
አዲስ አበባ፡- ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከመነቋቀር፣ ከስድብና ከንትርክ ወጥተው አለም በስጋት የተመለከተውን የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ በማድረግ ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ እንደነበር በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር እንዳለ አመለከቱ።
ዶክተር እንዳለ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በዘንድሮ ምርጫ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ከመነቋቆር፣ ከስድብና ከንትርክ በጸዳ መልኩ አማራጭ ፖሊሲያቸውን በጨዋነት ለሕዝብ አቅርበዋል።
ይህ አይነት ተግባር ኢትዮጵያ ለምትከተለው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እድገትም ሆነ በቀጣይ ለሚደረጉ ምርጫዎች መሰረት የሚጥል እና አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
ፓርቲዎቹ ከሁሉም አስበልጠው ለሰላም ቅድሚያ መስጠታቸው እጅግ የተፈራው የዘንድሮ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁ ሁሉንም ከስጋትና ከጭንቀት የገላገለ አኩሪ ተግባር እንደሆነ አስታውቀዋል።
በደም የተሳሰሩ፣ የጋራ ማንነት ያላቸውና ተጋብተው የተዋለዱ ሕዝቦች አብረው የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ ይበልጥ ምቹ ለማድረግና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መተባበር እንደሚገባም የጠቆሙት ዶክተር እንዳለ ፣ ልዩነትን ከመስበክ ይልቅ አንድነትን ለማጠናከር በሚደረገው ሂደት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አንዳንድ ፓርቲዎች በራሳቸውም ሆነ በሌላ አካል ጫና ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንቅፋት እንደሚኖረውም ያመለከቱት ዶክተር እንዳለ ፤ የተጀመረውን የሰላምና የልማት ጎዳና ለማሳካት ለውስጥ ችግሮች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል። ልዩነቶችን በሰለጠነ መንፈስ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የተለመደው መጠላለፍ ለማንም እንደማይበጅ ፓርቲዎቹ ተገንዝበዋል ያሉት ዶክተር እንዳለ ፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ ሰላም ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል። የሕዝቦችን ማንነት የሚያከብሩ፣ ለልማት ሰፊ ትኩረት የሚሰጡ ፓርቲዎች ዛሬም ሆነ ወደፊት አሸናፊ መሆናቸው እንደማይቀርም አስታውቀዋል።
ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንጻርም ምርጫ በተቃረበ ቁጥር በተወሰነ ቦታ ብቻ ደፋ ቀና ከማለት አስቀድመው እስከ ታች ወርደው የሕዝቡን ችግር መረዳትና አማራጭ መፍትሔ መፈለግ ጠቃሚ ነው ፤ ከአቅም መገንባትና አማራጭ ፖሊሲ ከማቅረብ አኳያም ፓርቲዎቹ በተለየ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም