የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል በተሽከርካሪ አካል ውስጥ በረቀቀ መንገድ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ 4 መትረዬስ ጠብመንጃ እና ከ46 ሺ በላይ ጥይት መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን አስታወቀ፡፡
የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2 አ/አ A 77608 በሆነ «አቶዝ» የቤት መኪና በባለሙያ በመፍታት ወደ አዲስ አበባ የገባ 4 መትረየስ ጠብመንጃዎች ጥር 28 ቀን 2011 ዓ/ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አዲሱ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ተይዞ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የጦር መሳሪያ ዝውውሩ እየተራቀቀ መምጣቱን ኮሚሽኑ ገልፆ አሁን በቁጥጥር ስር የዋለው የጦር መሳሪያ የመኪናዋን አካል በባለሙያ በመፍታት ፍፁም በማያስጠረጥር ሁኔታ መሳሪያዎቹ ተደብቀው የተገኙ ሲሆን 2 የክላሽን-ኮቭ ጠብመንጃ ባዶ ካርታ እና የሌላ ተሸከርካሪ የፊትና የኋላ ሰሌዳ እንዲሁም 47 ሺ የአሜሪካ ዶላር እንደተያዘ ኮሚሽኑ ከላከው ዘገባ መረዳት ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ዜና ከአማራ ብሄራዊ ክልል አዊ ዞን እንጅባራ ወረዳ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 53119 አ/አ የሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ከከሰል ጋር በመጫን 46, 404 ልዩ ልዩ የሽጉጥ ጥይቶች ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ/ም ከለሊቱ 9፡20 በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አጂፕ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ከሦስት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ስጋት ውስጥ ለመጣል እየሰሩ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቆ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ህገ-ወጥ ተግባር በማጋለጥ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካለት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ተቋማቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን