ልጆቼ እንዴት ሰነበታችሁ ዓመቱ አልቆ የፈተና ወቅት ደረሰ አይደል? በዚህ የፈተና ወቅት ላይ ደግሞ ማጥናት እጅግ አስፈላጊ ነው። ፈተና አልቆ ረጅሙን የእረፍት ጊዜ ምንባብን በመለማመድ ጎበዝ አንባቢ ለመሆን እንደምትዘጋጁ አልጠራጠርም። ልጆች በሃገራችን ያሉ ትልልቅ አባቶች በየክልሉ የሚገኙ ተረቶችን አሰባስበው አንድ ላይ ሰንደውልን ይገኛሉ።
ከነዚህ ተረቶች መካከል ለዛሬ ከኦሮሚያ አካባቢ የተገኘውን ተረት በዚህ መልኩ አቅርቤላችኋለሁ። ይህን ተረት ያዘጋጁት ጋሼ ለሙ ዋጪሌ ናቸው። እናም መልካም ንባብ።
በአንድ ወቅት ከሚስቱና ከሁለት ወንድ ልጆቹ ጋር የሚኖር ጠንካራ ገበሬ ነበር። በጣም ጎበዝ ሠራተኛም ስለነበረ በጣም ሐብታም ነበር። ነገር ግን ልጆቹ ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ ይፈልግ ስለነበር እርሱና ሚስቱ እንጂ እነርሱ ምንም ሥራ እንዲሰሩ አይፈልግም ነበር።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሚስቱ ስትሞት ልጆቹ ምንም ሥራ እንዲሰሩ ስለማይፈልግ የመስኩን ሥራም ሆነ የቤቱን ውስጥ ሥራ በሙሉ ራሱ ይሰራ ነበር። ነገር ግን ጊዜ እየገፋ ሲሄድ ስላረጀና ጤናውም እየታወከ ስለሄደ እሱ ሲሞት ልጆቹ ራሳቸውን ማስተዳደር እንደማይችሉ ስለገባው በዚህ ይጨነቅ ጀመር።
እናም ስለዚህ ጉዳይ ለብዙ ጊዜ ሲያስብበት ከቆየ በኋላ ልጆቹን ጠርቶ “እንግዲህ ለእናንተ የማወርሳችሁ ብዙ ወርቅ አለ። ወርቄንም በሙሉ በመስኩ ውስጥ ስለቀበርኩት መስኩን ቆፍራችሁ ወርቁን ማውጣት የእናንተ ፋንታ ነው።” አላቸው።
ጎረቤቶቹንም ጠርቶ “እኔ የምሞትበት ጊዜ እየተቃረበ ነው። ሆኖም ልጆቼ ራሳቸውን ማስተዳደር አይችሉምና እባካችሁ ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ምግባቸውን በማብሰል ተንከባከቧቸው።” ብሎ ተማፀናቸው። እናም ጎረቤቶቻቸው ለተወሰነ ጊዜ ምግብ ሰጧቸው።
ወንድማማቾቹም ወርቁ እንዲዘረፍባቸው ስላልፈለጉ ጉዳዩን ለማንም ሰው ሳይነግሩ ቁፋሮውን በራሳቸው ተያያዙት። በዚህ ዓይነት ማሳውን አንድ በአንድ ቢቆፍሩም ምንም ወርቅ አጡ።
በዚህ ጊዜ ወንድማማቾቹ ቁጭ ብለው ሲያስቡ አንደኛው “አባታችን ያታለለን ይመስልሃል?” ብሎ ሌላኛውን ጠየቀው።
ሆኖም ሌላኛው ወንድም “አይደለም፣ አባታችን ሊያስተምረን የፈለገው ግብርና ወርቃማ ሙያ መሆኑን ይመስለኛል። ሁሉንም ማሣዎች ብንቆፍርና ብናርሳቸው ሐብታም እንሆናለን።” ብሎ መለሰለት።
እናም እንደ ሌሎቹ ገበሬዎች ማሣዎቹን ሁሉ አርሰው ስንዴ በመዝራት በጣም ሐብታም ሆኑ። ልጆች በሥራ በጉብዝና መልካምና ትልቀ ቦታ መድረስ እንደሚቻል ከዚህ ተረት እንማራለን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም