በቀድሞው የወሎ ጠቅላይ ግዛት በላስታ አውራጃ በቡግና ወረዳ ‹‹ጨርጭር አቦ›› ተብላ በምትታወቅ ደብር ነው በ1957 ዓ. ም. የተወለዱት። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የገጠር ልጅ ከብት ሲጠብቁ፣ አደን ሲያድኑ፣ ሜዳ ገደሉ ላይ ሲቦርቁ ያደጉ ናቸው። አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሞላቸው በ1976 ዓመተ ምህረት ነበር የትጥቅ ትግሉን የተቀላቀሉት። የደርግን ስርዓት ለመገርሰስ በተደረገው ትግል አስተዋፅኦዋቸው የጎላ ነበር። ከኢህዴን ተራ ወታደርነት አንስቶ አሁን እስካሉበት ብርጋዲየር ጄኔራልነት ደርሰዋል።
በ2001 ዓመተ ምህረት ሚያዚያ ወር ላይ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገሃል›› የሚል ክስ ቀርቦባቸው ለዘጠኝ ዓመታት ታስረዋል- ብርጋዲየር ጄኔራል ተፈራ ማሞ። በትጥቅ ትግል ስላሳለፉት የህይወት ተመክሮ፤ ለእስር ስለዳረጋቸው ጉዳይ እና ስለ አገራችን ወቅታዊ ሁኔታ አነጋግረናቸዋል፤ ዝርዝሩን እነሆ!
ዘመን ፡- በአስራ ዘጠኝ ዓመትዎ ወደ ትጥቅ ትግል እንደገቡ ሰምተናል፤ በዚህ የእድሜ ዘመንዎ ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባት ምን አነሳሳዎት?
ጄኔራል ተፈራ፦ሁለት ነገሮች አነሳስተ ውኛል። በመጀመሪያ ደርግ ስልጣን ይዞ ወደ ተወለድሁበት አካባቢ ሲመጣ ሕዝቡና አውራጃውን ይመሩ የነበሩ ታዋቂ አመራሮች ደርግን ተቃወሙ።
ለምሳሌ በወቅቱ የአውራጃው ገዢ የነበሩት ብርሀነመስቀል ደስታ፤ የአውራጃው ብሄራዊ ጦር አዛዥ ሻለቃ ደሴ ስንቄ፤ የቡግና ወረዳ ገዢ ግራዝማች ጉግሳ አምባው፤ የቡግና ወረዳ ብሄራዊ ጦር አዛዥ ወንዴ ተፈራ ደርግን ተቃውመዋል። እነዚህ ባለሥልጣናት ሕዝቡን አደራጅተው ደርግ ወደ አካባቢያቸው እንዳይገባ ሲከላከሉ አባቴም ተሳታፊ ነበር። ‹‹ደርግ በሃይል የመጣ በመሆኑ አንፈልገውም›› በማለት ጥቃት ሰንዝረ ው የደርግን ኃይል እየመቱ የአውራጃውን ከተማ ተቆጣጠሩት፤ አውሮፕላንም አቃጠሉ። ደርግን ጠራርገው ሲያባርሩ መመልከቴ ተአምር እነደተሠራ ነበር የቆጠርሁት።
ከዚያ የደርግ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እያጠቃ መጥቶ ከተሞችን ተቆጣጠረ፤ ይሄ ሂደት በደርግ ላይ ጥላቻ አድሮብኝ ‹‹የኛ አይደለም›› ከሚል ስሜት ውስጥ ገባሁ። ይህ የመጀመሪያው ምክንያት ሆኖኝ ወደ ትጥቅ ትግል እንድገባ ገፋፋኝ። ሁለተኛ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኢህዴን/›› ይባል የነበረው ድርጅት በ1974 ዓመተ ምህረት አካባቢ ጥቃት ፈፅሞ ያደግሁበትን አካባቢ ተቆጣጠረ። በደርግና ኢህዴን መካከል ተደጋጋሚ ውጊያም ተደረገ። በዚህም ታጋዮችን የማየት አጋጣሚ ገጠመኝ። በርካታ አብሮ አደግ ጓደኞቼ ደርግን መርጠው ወደ ውትድርናው ሲገቡ እኔ በ1976 ዓመተ ምህረት ኢህዴንን ተቀላቀልሁ።
ዘመን ፡- ወደ ትጥቅ ትግሉ ሲቀላቀሉ የኢህዴን ታጋይ ብዛትና ብቃት ምን ይመስል ነበር?
ጄኔራል ተፈራ፦ እንደሚታወቀው ኢህዴን ከኢህአፓ ተገንጥሎ የወጣ ኃይል ሲሆን ከኢህአፓ የወጡ 37 አባላት ወደ ትግራይ ሄደው የመሠረቱት ፓርቲ ነው።
ኢህአፓ ሲፈርስ ኢህዴንን ከመሠረቱት ጥቂት አባላቱ ወደ ደርግ ሲገቡ ሌሎች ደግሞ ወደ ውጭ አገር ተሰደዱ። ከዚህ ባለፈ በእነፀጋየ ገብረመድኅን የሚመራና መሠረቱን በለሳ ያደረገ ሌላኛው የኢህአፓ ቡድን በቋራና መተከል አካባቢ የትጥቅ ትግል ያደርግ ነበር። ኢህዴንን የመሠረቱትና ከኢህአፓ የተገነጠሉት ሞትን ንቀው ‹‹ከትጥቅ ትግል ውጪ ምንም አማራጭ የለም›› ብለው የቆረጡ ነበሩ። እኔ በገባሁበት ወቅት ኢህዴን ሶስት መቶ አካባቢ ታጋዮች ያሉት ይመስለኛል፤ ከእኔ ጋር ስልጠና ወስደን የገባነው ደግሞ ሶስት መቶ ስልሳ እንሆናለን። ስልጠና ጨርሰን ከኢህዴን ታጋዮች ጋር ስንቀላቀል ሶስት ሀይሎች ነበር ያገኘነው። ለፕሮፓጋንዳው ሲባል ኃይሎች ተባሉ እንጂ ሶስት ሻምበሎች ብቻ ነበሩ ‹‹መትረየስ፣ ክላሽ፤ ሲመኖፍ›› የተሰኙ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። ኃይሎቹን ይመሯቸው የነበሩት የኢህዴን መስራቾች ናቸው፤ ጌታቸው ጀቤሳ /ያሬድ ጥበቡ/ አንዷን ኃይል፤ አዲሱ ለገሰ ሌላዋን ኃይል፤ አንዷን ደግሞ ኡስማን አሽኔ /እውነተኛ ስሙ ጌጡ/፤ እንዲሁም በረከት ስምኦን ሌላኛዋን ኃይል ይመሩ ነበር። እኛ ስንገባ ሌሎች ነባር ታጋዮች የኃይል አዛዦች ሆኑ። እነሸጋው ጓሌ፣ ከበደ ሙጃ፣ አያሌው እማሆይ፣ ደረጄ መፍሉስና ሌሎችም ወደ አዛዥነት አደጉ። ኢህዴን በሶስት ዓመታት ውስጥ ከሠላሳ ሰባት ታጋዮች ወደ ስድስት መቶ እድገት አሳየ። በዚህ ወቅት አምስት ኃይሎችን ይዘን በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ፈፀምን። ከሽምሽሃ ጀምረን በርካታ ቦታዎች ላይ ባደረግነው ጥቃት ድል ተጎናፀፍን። በዚህም የጎንደርንና የወሎን መሬቶች በስፋት በመያዝ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመርን፤ ኢህዴንም እየታወቀ መጣ። የተወሰኑ መሥራች አባላት ወደ ኋላ በመሆን በዋናነት የአመራር ሚናቸውን እየያዙ ሲመጡ ሌሎች ነባር አባላት ኃይሎቹን እየመሩ የወሎና የጎንደር ወጣቶች ድርጅቱን መቀላቀል ጀመሩ።
ዘመን፡- ታጋዮች ወደ ትጥቅ ትግሉ ሲገቡ የነበረው የስልጠና ሂደት ምን ይመስል ነበር?
ጄኔራል ተፈራ፦ የነበረው የስልጠና ሂደት የተሻለ የሚባል ነበር። ሽምቅ ውጊያ አንዱ ከአንዱ ልምድ እንዲወስድ እገዛ አድርጓል። ስለሆነም በትጥቅ ትግሉ የሁሉም ፋና ወጊ የሆነው ጀበሃ ጥሩ ስልጠና ይሰጥ ነበር። ሕዝባዊ ግንባርም /ሻዕብያ/ ሆነ ሕወሀት ጥሩ ወታደራዊ ስልጠና ይሰጡ ነበር። የመሳሪያ መፍታት፣ መግጠም፣ ተኩስ፣ የነፍስ ወከፍ ስልት ማጥቃት /በቀን፣ በሌሊት፣ በተለያየ የአየር ፀባይ፣ በውድድር፣ በፍጥነት/ የስድስት ወር መደበኛ ስልጠና ይሰጣል።
ዘመን ፡- በታጋይነት ዘመንዎ የማይረ ሷቸው ጀብዱዎች መቼና የት የተፈፀሙ ናቸው?
ጄኔራል ተፈራ፦ በተናጠል ለማንሳት በ1978 ዓመተ ምህረት አካባቢ ላስታ ደንበጣ ማሪያም ሲና በምትባል ተራራ ደርግ የ1977 እና የ1978 ዓመተ ምህረት ድርቅን ተከትሎ እየገባ የኛን ካድሬዎች መታና አካባቢውን ተቆጣጠረ። እኔ የነበርሁበት ዘጠኝ ሰው ያለው የኮማንዶ ቡድን ከአርማጨሆ ወደ ላስታ ሄዶ ቡግና ይንቀሳቀስ ነበር። በዚያ አካባቢ አንድ ሻምበል /ሰማንያ ሰው ያለው ቡድን/ የደርግ ሠራዊት ነበር። የዚህ ቡድን መሪ ሻምበል ባየ ይባላል። ሲና በምትባለው ተራራ ላይ መጥቶ ሰፍሮ እንደነበር እናውቃለን፤ አንድ ቀን ወደ ተራራው እየወጣን ባለንበት ወቅት መሀመድ የሚባለው አመራራችን በመነፅር ይመለከትና ሠራዊት መኖሩን አረጋግጦ ‹‹አይሆንም እንመለስ›› ይለንና ይመለሳል። እኔና ሞገስ የሚባል ሌላ ታጋይ ‹‹ባልተረጋገጠ ነገር እንዴት ኮማንዶ ይመለሳል›› ብለን የሲቪል ልብስ ለብሰን ወደፊት ቀጠልን። አብሮን አንድ አርሶ አደር አለ። በልብሳችን ውስጥ ታጣፊ ክላሽ ይዘናል። እየተጠጋን ሄደን እኔ ብቅ ስል ጠባቂውን አየሁት ‹‹ማን ነህ›› አልኩት ‹‹አንተ ማን ነህ›› አለኝ። አከታትለን ተኮስንበት ወደ ኋላ ተፈነገለ።
ያ ሻምበል ጦር እንዳለ ግልብጥ ብሎ መጣብን። ድብልቅልቅ ያለ ተኩስ ተደረገ። መጨረሻ ተቸገርን፤ ሊከቡን ሆነ። የቡዱኑን ዜና ራዴዎን ይዤ ስለነበር ዘንጉን መዝዤ የውሸት ሀሎ አልኩኝ። በርካታ ጦር እንደያዝኩኝ አድርጌ የቦታዎችን ስም እየጠራሁ ዝጋ አልኩኝ። በዚያን ጊዜ የደርግ ሠራዊት ጦር የጠራሁ መስሎት ግር ብሎ ሸሸ። እኛም ሸሸን። እኛ ስንሸሽ የተከተሉን የደርግ ጦር አባላት ነበሩ። ጦርነቱ ካለቀ በኋላ በአጋጣሚ የዚያችን ሻምበል አዛዥ አገኘሁት። ስለውጊያው ስጠይቀው ‹‹በዚያች ውጊያ ልናስቀራችሁ ነበር፤ ሬዲዮ ይዛችሁ ጦር በማዘዛችሁ ነው የተረፋችሁት›› አለኝ። ሌላኛው የማልረሳው የጋራ ጀብዱ በ1979 ዓመተ ምህረት እብእናት ላይ ባደረግነው ጦርነት የተከሰተውን ነው። ኤርትራ የነበረ የደርግ አየርወለድ ሻለቃ ጦር ጎንደር እብእናት ምሽግ ይዞ ተቀምጧል።
ይህንን ጦር መምታት ፈለገን። ወሩ የካቲት ነው። በስፍራው የነበረው የደርግ ሠራዊት ሶስት ሻምበሎች ከከተማው ደቡብ አቅጣጫ ካለች ጉብታ ዙ ሃያ ሶስት ይዘው ሰፍረዋል። ኢህዴን ከሰላሳ እስከ አርባ ሰው የያዘ ኮማንዶ አሳትፏል። በዚህ ኃይል የከተማውን ሰሜን ጫፍ ይዛ የነበረችውን አንድ ሻምበል የደርግ ጦር በአንድ ጊዜ ጠርገን መታናት። ሌሎች የኢህዴንና የሕወሀት ሠራዊት ደግሞ /በባህርዳር ከተማ የባህል ማእከል አዳራሽ የተሰየመለት ሙሉዓለም አበበ የሚመራውና የሕወሀት ሠራዊት ብርጌድ ሰባ ሶስት ተሳትፏል/ በከተማው ደቡብ አቅጣጫ የሰፈረውን የደርግ ጦር ቢሉት ቢሉት አልቻሉትም።
ከሰማንያ በላይ የወገን ኃይልን ሬሳ በሬሳ አድርጎ አልፈታም አለ። መጨረሻ ‹‹አማራጭ የለም፣ የወገን ውጊያ ተበላሸ፣ ቁስለኛ፣ ሬሳ ሳናወጣ ጉድ ስለሆንን ኮማንዶዎች ግቡ›› ተባልን። ስንገባ የደርግ ጦር የራሱ ወገን ነበር የመሰልነው። ወደ ጨበጣ መስመር ስንገባ ለይቶ ሲያውቅ ድብልቅልቅ ያለ የጨበጣ ወጊያ ተደረገ። ቁጥራችን ትንሽ ቢሆንም ፈንቅለነው ወጣን። በዘጠኝ መቶ እና በአንድ ሺህ ሠራዊት አልነካ ያለውን አየርወለድ ደርምሰን ደመሰስነው። አስራ ሁለት የደርግ ወታደሮችን ብንማርክም ሁሉም ቁስለኞች ነበሩ። እንዲሁም በ1980 ዓመተ ምህረት ሕወሀትና ኢህዴን በጋራ ሆነን የደርግን ሠራዊት ለመደምሰስ ማይጨው ያደረግነው ፍልሚያ ሌላኛው የማልረሳው ጀብዱ ነው። የሕወሀት ኮማንዶ ጦር ሙሉ ቀን ሲዋጋ ውሎ ቦታዋ አልተያዘችም፤ እኛ ሂዱ ተባልን። እዚያ ስንደርስ ‹‹ህውሀቶች ጥይትና ቦምብ ስለጨረስን የኢዴህን ታጋዮች መጥተዋል ይስጡን›› ይላሉ፤ እኛ ‹‹አንሰጣችሁም፤ እናንተ በገባችሁት እንገባለን›› አልን፤ እነሳሞራ የኑስ ‹‹ግቡ›› ብለውን እንደገባን ጠላትን ደምስሰን ድል አደረግን።
ዘመን፡- ኢህዴን መሠረቱ ህብረብሄ ራዊነትን ብሎም አንድነትን የሚደግፍ ድርጅት ሆኖ ሳለ አብሮ ይሰራ ወይም ይታገዝ የነበረው መገንጠልን አልያም አካባቢያዊነትን በሚያቀነቅኑ ድርጅቶች መሆኑ በትጥቅ ትግሉ ላይ ያስከተለው ችግር አልነበረም?
ጄኔራል ተፈራ፦ ኢህዴን ህብረብሄራዊ ድርጅት ነበር፤ ይህን ስል መሪዎቹ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ ናቸው። ኢህዴን ከኢህአፓ የተገነጠለ በመሆኑ ከደቡብ፣ ከመሀል፣ ከሰሜን፣ ከምእራብና ከምስራቅ ኢትዮጵያ የመጡ መሪዎች ያሉበት ነበር። በሂደት ደግሞ ታች ያለው ተዋጊ ሃይል የጎንደርና የወሎ ወጣት ነበር። የትጥቅ ትግሉ በተደረገባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወጣቱ ሰፊ ተሳታፊነት ነበረው። ከኤርትራ ጋር በሚደረግ ግንኙነት በሕዝባዊ ግንባር/ በሻዕቢያ/ የተማረኩ ምርኮኞች እየመጡ ህብረብሄራዊነቱን አጠነከሩት። በተቃራኒው ደግሞ በወቅቱ ኢህአፓና መኢሶን ደክመዋል። ኢህዴንም ቢሆን ሻዕብያንም ሆነ ሕወሀትን መጋፋት የሚያስችል አቅም አልነበረውም። ኢህአፓ ውስጥ እንደነበረው አይነት ኢህዴን አልነበረም። የመጀመሪያው ምሁራዊ አቅሙና አገራዊ ስነልቡናው ጫጭቶ ደክሟል። በዚህ ወቅት ለሻዕቢያም ሆነ ለሕወሀት ተፈላጊ ሆነ። ወደ መሃል አገር ለመምጣት መንደርደሪያ ሆናቸው። ሻዕቢያና ሕወሀት ከኢህዴን በፊት ብዙ ልምድ እና የሰው ኃይል ያካበቱ ከመሆኑ ባሻገር የውጭ ርዳታም ነበራቸው። ኢህዴን በሁለት እግሩ ለመቆም ገና እየተንደፋደፈ የነበረ ድርጅት ነው። ከዚህ የተነሳ አይጋፋቸውም ነበር። ለምሳሌ ሻዕብያም ሕወሀትም ‹‹የኢትዮጵያ ጉዳይ አይመለከተንም›› ብለዋል። ኢህዴን ደግሞ ‹‹የምታገለው ለሙሉዋ ኢትዮጵያ እንጂ ለጎዶሎዋ ኢትዮጵያ አይደለም›› ብሏል። ይህን ቢልም የኢህዴንን አቅመቢስነት ተረድተው ወደ መሃል ኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ጉዞ ምርኩዛቸው በመሆኑ ሳይወዱ በግድ ፈልገውታል። ወደ መሃል አገር ካልገቡ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ እጥረቶቻቸውን እንደማይፈቱ እየተረዱት መጥተዋል። ደርግም ጠብቆ የነበረው ትግሉ በኤርትራና በትግራይ ይቀራል ብሎ ነበር። በኋላ ከኢህዴን ጋር ግንባር ሲፈጥሩ ደርግም ተቸገረ። ወደ መሃል እንደሚመጡ አየ። ሕወሀትና ሻዕቢያ ህብረብሄራዊ ሀይሉ /ኢህዴን/ እንዲያድግ እና ከእነሱ ጋር እነዲወዳደር ካለመፈለጋቸው በዘለለ በእነሱ ተፅእኖ ስር እንዲወድቅ አድርገውታል። ምክንያቱም ሁለቱ ድርጅቶች ያበጡና የጎለበቱ ነበሩ።
ዘመን፡ – በ1981 ዓመተ ምህረት መሠረ ታዊ ዓላማቸው ተቃራኒ የሆኑ ኢህዴን እና ሕወሀት ኢህአዴግን ሲመሰርቱ ከሕወሀትም ሆነ ከኢህዴን አባላት ተቃውሞ አልተነሳም?
ጄኔራል ተፈራ፦ ተቃውሞ አልተነሳም፤ ቀድሞ ነገር ኢህአዴግን የመሠረቱት ተጣድፈው ነው። ምክንያቱም በ1981 ዓመተ ምህረቱ መፈንቅለ መንግሥት ደርግ ሰላሳ ጀኔራሎችን ፈጅቷል። እነዚህ ጀኔራሎች ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ታዋቂ፣ ተወዳዳሪ፣ ውጭ አገር የሰለጠኑ፣ ኢትዮጵያን በደንብ ያወቁ፣ የሱማሌ ወራሪ ኃይልን በመመከት በትክክል የመሩ፣ ሽምቅ ተዋጊውን ገትረውት የኖሩ ነበሩ። እነዚያ ጄኔራሎች ሲያልቁ እድሉ እንዳያመልጣቸው ሕወሀትና ኢህዴን ተጣደፉ። ከዚያም የኢህዴንና የሕወሀት ሠራዊት በጋራ አዲግራት ሄደን ተጨማሪ ስልጠና ወሰድን። በዚህ ወቅት ብዙ ልዩነት አልነበረንም። ልዩነት የሚያስነሳ ነባራዊ ሁኔታ አልነበረንም፤ እንዲያውም ልዩነትን ማቻቻል ነበረብን። ግንቦት ላይ መፈንቅለ መንግስቱ ተደርጎ ኢህአዴግ ክረምት ላይ ተመሠረተ። በዚህ ወቅት ወደ መሃል አገር ለማጥቃት በሙሉ ሰራዊቱ ስልጠና ላይ ነበር። ከአዲግራት ስልጠና በኋላ 1982 ዓመተ ምህረት መስከረም ላይ ማጥቃት ሰንዝረን እስከ ደብረታቦር መጥተናል።
ዘመን ፡- ነገር ግን ኢህአዴግ በ1981 ዓመተ ምህረት ተመስርቶ፤ ትግሉም ቀጥሎ በ1982 ዓመተ ምህረት አማራ ክልል ጉና ሲደረስ ‹‹ተልእኮዬን ጨርሻለሁ ከዚህ በኋላ የአማራ አገር ነው አይመለከተኝም›› ብሎ የተመለሰው የሕወሀት ሠራዊት ቁጥር በርካታ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ፤ የዓይን ምስክሮችም ይናገራሉ። ይህ ማለት የኢህአዴግ ምስረታን አለማወቅ ወይም ተቃውሞ ነበር ማለት አይቻልም?
ጄኔራል ተፈራ፦ በመጀመሪያ እንደዚሁ ስትመለከተው ወደ መሃል አገር መምጣቱን ሁሉም ፈልጎታል። ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት የሚያሟላው ነገርም ሆነ ሌላው ጉዳይ ያለው መሃል አገር ነው። የጉናው ጉዳይ የተፈጠረው ውጊያው እየከበደ በመምጣቱ ነው፤ ጦርነቱ ሲከብዳቸው ሰበብ አደረጉ እንጂ ወደፊት የመሄድ ፍላጎት ነበራቸው። ሰራዊቱ የቀድሞውን ሀሳብ እንደምክንያት ቢጠቀመውም ጦርነቱ ከብዶት ያደረገው ነገር ነው። ደብረታቦርን እኛ ከያዝነው በኋላ ደርግ 15ኛ ክፍለ ጦርን ከኤርትራ በማምጣት ልምድ ያለውን ጦር ተጠቅሞ የሕወሀትን ሠራዊት ብትንትኑን አውጥቶ ወደ ጋይንትና ወደ ጉና አባረረው። በዚህም ወደ 35 ሺህ የሚደርስ የሕወሀት ሠራዊት ደንብሮ ወደ አገሩ ሄደ። ይህ ሲባል ደግሞ ምንም የቀረ የሕወሀት ሠራዊት የለም ማለት አይደለም። ወደ አገራቸው የሄዱትም ተገደው ተመልሰዋል፤ ሕወሀት በፊት ሲቀሰቅሳቸው ‹‹እኛ ከኢትዮጵያ መገንጠል ነው ያለብን፤ ኢትዮጵያ የምትባለው የኛ አገር አይደለችም፤ ኢትዮጵያ በአማራ ፍላጎት ነው የተገነባችው›› በሚል ነበር። የህውሃት አመራሮች ወደ መሃል አገር ለመሄድ ሲያስቡ የሚፈልጉትን ነገር ጠቀሜታ ለሠራዊቱ በደንብ አድርገው አላስጨበጡትም ነበር፤ በዚህ ምክንያት የተፈጠረ አጋጣሚ ነው።
ዘመን ፡- ሂደቱ ቀጥሎ ኢትዮጵያን ያስተዳድር የነበረውን የደርግ ስርዓት በማሸነፍ ድል ተጎናፀፋችሁ፤ በዚህም ግዙፉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ተበተነ። እንዲህ መሆኑ አገርንም ሆነ ዜጎቿን እንደሚጎዳ እንደ ኢህአዴግ አልያም እንደ ጦር መሪ ውይይት አልተደረገበትም?
ጄኔራል ተፈራ፦ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት አልተደረገም፤ ነገር ግን የቀድሞው ሠራዊት ከተመታና ከተዳከመ ቆይቷል። ኤርትራ ውስጥ ናደው እዝ፣ ትግራይ የነበረው ሠራዊት፣ ቆቦ ላይ ሠራዊቱ መደምሰሱ፣ ደብረታቦር ላይ ክፉኛ መመታቱ፣ በዘመቻ ቴዎድሮስ በጎጃምና በጎንደር፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ ወለጋ በቢሊሱማ ወልቂጡማ ዘመቻ፣ በዘመቻ ዋለልኝ እየተመታ መምጣቱ ሰራዊቱ ደካማ እንዲሆን አድርጎታል። አዲስ አበባን ስንቆጣጠር መጀመሪያ የነበረውን ስም ጠብቆ የያዘ ሠራዊት አልነበረም። በፊት ጥሩ ተዋጊ የነበረው፣ ሱማሌ ላይ ድል ያደረገው ነባሩ ኃይል እየተመታ እየተዳከመ ሄዷል። ያም ሆኖ ግን የቀድሞው ሠራዊት /የደርግ/ እንዲፈርስና እንዲበተን ያደረገው ሕወሀት ነው። የሕወሀት አላማ ሰራዊቱን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ተቋማት ሙሉ በሙሉ አፍርሶ በራሱ እንደ አዲስ መስራት ነበር፤ ለዚህም አስቀድመው ሂሳብ ሰርተውበታል። ዓላማቸው አገራዊ አልነበረም። መጀመሪያውኑ አገራዊ አላማ ሲኖርህ ነው የአገርን ሀብት ለአገር እንዲውል የምታደርገው። የአገርን ሠራዊት መበተን ተገቢ አልነበረም። ልምድና የተሻለ እውቀት ያለውን በአገሩ ጉዳይ ላይ እውነተኛ ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ ማስቀጠል፤ ልምድ የሌለውንና ከገበሬ ማህበር የመጣውን ደግሞ ተገቢውን መብት በማስከበር መሸኘት ይገባ ነበር። ነገር ግን የአንድ አገር ሰዎች ሆነን እንደባእድ አገር ሰው ተያየን። በወቅቱ ሠራዊቱ በቅን ልቦና አገሩን ለማገልገል የዘመተ ነው። ሕወሀት ሁሉን ነገር ከበላይ ሆኖ መቆጣጠሩ የራሱ ዓላማ ብቻ እንዲንፀባረቅ አስገድዷል። አገራዊ ዓላማም ስላልነበረው በመላ አገሪቱ አገራዊ አላማ እንዲጠፋ አድርጓል። በአገሪቱ ባሉ ሁሉም ዘርፎች ላይ ተመሳሳይ ተግባር ተፈፅሟል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነባር ባለሙያዎች ተባረዋል፤ አየር ሀይሉን አፍርሰው የራሳቸውን ሰዎች ተክተዋል።
ዘመን፡- በ1985 ዓመተ ምህረት የኢህዴንን አመራርና አባላት ያነታረከው የደሴው ውይይት አጀንዳና አላማ ምን ነበር?
ጄኔራል ተፈራ፦ በኢህአዴግ ደረጃ ሁሉም ድርጅቶች ውይይት እንዲያደርጉበት የመጣ አጀንዳ ነው። አጀንዳውን ያመጣው ሕወሀት ሲሆን ‹‹ግለኝነት አለ›› የሚል አጀንዳ ነው። በዚህም መሰረት ኢህዴን ደሴ ላይ ውይይት አደረገ። ወቅቱ ሕወሀት በተደራጀ መልኩ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ራሱ የሚሰበስብበት ወቅት ነበር። ከደርግ ሠራዊት መደምሰስ ጀምሮ /ልክ ከትግራይ መሬት ማስወጣት አንስቶ/ ጎንደር፣ ጎጃም፣ በምእራብ ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የአገሪቱን ባንኮች፣ ጀነሬተሮችን፣ የዳቦ መጋገሪያዎችን የሚዘርፍበትና የሚጭንበት ወቅት ነበር። ይህንን ሲያደርግ የሚቀናቀነው ህዝባዊ ግንባር / ሻእቢያ/ ሎጂስትኩ አብሮ ስለነበር እሱም አብሮ ይጣደፍ ነበር። ሕወሀት ይህንን የሚያደርገው እንደድርጅት ቢሆንም ስጋት አደረበት። ከራሱ አባሎች አንዳንዶቹ አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ግል ካዝናቸው ማስገባት፣ መኪና መሸጥ፣ መስረቅ ጀመሩ። ይህንን የተገነዘበው ሕወሀት ‹‹ግለኝነት አለ›› የሚል አጀንዳ አመጣ። ‹‹ሌባ እናት ልጇን አታምንም›› እንደሚባለው በአጀንዳው መሠረት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አባሎቻቸውን እንዲገመግሙ ተደረገ። በወቅቱ የኢህዴን አመራሮች አጀንዳውን ሲያቀርቡ በአመራሩና በአባላቱ መካከል ከፍተኛ ክርክር ተደረገ። በኢህዴን በኩል የግለኝነት ተግባር እየተፈፀመ አለመሆኑን ብዙዎች አነሱ። ሕወሀት ራሱን እዲመለከት በውይይቱ ሰፋ ያሉ ሀሳቦች ተንፀባረቁ። በተደረገው ክርክር በአስተሳሰብ ደረጃ አለ ቢባልም ሕወሀት ባሰበው መልክ መሄድ አልቻለም፤ ምክንያቱም ኢህዴን ንፁህ ነበር።
ዘመን ፡- አቶ ታምራት ላይኔ ‹‹የፖለቲካ ደባ ተፈፅሞብኝ እንጂ ሙስና ሰርቼ አልታሰርሁም›› ሲሉ በተደጋጋሚ ይገልፃሉ፤ እውነት ደባ ተፈፅሞባቸው ነው የታሰሩትʔ
ጄኔራል ተፈራ፦ አቶ ታምራት ከሕወሀት ጋር ተጣብቆ የኖረ ሰው ነው። ሕወሀት ያደርግ የነበረውን ዘረፋ ያውቃል። ዘረፋውን በማወቁ እሱም በዚያች አጋጣሚ ቆንጠር አድርጎ የሰራው ስህተት ሊኖር ይችላል፤ ታምራት ላይኔ የታሰረው በዋነኛነት የመለስ ዜናዊን ተክለ ሰውነት ለማግዘፍ ሲባል ነበር። መለስ ተቀባይነት እንዲኖረውና ጥሩ መሪ መሆኑን ለማሳየት ታምራትን በማጥላላት መለስን የማጀገን ስራ ተሰርቷል። በትክክል ከታየ ግን ታምራት ከበፊት ጀምሮ ከማንም በተሻለ መልኩ ጥሩ የሕወሀት አገልጋይ ነበር። ታምራትን የብአዴን አመራሮች እነበረከት አልደገፉትም። በእርግጥ በትግሉ ወቅትም ቢሆን ታምራትና በረከት አይግባቡም ነበር። ከዚህ የተነሳ በረከትም ታምራትን ገፍቶ ገደል ሊከተው እያደባለት ነበር። ምክንያቱም በረከት በባህሪው የስልጣን ፍላጎቱ ገደብ የለሽ ነው። ይህን ፍላጎቱን ለማርካት ታምራት እንዲወገድለት ይፈልጋል። ታምራትም ወደ ኢህዴን አሊያም ብአዴን ሳይሆን ወደ ሕወሀት ተሸጎጦ የኖረ ነው። በመሆኑም የብአዴን አመራሮች ሊከላከሉለት አልፈለጉም፤ ለመከላከል አቅሙም አልነበራቸውም። ሕወሀት ደግሞ ከተጠቀመብህ በኋላ ይጥልሀል። ታምራት ከሕወሀት ጋር ከመጠን ያለፈ ተለጥፎ ስለነበር የሕወሀት አባላት ‹‹ታምራት ወደር የለውም›› ይሉ ነበር፤ የብአዴን አባላት ታምራትን እንደማይከላከሉለትም ሕወሀት ያውቅ ነበር።
ዘመን ፡- በእርስዎ እምነት የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት እውነተኛ ምክንያት ምን ነበርʔ
ጄኔራል ተፈራ፦ እንደእኔ እምነት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መንስኤ ሁለቱ ኃይሎች ማለትም ሕወሀት እና ሻዕብያ የኢትዮጵያን ሀብት በመዝረፍ ሂደት አለመስማማታቸው ነው፤ አገሪቱን ለተከታታይ ሰባት ዓመት ዘረፏት። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተፋቀሩትም በኢትዮጵያ ሀብት ነው። በወቅቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሰላም መፈጠሩን ይሰብኩ ነበር። ያገናኛቸው መርህ የለሽ ዘረፋ እና ቅጥ ያጣ ግንኙነታቸው ለፀብ ዳረጋቸው። ሻእብያ በኢኮኖሚ ዘረፋው ሕወሀትን እየቀደመ በመምጣቱ በዓለም ቀዳሚ የቡና ላኪ እስከመሆን ደረሰ። በዘረፋ የኢትዮጵያን ቋት ሲከፋፈሉ ‹‹አንተ ብዙ ወሰድህ፤ የእኔ ትንሽ ነው›› በሚል ተጋጭተው የጦርነቱ ምክንያት ሆነ፤ ለጦርነቱ መነሻ ድንበር እንደነበር የሚነገረውም ውሸት ነው።
ዘመን ፡- በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እስካሁን ድረስ በትክክል አይታወቅም፤ እርስዎ ደግሞ በወቅቱ የጦር መሪ ስለነበሩ አጠቃላይ ሪፖርት የመስማት እድል ይኖረዎታል ብለን እናስባለን፤ ምን ያህል ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋልʔ ጄኔራል ተፈራ፦ ቁጥሩን ለመናገር በጣም ያስቸግራል፤ እኔ ላውቅ የምችለው የምመራውን ጦር ብቻ ነው። እንዳልኸው በጦርነቱ የሞቱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከፍ እና ዝቅ ተደርጎ ይነገራል። በኤርሚያስ ለገሰ መጽሐፍ እስከ 120 ሺህ፤ በሌሎች መረጃዎች 80 ሺህ የሚሉም አሉ። እንደአጠቃላይ ሲታይ ግን በጦርነቱ ኪሳራ የደረሰው በኢትዮጵያ ላይ ነው፤ ይህ የሆነበት ምክንያት አንዱ የኛ ዝግጅት የአጭር ጊዜ /የስድስት ወር/ መሆኑ ነው። ሁለተኛ እኛ አጥቂ ስንሆን ኤርትራ ለዓመታት /ለሰባት አመታት/ ተዘጋጅቶ ምሽግ ይዞ ተከላካይ መሆኑ ነበር።
ዘመን ፡- በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የቀድሞ ሠራዊት አባላት የነበሩ ተሳትፈዋልʔ
ጄኔራል ተፈራ፦ አዎ ተሳትፈዋል፤ ጥቂት የሚታወቁ ከፍተኛ የጦር ጀነራሎች እና በርካታ ቁጥር ያላቸው የሠራዊቱ አባላትና ብዙ ኮሎኔሎች ተሳትፈዋል። ከጀበሃ ጀምሮ ልምዳቸው ከፍተኛ በመሆኑ የሻእቢያን ስልት በደንብ ያውቁት ስለነበር የተወጡት ሚና ከፍተኛ ነበር። ከታች ስልታዊ አሰላለፍ ጀምሮ እንዴት መሆን እንዳለበት፣ በቅን ልቦና በደንብ ሠርተዋል። የከባድ ማሳሪያ ስልጠና በቅን ልቡና አሰልጥነዋል። ለአገራቸው በሙያቸው በሁሉም ዘርፍ አገልግለዋል። ከዚህም በተጨማሪ የቀድሞው ሠራዊት አብዛኛው ያሉበት 3ኛ ክፍለ ጦር ዘመቻ ውስጥ የነበረ ኮሎኔል ግርማ የሚመራው 10ኛ የሚባል አንድ ክፍለ ጦር ተዋቅሯል። በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ሻእቢያ ጠጠር ብሎ ስለነበር እንዲያውም በተራራ ውጊያ መለሰን። ለምሳሌ በባድሜ ባደረግነው የመጀመሪያው ውጊያ አቆመን፤ በተመሳሳይም በፆረናም ያደረግነውን ውጊያ ቀለበሰው። በዚህ ጊዜ የቀድሞው ጦር ጥሪ ተደረገለት፤ አገር ጦርነት ውስጥ ስለነበረች የደርግ ሠራዊት አባላት ለአገራቸው ጥሪ በጎ ምላሽ ሰጥተው ሚናቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል።
ዘመን ፡- ከጦርነቱ በኋላ ጥቅማቸው ተከብሮላቸው ነው የተሰናበቱት?
ጄኔራል ተፈራ፦ በአጠቃላይ ከጦርነቱ በኋላ በዛ ያለ ሠራዊት ተቀንሷል፤ የተወሰነ ቢደረግም ትርጉም ያለው ድጋፍ አልነበረም።
ዘመን ፡- ከ1997 ዓመተ ምህረት ምርጫ በኋላ በሠራዊቱ ውስጥ ጥልቀት ያለውና ሰፋ ያለ ግምገማ ሲደረግ የተለየ ምክንያት ነበር? ጄኔራል ተፈራ፦ በመሠረቱ በ1997 ዓመተ ምህረት ምርጫ ኢህአዴግ ከትግራይ ክልል ውጪ አልተመረጠም። በዚህ ጊዜ ህወሀቶች እንዳልተመረጡ ሲያውቁ ብጥብጡ ወደፊት ይቀጥላል ብለው ስጋት ገባቸው። ብጥብጡ ሲቀጥል ከሕዝቡ ይልቅ ስጋት የሚሆነው ውስጥ ያለው ሰራዊቱ እንደሆነ አመኑ፤ በዚህ የተነሳ አገራዊ ስነልቡና ያላቸውን፣ የአንድነት መንፈስ ያለውን የሠራዊቱን አባላት ማባረር፣ ማሰር ጀመሩ። ከምርጫው ጥቂት ወራት በኋላ እነ ከማል ገልቹ አንድ ሻለቃ ጦር ይዘው ወደ ኤርትራ ገቡ። አማራውን፣ ኦሮሞውን፣ ጉራጌውን በአጠቃላይ የአንድነት አስተሳሰብ ያለውን የሠራዊት አባል መልቀምና ማስወጣት ጀመሩ። ምክንያታቸው በምርጫው ቀይ መብራት በመመልከታቸው ብጥብጡ ሲቀጥል ሕዝቡን ለመጨፍጨፍ በሚደረግ ሂደት ሰራዊቱን ማፅዳት እንዳለባቸው በመወሰናቸው ነው። የብዙዎቹን ጀኔራሎች ሁሉ ሳይቀር ማእረጋቸውን ገፈፉ። በወቅቱ እኔ ‹‹ለምንድን ነው የሚገፈፉት›› ብዬ ስጠይቅ ‹‹ማእረጋቸውን ይዘው ወደ ሕዝቡ ከሄዱ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥ ይገቡና ሻምበል እገሌ፣ መቶ አለቃ እገሌ ሲባሉ ሕዝቡ ስለሚቀበላቸው ማእረጋቸው መገፈፉ ተገቢ ነው›› አሉኝ፤ እነ ሜጀር ጀኔራል አለምእሸት ደግፌ፣ እነ ብርጋዲየር ጀኔራል አሳምነው ፅጌና ሌሎች ብዙዎች ማእረጋቸው የተገፈፈው በዚህ የተዛባ ስሌት ነው፤ እርምጃው በንቃት የሄዱበት ነበር።
ዘመን ፡- የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ በተደረገው የሠራዊቱ ግምገማ ሰለባ ከሆኑት መካከል አምስት ኮሎኔሎች እነ ኮሎኔል አበበ አስራት፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ኃይሉ… ‹‹ለቅንጅት አብራችኋል›› የሚል ክስ በጦር ፍርድ ቤት ቀርቦባቸው እስከ 25 ዓመታት ተፈርዶባቸዋል፤ ከእስር የወጡት ደግሞ የጉዳዩ ባለቤቶች (ዋነኞቹ) የቅንጅት አመራሮች በይቅርታ ከወጡ ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር፤ እንዲህ መደረጉ በሠራዊቱ ውስጥ የፈጠረው ነገር የለም?
ጄኔራል ተፈራ፦ አምስቱ ኮሎኔሎች ኮሎኔል አበበ፤ ኮሎኔል ተስፋዬ /ሁለቱ ተስፋዬዎች/ ኮሎኔል ጎሳዬ፣ ኮሎኔል ጌትነት ከ30 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸውና አገራቸውን ያገለገሉ የደርግ ወታደሮችና ሙያተኞች ናቸው። ሕወሀት የእነዚህን ባለሙያዎች ቦታ መያዝ ስለፈለገ የጠነሰሰው ሴራ ነው። ኮሎኔል ጌትነት ጋፋትን ሲመራ የነበረ ጎበዝ ባለሙያ ነው፤ ይህንን ቦታ ህወሀቶች ስለፈለጉት ወነጀሉት። ሁሉንም በውሸት ‹‹በቅንጅት ስብሰባ ተገኝታችኋል›› አሏቸው። እነዚህ ባለሙያዎች ሙያቸውን በብቃት ከመስራት ውጪ የትኛውም ስብሰባ ላይ አልተገኙም። በመጀመሪያ በምርጫ 97 ካሰሯቸው በኋላ መረጃ ስላጡባቸው ለቀቁአቸው። መልሰው ከሁለት ዓመት በኋላ በደመነፍስ የሚፈርዱ ዳኞችን ሰብስበው ለሠራዊቱ መቀጣጫ ለማድረግ እንደ ደርግ ማእረግ ለመቁረጥ አስበው ተከሳሾቹ የክብር ልብሳቸውን ለብሰው እንዲመጡ ቢታዘዙም ሳይለብሱ መጡ። በውሸት የተሰየመው የጦር ፍርድ ቤት ፈረደባቸው። እነዚህ ሰዎች ንፁሀን ናቸው፤ ለምሳሌ ኮሎኔል ጎሳዬ በጦርነት ውስጥ ተጎድቶ አንድ እጅ የለውም፣ ሆኖም በአንድ እጁ የሚሠራ ጎበዝ ባለሙያ ነው።
ዘመን ፡- 2001 ዓመተ ምህረት ሚያዚያ ወር ላይ እርስዎና ባልደረቦችዎ ሕገ-መንግሥት በመናድና በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተወንጅላችሁ በቁጥጥር ስር ዋላችሁ፤ መፈንቅለ መንግሥት አድርጋችሁ ወይም ሞክራችሁ ነበር?
ጄኔራል ተፈራ፦ መፈንቅለ መንግሥት ነው? ምንድን ነው? የሚለው ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ነው። በወቅቱ ሕወሀት ራሱን ካስተካከለ በኋላ አማራውንና የአማራውን ተወላጅ መምታት ጀመረ። ለምሳሌ የምስራቅ አማራ ወጣቱን፣ ሲቪሉን፣ ወታደሩን አፋር በረሃ ጭፍራ ላይ አሰሩት፣ የጎጃሙን፣ የጎንደሩን ብርሸለቆ አሰሩት፣ የአዲስ አበባውን ደግሞ ወደ 50 ሺህ እናስራለን ብለው ዴዴሳ፣ ብላቴ፣ ጦላይ አሰሩት። ይህን ሲያደርጉ ‹‹አማራውን እንምታው፣ እንጨፍጭፈው በስነልቡና እናዳክመው›› ብለው ነው። እኛ የተቃወምነው ይህን ድርጊት ነው። ምርጫ 97ትን ተከትሎ ያደረጉትን ድርጊት ተቃወምን። ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አብረን የምንቀጥልበት ሁኔታ የለም አልን። የዘር ማጥፋት አካሄድ እየተከተሉ ሲመጡ ራሳችንን የመከላለከል ስራ ነው የሰራነው። ከሠራዊት በግፍ የተባረሩት የትም ቦታ ስራ እንዳይቀጠሩ በተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ እንዲደነገግ አድርገዋል። የተፈለገው የተባረረው ኃይል በረሃብ እንዲሞት ነው። ይህንን ስናይ ይሄ ነገር መቆም አለበት አልን። ግንባር ቀደም የሆንን እየተገናኘን መወያየት ጀመርን፤ ይሄንን እንዴት አስኬድነው ወደፊት ግልፅ ይሆናል።
ዘመን ፡- በዚህ ምክንያት የት ተያዙ? ወዴትስ ተወሰዱ?
ጄኔራል ተፈራ፦ በወቅቱ ትምህርት ላይ ነበርሀ፤ ዓለም አቀፍ ሥራ አመራር (ኢንተርናሽናል ሊደር ሺፕ) እያጠናሁ ነበር። ከፖሊስና ከደኅንነት የተዋቀረ ከአንድ ሻምበል በላይ ጦር ከምማርበት ቦታ ድረስ መጣ። በተመሳሳይ ሰዓት በመላው የአገሪቱ ክፍል የሚያዙ ሰዎችን እየያዙ ነበር። መረጃውን በተለያየ መንገድ አግኝተውታል ማለት ነው፤ ከዚያ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝና አንዲት አነስተኛ ክፍል ውስጥ ብቻዬን አሰሩኝ። ዘመን ፡- ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ለብቻዎት የታሰሩባት ክፍል ምን ትመስላለች?
ጄኔራል ተፈራ፦ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ስገባ ከኔ በላይ እዚያ ይፈፀም የነበረው ግፍ ነው የመጣብኝ፤ በነበርሁባት ክፍል ግድግዳ ላይ በአማርኛም በኦሮምኛም የተጻፉ መልእክቶች ይታያሉ። የጽሑፎቹ መልእክት የሚፈፀመውን ግፍ ያመላክታል። ለምሳሌ የነቀዘች ህይወት፣ ተስፋ የሌላት ህይወት እና መሰል መልእክቶች ተጽፈው አንብቤያለሁ፣ ክፍሏ ለማንበብ የምታስቸግር አነስተኛ መብራት አለቻት፣ በዚያች ክፍል ከማንም ጋር መገናኘት አይቻልም፤ በዚች ክፍል ውስጥ አርባ ምናምን ቀን ቆየሁ፤ በእነዚህ ቀናት ከቤተሰብም ሆነ ከማንም ጋር ተገናኝቼ አላውቅም።
ዘመን ፡- የምርመራ ሂደቱስ ምን ይመስል ነበር?
ጄኔራል ተፈራ፦ ምርመራው እኛ ላይ ሌላ ነገር የለውም። ‹‹ስርዓታችንን ትቃወማላችሁ›› አሉን፤ አዎ አልናቸው። ምንም አዲስ ነገር አይደለም። በግልፅ ‹‹ይህ ስርዓት የኛ ስርአት አይደለም፤ የራሳችንን ስርዓት እንፈልጋለን፤ እናንተ አይደለም ለአብሮነት ለጉርብትናም አትሆኑም›› አልናቸው። በግሌ በምርመራ ማሰቃየት አልደረሰብኝም። ሌሎች ‹‹መሰቃየት እየደረሰብን ነው›› ብለው ፍርድ ቤት ያቀረቡ ነበሩ። ጥፍራቸው የተነቀለ፣ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ተጨመርን እና ሌሎች ቅሬታዎችን ያቀረቡ ነበሩ። ለምርመራ ሲወስዱን ብዙ ጊዜ አይናችንን ሸፍነው ያወጡናል፤ ከዚህ ወጭ የደረሰብኝ እንግልት አልነበረም። የኔን ጉዳይ የደኅንነት ኃላፊ የነበረው ጌታቸው አሰፋ ነበር የሚመረምረው፤ ከእሱ ጋር በግልፅ ተነጋግረናል፤ ስርዓቱ የኛ እዳልሆነ አስረድቼዋለሁ።
ዘመን፡- በአገራችን አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ እንዴት አዩት? ጄኔራል ተፈራ፦ በመሠረቱ ይህ ለውጥ የሕዝብ አመፅና ግጭት ውጤት ነው። ምክንያቱም የነበረው አገዛዝ ከባእድ አገዛዝ አይለይም፤ በግልፅ ለመናገር ከባእድ አገዛዝ የከፋ ነው። ስልጣኑን በሙሉ ጠቅልለው ያዙት ሕወሀቶች ነበሩ፤ የክልሎች ስልጣንም የውሸት ስልጣን ነበር። ይህን ስልጣን ከያዙ በኋላ የአገሪቱን ሀብት ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እየጎተቱ ነው ያጋዙት። አገሪቱ በብድርና በእዳ የምታመጣውን ገንዘብ በቀጥታ ወደ እነሱ ይወስዱታል። መጀመሪያ ወደ ብሄራዊ ባንክ ይገባል፤ ከብሄራዊ ባንክ ወደ ልማት ባንክ ይገባል፤ ከልማት ባንክ የሕወሀት የልማት ድርጅቶች ይወስዱታል። በተለየ መልኩ የሚፈቀድላቸው ግለሰቦች ይወስዱታል። ከዚያ በኋላ ገንዘቡ ‹‹የተበላሸ አካውንት›› ነው እየተባለ አይመለስም። ‹‹አናሳ›› የሚሏቸውን ክልሎች በተዘዋዋሪ የሚመሯቸው ሕወሀቶች ናቸው። የክልሎቹ በጀትም ወደየክልሎቹ ከሄደ በኋላ ተመልሶ ወደ ሕወሀት ይገባል። አንዱ ጋ 24 ሰዓት መብራት እያለ ሌላው ጋ ጨለማ ነው። ለዚህ እንዲመች ሥልጣኑን ጠቅልለው የያዙት የአንድ አካባቢ ልጆች ናቸው። መንገድ በአንዱ ክልል በአምስት አቅጣጫ አስፋልት ሲሆን ሌላው ጋ ጠጠር መንገድ የለውም። አንዱ ክልል ምርጦች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ሲገነባ ሌላው ጋ ትውልድ ገዳይ ትምህርት ቤት ነው ያለው። በየትኛውም ነገር አብሮ የሚያኗኑር ስራ አልነበረም ሲሠሩ የኖሩት። ጣሊያኖች እንኳ ኢትዮጵያን እንደዚህ አላደረጉም፤ እናም ለውጡን እየመሩ ያሉት ስርዓቱ ከአቧራ አንስቶ ለዚህ ያበቃቸው ናቸው።
ዘመን ፡- አንዱ ክልል ለምቶ ሌላው ሳይለማ መቅረቱ ያለማውን ክልል ያስተዳድሩ የነበሩ አመራሮች ችግር አይደለምʔ
ጄኔራል ተፈራ፦ የነበሩት የየክልሎቹ አስተዳደሮች የየክልላቸው መሪዎች ነበሩ ማለት አይቻልም፤ ወደ ፊት ምርጫ መጥቶ ካልተጠረጉ አሁንም ያሉት መሪዎች መሪ ናቸው ማለት አይቻልም። ምክንያቱም አሁን ያሉትም በሕዝብ ተገፍተው መጡ እንጂ የነበረው ስርዓት ዘቦች ናቸው። በዚህ ለውጥ ሂደት ውስጥ ብሄራዊ ጀግና ገና አልመጣም። አሁን አገሪቱ ችግር ላይ የሆነችውም የነበሩት አመራሮች አሁንም መኖራቸው ነው። ለውጡ ጥገናዊ ለውጥ ተደርጎለት እየሄደ ነው። ሕዝቡ ማየት የማይፈልጋቸውን ሲያባርር አሁን ያሉት ቦታው ባዶ መሆን ስለሌለበት የተቀመጡ አመራሮች ናቸው። ለውጡ የሚወገደውን ያስወገደ ለውጥ አይደለም። የነበረው አመራር ግፍ የፈፀመ አመራር በመሆኑ ለህዝብ መታየት አይገባቸውም ነበር። በኢኮኖሚ አሻጥሩ፣ በሰብአዊ መብት ረገጣው የከወኑት ተግባር ዘግናኝ ወንጀል ነው። ይህ ሲደረግ በየደረጃው የነበረ አመራር ምን ይሠራ ነበርʔ ክልሎቹም መጠየቅ አለባቸው። አሁን በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ሕዝቡ ‹‹እነዚህን አመራሮች አንፈልግም›› ብሎ እየጮኽ ያለው ለዚህ ነው። ወጣቱን እየለቀመ እያስያዘ ግፍና መከራ እንዲደርስበት ያደረገው የነበረው አመራር ነው። አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር እንኳ አንድ ወጣት አላግባብ በሌሎች ተይዞ ለስቃይ ሲዳረግ ለምን ብሎ መጠየቅ አለበት። ይህን የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ወጣቱ እየታፈሰ እስርቤት ሲማገድ በየደረጃው የነበረው አመራር ምን ይፈይድ ነበር ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ልማትም ላይ በተመሳሳይ መልኩ ፍትሀዊነት የጎደለው ለአንዱ ክልል ብቻ ያደላ አካሄድ ተካሂዶበታል። በዚህ ረገድ የየክልሎቹ መሪዎች መጠየቅ ቢገባቸውም ትክክለኛው ስልጣን ሳይኖራቸው ለይስሙላ ተቀምጠው የነበሩ በመሆናቸው የተደረገ ድርጊት ነው። ለውጡንም እየመሩት ያሉት በዚህ ረገድ የመጡ መሪዎች በመሆናቸው እስከ መጨረሻ እየተዳሙ ለውጡን የማስቀጠል ችግር እየተፈጠረ ነው። አደጋው ደግሞ ይሄ በመሆኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰዎችን የማፈናቀል፣ የመግደል ተግባራት በስፋት እየተፈጸሙ ናቸው።
ዘመን፡ – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለውጥ ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል በጦር ሠራዊቱ የተደረገውን ለውጥ አሞካሽተዋል፤ በተቃራኒው ደግሞ በኢትዮጰያ እየተደረገ ያለውን ለውጥ እያደናቀፉ የሚገኙት በሠራዊቱ አመራር ቦታ ላይ የተቀመጡ አንዳንድ አካላት ጭምር እንደሆኑ የሚገልፁ አሉ፤ እርስዎ ምን ይላሉʔ ጄኔራል ተፈራ፦ አንደኛ በሠራዊቱ ለውጥ አለ ብዬ አላምንም፤ አንድን የተደራጀ ሠራዊት በአምስትና ስድስት ወር ውስጥ መለወጥ አይቻልም፤ ሁለተኛ አሁንም በሠራዊቱ ውስጥ ያሉት አመራሮች ሕውሀቶች ናቸው፤ እነዚህ ደግሞ ለውጡን እያደናቀፉት ነው። ለምሳሌ ሱማሌ ክልል ሕዝቡ ሲጨፈጨፍ ዝም ብለው ሲመለከቱ የነበሩ አመራሮች ናቸው። ሕዝቡን አስመትተውታል። ሰሜን ጎንደር ጭልጋ ላይ ሠራዊቱ ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራ አይደለም። ሠራዊቱ ትርጉም ያለው ሥራ ባለመሥራቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች ይስተዋላሉ። ይህ ደግሞ የሠራዊቱ መሪዎች በአግባቡ ባለመሥራታቸው የመጣ ነው። እነዚህ የሠራዊቱ መሪዎች ሜይቴክ ሲዘርፍ አብረው ሲዘርፉ የነበሩ፤ ሜይቴክ ጥሩ ሠርቷል ሲሉ የነበሩ ናቸው። ስለዚህ በሠራዊቱ ውስጥ ለውጥ የለም፤ ውሸት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስበክ ነው የያዙት። ለውጥ ካለ ቤተመንግሥት ድረስ የሚመጣ ሠራዊት አይኖርም፤ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ብጥብጦችን ማስቆም ይቻል ነበር። ሠራዊቱ እየሠራ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ከአካባቢያቸው በሚፈልሱ ሰዎች ቁጥር የአንደኝነት ደረጃን እየያዘች ነው። ከሠራዊቱ ይልቅ እየሠራ ያለው የየአካባቢው ነዋሪ ሲሆን በራሱ እየተነሳሳ ግጭትን እየተከላከለ ነው። በሠራዊቱ ውስጥ ተደረገ የተባለው ለውጥ በድፍረት የሚያናግር አይደለም።
ዘመን፡ -ታዲያ ምን ቢደረግ ይሻላል ይላሉʔ
ጄኔራል ተፈራ፦ እኔ በኢህአዴግ ለውጥ ይመጣል ብዬ አልጠብቅም፤ ለውጥ የሚመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመረጠው እንዲተዳደር እውነተኛ ፓርቲዎች ወደፊት ሲመጡ ነው፤ አሁን ያለው አስተዳደር ብልጣብልጥና ወደ ሞቀበት የሚሄድ አስተዳደር ነው። ኢህአዴግ ጥሩ ሲሆን ወደ ኢህአዴግ፤ ጥሩ ሳይሆን ወደ ሌላው ሲዋልል የመጣ፤ እድል እየተጠቀመ እየጠለፈ የሚኖር አስተዳደር ነው። ለውጥ መጥቷል የምለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትክክለኛ፣ እውነተኛ ምርጫ አካሂዶ በመረጠው ሲተዳደር ብቻ ነው።
ዘመን፡- የወደፊት እቅድዎ ምንድነውʔ
ጄኔራል ተፈራ፦ ወደፊት ሕዝብ በሚያደርገው ትግል ውስጥ መሳተፌ አይቀርም፤ በእርግጥ በአሁኑ ሰዓት ወደ ፖለቲካው የመግባት ዓላማ የለኝም፤ በአገራችን ሰላም ሰፍኖ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖር ፅኑ ፍላጎቴ ነው። ከዚህ ባለፈ ሰፊ ጊዜ ወስጄ ያቀድሁት ያለምኩት ነገር የለኝም። ዘመን፡ በጣም አመሰግናለሁ!
ጄኔራል ተፈራ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዘመን ጥር 2011 ዓ.ም
በሳሙኤል ይትባረክ