በኢትዮጵያውያን አይን በስስት የሚታይ፤ ፈጻሜው በጉጉት የሚጠበቀው ፤ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ጎልቶ የሚነገርለት ፣ የአንድነት አርማ መታወቂያችን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል። ከተጀመረ አስረኛ ዓመት ልደቱን ያከበረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተያዘለት ጊዜ እና ወጪ መጠናቀቅ ባይችልም ህዝብና መንግስት ግን ስራውን ከፍጻሜ ለማድረስ ዛሬም አልቦዘኑም ።
የጥቅሙ ተጋሪ የሆኑ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የግል ተጠቃሚነታቸውን ብቻ አስቀድመው ኢትዮጵያ የሀብቱ ተጋሪ እንዳትሆን ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም የውሃ ሙሌቱ እንዳይከናወንና በአጠቃላይ የግንባታ ሥራው እንዲስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። አሁንም ከእኩይ ተግባራቸው አልተቆጠቡም። ሆኖም ኢትዮጵያ ቃሏን አታጥፍም ከአቋሟም አትናወጥምና ወኋላ ሊመልሷት አልቻሉም። ህዝቡም ከሞራል እስከ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሯል።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናከር ከሚያስፈልጉ ሥራዎች ወይንም ድጋፍ አንዱ ለግድቦች ትልቅ ሥጋት የሆነውን በደለል የመሞላት ችግር መቅረፍ ነው። ችግሩን ለመቀነስና አካባቢውን ከተፈጥሮ አደጋ ሥጋት ነፃ ማድረግ የሚቻለው አረንጓዴ አሻራን በማሳረፍ ነው። በዚህ ረገድም ከሶስት አመት በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበር የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መልካም አጋጣሚ ነው።
በግድቡ ዙሪያ እየተከናወነ ስላለው የአረንጓዴ አሻራና የተፋሰሶች ልማት አጠቃላይ እንቅስቃሴን በተመለከተ የተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን የተፋሰስ እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ለገሠ ጋር ቆይታ አድርገናል። አቶ ደጀኔ እንዳሉት፤ ባለሥልጣኑ የህዳሴ ግንባታው በሚከናወንበት ሥፍራ የአባይ ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት አለው። ትላልቅ ፍሰት ያላቸውን ወንዞች የሚከታተል በአሶሳ ላይም ቅርጫፍ ተከፍቶ በሥራ ላይ ይገኛል። ነቀምትና ደብረማርቆስ ላይም ተጨማሪ ቅርጫፎች በተመሳሳይ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው። በአጠቃላይ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚሰሩ ሥራዎችን የተቀናጀ የውሃ ሐብት ልማት በተፋሰስ ውስጥ ማረጋገጥና በልማቱ መሠረት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ነው።የሚከናወነው ሥራም ኃይል ማመንጨት፣መስኖ፣መጠጥ ውሃን ያካትታል።እነዚህን በተፋሰሱ ውስጥ ያለውን ሀብት በተቀናጀ መልኩ ማስተዳደር፣ማልማትና የክፍያ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ በማዘጋጀት ጭምር ማከናወን የባለሥልጣኑ ኃላፊነትና ተግባር ነው።
እንደ አቶ ደጀኔ ማብራሪያ፤ የተፋሰስ ሀበት ልማትን የክፍያ ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ሲባል በቧንቧ በየቤቱ የሚደርሰውን ሳይሆን፣ለመሥኖና ለተለያየ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውለውን ነው።የውሃ ሀብቱ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ዋጋ ለማሳየት ሲባልና ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ ተመልሶ ለተፈጥሮ ሀብቱ ልማት ወይንም የአካባቢ ጥበቃ እንዲውል ለማስቻል ነው።
ውሃን በመጠቀም ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ መስኖ ነው።ለመሥኖ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ውሃ በክፍያ ሥርአት ውስጥ ይለፍ ሲባል በአንድ ሜትር ኪዩብ ውሃ ወይንም አንድ በርሜል ውሃ የሚከፈለው ምን ያህል ይሁን የሚል ሥርአት የለም።ምንም እንኳን ለመሥኖ የሚውለው ውሃ በተፈጥሮ የተገኘ ቢሆንም መጠቀም በሚገባው ልክ ጥቅም ላይ እንዲውል ሲደረግ፣ሥርአት ሲበጅለት ውሃ በዘፈቀደ ጥቅም ላይ ማዋልን ያስቀራል።አይባክንም ሁሉም ዋጋ ይሰጠዋል።የሚገኘው ገቢ መልሶ ለተፈጥሮ ጥበቃና እንክብካቤ ልማት ሲውል የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብም ከደለል ይጠበቃል።የመንግሥት ወጭም ይቀንሳል።በመሆኑም ለመሥኖ የሚውለው ውሃ የክፍያ ሥርአት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
ኢትዮጵያ የውሃ ማማ እንደሆነች ይነገራል።ነገር ግን እንደተባለው ናት?ለአቶ ደጀኔ ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር።እርሳቸውም በምላሻቸው ኢትዮጵያ የውሃ መነሻ ማማ እንጂ የውሃ ሀብት የሚባለው ለህዝቡ የሚካፈለው አሁን ባለው መረጃም የነፍስወከፍ ውሃ ከአንድ ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ በላይ አይሆንም።እንደውም የውሃ እጥረት ካለባቸው ሀገሮች ውስጥ ትመደባለች።ውሃ ማማ ሲባል ከከፍተኛ ቦታ ውሃ ይመጣል ማለት ነው። ሰባት ወንዞች ወደውጪ ነው የሚፈሱት። ከዚህ አንፃር ከፍተኛ ሀብት አለ ተብሎ የሚነገር አይደለም።ኢትዮጵያን የሚበልጡ ብዙ ሀገሮች አሉ። ኮንጎን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በክረምት ጊዜ የሚዘንበውን ውሃ በአግባቡ መያዝ ከተቻለ ጥቅሙ የጎላ በመሆኑ እዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል። ህዳሴ ግድብ የተፈጥሮ ውሃን በመያዝ ትልቅ ድርሻ አለው፤ ስለዚህ ግድቦችን መሥራት ጠቃሚ ነው።ይህ ሲሆን የውሃ ልማቱ ያድጋል።ከከርሰምድርና ገፀምድር የውሃ ሀብት የገፀምድሩ 50 በመቶ የሚሆነው ሀብትም በአባይተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣አጠቃላይ አመታዊ ሀብቱም 123 ቢሊየን ሜትሪክ እንደሚሆን ይገመታል።ከዚህ ውስጥም ወደ 54 በመቶ የሚሆነው የገፀምድር ውሃ አባይ ውስጥ ነው የሚገኘው። ተከዜ፣ ባሮአኮቦ ሲደመር የናይል ፍሰቱን ወደ 70 በመቶ ከፍ ያደርገዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ከፍተኛው የውሃ ሀብት አባይ፣ ተከዜና ባሮ አኮቦ ተፋሰሶች ውስጥ ነው። ኢትዮጵያ በድምሩ ካሏት 12 ተፋሰሶች ውስጥ ደናክል፣ ኦጋዴንና አይሻ የተባሉት ደረቅ ተፋሰሶች ናቸው።የተቀሩት ሪፍትቫሊን ጨምሮ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ የወንዝ ተፋሰሶች ናቸው።የሚያስገርመው ነገር ከነዚህ ሁሉ ሀብቶች ሰባት ያህል ተፋሰሶች ወደ ውጭ የሚሄዱ መሆናቸው ነው። ከቀሩት ውስጥም ደረቅ ተፋሰሶች የተባሉት ናቸው።
ባለሥልጣኑ የተቋቋመበት አንዱ ምክንያትም ድንበር አቋርጠው የሚሄዱ ተፋሰሶችን ለመከታተል ነው። ይህንኑ የሚከታተል በባለሥልጣኑ አንድ ክፍል ተደራጅቷል። ባለሥልጣኑ የልማት ሥራውን በተቀናጀ መልኩ ለመሥራት ሲንቀሳቀስም ከአፈሩ፣ ከአየሩ፣ ከአካባቢው ጥበቃ ጋር ተቀናጅቶ የውሃ ሀብቱ ማዕከል ሆኖ ሌሎች የልማት ሥራዎች በተሻለ እንዲከናወኑ ለማስቻል ነው።እያንዳንዱ የተፋሰስ ልማት ሥራ እንደ ህንፃ ግንባታ ወይንም የቤት ሥራ ሁሉ በማስተርፕላን ነው የሚከናወነው።የተፋሰስ ዕቅድም ተነድፏል።ከዚህ ውስጥም አንዱ የአባይ የተፋሰስ ልማት ዕቅድ ይገኝበታል።በዕቅዱ መሠረትም ምን አይነት የዕርከን ሥራ መሰራት እንዳለበት በሳይንሳዊ መንገድ ከተቀመጠ በኋላ አርሶአደሩ በነፃ ጉልበቱ እንዲሰራ ይደረጋል። ልማቱ የታችኛውንም ተፋሰስ ያለማል። ይሄ በብዙ መጠን ወደ ወንዝ የሚገባውን ደለል በመቀነስ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተፋሰስ ልማቱ ባለሥልጣኑ በአባይ ላይ ብቻ ከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት ይደረጋል። ለአካባቢው ልማት የሚውሉ ችግኞችን በማዘጋጀት፣ ችግኞቹም ቅድሚያ በሚሰጣቸው የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲተከሉ በማድረግ ሥራዎች ይሰራሉ።በዚሁ መሠረት በተከናወነው ሥራ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ወደ 40 ሄክታር መሬት ችግኝ በመትከል የልማት ሥራ ተከናውኗል። በአባይ ተፋሰስ ውስጥ ብቻ ለሰባት አመት ሲከናወን የነበረውን ፕሮጀክት ጨምሮ ልማቱ ብዙ ውጤት አስገኝቷል።
በአባይ ላይ እየተሰራ ያለው ጣና ሐይቅ የግድቦች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ጣና ዙሪያ በአረንጓዴ በማልማት ከደለል ለመጠበቅ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። ዙሪያውን ወደ 246 ኪሎ ሜትር ወደኋላ የሚፈሰውን ታላቁ የህዳሴ ግድብንም በተመሳሳይ ዙሪያውን በማልማት ደለሉ አረንጓዴ ልማቱ ላይ እንዲቀርና ወደ ግድቡ እንዳይገባም በተመሳሳይ ሥራዎች ተጠናክረዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሚጠበቀው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ብቻ ሳይሆን፣ለቱሪዝም ኢንደስትሪውም መስህብ፣የአሣ ሀብትም የሚገኝበት በመሆኑ የተቀናጀ ፋይዳ ያለውና ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።ከዚህ አንፃር አረንጓዴ ልማቱ መጠናከሩ አጠያያቂ አይሆንም።
‹‹ከተፋሰስ ማስተርፕላን የሚወጣ የ15 አመት ዕቅድ ተነድፎ ወደ ትግበራ ተገብቷል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የተፋሰስ ልማት ሲሆን፣ሌላው የውሃ ሀብት አስተዳደርና ውሃ ሀብት መረጃ ነው።ምን ያህል የውሃ ሀብት እንዳለና የወንዝ ፍሰቱ ምን ይመስላል በየወንዙ ምን አይነትና ከየት አካባቢ ደለል ይገባል የሚል እራሱን የቻለ የመረጃ አስተዳደር ተዋቅሯል። በዚያው አግባብ የተቀናጀውን ልማት በተፋሰስ ውስጥ ያለውን የሚይዝልን የተፋሰስ ዕቅድ ነው።ዕቅዱም በጽህፈት ቤቶቻችንና በቅርጫፎቹ አማካኝነት ወደትግበራ የሚገባበትን ስትራቴጂ ወጥቶ የሥራ ማስኬጃ በጀት እየተጠበቀ ነው። እነኚህ በጀት የሚጠብቁ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሲሆኑ የአሣ ሀብቱን ፣ የቱሪዝም ኢንደስትሪውን በአጠቃላይ ተፋሰሱ ምን አለው፣እንዴትስ መጠቀም አለብን ከሚለው ጀምሮ በዝርዝር በመያዝ የተሻለ ልማት እንዲመጣ የሚያግዝ ዕቅድ ነው የተነደፈው››በማለት አብራርተዋል።
ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተናብቦ ለመስራት ስላለው እንቅስቃሴም አቶ ደጀኔ እንደገለጹት፤አንድ ዕቅድ፣ በጀት እና ሪፖርት ፕሮግራም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ውስጥ ዕቅድ ተዘጋጅቷል። በተፋሰስ ውስጥ ያገባኛል የሚሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ጽህፈት ቤቱ በማስተባብር ያወያያል። ምክክር እንዲያደርጉም ያደርጋል።እንዲህ ያለው አካሄድ ማን ምን ሰራ የሚለውንም እንዲናበቡ ያስችላል።
በተፋሰሱ ውስጥ ለአረንጓዴ ልማት ሥራው ምን ያህል ችግኝ እንደተዘጋጀና በጀት እንደተያዘ ይታያል። በአባይ ተፋሰስ ትልቁ የመሬት ድርሻ ወይንም 46 በመቶውን የሚወስደው የአማራ ክልል፣31 በመቶ ኦሮሚያ ክልል፣ቀጥሎ ደግሞ የቤኒሻንጉል ክልል ነው። በመሆኑም ክልሎቹ ዕቅዳቸውንና ክንውናቸውን በአካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤቶቻቸው በኩል በየአመቱ በሚያቀርቡት ይገመገማል። የመናበቡ ሥራ በዚህ መልኩ ይከናወናል።
በሐይቆች ላይም በተመሳሳይ የሚያከናውኑ ባለድርሻ አካላት አሉ። አባይ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ ዓረም ለመከላከል ወደ 18 የሚሆኑ ተቋማት በቅንጅት ሲንቀሳቀሱ ነበር። በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙሃንም ሚና እንዲኖራቸው ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር አከናውኗል። እስካሁን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የአረንጓዴ አሻራ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊየን ችግኞች በአባይ አካባቢ ተተክሏል። በሶስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርም ከዚህ ያላነሰ ዕቅድ ይተገባራል። በተፋሰስ ልማት ተቋም ብቻ 35ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የላይኛውና የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራትንም ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በጋራ የመልማትና የማደግ ዓላማ በመያዝ የምትንቀሳቀስ ሀገር መሆኗ ይታወቃል።በዚህ ረገድ የላይኞቹና የታችኞቹ የተፋሰስ ልማት ተጠቃሚዎች ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚናም አቶ ደጀኔ እንዳስረዱት፤ሳይንሱ እንደሚለው ሁሉም በጋራ ማልማት ይጠበቅባቸዋል።ጥቅሙ የጋራ በመሆኑ መሳተፍ ነበረባቸው።ልማቱ ወደነርሱ ሊሄድ የሚችለውን ደለል ነው የሚያስቀረው። አመታዊ የወንዙን ፍሰትም የተስተካከለ እንደሚያደርግላቸውም አልተገነዘቡም። በመስኖ በመጠቀምም ከኢትዮጵያ በተሻለ ድርሻ እንዳላቸው አላወቁም። አሁን ባለው ሁኔታ ሀገራቱ በልማቱ ለመሳተፍ ቀርቶ ኢትዮጵያም እንዳታለማ ለማደናቀፍ ነው ጥረታቸው። ኢትዮጵያ ያላት ብቸኛ አማራጭ በእጇ ያለውን ሀብት ማልማት ነው ።
‹‹ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆኑና ብዙ ዕድሎችንም የሚያስገኝ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።የሥራ ዕድልና ሌሎችንም ጥቅሞች ያስገኛል። ይሄን በመገንዘብ ሁሉም ሊንከባከበው ይገባል።በተለይም በዙሪያው የእርሻ ሥራ እንዳይከናወን፣የአካባቢ ብክለትን ማስቀረት። ህዝቡ አሁን ላይ እያከናወነ ያለውን የተፋሰስ ልማት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል››ያሉት አቶ ደጀኔ ማህበረሰቡ ችግኞች ሲተከሉ ውሃ እንዲገኝ፣ ንጹህ አየር ለመተንፈስ፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚረዳ መሆኑን ተገንዝቦ የጀመረውን መረባረብ እንዲያጠናክር መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2013