የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት እስከምን?
ጦርነቱ የተጀመረው እ.ኤ.አ አቆጣጠር ግንቦት 6/1998 ነበር፤ በገበያ ስፍራነቷ በምትታወቀው የባድሜ ከተማ ነበር። ከተማዋ ወርቅ ወይም ነዳጅ አልተገኘባትም፣ ለወሬ ሰሚውም ይሁን ለወሬ ነጋሪው የጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት ይህቺ ስፍራ መሆኗ፣ ጉዳዩም ይህቺን ስፍራ መቆጣጠር መሆኑ አነጋጋሪ ነበር። ከተፈጠረው ከዚያ ፍትጊያ አልፎ በሁሉም የድንበር አካባቢዎች በከፍተኛ ፍጥነት የተስፋፋው ጦርነት በእነዚህ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ይሆናል ተብሎ የማይገመት ደም መፋሰስን አስከተለ። ከ60-80 ሺህ የሚገመት ሰው በጦርነቱ ሕይወቱን አጥቷል፣ እጅግ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ባልገመቱት አጋጣሚ ከድንበር አካባቢዎች ተፈናቅለዋል። አንዱ ሀገር የሌላውን ዜጋ ከሀገሩ ማሳደድ ቀጠለ። በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ከፍተኛ የዜጎች መንገላታት ደረሰ።
እጅግ በፍጥነት እና በቅልጥፍና ይከናወን የነበረው የድንበር ላይ የንግድ እንቅስቃሴ ውሃ ተቸለሰበት። ጦርነቱን በስምምነት ለማስቆም እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ2000 የሰላም ስምምነት ተፈርሞ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ መፍትሔ እንደሚሰጥ ቢጠበቅም ውሳኔው ባድሜን ለኤርትራ የሚሰጥ በመሆኑና ኢትዮጵያም በአተገባበሩ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጧ ሁለቱን አገሮች ሳያስማማ ቆይቷል። በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ አፈጻጸም ያልተስማሙት ሁለቱ አገሮች እንደገና ሌላ መልክ ወዳለው ፍትጊያ ገቡ። በቀጥታ ከሚደረጉ የድንበር ግጭቶች በተጨማሪ አንዱ የአንዱን ሀገር ዐማፂ በማስታጠቅም የማዝመት ሥራ መሥራት ሥራቸው አደረጉት። ያንን ተከትሎም ኤርትራ በሚቀርቡባት ዓለም አቀፍ ክሶች እና ማዕቀቦች ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገባች። በኤርትራ ያለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነጻነት ጉዳይ እንዳስመረራቸው የሚናገሩ ወገኖችም ድንበር እያቋረጡ መፍለሳቸውን ቀጥለው ነበር።
ጫናው ደግሞ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለነበር በአንድም በሌላም መንገድ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈልግ በርካታ ወገኖች ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በ መ ጨ ረ ሻ ም በኢትዮጵያ የተደረገውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ የነበረውን የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ወደ ሰላም ለመመለስ ኢትዮጵያ በወሰደችው እርምጃ መሠረታዊ ሰላማዊ ውጤት ተገኘ። በኢትዮጵያ የለውጡ መሪ ሆነው የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የማደሱ እርምጃ እጅግ አጣዳፊ እና ስልታዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በመረዳት ተግባራዊ እንቅስቃሴ አደረጉ። በመጨረሻም ለሁለት አሥርት ዓመታት ከተደረገው ጦርነት፣ የሤራ ፖለቲካ እና ውጥረት በኋላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አዲስ የሰላም ሰምምነት ተፈራርመው ግንኙነታቸውን ለማደስ እና ወደ ቀደመው ወንድማማችነት ለመመለስ እየሠሩ ነው።
ሁለቱ አገሮች በሳዑዲ አረቢያ ተገኝተው በይፋ የፈረሙት የሰላም ስምምነት አምስት አንኳር ጉዳዮችን የያዘ ነበር። ሰላም፣ ኢኮኖሚ፣ የድንበር ጉዳይ፣ አካባቢያዊ ሰላምና ትብብር፣ ሕገ ወጥነትን መከላከል ናቸው። ሰላምን ማስፈን የ መ ጀ መ ሪ ያ ው የስምምነታቸው መገለጫ በሁለቱ አገሮች መካከል የቆየውን የጦርነት ሁኔታ ሁሉ ማስቆም እና አዲስ የሰላም ዘመን ማብሰር ሲሆን ወንድማዊ ግንኙነቶችን አጠናክሮ አጠቃላይ ትብብር ማምጣት ነው። ሁለንተናዊ ትብብር ሲባልም ፖለቲካዊ፣ የፀጥታ፣ የንግድና ኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንት፣ የባህል እና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን የሚመለከቱ ናቸው።
ይሄንን ስምምነት ተከትሎ ግንኙነቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆየው ዓለም አቀፍ ማዕቀብን ማንሣት የግድ ይል ነበር። በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያ አዎንታዊ አቋም በመያዟ እና የአካባቢው አገሮችም ተመሳሳይ አቋም እንዲይዙ በማግባባት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2009 ጀምሮ በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆየው የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ዝውውር ማዕቀብ እንዲነሣ ተጠይቋል። በአሜሪካ እና እንግሊዝ ተረቅቆ በቀረበው ረቂቅም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተወያይቶ ማዕቀቡን በይፋ አንስቷል።
ኤርትራ ‹‹ለአልሸባብ የጦር መሣሪያ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ትሰጣለች›› በሚል ክስ ተጥሎባት የቆየውን ማዕቀብ ‹‹ፖለቲካዊ እርምጃ ነው›› በማለት ስታጣጥል ቆይታለች። እንዲያውም ‹‹የአሜሪካ የደኅንነት ኃይሎች ተገዳዳሪዋ ከነበረችው ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያቀናበሩት ክስ ነው›› ስትል ሁሉ ትደመጥ ነበር። በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ አራማጅ መንግሥት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም ግን ግንኙነቱ በመታደሱ የተጣለው ማዕቀብም መነሳቱ ለሁለንተናዊ ትብብር አስተማማኝ ዓውድ መፍጠሩ እየተነገረ ነው። ኤርትራ በስፋት የምትቆጣጠረው የቀይ ባህር አካባቢ ለአውሮፓ፣ ለአፍሪካ እና ለምሥራቁ ዓለም ዋነኛ መተላለፊያ በመሆኑ በሀገሪቱ የተጣለው ማዕቀብ ከየትኛውም ሀገር ጋር ለምትፈጥረው ግንኙነት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር።
ኤርትራንም ልታገኝ የምትችለውን በርካታ ጥቅም አሳጥቷት ቆይቷል። ስለዚህ የዚህ ማዕቀብ መነሣት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለሚደረገው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት መደላድል መሆኑን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ይገልጻሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለም ሁለቱ አገሮች አንዱ በአንዱ ሀገር የነበሯቸውን ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተው ሥራ ማስጀመራቸው ትብብሩን ለማፋጠን እያገዘ ነው። በተጨማሪም መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመገልበጥ ይታገሉ የነበሩ ተቃዋሚዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ኤርትራ ለአማጽያኑ የምትሰጠውን ድጋፍ አቋርጣለች፤ ድርጅቶቹም ወደ ሀገር ቤት በመግባት ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል፤ እንቅስቃሴም ጀምረዋል።
ኢኮኖሚ
ሁለቱ አገሮች የጋራ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን የማበልጸግ እና የጋራ የኢኮኖሚ ዞኖችን ለማቋቋም እያቀዱ ነው። የዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተንታኝ የሆነው ጃሬድ ጄፍሪ (Jared Jeffery) ለሲ.ኤን.ቢ.ሲ. እንደተነተነው ከሆነ የኢትዮ-ኤርትራ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል የሚያግዛት ነው። በከፈተቻቸው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች ለኤክስፖርት ገበያው ተደራሽ እንዲሆኑ የኤርትራ ወደቦች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። እጅግ ጎስቋላ በሆነው የኤርትራ ገበያ ውስጥም ምርቶቿን ለማቅረብ እያስቻላት ነው።
በተጨማሪም የወደብ ዋጋ ውድነት ኢኮኖሚዋን እንዳይጎዳ የምታጫርትበት ዕድል ሰፊ ሆኗል። የጂቡቲን የወደብ አገልግሎት ሞኖፖሊም ያረግባል። ኢትዮጵያ በዚህ የታገዘ የኢኮኖሚ መነቃቃት በወጣት ለተሞላው ሰፊ ማኅበረሰቧ የሥራ ዕድል ለማስፋት ያስችላታል። ኤርትራ የወደብ አገልግሎት ለማስፋፋት ዕድል ተፈጥሮላታል። ጂቡቲ በብቸኝነት ይዛው የነበረውን ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የወደብ አገልግሎት እና የባሕር ላይ ንግድ የማቀላጠፍ ሥራ ኤርትራም ተጋሪ ትሆናለች። ምንም እንኳን ጂቡቲ በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ ያቀናቸውን የወደብ መሰረተ ልማት፣ የባቡር ትራንስፖርት እና የመሳሰሉትን በአጭር ጊዜ ገንብታ የጂቡቲን ወደብ ትርጉም ባለው ደረጃ ጫና ልታሳድርበት ባትችልም የሰሜን ኢትዮጵያን የወደብ አገልግሎት ፍላጎት በተወሰነ መጠን በማርካት ተጠቃሚ መሆን ትችላለች። የሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በወደብ ልማት ዘርፍ ኤርትራ ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ያሳዩት ዝንባሌም ለኤርትራ ተስፋ ሰጪ ነው። የኤርትራ ወደቦች በንቃት ሥራ ላይ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በቱሪዝም ሴክተር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንድታደርግ ዜጎቿም ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተቋዳሽ እንዲሆኑ በር የሚከፍት ነው።
የኢትዮ-ኤርትራ ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ፣ ኤርትራም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተገልላ የኖረችበት ያለፈው ዘመን ካበቃ በኋላ ባለድርሻ አካላት፣ የሲቪክ ማኅበረሰቡ፣ የግል ኩባንያዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች (ጎረቤት አገሮች) ያላቸውን የኢኮኖሚ ዕድል ሁሉ አሟጠው ለመጠቀም በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የኤርትራ መንግሥት እና ህዝብ በኢኮኖሚው መስክ ለውጥ እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል። ለዚህ የሚያግዙ መንደርደሪያዎች ሁሉ እየተመቻቹ ነው፤ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን መጠቀም ጀምራለች፤ በሁለቱ አገሮች መካከል የስልክ ግንኙነት ተጀምሯል።
የሁለቱ አገሮች አየር መንገዶችም አንዱ ወደ ሌላው መብረር ጀምረዋል። የድንበር ጉዳይ ሁለቱ አገሮች የሰላም ጉዳያቸውን ከፍሬ ለማድረስ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግም ይንቀሳቀሳሉ። ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ለመተግበር ቁርጠኝነቷን ያሳየች በመሆኗ በሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለሚደረጉ የትብብር ግንኙነቶች ውሳኔውን መተግበር ምቹ ዐውድ እንደሚፈጥር ታምኖበታል። በድንበር አካባቢ የሚታየው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱም የድንበር ውዝግቡን ለመፍታት አመቺ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያል።
አካባቢያዊ ሰላም አገሮች የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢያዊ ሰላም፣ ፀጥታ እና ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ በጋራ የሚሠሩበት ዕድል እየተመቻቸ ነው። ኦማር ሞሃመድ /Omar S. Mahmo / እና መረሳ ደሱ /Meressa K. Dessu/ የተባሉ የፖለቲካ ሊቃውንት እንደጻፉት የሁለቱ አገሮች ስምምነት በአካባቢው ሰፍነው የነበሩ የግጭት አዙሪቶች እና የውክልና ጦርነቶችም እንዲረግቡ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኗል። በሶማሊያም አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ኤርትራም የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታትን ዳግም እንድትቀላቀል በር ከፍቷል። ኤርትራ እና ኢትዮጵያ መስማማታቸው ለኤርትራ እና ጂቡቲ ግጭትም ሁነኛ መፍትሄ እንደሚያመጣ ይታመናል።
የሁለቱም አገሮች ሸሪክ ለመሆን የበቃችው ኢትዮጵያ በአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ትብብሮችን በማስፋት በጂቡቲ እና ኤርትራ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ለመሻሻል የራሷን አሻራ እያሳረፈች ነው። በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ደህንነቷን በማስጠበቅ ረገድ ከኤርትራ ጋር ለመሥራት ዕቅዱ አላት። በተለይም የባህር ኃይል ኃይሏን መልሳ ለመመሥረት ለምትፈልገው ኢትዮጵያ ኤርትራ ተስፋ እንደሆነች መገመት አያዳግትም። አሜሪካን፣ ቻይናን፣ ጃፓንን እና ፈረንሳይን በመሳሰሉ ኃያላን አገሮች የባህር ኃይሎች ቅርምት ውስጥ የገባችው ጂቡቲ የኢትዮጵያ ወሳኝ የወደብ አገልግሎት ሰጪ በመሆኗ በአካባቢው የሚፈጠር ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሁሉ ስጋት በመደቀኑ፤ 11 የሚደርሱ የንግድ መርከቦቿን ለመከላከል የሚያስችል ኃይል በማስፈለጉ ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራትን የባሕር ኃይል እንደ ገና ለማደራጀት እየተንቀሳቀሰች ናት። ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቿንም እያሰፋች ትገኛለች፤ በፖርት ሱዳን፣ በሞምባሳና በበርበራ ለመጠቀም ከሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሳለች። ከኤርትራ ጋር ያለው ትብብር ደግሞ ወደቦቹን ለኢኮኖሚ ከመጠቀም ባሻገር በባህር ኃይሎቻቸውም በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ዕድል እንደሚኖር ይታሰባል።
የባሕር ኃይሉ በምስራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል እውን እንዲሆን የሚፈለገው የኢኮኖሚ ውህደት እየሰመረ ከመጣ ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚኖረው የደኅንነት እና መከላከያ ትብብር እንደሚያድግ ይጠበቃል። ሕገ ወጥነትን መከላከል በዓለም አቀፍ ስምነቶች መሠረት ሽብርን፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ እና አደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመከላከል በጋራ ይሠራሉ።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የሽብርተኞች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ይታመናል። ኢትዮጵያ የአልሸባብን እንቅስቃሴ በጽናት እየመከተች የቆየች ሲሆን፣ ከኤርትራ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት ደግሞ አልሸባብን ጨምሮ በአካባቢው አገሮች ያለውን የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴ በጋራ ለመመከት ያስችላቸዋል። ምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የጦርነት እና የድህነት ቀጠና በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ይታያል። እነዚህ ሰዎች በሕገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት የሚዘዋወሩ ሲሆን፣ በሕገ ወጥ መንገድ መንቀሳቀሳቸው ደግሞ የህግ ከለላ እንዳያገኙ እያደረገ ነው። በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩት ሰዎች ለጉልበት ብዝበዛ እና ለወሲብ ጥቃት እየተጋለጡ ናቸው።
የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ካለባቸው ከፍተኛ የሥራ ዕድል ጥማት የተነሳ በሕገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ለሕገ ወጥ ዝውውሩ ሰለባ ናቸው። ብዙዎቹ ወደ ባህረ ሰላጤው አገሮች እና ግብጽ የሚያመሩ ናቸው። በዚያም ለስቃይ እና እንግልት እየተዳረጉ ነው። ለአጋቾች የሚዳረጉ፣ ለሽብር ቡድኖች የሚመለመሉ ወጣቶችን ቁጥርም ለመቀነስ በዚህ ረገድ የሚሠራው ሥራ አመርቂ እንዲሆን ይፈለጋል። ይሄንን ዓይነት የሀገራቱን ደህንነት እና ክብር የሚነካ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ተስማምተዋል። አደንዛዥ ዕፅ ሌላው የምሥራቅ አፍሪካ ራስ ምታት ነው።
ምሥራቅ አፍሪካ የሄሮይን፣ ካናቢስ እና ኮኬኛን ዋነኛ መተላለፊያ ሆኗል። ለእስያ፣ ለአውሮፓ እና አሜሪካ ገበያዎች ለማቅረብ ዋነኛ መተላለፊያ በመሆን እያገለገለ ያለው ምሥራቅ አፍሪካ ነው። መነሻው ብራዚል፣ ፓኪስታን እና ህንድ የሆነው የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ዋነኛ መተላለፊያ ምስራቅ አፍሪካ ሆኖ መዳረሻው ደግሞ በዋናነት ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ሆንግ ኮንግ፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም መሆናቸው የተረጋገጡባቸው ተደጋጋሚ የእጅ ከፍንጅ የወንጀል ድርጊቶች በአካባቢው የተመዘገቡ በመሆኑ ከዚያ አንጻር ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የሚኖራቸውን ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ይታመናል። ስለዚህ ሁለቱ አገሮች የሚሠሩበት ሌላ የጋራ ጉዳይ ሆኗል። ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን በተመለከተም ሁለቱ አገሮች በጋራ የሚሠሩ ሲሆን፣በተለይ በኢትዮጵያ የሚታየው የእርስ በርስ ግጭት በሕገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር ምክንያት እንዳይባባስ በጋራ ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ ናቸው። ቅንጅታዊ አሠራር መዘርጋት የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ፣ የሚፈጸሙ ወሳኝ ተግባራትን ሁሉ የሚመሩ ከፍተኛ የጋራ ኮሚቴዎች እና ንዑሳን ኮሚቴዎች እየተቋቋሙ ሲሆን፣ ሁለቱ መንግሥታት በተስማሙባቸው አካሄዶች መሠረት ግንኙነቶቻቸውን መሬት ላይ ለማውረድ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። የሁለቱ አገሮች የትብብር ግንኙነት ኮሚቴ በሁለቱ አገሮች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማለትም በኢትዮጵያው ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና በኤርትራው ኦስማን ሳላህ ሞሃመድ የሚመራ ነው።
ማጠቃለያ
የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት መሰረቱ ሰፊ እንዲሆን እና ለምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ውሕደት ማዕከል እንዲሆን እየተሠራ ነው። ለዚህም የሁለቱ አገሮች የፖለቲካ መሪዎች ቁርጠኝነት እና እጅግ የሞቀ ተቀባይነት ያገኘው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። ወንድማማች የሆኑት እና ረጅሙን የታሪክ ዘመናቸውን በአንድ ሀገርነት ያሳለፉት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝቦች ሁለት አገሮች ሆነው መቆማቸው እንዳለ ሆኖ በመሀል የተከሰተው ደም አፋሳሽ ጦርነት እጅግ የሚያጸጽት ሆኖ አልፏል። ይሄንን የሚያካክስ ብርቱ ግንኙነት ለመመሥረት ደግሞ እመርታዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ ለሁለቱ አገሮች ህዝቦች ከፍተኛ ተስፋ ሆኗል። በመሆኑም ይህ ጅምር በሁለቱ ህዝቦች ጠንካራ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ እየተከናወነ በመሆኑ ግንኙነቱ የተሳካ እንዲሆን ከአሁኑ በበለጠ ፍጥነትና ትጋት መሥራት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን።
ዘመን ጥር 2011 ዓ.ም
ማለደ ዋስይሁን