ወላጆቻቸው ካፈሯቸው ስድስት ልጆች የመጨረሻው ናቸው፤ በወቅቱ ፋሽስት ጣልያን ኢትየጵያን ለቆ ለመውጣት በዝግጅት ላይ ስለነበር ወላጆቻቸው በመደሰት ‹‹ፍሥሐ›› ሲሉ ስም አውጥተውላቸዋል፤ ፍሥሐ ‹‹ደስታ›› ማለት ነው። በ1933 ዓመተ ምህረት ከብላታ ደስታ ወልደማርያምና ከወይዘሮ ህሪተስላሴ ትኩ አድዋ ከተማ ነው የተወለዱት። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እንደ ሌላው የአካባቢ ልጆች ወደ ቤተ ክህነት ሳይሆን ታላቅ ወንድማቸው ምክትል ዳይሬክተር ሆኖ በሚሰራበት ንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ ሰባተኛ ተምረዋል፤ ከሰባተኛ ክፍል በኋላ ያለውን ደግሞ አዲግራት አግአዚ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በ1947 ዓመተ ምህረት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኮተቤ) ገቡ። በ1952 ዓመተ ምህረት ደግሞ የኮተቤ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ኮሌጅ በመግባት የሕግ ትምህርት በመማር የታላቅ ወንድማቸውን ፈለግ የመከተል ፍላጎት ቢኖራቸውም በወቅቱ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ (ሐረር የሚገኘው) የጦር አካዳሚ ስልጠና ጀምሮ ስለነበር የእሳቸውም እጣ ክፍል ወደዚያ መጓዝ ሆነ። ወታደራዊ ትምህርት ቤት መመደባቸው ያልጠበቁት ዱብ እዳ የሆነባቸው ኮሎኔል ፍሥሐ የተመረጡት ሰልጣኞች ወደ ሐረር ሲንቀሳቀሱ ለመጥፋት አስበው ወደ ኋላ ቢቀሩም ከሳምንት በኋላ ቸርችል ጎዳና ላይ በፖሊስ ተይዘው ወደ አካዳሚው ተልከዋል። ምንም እንኳን ፍላጎቱ ባይኖራቸውም መሰረታዊ የውትድርናና የቀለም ትምህርት በመማር ከኮሌጁ በምክትል መቶ አለቃነት ማእረግ በዲፕሎማ ተመረቁ። በ1962 ዓመተ ምህረት አሜሪካ በሚሰጠው የእግረኛ መኮንኖች ኮርስ ለመሳተፍ ተወዳድረው ስላለፉ ስልጠናውን በመከታተል በከፍተኛ ነጥብ ተመርቀዋል። ትምህርት በቃኝ የማይሉት ኮሎኔል ፍሥሐ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባትም የመጀመሪያ ፍላጎታቸው የሆነውን የሕግ ትምህርት አጥንተዋል። ኮሎኔል ፍሥሐ በንጉሱ ጊዜ የነበረው ዘውዳዊ አገዛዝ በወታደራዊ አገዛዝ ከተቀየረ በኋላም በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ለበርካታ ዓመታት አገራቸውን አገልግለዋል። ኮሎኔል ፍሥሐ ወታደራዊው ስርዓት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር ከታሰሩት የደርግ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ነበሩ።
በቀረበባቸው ክስ የሞት ፍርድ ቢፈረድባቸውም ወደ እድሜ ልክ እስራት በመቀየሩ ከሃያ ዓመታት እስር በኋላ ተፈትተዋል፤ ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚል ርእስ መጽሐፍ አዘጋጅተው ለንባብ አብቅተዋል፤ በመጽሐፋቸው ባነሷቸውና በአገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከዘመን መጽሄት ጋር ያደረጉትን ውይይት ይዘንላችሁ ቀርበናል። ቅድመ የካቲት 1966 ጦሩ በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ስለነበር ኑሮው እንዲሻሻልለት ብዙ ጊዜ ጠይቆ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በዚህ የተነሳ የምድር ጦር አምፆ አዛዦቹን አሰረ፤ የምድር ጦር አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ድረሴ ዱባለም ሁኔታውን ለማስተካከል ነገሌ ሲሄዱ እሳቸውም ታሰሩ፤ ሆኖም ንጉሡ ሰዎች ልከው አስፈቷቸው። ነገሌ ላይ ጥር 1966 የጀመረው እንቅስቃሴ ወደ አዲስ አበባም መምጣት ጀመረ። ከዚያ በኋላ በተከታታይ የስራ ማቆም አድማ፣ ተማሪውም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ በየመስሪያ ቤቱም አለቆቻችን ይነሱልን ማለትና አጠቃላይ ህዝባዊ እንቅስቃሴ እያደገ፣ እየሰፋ መጣ። ህዝባዊው እንቅስቃሴ አዲስ አበባ በረድ ሲል አስመራ ይቀጣጠላል፣ ኤርትራ በረድ ሲል አዲስ አበባ ይጧጧፋል። የነበረው ካቢኔ ሁኔታውን መቆጣጠር ስላልቻለ የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ካቢኔ በገዛ ፍቃዱ ስራ ለቀቀ።
የሠራዊቱ እንቅስቃሴ ሲጀምር በደመወዝ ጥያቄ ሲሆን የኮንጎ ዘማቾች ያልተከፈለ ክፍያ ነበር፤ በዚህ የተጀመረ እንቅስቃሴ አላማው እየሰፋና እየዳበረ ሄዶ የፊውዳሉን ሥርዓት አስወገደ። የተካሄደውን አብዮት ከግብ ለማድረስ በሠራዊቱ ውስጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ። የእንቅስቃሴው አንዱ አካል በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የነበረው ሠራዊት ተወካዮቹን መርጦ ወደ አዲስ አበባ አራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ መላክ ነበር። የክብር ዘበኛ የሶስተኛ ብርጌድ ሠራዊት ተወካይ ሆነው የተመረጡት ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ነበሩ። በዚህ ኃላፊነታቸው አራተኛ ክፍለ ጦር ተሰብስበው ከነበሩ መሰል ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው አብዮቱ ስኬታማ የሚሆንበትን መንገድ መክረዋል። በወቅቱ በተደረገው ጉባኤ የፖሊስና ጦር ኃይሎች አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠው ጉባኤውን አስተባብረዋል። ከዚህ ጉባኤ በኋላ ኮሎኔል ፍሥሐ የአስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር፣ የመማክርት ሸንጎ አገናኝ መኮንን፣ የአስተዳደርና የሕግ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ኃላፊ፣ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ረዳት ጸሐፊ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል። የመከላከያ፣ የአስተዳደር፣ የደህንነት እና የፍትሕ መምሪያ ኃላፊ ሆነዋል። በመቀጠልም የቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ሰርተዋል።
የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት በ1979 ዓመተ ምህረት ሲጸድቅ የኢፌዴሪ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ። ደርግ አብዮቱን ተጠቅሞ ወደ ስልጣን በመምጣቱ ‹‹የሕዝብን አብዮት ቀምቷል›› ብለው ወገባቸውን ይዘው የሚሞግቱ በርካቶች ቢሆኑም ኮሎኔል ፍሥሐ ግን ‹‹ደርግ የማንንም አብዮት አልቀማም›› ባይ ናቸው። እንደእሳቸው አባባል ሠራዊቱ በሕዝብ ግፊት ያንን ኮሚቴ እንዲያቋቁም የተደረገው ሕዝቡ ‹‹ወታደሩ ደመወዙን አስጨምሮ ጥሎንና ከድቶን ወደ ካምፕ ተመለሰ›› የሚል ወቀሳ በማሰማቱ ነው። ይህንን ሀሳብ የሚያንፀባርቁ ወረቀቶች ከመበተናቸው ባለፈ፣ የነበረው ቅስቀሳ ወታደሩ ዩኒፎርም ለብሶ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮበት እንደነበር ኮሎኔሉ ያወሳሉ። አብረዋቸው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች እንኳ ‹አገሪቱ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ እያለች ለምንድን ነው ጥላችሁን ወደ ካምፓችሁ የተመለሳችሁት?› የሚል ጥያቄ አዘል ወቀሳ ያቀርቡላቸው እንደነበርም ይናገራሉ። በወቅቱ አንድም የተደራጀ የፖለቲካ ድርጅት አልነበረም። ኢሕአፓ እና መኢሶን እንኳ ደርግ እንቅስቃሴ ከጀመረና ጥሪ ካደረገላቸው በኋላ ነበር የፖለቲካ ፓርቲ ሆነው ለመቋቋም የሞከሩት። እናም የተደራጀ ፖለቲካዊ ኃይል በሌለበት የማንን አብዮት ነጠቅን ይባላል? ሲሉ ኮሎኔሉ ይጠይቃሉ። እንዲያውም በአገሪቱ የነበረውን አደገኛ እንቅስቃሴ ያስቆመው ደርግ እንደሆነ ያምናሉ። ደርግ ከሠራዊቱ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ተመርጦ የመጡ አባላትን የያዘ በመሆኑ የሕዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጠ መደረግ ያለበትን ነገር ለማድረግ አቅሙ የፈቀደውን ያህል አደረገ እንጂ እንደሚባለው አብዮት እንዳልቀማ ያስረዳሉ። አብዮታችንን ተነጠቅን የሚሉትም በወቅቱ ያልነበሩ መሆናቸውንና ኢሕአፓ ራሱ በእድገት በሕብረት ዘመቻ ወጣቱን እንደልቡ አግኝቶ በመመልመሉ መስፋፋቱን ይጠቁማሉ። ኮሎኔሉ እንዳሉት መኢሶን ከአውሮፓ መጥቶ የማደራጀት ስራ ቢጀምርም በአገራችን አንድም ስልጣኑን ሊረከብ የሚችል የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል አልነበረም። በእርግጥ በ1966ቱ አብዮት በርእዮተ ዓለም የበሰሉ፣ በሃገር ፍቅር የነደዱ፣ ቆራጥ ወጣቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር። ቢሆንም አገሪቱን ከደም መፋሰስ አልታደጓትም፤ ለምን? ለምንስ አብረው መስራት አልቻሉም? የሚሉት ጥያቄዎች የብዙዎች ነው። ደርግ ጥሪ ካደረገ በኋላ የተቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉም ምንጫቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች እንቅስቃሴና የተገኙ የውጭ አገር ተሞክሮዎች ናቸው። እንደ ኮሎኔል ፍሥሐ ገለፃ የድርጅቶቹ ልዩነት የሚጀምረው አብዮቱ እንደፈነዳ ሳይሆን ከአብዮቱ በፊት ነው። መኢሶንና ኢሕአፓ በተማሪ እንቅስቃሴ ወቅት አንድ ላይ ቢሆኑም ለመከፋፈል ያበቃቸው ጉዳይ አመለካከት ነው። ኢሕአፓ በዚያን ወቅት ፓርቲ ሳይሆን በድርጅት ደረጃ የነበረና ‹‹መሳሪያ ይዘን ከገጠር ወደ ከተማ በመሄድ የፊውዳሉን ስርዓት እንጥላለን›› ይላል። መኢሶን በበኩሉ ‹‹የኢሕአፓ ዓላማ ሕዝብን ያስፈጃል፤ ምክንያቱም ሕዝቡ አልነቃም፣ አልተደራጀም፣ አልታጠቀም፤ ስለዚህ የታጠቀ፣ የተደራጀ፣ የነቃ ሕዝብ መፍጠር አልብን፤ ሕዝቡ ውስጥ ገብተን ፖለቲካውን መስራት መቅደም አለበት። በዚህ አይነት መንገድ ነው የፊውዳሉን ስርዓት ማስወገድ የሚቻለው›› የሚል እምነት ያዘ። በዚህ ልዩነት ለመከፋፈል በቁ። አብዮቱ ድንገት ሲፈነዳ ልዩነታቸውን እንደያዙ የሁለቱም አባላት አገር ቤት መጡ። ተነጋግረው፣ ተቻችለው እንደመሥራት በጥቃቅን ልዩነቶች ለምሳሌ በ‹‹ሸ›› እና ‹‹ቸ›› ፊደል ሳይቀር ልዩነቶቻቸውን እያሰፉ ሄዱ፤ በዚህ የተነሳ አብሮ በመስራት አገርን መታደግ አልተቻለም። ኮሎኔል ፍሥሐ እንደሚሉት በወቅቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ትልቁ ልዩነት የመጣው ደርግ ጊዜያዊ ሕዝባዊ ድርጅት አቋቁሞ ተራማጆችን ሁሉ በጠራበት ወቅት ነው። ደርግ ተራማጆችን የጠራበት ምክንያት ሕዝቡን እንዲያደራጁ፣ እንዲያነቁና ለሚባለው ሶሻሊዝም ግብ አገሪቷን መምራት እንዲችሉ ነበር።
አገርን በጋራ እንዲመሩ ድርጅት ሲቋቋም መኢሶን ለደርግ ሂሳዊ ድጋፍ ለመስጠት ጽሕፈት ቤቱን ተቀላቀለ። ኢሕአፓ ግን ‹‹ከፋሽስት ደርግ ጋር አልሰራም›› አለ፤ ቆይቶ ደግሞ ከሁለቱም ጋር ቅራኔ ተፈጠረ። በዚህ አይነት ሁሉም መነጋገር ሳይቻቻሉ ቀሩ። በዚያን ወቅት በምስራቁ የሱማሌ ወረራ፣ በሰሜኑ በኩል የጀበሓ እና የሻዕብያ እንቅስቃሴ፣ በሰሜን ምዕራብ ደግሞ የኢድዩ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያን ወጥረዋት ነበር። በእነዚህ ሁኔታዎች ደርግ በቀላሉ ሊወድቅ ስለሚችል ትግሉን ከገጠር ወደ መሃል አሸጋግሮ ሽብር በመፍጠር የመንግሥትን ስልጣን እይዛለሁ ብሎ ኢሕአፓ እንደተነሳ የቀድሞው ኢፌዴሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ያብራራሉ። በሂደቱም በተለይ የመኢሶን ተራማጅ አባላትንና ሌሎችን መግደል ተጀመረ። በዚህ አይነት መንገድ ደም መፋሰሱ መጣ። ነጭ ሽብር ተብሎ ተጀመረ፤ አፀፋው መመለስ ስለነበረበት መኢሶን ደግሞ ‹‹ነጭ ሽብር በቀይ ሽብር ይደመሰሳል› ብሎ ሲነሳ ደርግም ተባባሪ ሆነ›› ይላሉ። ይህን ዘግናኝ የአገር ታሪክ ሰነዶች ‹‹ቀይ›› እና ‹‹ነጭ ሽብር ›› ብለው መዝግበው ያዙት። መደማመጥ፣ መነጋገር ጠፍቶ ‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ይፈፀም›› በሚል የከረረ አቋም በርካቶችን አሳጣን፤ ሀገርንም ጭንቅ ውስጥ ከተተ፤ የታሪክ ጠባሳም አኖረ። የታሪክ ጠባሳው ሁሌም የሚያንገበግበው ኢትዮጵያዊያን የአንድ አገራቸውን ተልኮ በራሳቸው መነፅር ተመልክተው ለማሳካት ሲባል እርስ በርሳቸው መተላለቃቸው ነው። የእልቂቱን መጠን የተለያዩ አካላት የተለያየ ቁጥር ይሰጡታል። አንዳንዶች በተለይም ደርግ ኢሕአፓን ለመደምሰስ ‹‹ያን ትውልድ›› ጨርሷል ይላሉ። ኮሎኔል ፍሥሐ እንደሚሉት ደግሞ የተጠቀሰው ቁጥር የተጋነነ ከመሆኑ ባሻገር ደርግን ጭራቅ አስመስሎ ለመሳል የተደረገ የፈጠራ ተረክ ነው። ደርግ ከኢሕአፓ ጋር ባደረገው ትግል አንድ ትውልድ ጨርሷል እንዴት ይባላል? አንድ ትውልድ ማለት ኢሕአፓ አንድ ትውልድ ነበር ማለት ነው? ›› ሲሉም ይጠይቃሉ፤ ‹‹አንካሳ ያወራውን ፈረሰኛ አይመልሰውም›› እንደሚባለው አሸናፊው አካል አንድ ጊዜ በፕሮፓጋንዳ መልክ የነዛው ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ። ‹‹አቃቤ ሕግ ክስ በሚያቀርብበት ጊዜ ‹ትውልድ አልቋል› ይል ነበር፤ ፍርድ ቤት ምስክሮች ቀርበው፣ የደኅንነት መስሪያ ቤቱ ተበርብሮ፣ በቀበሌዎችና በከፍተኞች የነበሩ የሰነድ መረጃዎች ተፈትሸው እንደ ተባለው ሳይሆን በቀይ ሽብር የተገደሉት በአዲስ አበባ ወደ 950 አካባቢ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ 2 ሺህ 500 የሚደርሱ ሰዎች ናቸው።
ይሄ ከሳሽ (የቀይ ሽብር ኮሚቴ) ተቋቁሞ ያረጋገጠው ቁጥር ነው። በነጭ ሽብርም የዚያኑ ያህል የተገደሉ ነበሩ፤ በአጠቃላይ በነጭና ቀይ ሽብር የተገደሉት አምስት ሺህ ሰዎች ቢሆኑ ነው›› ሲሉ ኮሎኔል ፍሥሐ ያብራራሉ። በእርግጥ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር አሳንሶም ሆነ ጨምሮ ለትውልድ መንገር ከዚያ ከአፀያፊው የአንድ ወቅት የአገር ታሪክ ወጣቱ እንዲማር ከማድረግ ያለፈ ዋነኛ ጉዳይ መሆን የለበትም፤ ጥሩውንም ሆነ መጥፎውን ታሪክ በትክክለኛውና በአግባቡ ሰንዶ ማስተላለፉ ትውልድ ተምሮበት መፃኢ የአገር እጣ ፈንታ የተሻለ እንዲሆን የራሱ ሚና እንዳለው የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ። ይህን በመረዳት ይመስላል በቀይ ሽብር ሰለባ የሆኑትን ለመዘከር ሲባል ‹‹የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም›› የተገነባው። መታሰቢያ ሙዚየሙ በነጭ ሽብር ሕይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያዊያን ጭምር መሆን እንደነበረበት የኮሎኔል ፍሥሐ እምነት ነው።
እንደ እሳቸው አባባል የተለያየ አመለካከት ይዘው ቢገዳደሉም ሁለቱም ኢትዮጵያዊያን ከመሆናቸው ባለፈ የነተስፋዬ ደበሳይ እናቶችን ለማስደሰት ክስ ሲቀርብ፤ በነጭ ሽብር ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸው ፊት እና በየመንገዱ የተገደሉት የእነፍቅሬ መርእድ ቤተሰቦችንም ማሰብ ያስፈልጋል። ሌላው ቀርቶ ኢሕአፓ በሶማሌ ጦርነት ሰርጎ በመግባት በጦርነቱ ላይ የሚሊሻ ሠራዊቱን ‹አፈግፍጉ› እያለ ያስጨረሳቸው ኢትዮጵያዊያን በመታሰቢያ ሙዚየሙ ተካትተው ሊታሰቡ እንደሚገባ ያስረዳሉ።
‹‹የሚያሳዝነው ኢሕአፓ የሠራውን ስህተት ዛሬም ካለማመኑ በተጨማሪ ሁሉን ጥፋት ደርግ ላይ ብቻ መደፍደፉ ነው፤ ነገር ግን ሁለታችንም አጥፍተናል፤ ጥፋተኞች በመሆናችን ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ ካለብን ሁላችንም ነን፤ የቀይሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየሙ ግን የአሸናፊዎች ሙዚየም ነው›› ይላሉ ኮሎኔል ፍሥሐ።
በመታሰቢያ ሙዚየሙ ከተካተተው ታሪክስ ቢሆን ትምህርት ተወስዶ የተሻለ አገር ለመፍጠር እና የተቃና ፖለቲካ እንዲኖር የመነጋገር፣ የመወያየት፣ የሁሉም ሀሳብ የሚንፀባረቅበትና ወደ ተግባር የሚቀየርበት መድረክ ለመፍጠር ማስተማሪያ ሆኖ እንዳላገለገለ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። ኮሎኔል ፍሥሐ እንደሚያስረዱት ባለንበት ወቅትም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች እየተሳተፉ ቢገኙም ያለፈው ጥፋት ተሞክሮ ሆኗቸው ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለህዝቦቿም እውነተኛ ተጠቃሚነት እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ እዚህ ግባ የማይባልና እርስ በርስም ተስማምተው በአንድነት የማይሰሩ ናቸው። በዚህ ምክንያት አገሪቱን ወደ ሁለት ጫፍ እየጎተቷት ይገኛሉ፤ እሳቸው እንደሚያስረዱት እነዚህ ፅንፍ የወጡ ሁለት አስተሳሰቦች ከተማሪ እንቅስቃሴ የጀመሩ ናቸው፤ በዚያን ወቅት አንደኛው ህብረብሄራዊ ድርጅት ሆኖ የመደብ ትግል የሚያካሄድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በብሄር ተደራጅቶ የብሄር ብሄረሰብ መብት እስከ መገንጠል የሚለውን የማርክሲስት ርእዮተ ዓለም ይዞ የሚንቀሳቀስ ነበር። በሂደት ህብረብሄራዊው እየተሸነፈ የብሄር እንቅስቃሴ የሚያደርጉት እንደህወሀትና ኦነግ የመሳሰሉት ድርጅቶች በለስ ቀንቷቸው የኢትዮጵያን መንግሥት ስልጣን ለመጨበጥ በቁ።
አሁንም በተመሳሳይ መልኩ ብሄር ተኮሮቹና ህብረብሄሮቹ ሊስማሙ አልቻሉም። እነዚህን አስተሳሰቦች ወደ ጋራ አመለካከት ማምጣት ያስፈልጋል። የመደብ ትግሉ በአብዮቱ ጊዜ ተካሄዷል፤ በዚህም መሬት ላራሹን የመሰለ ውጤት ተገኝቷል፤ የፊውዳሉ ሥርዓትም ተደምስሷል። ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ‹‹የብሄር ብሄረሰብ መብት እስከ መገንጠል›› የሚለውን ከፋፋይ መመሪያ ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያ አሁን ወደ ገባችበት ችግር እንድትገባ መዳረጉን ኮሎኔል ፍሥሐ ያመላክታሉ። ‹‹በቋንቋ ብቻ ክልሎች መዋቀራቸው ብሄርተኝነት እንዲጠናከር፣ የብሄራዊ ስሜት እየቀዘቀዘና እየተዳከመ እንዲመጣ በማድረጉ አሁን ለብዙ ግጭቶቻችን ምክንያት ሆኗል፤እርግጥ ነው የአንድ ብሄረሰብ ቋንቋ መከበር አለበት፤ ይህንን ማንም ሊሞግተው የሚችለው ነገር አይደለም። ነገር ግን አከላለል አስተዳደራዊ አመቺነትን፣ ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ ግንኙነትን፣ ባህልን፣ ታሪክን፣ ሁሉ አገናዝቦ መዋቀር ነበረበት፤ ይህ ቢሆን ኖሮ አሁን ለደረስንበት ችግር አንጋለጥም ነበር›› የሚል አመለካከት አላቸው።
አሁን ላይ ክልላዊ ስሜት በጣም ገኖ የይገባኛል ጥያቄና የመሬት ጥያቄ ከአጎራባች አገራት ጋር እንደሚደረግ ትግል ተደርጎ በርካቶች በገዛ አገራቸው እየተሰደዱ፣ እየተባረሩ ነው። ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሚሊዮኖች እየተፈናቀሉ ናቸው፤ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ተዘዋውረው ሰርተው የሚበሉበት፤ ነግደው የሚያተርፉበት ጊዜ እየቀረ የመጣ እንደሚመስል ኮሎኔል ያብራራሉ። ዘርን ወይም ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፍረጃ ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብ ምደባ ከደርግ ዘመነ መንግሥት ማብቂያ የጀመረ ነው፤ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን ሌተናል ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ከኢፌዴሬ ምክትል ፕሬዚዳንትነት የተሰናበቱበትን ምክንያት ማወቅ በቂ ነው። እንደ እሳቸው ገለፃ ከስልጣን የተሰናበቱበትን ምክንያት በትክክል ባያውቁትም ለእውነት የቀረበ ግምት ግን አላቸው። እንደ አጋጣሚ በትግራይ ክልል አድዋ ተወላጅ መሆናቸው ከስልጣን እንዲወርዱ እንዳደረጋቸው ይገምታሉ። ጦርነቱ እየገፋ እና ህወሓት እየተጠናከረ ሲመጣ ብሎም በደርግ ሠራዊት ዘንድ ሽንፈት ሲደርስ ነገር ፍለጋ መጣ። ከደርግ ባለስልጣናት መካከል ምስጢር እንደሚወጣም ይገመታል፣ ሊያወጣ የሚችለው ደግሞ ከነፃ አውጪዎች ዘር የመጣ እንደሆነ ይደመደማል።
ኮሎኔል ፍሥሐ አማፅያኑ ከበቀሉበት ዘርና አካባቢ በመምጣታቸው ፍረጃው እሳቸው ላይ ወደቀ። በመሠረቱ ኮሎኔል ፍሥሐ ከማንም ያነሰ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብም ሆነ እምነት አልነበራቸውም፤ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምም ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሆኖም ግፊቱ ሲበዛባቸው ፍሥሐ ደስታን ከኢፌዴሪ ምክትል ፕሬዚዳንትነት አነሷቸው፤ ኮሎኔል ፍሥሐ ‹‹በወቅቱ ለህወሓት ምስጢር የምሰጥበት ምንም ነባራዊ ምክንያት አልነበረም፤ ከአገር ምክትል ፕሬዚዳንትነት የትግራይ ገዢ ለመሆን መረጃ አልሰጥም። እንዲሁም ህወሓት የሚከተለው የአልባኒያ ኮሚኒዝም ሲሆን ደርግም የሶቪየት ኮሚኒዝምን እያካሄደ ነበር፤ የኤርትራን መገንጠል ወይም ነፃ መውጣት አላምንበትም፤ ትክክልም አይደለም፤ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል ያለው ሕዝብ ነው፤ ይህ አሁንም ያለ አቋሜ ነው›› በማለት ፅኑ እምነታቸውን ያስረዳሉ። ኮሎኔል ፍሥሐ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሀይለማሪያም ጋር ለበርካታ ዓመታት የቅርብ ጓዶች ነበሩ፤ በሚገባ ያውቋቸዋል፤ እሳቸው እንደሚሉት ኮሎኔል መንግስቱ በጣም ትሁት፣ የቀድሞ አለቆቻቸውን ሁሉ አንቱ ብለው የሚጠሩ፣ ሰውን በሁለት እጃቸው የሚጨብጡ፣ ቀልድና ጨዋታ ወዳድ ናቸው፤ የአኗኗር ዘይቤያቸውም በጣም ቀላል ሲሆን እንደሌላው ፕሬዚዳንት የተቀናጣ አኗኗር አልነበራቸውም፤ አጠቃላይ ማኅበራዊ ሰብእናቸው ጥሩ ሰው የሚባልና ሰው ሰው የሚሸት ሲሆን የፖለቲካ ሰብእናቸው ግን ከዚህ የተለየ መሆኑን ያብራራሉ።
ዓለምአቀፍ እውቅና ጭምር የነበራቸውን የአፄ ኃይለስላሴ ባለስልጣናት እንዲረሸኑ የፕሬዚዳንት መንግስቱ ውሳኔ ትልቁን ሚና ተጫውቷል። ኮሎኔል ፍሥሐ እንደሚሉት የአፄ ኃይለስላሴ ባለስልጣናት እንዲገደሉ‹‹አስራችሁ ለምን ትቀልባላችሁ? የፊውዳል ስርዓቱ መደምሰስ አለበት፣ የማርክሲስት አመለካከት ጠላትህን እንዳለ ደምስስ ስለሚል ይደምሰሱ›› የሚሉ የተለያዩ ግፊቶች ነበሩ። ነገር ግን በመጨረሻ ላይ ከጀኔራል አማን አምዶም አጋጣሚ ጋር ተያይዞ ሁኔታዎች ተቀየሩ። ከፍርሀት የመነጨ አሊያም ተቀባይነት አናገኝም ከሚል ወይም ሰዎቹ ቢለቀቁ አደጋ ሊጥሉ ይችላሉ ከሚል ስጋት ሊሆን ይችላል የአፄው ባለስልጣናት ግድያ ተፈፀመ። በተለይ ሊቀመንበር መንግስቱ በዚህ በኩል ግልፅ አቋም ወስደዋል። ኮሎኔል ፍሥሐ በመጽሐፋቸውም እንደገለፁት መንግሥቱ በጻፉት ደብዳቤ ስልሳዎቹ ሰዎች እንዲገደሉ ቀደም ብለው ወስነው ነበር፤ ነገር ግን ያ ውሳኔ የብቻቸው እንዳይሆን አንድ ቀን ቀደም ብለው ማለትም በአስራ ሶስት የጻፉትን ደብዳቤ በአስራ አራት ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው በሰዎቹ ላይ ርምጃ መውሰድ የሚያስችል ውሳኔ በድምፅ እነዲወሰን አመቻቹ፤ ጉባኤውም የእሳቸውን ሀሳብ አፀደቀላቸው፤ ውሳኔውም ስልሳ ምርጥ ኢትዮጵያዊያንን አሳጣን። ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ እንደሚያገኙ በሚጠብቁ አገራቸውን ያገለገሉ ኢትዮጵያዊያን ላይ ድርጊቱ መፈፀሙ ሁላችንንም ሊፀፅተን የሚገባ አሳዛኝ ድርጊት ነበር፤ ድርጊቱ በአብዮቱ ላይ አንድ ጥቁር ነጥብ ጥሎ አልፏል። ነገር ግን በተራማጆች በኩል የሰዎቹ መገደል እንደትልቅ ርምጃ መወደሱን የሚናገሩት ኮሎኔል ‹‹ጉዳዩ ካለፈ በኋላ ተወገዘ እንጂ በወቅቱ ደርግ ከፊውዳሉ ስርዓት ስለተገላገለ ከተራማጆች ጋር ቆሟል የሚያሰኝ ርምጃ ነው ተብሎ ተደንቋል›› ይላሉ። በእርግጥ አብዮቱ ያመጣው ስርዓት በሚታወቅም ሆነ በማይታወቅ መንገድ የበላቸው 60ዎቹን የአፄውን ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ ባለምጡቅ አእምሮና ታዋቂ ኢትዮጵያዊያንን ጭምር ነው፤ ከእነዚህ ውስጥ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ይጠቀሳል። ኮሎኔል ፍሥሐ መጻሕፍቱን ከማንበብ ውጭ በአሉ ግርማን ቀርበው አያውቁትም። በአሉ ግርማን ለሞት የዳረገው ‹‹ኦሮማይ›› የተሰኘው መጽሐፍ ነው። ሠራዊቱ ውጊያ ላይ እያለ የነበረውን ሁኔታ በምርጥ ክህሎቱ እንደዚያ አድርጎ ሲገልፀው በጦር ሜዳ የነበረው ሠራዊት ተቆጥቷል፤ አንዳንድ የጦር አዛዦችንም ዘለፍ አድርጓል፤ አዘዦችን ደስ በማይል ሁኔታ ገልጧቸዋል። ያነሳው ጉዳይ ትክክለኛ ሊሆን ቢችልም ወቅቱን ያልጠበቀ እንደነበር የኮሎኔል ፍሥሐ እምነት ነው። በአሉ በነበረው ኃላፊነት የነበረውን መረጃ ተጠቅሞ መጽሐፉን ማዘጋጀቱ በጦሩ ውስጥ ትልቅ ችግር ፈጥሮ ካድሬዎችም እንደተነሱበት ኮሎኔል ያስታውሳሉ፤ ኮሎኔል እንደሚመስላቸው ፕሬዚዳንት መንግሥቱን በአሉ በመጽሐፉ ስላመሰገናቸው ከሳቸው ግፊት ሳይሆን ከጦሩ በመጣ ግፊት ያንን ውሳኔ ለማሳለፍ ተገፋፍተዋል፤ በወቅቱ የደኅንነት ሚኒስትር የነበረው ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ለኮሎኔል ፍሥሐ እንደነገራቸው ትእዛዙ ከፕሬዚዳንቱ መጥቶ በዚያው አግባብ ግድያው ተፈፅሟል፤ በደኅንነት መሥሪያ ቤትና በፓርቲው ውስጥ የነበሩ ባለስልጣናት በኦሮማይ የተወረፉና ስማቸው የተነሳ ሰዎችም ግፊት ለሞት አብቅቶታል የሚል ጥርጣሬ አላቸው።
ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም የነበራቸው የፖለቲካ አቋም የማይናወጥና የማይቀየር ይመስል ነበር፤ ‹‹አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስከሚቀር መስዋዕት እከፍላለሁ›› የሚል ፉከራ ሲያሰሙም አድናቆት ጎረፈላቸው፤ አገር ወዳድነታቸውና ጀግንነታቸው በሰፊው ተነዛ፤ ነገር ግን አድናቆቱ ተወርቶ ሳይጠገብ መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ዚምባብዌ ኮበለሉ የሚል ዜና ተሰማ። ኮሎኔል ፍሥሐ ይህንን ዜና የሰሙት ጧት ሶስት ሰዓት ላይ ነበር። የቀድሞ ረዳታቸው ደውሎ ሲነግራቸው ለማመን ተቸገሩ፤ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥቱ አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀየር ድረስ እንፋለማለን ሲሉ አምነዋቸው ነበር። ብዙዎች መንግሥቱ ኃይለማርያም መሸሻቸው ደም መፋሰስን እንዳስቀረ ይናገራሉ፤ ኮሎኔል ፍሥሐ ግን ጉዳዩን በሁለት መንገድ ያዩታል።
እሳቸው እንደሚሉት መንግስቱ ቢኖሩ ኖሮ ደም መፋሰስ ይኖር ነበር ወይ? ህወሓት ኢህአዴግ ደፍሮ ይገባ ነበር ወይ? ሠራዊቱስ ይበተን ነበር ወይ? ሠራዊቱ እያለ ደግሞ ህወሓት ኢህአዴግ አሸንፎ ይገባ ነበር ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን በአግባቡና በጥልቀት አይቶ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ፕሬዚዳንት መንግስቱ እያሉ እንግሊዝ አገር ድርድሩ እየተካሄደ በመሆኑ እሳቸው ባይሸሹ ሠራዊቱ ስለሚቆይና ለመቋቋም ስለሚሞክር ድርድሩ ሊሳካ ይችል እንደነበር ይገምታሉ። ድርድሩ ደግሞ በመሰረተ ሀሳቡ ኢሰፓንም ጨምሮ በሽግግር መንግስቱ እንዲካተት የሚያስችል ቢሆንም ፕሬዚዳንቱ ወደ ዚምባብዌ ሲሄዱ ጀኔራል ተስፋዬ ገ/ኪዳን ሠራዊቱ መሳሪያውን አስቀምጦ እንዲሰናበት ስላደረገ ህወሓት ኢህአዴግ አዲስ አበባ ገባ፤ ኢሠፓም በድርድሩ ሽግግሩ ውስጥ ሳይገባ ያ ሁሉ ሽንፈት መጣ፤ ፕሬዚዳንቱ ባይሸሹ ደግሞ በአዲስ አበባ ደም መፋሰስ ሊኖር ይችል እንደነበር ለሚናገሩ ሰዎች የኮሎኔሉ ምላሽ ‹‹ከትግራይ ተነስቶ አዲስ አበባ እስኪደረስ ድረስ ብዙ ደም መፍሰሱ እየታወቀ አዲስ አበባን የተለየ የሚያደርገው ነገር የለም፤ ደም መፋሰስ ካሳሰበን የትኛውም ቦታ ለፈሰሰው ደም ነው መቆርቆር ያለብን፤ ባጠቃላይ ሲታይ ግን የፕሬዚዳንት መንግስቱ መሄድ ብዙ ነገሮችን ለውጧል›› የሚል ነው።
ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከስልጣን እንዲወርዱ የተለያዩ ጫናዎች እንደነበሩ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፤ ኮሎኔል ፍሥሐ እንደሚያሰረዱት ከመጀመሪያው ጀምሮ አሜሪካኖች የርዕዮተዓለም አቅጣጫ እንዲለውጡ፣ የፖለቲካውን ሁኔታ እንዲያሻሽሉ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ቢያቀርቡላቸውም ፕሬዚዳንት መንግስቱ አልተቀበሉትም።
የፕሬዚዳንት መንግስቱ የፖለቲካ አቋም ግትር በመሆኑም አሜሪካኖች ለጠየቋቸው የለውጥ ጥያቄዎች ዝግጁ አልነበሩም እንጂ ተደጋግመው ተጠይቀዋል፤ መጨረሻ ላይ የሆነው ነገር የአሜሪካ ሴናተር የነበሩት እነቦሽዊትስ እንዲሁም የአፍሪካ ዲፓርትመንት ኃላፊ የነበሩት ሰው ከደርግ ውድቀት አንድ ወር በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ‹‹ደም ከሚፋሰስ እርስዎ ቢወጡ ይሻላል›› የሚለውን ግፊት አድርገው እንደነበር ኮሎኔል ፍሥሐ ያስረዳሉ። ደርግ በእውቀት የታነፀ፣ በዘመናዊ መሳሪያ የተገነባ በርካታ ቁጥር ያለው ሠራዊት ኖሮት የተሸነፈበት ምክንያት በተለያዩ አካላት የተለያየ ነገር ይባላል፤ አንዳንዶች የሙስና መስፋፋት፤ ሌሎች ደግሞ በስልጣን መባለግና በተገቢው ቦታ ተገቢው ሰው አለመመደብ፣ ለቀድሞው ሠራዊት ሽንፈት ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።
ኮሎኔል ፍሥሐ እንደሚሉት ግን ህወሓት ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ‹‹ትልቁን የደርግ ሠራዊት አሸንፌአለሁ›› እያለ የነዛው ፕሮፓጋንዳ ትክክል አይደለም ይላሉ። ለቀድሞው ሠራዊት ሽንፈት አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደነበሩም ኮሎኔል ያወሳሉ፤ ደርግ በነበረባቸው አስራ ሰባት ዓመታት ከፍተኛ ውጊያዎች ተደርገዋል፤ መጀመሪያ የሶማሌ ጦርነት፣ ከዚያም በኤርትራ ለበርካታ ዓመታት ውጊያ ውስጥ የነበረ ሠራዊት በመሆኑ ወደ መሰላቸት መግባቱ አንደኛው ምክንያት ነው፤ ሁለተኛው ደርግ በብሄራዊ ውትድርና ምልመላ ከህብረተሰቡ ጋር ቅሬታ ውስጥ መግባቱ ለሠራዊቱ መዳከም አንዱ ምክንያት ነበር፤ ሶስተኛው የወታደሩ አመራር ሁኔታ የምስራቁ አይነት ‹‹ካድሬ፣ ደህንነት፣ አዛዥ›› የሚባል የሶስት ማዕዘን አመራር መምጣቱ ነው።
በአንድ ሰው መታዘዝ የሚገባውን በማዕዘናዊ ሲታዘዝ በአዛዦቹ መካከል ቅሬታና አለመግባባት እየሰፋ ሄደ፤ ስለዚህ በአንድ ልብ ሆኖ መስራት ሳይሆን ሶስቱም ለየራሳቸው አካል ሪፖርት የሚያደርጉት ደኅንነቱ ለወታደራዊ ደኅንነት፣ ፖለቲካ ኃላፊው ለፖለቲካው አካል፣ አዛዡ ደግሞ ለበላይ አዛዡ ነበር፤ በመካከላቸው ቅራኔ ተፈጠረ፤ የስልጣን አለመመጣጠንም ተከሰተ። አንድ መቶ አለቃ ወይም አንድ ሻለቃ ለአንድ ጄኔራል የፖለቲካ ካድሬ ይሆናል፤ ይህም በፖለቲካው ‹አመራር ልስጥ› ይላል፤ በምስራቅ አገራት የሶስት ማዕዘን አመራር ይሠራበታል። ኮሎኔል ወደብዙ የምሥራቅ አገሮች ሄደው ልምዳቸውን ቀስመዋል፤ ‹‹የሶስት ማዕዘን አመራሮች በማዕረግም በችሎታም ተቀራራቢ ናቸው፤ በኛ አገር ግን እንደዚያ አልሆነም፤ አንድ ሃምሳ አለቃ ከአንድ ኮሎኔል ጋር የፖለቲካ ካድሬ ሆኖ በሚሰራበት ጊዜ አለመጣጣም ብቻ ሳይሆን የመናናቅ ሁኔታም ተፈጠረ፤ እንዲህ መሆኑ ለግዙፉ ሠራዊት ሽንፈት አስተዋፅኦ አድርጓል። ለሽንፈቱ አራተኛ ምክንያት የዓለም ሁኔታ ሲለወጥና ሶቪየት ኅብረት ሲፈርስ ዋናው ትልቁ አጋርና የመሳሪያ አቅራቢ ፈርሶ ጎርባቾቭ ሲመጣ ነገሮች ሁሉ ተለዋወጡ፤ ኢትዮጵያም በርዕዮተ ዓለም የዚያው አካል ስለነበረች ተጎጂ ሆናለች።
እነ አሜሪካ በደርግ ላይ ብዙ ተቃዋሚዎች፤ ቄሶች ሳይቀሩ እንዲሰለፉበት አድርገዋል ‹የኮሚኒዝም ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ስር ከሰደደ አፍሪካን ያጥለቀልቃል› የሚል ስጋት ስለነበራቸው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስቀረት ቆርጠው ተነስተው ነበር። አምስተኛው ምክንያት ጄኔራሎች ውጊያውን ትተው የፖለቲካ መፍትሔ ፈላጊ መሆናቸው ነው፤ ጄኔራሎቹ ለምንድን ነው ፖለቲካዊ መፍትሔ የማይገኘው ወደሚል ሄዱ፤ ይህ አልሳካ ሲላቸው መፈንቅለ መንግሥት አደረጉ። መፈንቅለ መንግሥቱ ደግሞ ሠራዊቱ በሳል እና የተማሩ አዛዦቹን አሳጣው። በሠራዊቱ ውስጥ መናጋት ቀጠለ፤ የእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ድምር ውጤት የቀድሞው ሠራዊት እንዲሸነፍ አደረገ›› ይላሉ። በተጠቀሱትና በሌሎች ምክንያቶች የደርግ ሥርዓት ወድቆ የኢህአዴግ ሥርዓት ተተካ፤ ነባሩ ሠራዊትም እንዲበተን ተደረገ፤ መበተኑ ትክክለኛ ውሳኔ አለመሆኑን የሚገልፁ ብዙዎች ናቸው።
የሠራዊቱን መበተን ትክክለኛ ውሳኔ አለመሆኑን ኮሎኔል ፍሥሐም ይስማሙበታል። እሳቸው እንደሚያስረዱት ደርግ ከመምጣቱ በፊት በኮንጎ፣ በኮሪያ ዘምቶ የነበረውን ሠራዊት ደርግ ይዞ በመቀጠሉ ይህ ሠራዊት እንደ ህወሓት ኢህአዴግ አይነት ሠራዊትም አልነበረም፤ የህወሓት ሠራዊት ከአንድ ብሄር የወጣ ጦር ስለሆነ የህወሓት ሠራዊት ሊባል ይችላል፤ በደርግ ጊዜ የነበረው ሠራዊት ግን የደርግ አልነበረም፤ የመንግሥት ሠራዊት ነበር። አንዱ ስህተት የደርግ ሠራዊት ብሎ በመፈረጅ መበተኑ እንደሆነ ኮሎኔሉ ይጠቅሳሉ፤ እንደ ኮሎኔል ፍሥሐ ገለፃ በተበተነው ሠራዊት ውስጥ የነበሩ ጥሩ የሙያ ስልጠናና ልምድ የነበራቸውን ባለሙያዎች በትኖ ተራ ተዋጊ የነበሩትን የጄኔራልነት ማዕረግ እየሰጡ መቀየራቸው ዓለም ላይ ታዋቂ የነበረውን የአገሪቱን ሠራዊት ድምጥማጡን አጠፋው። እንዲህ መደረጉ ከኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ውጪ መሆኑንና በመንግሥት ደረጃ ሀገርን የሚመራ አካል መበቀል፤ በተለይም ሕዝብን መበቀል እንዳልነበረበት ሐዘን በተሞላበት ሁኔታ ይተቻሉ ‹‹ያ ሠራዊት፣ ያ ባህር ኃይል፣ ያ አየር ኃይል… መበተን አልነበረበትም›› ይላሉ። ትልቁ ባህር ኃይል መፍረስ ከኤርትራ መገንጠል ጋር የተያያዘ ነው፤ ‹‹ችግር ሲመጣ የተጠራው ያ በግፍ የተበተነው ሠራዊት ነው፤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጥሪ ተደርጎላቸው የተሳተፉና ጉልህ ሚና የተጫወቱት ተበትኖ የነበረው ሠራዊት አባላት ነበሩ።
ይህን ጦርነት በድል ከተወጡ በኋላም ዳግም ተበትነዋል፤ ይህ ትክክል አይደለም›› የሚሉት ኮሎኔል የቀድሞው ሠራዊት የጠላት ጦር ሳይሆን ለአገር አንድነት መስዋዕትነት የከፈለ፣ የሌሎችን መሬት ፈልጎ ሳይሆን የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የታገለ ሠራዊት በመሆኑ ሠራዊቱን መበተን በየትኛውም ታሪክ ተደርጎ አይታወቅም ባይ ናቸው። ኮሎኔል ፍሥሐ እንዳሉት በዓለም ላይ እንደቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የተበተነ የናዚ ጀርመን ሠራዊት ብቻ ነው። የቀድሞው ሠራዊት የፋሺስት ወታደር ሳይሆን በአገር ፍቅር የነደደ፣ በሙያ የሰለጠነ፣ ብቃቱ የተረጋገጠ የአገር ሠራዊትን መበተን ወታደሩንም አገርንም መበደል ነው።
ስርዓቶች ቢለዋወጡም አገር መቀጠሏ ስለማይቀር ከማንኛውም የፖለቲካ ወገን ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት አብረው የሚቀጥሉበትን ሥርዓት መዘርጋት ቀዳሚው ተግባር መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ። ኮሎኔል ፍሥሐ የመጀመሪያ ህልማቸው ያልሆነውን የጦር ትምህርት በመማር ጀምረው በነበረው ሠራዊት ውስጥ ተሳትፏቸውና አስተዋጿቸው አድጎ ከደርግ ሥርዓት ቁንጮ ባለስልጣናት መካከል አንዱ (የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት) ለመሆን በቅተዋል። በስልጣን በነበሩበት ወቅት እንደሥርዓት አንዱ መሪ ሆነው የፈፀሟቸው ችግሮች እንደማይጠፉ ሁሉ ለአገራቸውና ለህዝባቸው ያበረከቷቸው፤ ሁሌም የሚጠቀሱላቸው አስተዋፅኦዎች መኖራቸው አያጠራጥርም። የኮሎኔል ፍሥሐ ተጠቃሽ አገራዊ አስተዋፅኦ የሚጀምረው ከኢትዮ-ሶማሌ ጦርነት ነው፤ የሶማሌ ጦርነት እንደተጀመረ ሀገር በመወረሯ ህዝባዊ ጥሪ ተደረገ። ሕዝቡ ተነስ ዝመት ተባለ፤ ሕዝቡ ከጫፍ እስከጫፍ ጥሪውን ተቀብሎ ታጠቅ ጦር ሰፈር ሲከት አገሪቱ መሳሪያ አልነበራትም። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወደ ሶሻሊስት አገራት ሄደው መሳሪያ ለምነው እንዲመጡ ኃላፊነት የተሰጠው ለኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ነበር። በዚህ መሠረት ወደአራት ሶሻሊስት አገራት ሄደው ከፍተኛ ጥረት አደረጉ።
ለአራት ክፍለ ጦሮች የሚሆን ሙሉ ትጥቅም አስገኙ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግንኙነት የነበረው ‹‹ኢምፔሪያሊስት›› ተብላ ከምትጠቀሰው ከአሜሪካ ቦይንግ ጋር ነበር። ደርግ ሶሻሊስት በመሆኑ አየር መንገዱ የኢምፔሪያሊስት መሳሪያ መሆን ስለሌለበት ግንኙነቱን በሶሻሊስት አገር አየር መንገድ መተካት አለበት ተባለ። በምን ይተካ ሲባል በሶቪየት ኤሮፍሎት ተተክቶ ቦይንግ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ በተራማጅ ኃይሎች ትልቅ ግፊት ተደረገ። ይህንን አቋም ግን ኮሎኔል ፍሥሐ አልተቀበሉትም። በቦይንግና በኤሮፍሎት መካከል ያለውን ልዩነት በኮሚቴ እንዲጠና አስደረጉ፤ የሁለቱ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች በነዳጅ፣ በቴክኒካል ብቃትና በሁሉም መመዘኛዎች ጥናት ሲደረግ በፍፁም የማይገናኙ ተቋማት ሆነው ተገኙ። የሶቪየቱ ከሶሻሊስት አገራት ውጭ ማንም ሊሄድበት የማይችል፣ ታዋቂነት የሌለው መሆኑ ተረጋገጠ።
በወቅቱ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ፕሬዚዳንት መንግስቱ የኮሎኔል ፍሥሐን አቋም ደግፈው ስለነበር አሁን ድረስ ኮሎኔል ፍሥሐ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሀይለማሪያምን ያመሰግናሉ። ሌሎች ጓዶቻቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሩሲያው ተቋም ጋር ግንኙነት እንዲጀምር ከፍተኛ ጫና አድርገው ነበር። በመጨረሻ ኮሎኔል ፍሥሐ ተሳክቶላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግንኙነት ከአሜሪካው ቦይንግ ጋር እንዲቀጥል ተደረገ። የዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግንኙነቱን ቀይሮ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ መድረስ አይችል እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ። ኮሎኔል ፍሥሐ እና ባልደረቦቻቸው በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ያበረከቷቸው አገራዊ አስተዋፅኦዎችም ሆኑ የሰሯቸው ጥፋቶች ተከታዩ ሥርዓትና ትውልድ ትምህርት ሆነውት እንደሚያገለግሉት ለሁላችንም ግልፅ ነው።
በዚህ ረገድ ኮሎኔል ፍሥሐን ‹‹ኢህአዴግ ከደርግ ትምህርት ወስዶ የተሻለ ሥርዓት ዘርግቷል ማለት ይቻላል?›› የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው ‹‹ህወሓት ኢህአዴግ አንድ ትልቅ እድል ገጥሞት ነበር፤ ትልቁ እድል የሶሻሊዝም ሥርዓት ስለወደቀ ምዕራባውያን በሙሉ ለኢትዮጵያ ርዳታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማበርከት ጀመሩ። ገንዘብም ሆነ ሌሎች ርዳታ በገፍ ተገኝቷል። በእርግጥ በዚህ ርዳታ ምንም የተሰራ ነገር የለም ማለት አይቻልም። መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተሰርተዋል።
የዚያን ያህሉ ደግሞ ኢህአዴግ ከደርግ ሥርዓት ትምህርት ሳይወስድ ያጠፋቸው ብዙ ጥፋቶች አሉ›› በማለት መለሱልን ። እንደ እሳቸው ገለፃ ኢህአዴግ ደርግ የፈፀማቸውን ችግሮች ላለመድገም እንዲሁም የሰራቸውን መልካም ነገሮች ይበልጥ ለማጎልበት ተሞክሮ ወስዷል ማለት አይቻልም። ተሞክሮ የሚወስድ ሥርዓት ቢሆን ኖሮ ቢያንስ በአገሪቱ ክልሎች አከላለልና አደረጃጀት ላይ ተሞክሮ መውሰድ ይችል ነበር። የክልሎችን አከላለልና አደረጃጀት በተመለከተ አሁን እየታዩ ላሉ በርካታ ችግሮች መንስኤ የሆኑት ባለፉት 27 ዓመታት ሙሉ የተዘሩ ችግሮች ናቸው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢህአዴግ ተሞክሮ ባለመውሰዱ የዘራውን ችግር አሁን በማጨድ ላይ እንገኛለን። ይሄ የኢህአዴግ አንዱ ስህተት ነው፤ እንዴት ይታረማል የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው።
በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ብዙዎች ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል። ኢህአዴግ እንደሚለው መፈናቀሉ፣ መገደሉ ዛሬ የጀመረ አይደለም። ዶክተር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆነ ግድያው፣ መፈናቀሉ ተባብሷል ሲባል ይሰማል፤ ይህ ትክክል አይደለም። ላለፉት 27 ዓመታት በስፋት በየቦታው መፈናቀል ሲከሰት፣ ግድያ ሲፈፀም ነበር፤ ኢህአዴግ የደርግ ባለስልጣናትን ‹‹ሰው ገድለዋል›› እያለ ይከስስ ነበር፤ ግን ራሱ ከግድያ ሊወጣ አልቻለም፤ ከደርግ አልተማረም ማለት ነው። ‹‹የሕግ የበላይነት ይከበር›› ይላሉ፣ ሕገ መንግሥት አለ፣ ሕገ መንግስቱን አላከበሩትም፣ የሕግ የበላይነትም አልተከበረም።
ብዙ አዋጆች ሰውን ለማሰር፣ ለማሰቃየት የወጡ ናቸው፤ ምክንያቱም ህወሓት/ኢህአዴጎች ከደርግ ውድቀት አልተማሩም- እንደ ኮሎኔል ፍሥሐ እምነት። እዚህ ሀገር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በኢህአዴግ ዘመን ሙስናው ከመስፋፋቱ የተነሳ በቁጥር ለመግለፅ እንኳ እንደሚከብድ ኮሎኔል ፍሥሐ ያስረዳሉ ‹‹የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በኢትዮጵያ ተደርጎ አይደለም ተሰምቶ አይታወቅም፤ ከባህላችን ውጪ የሆኑ የመብት ጥሰቶች ከደርግ በባሰ ሁኔታ በኢህአዴግ ዘመን ተፈፅሟል›› ይላሉ። ኮሎኔል ፍሥሐ እንዳሉት ከደርግ ሥርዓት ምንም ትምህርት አልተወሰደም፤ በመገናኛ ብዙኃን እንደምንመለከተው ለዓይን የሚሰቀጥጡ፣ ለጆሮ የሚከብዱ፣ ሰው አለመሆንን የሚያስመኙ ጥሰቶች ተፈጽመዋል፤ ህወሓት ከደርግ በበለጠ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅሟል፤ ይህንን ችግር ለመደበቅ ሲል ጥፋቱን ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሊያያይዘው ይሞክራል። እንዲህ መሆኑ ማንንም ከተጠያቂነት እንደማያድንና አሁን እየታየ ያለው ወደ ትግራይ የመሰባሰቡ አዝማሚያ የትግራይ ሕዝብ ይዋል ይደር እንጂ እየተገነዘበው፣ እንደሚመጣ ሙሉ እምነት አላቸው።
ኮሎኔል ፍሥሐ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ዘራፊዎችንና የሰብአዊ መብት ጣሾችን ዝረፉና እግር ቁረጡ ብሎ አልመረጣቸውም፤ ለሕዝቡ ብለውም ይህንን ድርጊት አላደረጉም፤ ሕዝቡም ተካፋይ አልነበረም፤ እነዚህ አካላት መሸሺያ ሲያጡ ሕዝቡን መሸሸጊያ አድርገውታል፤ የትግራይን ሕዝብና ህወሓትን ለዩ ሲባሉ የትግራይ ሕዝብና ድርጅታቸው አንድ ናቸው የሚሉት የራሳቸውን ገበና ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥረት ነው። እንዲህ ማድረጋቸው በጣም አሳዛኝ ጉዳይ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ይህንን ደባቸውን ሊያውቀው ይገባል። የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍም በድርጅት ተቀስቅሶ የተካሄደ እንጂ በትግራይ ሕዝብ በራሱ የተደረገ አይደለም›› ይላሉ። በአንድ ለአምስት ተጠርንፎ፣ የሚሰራበትና የኮሚኒዝም ሥርዓት በትክክል እየተተገበረ ያለው ትግራይ ክልል ውስጥ እንደሆነም ኮሎኔል ያብራራሉ። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው እስረኞችን የመፍታት፤ ከአካባቢው አገራት ጋር ዲፕሎማሲን ማጠናከርና ማሻሻል ብሎም ሌሎች የተከናወኑ ወሳኝ ለውጦች እንደሚያስደስቱ ኮሎኔል ፍሥሐ ያስረዳሉ።
ባለፉት 27 አመታት ከአንድ ብሄር የወጣ ድርጅት ስልጣኑን ይዞ በቆየበት ጊዜ ጥያቄ እንደሚያስነሳ የታወቀ ጉዳይ መሆኑን ምልክቶች ቢታዩም አመራሩ ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ አለመሆን ብቻ ሳይሆን የነበሩት አመራሮች የተሰማሩት ለራሳቸው ጥቅምና ለመዝረፍ እንደነበርም ኮሎኔል ይገልፃሉ። በመጨረሻም ሌተናል ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንዳይደናቀፍና እንዳይቀለበስ በጋራ መተባበር አለበት፤ የአገራችን ሕዝብ ሁሉ በባህል በታሪክ በሌሎችም መሰል ነገሮች የተያያዘ እንጂ በክልልና በቋንቋ ብቻ የኖረ ሕዝብ አይደለም።
ይሄ ታላቅና ታሪክ ያለው ሕዝብ አንድ ላይ ተባብሮ ለውጡን ደግፎ ዴሞካራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ፣ የሕግ የበላይነት የተከበረባት አገር እንድትኖር የመስራት ኃላፊነት አለበት። ለውጡን እንዳልደገፉ የሚነገርባቸው የህወሓት ፖለቲካ አመራሮችም ለውጡን ደግፈው መቆም ይገባቸዋል፤ ይህ ካልሆነ ግን የትግራይ ሕዝብ አጋልጦ መስጠት ግድ ይለዋል። የትግራይ ሕዝብ ብዙ ችግር ቢያሳልፍም አሁንም ከችግር ባለመውጣቱ ሌላ ችግር እንዳይጨመርበት መወናበድ የለበትም። ይህንን ለውጥ ደግፎ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ኢትዮጵያን የማሳደግ አደራ አለበት፤ ይህንንም እንደሚያደርግ ሙሉ እምነት አለኝ›› የሚል መልእክታቸውን አስተላልፈው ቆይታችንን አበቃን።
ዘመን ጥር 2011 ዓ.ም
ሳሙኤል ይትባረክ