ከማልመሰጥባቸው ቃላት አንዱ ነው – ዲያስፖራ። ዲያስፖራ ከመጠሪያ ድምፁ ጀምሮ እስከነ ትርጉሙ ለጆሮዬም አይመቸኝም። ምን እንደሆነ አላውቅም ብቻ ቃሉን ከእኛ ከኢትዮጵያዊያን አንፃር ሳብላላው ካብ አይገባ ድንጋይ ይሆንብኛል። በተለይ አንዳንዴ እንደ መመፃደቂያ ተደርጎ ሲወሰድ ማየትና መሰማቱም ሊሆን ይችላል። ወይም፣ በተደረጉ ጥናቶች “ዲያስፖራ” በሚለው ስር ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ተካትታ አለማየቴም ሊሆን ይችላል። ወይም ከአጠቃላይ ትርጉሙ ጀምሮም ሊሆን ይችላል ብቻ ቃሉ አይመችም – እንደውም “ስደት የሚለው ይሻላል” ከሚሉት ወገን መሆንን ይመርጣል ይህ ብዕር። ለማንኛውም የእለቱ ርእሰ ጉዳያችን ይህ ባለመሆኑ እንዝለለውና ወደ ጉዳያችን – ወደ “ትውልደ ኢትዮጵያዊያን” (“ትቅደም”ም “ትውደም”ም ያሉት) እንዝለቅ።
ከዲያስፖራ (በግሪክኛ “διασπείρω” (diaspeirō)) ጋር ከመለያየታችን በፊት ግን እቺ በቅርብ ጊዜ የመጣ፤ ከ”አፍሪካ አሜሪካዊያን” እቅፍ ውስጥ ወጥቶ “ኢትዮጵያ አሜሪካዊያን” (በተለይ በአሁኑ የባይደን ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ጎልቶ የወጣ መነጠያ ነው) ሲባል “አቤት” የሚባለው ነገር ዛሬውኑ ቢቆም ተገቢ አይደለም ማለት አለመሆኑን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ይህ በሁለተኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መቀስቅስ ለዚህ ገጽ የበቃ ጽሑፍ ማለት የተፈለገው ጉዳይ ዝርዝር ሳይሆን ጥቅል፤ ውስብስብ ሳይሆን ግልፅና አጭር (ወይም፣ “ሾርት ኤንድ ፕሪሳይስ”) ነው። “ሾርት ኤንድ ፕሪሳይስ” ያደረግንበት ዋናው ምክንያት ደግሞ የጊዜ ጉዳይ ነውና ፍጥነት የግድ ነው!!! ታዋቂው የሬጌና የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ (ባለሙያዎቹ ናቸው ያሉት) ቴዲ አፍሮ “ወዳ’ገር ቤት …” እንዳለው …፤ ከዛ በፊትም ቦብ ማርሌይ …
በእርግጥ ይህ የ”ወዳ’ገር ቤት …” ጉዳይ አዲስ ሀሳብ አይደለም፤ ከመሬትና ሰማይ መላቀቅ ጀምሮ የነበረ ሲሆን ማስረጃችንም ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከዛም እያለ እያለ እስከ ሙዚቃው ድረስ የወረደ ሲሆን በተለይ በሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ (“ኤክሶደስ”) ነግሶ እስከኛዎቹ ወጣት ድምፃዊያን ድረስ ተገቢው ቦታ ተሰጥቶት ይገኛል። ወደ ተነሳንበት ከመሄዳችን በፊት፤ “ዲያስፖራ – ወዳ’ገር ቤት … ፍጠን!!!” በማለት ጽሑፋችንን የሰየምንበትን ምክንያት ቢያፀናልን አንድ “እንደ ወረደ መረጃ”ን እናስቀምጥ።
እንደ ድርጅቱ “Mapping of Ethiopian Diasporas Residing in the United States of America” (2018) ጥናት በአጠቃላይ አለማችን ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች የሚገኙ ሲሆን፤ በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አውስትራሊያ እና አፍሪካ ብቻ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ይገኛሉ። መረጃው በተናጠል ሲታይም ከአንድ ሚሊዮን በላይ በመካከለኛው ምስራቅ፣ ከ600ሺህ በላይ በአፍሪካ፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በሰሜን አሜሪካ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በአውሮፓ፣ አውስትራሊያ እና እሲያ ይገኛሉ።
መነሻችን ባለፈው ማክሰኞ የተጀመረው ሁለተኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መሆኑን ከላይ ገልፀናል። ያ ማለት በሌላ መንገድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ደረጃ 80 በመቶን እየዘለለ መሆኑን እየተናገርን ነው ማለት ነውና (“ውሾቹ ይጮሀሉ፣ ግመሉ ጉዞውን ቀጥሏል” እዚህ ጋር በትክክል እንደሚሰራ አየሁት) “ወዳ’ገር ቤት ….” ለማለትም ያበቃን እሱው ነው። በመሆኑም ከወዲሁ፣ 100 ከመሙላቱ በፊት ዝግጅት ያስፈልጋል ማለት ነው -”ወዳ’ገር ቤት ….”ን ስንፈክረውም ይህንኑ የማጠናቀቂያውን ምዕራፍ ተደግፈን ነውና ኋላ ውርድ ከራሴ …
እኛ (እንደ አገር) ስደትን የተቀላቀልነው አሁን ከ1960 መጨረሻ፣ በተለይም ከ70ዎቹ ወዲህ ነው (ለዚህም ነው ይህ ጽሑፍ “እኛ ለአቅመ ዲያስፖራ አልደረስንም” የሚለው – እስከሚታወቀው ድረስ በባርነት ተግዞም ይሁን ተገዝቶ አሜሪካንን ያቀና አበሻም የለም)። ሌላው ጎሞራው “ከጥንት ጀምሮ ስናየው የኖርነው …” እንዳለው፣ ሌላው ከጥንት ጀምሮ በስደት ነው የሚታወቅ የነበረው። ለምሳሌ አረቦች አገራቸው “ሀሎ … ስማ፣ የሰማህ ላልሰማ አሰማ … በተለያዩ አገራት ያላችሁ የአረብ ተወላጆች (አረባዊያን) በሙሉ … ነዳጅ ወጥቷልና ፈጥናችሁ ወዳ’ገራችሁ ግቡ፤ ፍጠኑ …” (ጥቅሱ ቀጥታ አይደለም) ብለው እስከ ጠሩበትና ዜጎቹም በተጠሩበትም ፍጥነት ወደ አገራቸው እስከተመለሱበት ቀን ድረስ እዚህ እኛ አገር ሳይቀር በስደት ኑሮና ቢዝነስ (ሱቅና የመሳሰሉት) ተግባራት ላይ ተሰማርተው ነበር። (ዛሬ ውጡልን ቢሉም ታሪኩ ግን ይህ ነው።)
ይህ ጽሑፍ “ሀሎ …… ነዳጅ ወጥቷልና ፈጥናችሁ ወዳ’ገራችሁ ግቡ፤ ፍጠኑ …” ለማለት አይደለም የተነሳው። ከላይ እንደተጠቀሰው በሁለተኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መቀስቅስ ለዚህ አቅመ ጽሑፍ የበቃ እንደ መሆኑ መጠን የሚያነሳውም ሀሳብ ስለ ነዳጅ መውጣት (እና መግባት) ሳይሆን ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (ዲያስፖራውንም ጭምር)ና ያለበት ሁኔታ ነው።
የሬጌው ንጉስ ቦብ ከስደት ወደ አገር ቤት መመለስ ተገቢና ጊዜ “አሁን” (ያኔ ማለት ነው) መሆኑን ከታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ይሁነኝ ብሎ በተዋሰው “Exodus” ዜማው ተጣርቷል። የተጣራበት ምክንያት ለምን፣ ማንን፣ ከየት፣ ወዴት …? እንደሆነ አገር ያወቀው፤ ፀሀይ የሞቀው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ … ጉዳይ ስለሆነ እንለፈው። የወቅቱ የአረብ መንግስትም “ሀሎ … ስማ፣ የሰማህ ላልሰማ አሰማ … በተለያዩ አገራት ያላችሁ የአረብ ተወላጆች በሙሉ … ነዳጅ ወጥቷልና ፈጥናችሁ ወዳ’ገራችሁ ግቡ፤ ፍጠኑ …” ያለበት ምክንያት “ሾርት ኤንድ ፕሪሳይስ” በሆነ መልኩ የተቀመጠ በመሆኑ እሱን ለማብራራትም አንፈልግምና ይዘለል። ባለፈው ማክሰኞ የተጀመረው ሁለተኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መጀመሩንና በሚፈለገው መልኩ (እንደውም በላይ) ጢም እያለ መሆኑን ማወጅ ግን፣ ከመረጃና ማስረጃው አዲስነት አኳያ፣ ተገቢ ነውና ይህንን እናበስራለን። መንግስትም ለተለያዩና ጉዳዩ ያገባናል (አያገባችሁምም) ለሚሉት በደብዳቤ “እንኳን ደስ አለን፤ እንኳን ደስ አላችሁ” ሲል ያሳወቀ እንደ መሆኑ መጠን እኛም ይሄንኑ እናጠናክራለን።
ይህን ጽሑፍ ለየት የሚያደርገው አረቦች “ሀሎ … ስማ፣ የሰማህ ላልሰማ አሰማ … በተለያዩ አገራት ያላችሁ የአረብ ተወላጆች በሙሉ … ነዳጅ ወጥቷልና ፈጥናችሁ ወዳ’ገራችሁ ግቡ፤ ፍጠኑ …” ተብለው እንደተጠሩት ሁሉ በየአገሩ (በወዳጅም በጠላትም አገራት) የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ይህንኑ ከአረቦች ለአረቦች የተላለፈውን “ኤክሶደስ” እነሱም ከወዲሁ በልባቸው እንዲጥፉትና በቀረችው የ20 በመቶ አፈፃፀም እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ማስታወሱ ነው። ወዳ’ገር ቤት …!!!!!!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2013