማሻሻል ረገድ የሚለውጡት በጎ ነገር አለ።
ለአብነት በቆሻሻ የተሸፈነ እና ለኮቪድም ሆነ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ሊዳርግ የሚችለውን የተጨናነቀ የአትክልት ተራ ገበያ በማዘመን ህብረተሰቡ በየአቅጣጫው የሚገበያይበትን አማራጭ መስጠት ተችሏል።
በተጨማሪ የመርካቶ የከተማ አውቶቡስ መናኸሪያ ግንባታ በማከናወን ህብረተሰቡ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ አግዟል። እነዚህ ስራዎች ኗሪዎች እራሳቸውን ከተላላፊ በሽታዎች እየጠበቁ ለህክምና የሚያወጡትንም ወጪ በመቀነስ ረገድ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አለ።
የከተማዋን ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ማየት ቢቻል አካባቢያቸውን ዘመናዊ ከማድረግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል። ስለዚህ ፕሮጀክቶቹ የታለመላቸውን ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም ከሚጠበቅባቸው አገልግሎትም በላይ ጥቅም እየሰጡ ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– የ10 ዓመት ፍኖተ ብልጽግና ዕቅድ የሚል የረጅም ጊዜ ፕላን አዘጋጅታችኋል የፕላኑ ዋና ግብ ምንድን ነው?
ዶክተር መስከረም፡– የ10 ዓመት ፍኖተ ብልጽግና ዕቅድ በዋናነት ከተማዋ ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካ ደረጃ የብልጽግና ተምሳሌት መሆን አለባት የሚል ራዕይ ያለው ነው።
የብልጽግና ተምሳሌት የሚለው ሃሳብ ሰፊ ሃሳብ የያዘ እና እቅዱ ላይ በጥቂት ዓመታት ቢደረስ እንኳን የእስካሁኑ ይበቃል ተብሎ ስራዎች የሚያበቁበት ሁኔታ አይኖርም። ፍኖተ ብልጽግና እቅዱ ለሳምንት ያቀድነውን በአንድ ቀን በመስራት ከቻልን በቀሪዎቹ ቀናት ተጨማሪ መስራት አለብን የሚለውንም ከአስተሳሰብ ለማስረጽ ይረዳል።
ጥራትንም መሰረት ያደረገ ነው። ትምህርት ቤቶችን መገንባት ወይም በኢኮኖሚ እድገት አኳያ ቁጥር ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን በተጓዳኝነት ምን አይነት ተጨባጭ ልማት ተመዝግቧል የሚለውንም የሚያረጋግጥ ነው።
ጥራትን መሰረት ያደረገ እና ሁል ጊዜም የተሻለ ለውጥን ለማምጣት ጥረት መደረግ እንዳለበት የሚመራ እቅድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ከጤናና ትምህርት አገልግሎቶች በተጨማሪ ሌሎችንም ጉዳዮች ባጠቃለለ መልኩ የተዋቀረ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ነው።
ከተማዋ ለሰዎች መኖሪያነት ይበልጥ ምቹ እንድትሆን ከሰላምና ጸጥታ፣ ከትራንስፖርት አማራጭ፣ ከመሰረተ ልማት ግንባታ እና ቱሪዝም ሃብትነት የተሻለች እንድትሆን ራዕይ አስቀምጦ የሚያሳይ እቅድ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ የ10 ዓመት ፍኖተ ብልጽግና በከተማ ግብርናም ሆነ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ከብሔራዊው የ10 ዓመት ፍኖተ ብልጽግና ፕላን ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ነው። በዚህ አካሄድ አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም በሰላምና ልማት ተምሳሌት እንድትሆን ይሰራል።
አዲስ ዘመን፤ በቀጣይ ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመተግበር አኳያ በእቅድ የተያዙ እና የሚጠበቁ ስራዎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር መስከረም፡– አዎ ወደፊት ትላልቅ ስራዎችን እናከናውናለን በከተማ ደረጃ። በቅርቡ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የሆስፒታል ግንባታ አለ። ለኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራትንም መሳብ የሚችል ትልቅ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ይገነባል።
ሆስፒታሉ ለጤና ቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ ማገልገል የሚችል ነው። ለአፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር የተያዘለት ውጥን እንደሚያሳየው ግንባታው ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሰጡ የህክምና እርዳታዎችን ጭምር መስጠት እንዲችል አድርጎ ለማደራጀት ትኩረት ተሰጥቶታል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሰፋፊ የገበያ ማዕከላት (ሞል) እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በከተማዋ ይከናወናሉ። የግል ዘርፉንም ባሳተፈ መልኩ ከሆቴል ኢንቨስትመንት፣ በትምህርት ዘርፍ፣ በማምረቻ እና አገልግሎት ዘርፎች ላይ ለመስራት ከተማ አስተዳደሩ በሩን ክፍት አድርጎ እየጠበቀ ነው። በመንግስትና በግል ዘርፍ ትብብር የሚከናወኑ ግንባታዎችም ይቀጥላሉ።
በቀጣይ ጊዜ ምን አይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በአዲስ አበባ ይከናወናሉ የሚለውን ጊዜው ሲደርስ የምናሳውቅ ሆኖ በዋናነት ግን የህብረተሰቡን አኗኗር ሊያሻሽሉ የሚችል ፕሮጀክቶችን በማስቀጠል ረገድ ፊታችን ያለው መንገድ ብሩህ ነው የሚለውን ማየት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡– የከተማ አስተዳደሩ የመሬት አስተዳደር ፕላን ስራዎች በተመለከተ የህዝብ አመኔታ ኖሮበት እንዲሰራ እንደአንድ ባለሙያ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶክተር መስከረም፡– በእርግጥ የመሬት አስተዳደር ስራ የሚመለከተው የመሬት ተቋምን ነው። እንደአንድ ባለሙያ አስተያየት ለመስጠት ግን በተለይ ባለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት እይታችን፣ አሰራራችንም ሆነ አሰራራችን ሁሉ ተቀይሯል ማለት እችላለሁ።
የመሬት አጠቃቀም ሰው ተኮር መሆን አለበት፤ አሰራሩም ግልጽ መሆን አለበት በሚል ነው የሚሰራው፤ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተባሉ እስከዛሬ ተከማችተው የተቀመጡ በከተማ ደረጃ የሚገኙ የመሬት ችግሮችንም ወደመፈተሽና መፍታት ነው የገባነው።
የመሬት ተቋም ደግሞ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው አመራሩ ወደስራ ሲመጣ በቅድሚያ ተቋማዊ ለውጥ ነው ያደረገው። የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን ማስተካከል ላይ አተኩሯል። በብልሹ አሰራር የሚጠረጠሩና አላግባብ ችግር የሚፈጥሩ 400 ሰራተኞችን እንዲቀየሩ አድርጓል።
ይህም ከማህበረሰቡ በሚደርሱ ጥቆማዎች አማካኝነትና በምርመራ የተገኙትን በማቀናጀት በተከናወነ ግምገማ ነው። የተቋማዊ ለውጥ በመከናወኑ አዲስ አስተሳሰብ ያለው የሰው ኃይል መተካት ተችሏል። አሁን ተጠያቂነት ባለው መንገድ ነው የመሬት አስተዳደር ስራዎች የሚከናወኑት።
ውጤት ያመጣ አካሄድ በመሆኑ አሁንም የተቋማዊ ለውጡ ሂደት መስመሩን ሳይለቅ የሚጓዝበትን ሁኔታ ማጠናከር ያስፈልጋል። በተጨማሪ ስራዎች የህዝብ አመኔታ ኖሮባቸው እንዲሰሩ ግልጽነት ባለው መልኩ የተጠያቂነቱን አሰራር ማጎልበት ይጠይቃል።
ህዝብ የተሰራውን እያየ ያደንቃል፤ ስህተት ሲኖር ደግሞ ይናገራል። በመሬት ጉዳይም ከህዝብ ዘንድ የሚመጡ ቅሬታዎችን በአግባቡ በመፈተሽ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ላይ አፋጣኝ መፍትሄ እየሰጡ መቀጠል ይገባል። ይህን እና ተጨማሪ አቅምን የሚያጠናክሩ ስራዎችን መስራት ከተቻለ የህዝብ አመኔታውንም እያጠናከሩ መሄድ ይቻላል የሚል ሃሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ፕላንና ልማት ኮሚሽን ተቋምን ይበልጥ አላሰራ ያሉ ችግሮችና እነዚያ ችግሮች ቢፈቱለት ይበልጥ መስራት ያስችለዋል የሚሏቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ዶክተር መስከረም ፡– በተቋሙ ስር ያሉት ስራዎች በርካታ ናቸው። የማህበራዊ ፕሮጀክቶች ፕላን ስራ አለ። የስፓሻል ስራዎች አሉ እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ዘርፍ እና ሌሎችም ብዙ ስራዎች ናቸው በተቋሙ ታጭቀው የተቀመጡት።
የስራዎቹ ብዛት እንዳለ ግን የሰው ኃይልም ሆነ የፋሲሊቲ ጉዳዮች ላይ ችግር አለብን። በተጨማሪ አንድ አይነት ስራ የሚሰሩ እና የትምህርትም ሆነ የስራ ልምዳቸው ተመሳሳይ የሆኑ ሰዎች ሁለት አይነት ደመወዝ ያገኛሉ። የጂኤጂ ትግበራ ከተፈጸመ በኋላ በሲቪል ሰርቪስ የተቀጠሩ ሰራተኞች ደመወዝ ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነው።
በፊት ተቋሙ ፕላን ኢንስቲትዩት እየተባለ በሚጠራበት ወቅት በተለያዩ ፕሮጀክቶች ድጎማ የሚመጡ ገንዘቦች ሲገኙ ከፍተኛ ደመወዝ ይከፈል ነበር። ከጂኤጂው ትግበራ በኋላ ደግሞ የሚከፈለው ደመወዝ ዝቅተኛ ሆኗል። ይህ ደግሞ በርካታ ብሩክ አዕምሮ ያላቸውን ሰራተኞች እንድናጣ አድርጎናል።
መንግስት ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያየዙና በደመወዝ ጉዳዮች ላይ ያለከውን ችግር መፍትሄ ይሰጠዋል ብለን እናምናለን። በስራ ባህሪ ምቹነት እና ግብአት አቅርቦት ስራዎች ረገድ ሰራተኛውን የሚያስደስት የተመቻቸ ሁኔታ ከሌለ በእኔ እይታ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው የሚሆነው።
በውጤቱ የስራ መጓተት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መበራከት እና ሌሎችም ችግሮች እንዲፈጠሩ ያደርጋልና፤ ከበላይ አካል መፍትሄ ያሻቸዋል። በግብአት ረገድ፣ በሰው ኃይል ማጠናከር እና በጥቅማ ጥቅም ጋር ተያይዞ የሚነሱትን ማሻሻል ከተቻለ ተቋሙን አሁን ካለበትም የበለጠ እንዲሰራ በማድረግ ከተማዋን የሚፈለገውን ገጽታ እንድትይዝ ይረዳል።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ዶክተር መስከረም ፡– እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2013