የሥራ ቅጥር ለቀጣሪው ተቋምም ሆነ ለተቀጣሪው ግለሰብ በትክክለኛ እና በግልፅ መመሪያ ተደግፎ መፈፀም እንደሚገባው አያጠያይቅም። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ ከመመሪያ ውጪ የሚፈፀም የቅጥር ሂደት የሚያስከትለው ውዝግብ እና የሚኖረው ኪሳራ ከባድ ነው። ሆን ተብሎም ሆነ ባለማወቅ ብዙ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ የሚካሄድ የቅጥር መሰረዝ ጉዳይ አጠያያቂ ሆኖ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ እንደሚያልፍ ነጋሪ አያሻም።
በቅድሚያ ሰራተኛ መድቦ፤ የፈተና ቁሳቁሶችን አዘጋጅቶ፤ ፈተና አውጥቶ እና ጊዜውን ሰውቶ ቅጥር ለማከናወን ብዙ ሥራ የሰራው ተቋም ቅጥር ሲሰርዝ ያ ሁሉ ድካም በኪሳራነት ይመዘገባል። በሌላ በኩል ለመቀጠር ማመልከቻ ከማስገባት ጀምሮ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው ለፈተና የቀረቡ ግለሰቦችም በጊዜ እና በገንዘብ የሚደርስባቸው ኪሳራ በላይ የሚደርስባቸው የሞራል ጉዳት ቀላል አይደለም።
በበርካታ መልኩ የሚፈጸሙ አድሏዊ የቅጥር አካሄዶች ቢኖሩም ለዛሬ የምንመለከተው ግን ‹‹ቅጥሩ ተሰርዟል ››በሚል ሰበብ የተፈጸመን አድሏዊ አሰራር እንመለከታለን። ይህ በደል እንደተፈጸመባቸው ከሚናገሩት ውስጥ ዶክተር አስማማው ቢሆነኝ እና አቶ ፍቅሩ በንቲ ይገኙበታል።
የመጀመሪያው የዶክተር አስማማው የቅጥር ውድድር ሂደት
ዶክተር አስማማው እንደሚናገሩት፤ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ወጣ። እርሳቸው እና ሌሎች ተወዳዳሪዎችም መረጃቸውን ካስገቡ በኋላ ምልመላ ተደርጎ፤ የፅሁፍ ፈተና ተፈተኑ። የፅሁፉ ፈተና ውጤት ከተገለፀ በኋላ ፈተናውን ላለፉት ተወዳዳሪዎች የቃል ፈተና ተሰጠ። በመጨረሻ ከ20 ቀናት ቆይታ በኋላ ውጤት ተገለፀ። በዛ ወቅት ሁለት ሰዎች ‹‹አልፋችኋል›› የተባሉ ሲሆን፤ ካለፉት ተወዳዳሪዎች መካከል ዶክተር አስማማው አንዱ መሆናቸው ተገለፀ።
የተለጠፈው ማስታወቂያ ‹‹ስራ ላይ ካላችሁ የሥራ መልቀቂያ ይዛችሁ መጥታችሁ ለመቀጠር መመዝገብ ትችላላችሁ›› የሚል እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር አስማማው፤ ማስታወቂያውን መሰረት በማድረግ በማለፋቸው ‹‹ጥሪ ተደርጎልኛል›› ብለው አምነው፤ ለመመዝገብ ወደ ዩኒቨርስቲው ማቅናታቸውን ይገልፃሉ። ሆኖም የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ሰው ሃብት ቢሮ ‹‹የእንስሳት ህክምና ትምህርት ክፍል ላይ ተወዳድራችሁ ያለፋችሁ ለቅጥር መመዝገብ አትችሉም ተብሏል። ›› መባላቸውን ያስታውሳሉ።
እነዶክተር አስማማው ‹‹የማንመዘገበው ለምንድን ነው? ›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ የሰው ሃብት ቢሮ የሰጣቸው ምላሽ ‹‹ተደውሎ እንዳትመዘግቡ ተብለናል›› ከማለት ውጪ ምክንያቱን ለመግለፅ ፈቃደኛ አልሆነም። ሆኖም ደዋዩ ወይም ቅጥሩ እንዳይፈፀም ያገደው ማን እንደሆነ ለማጣራት ሞክረው ያገኙት ምላሽ፤ የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ፕሬዚዳንት መሆኑ ስለተነገራቸው፤ በአካልም ሆነ በስልክ ግለሰቡን ለማግኘት አልቻሉም። በዛው ከተማ ቆይተው ከሁለት ቀናት በኋላ የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ፕሬዚዳንትን ሲያገኙ የተሰጣቸው ምላሽ ‹‹ቅጥሩ ላይ ቅሬታ ስለቀረበበት መመዝገብ አትችሉም።›› የሚል ነበር።
የቅጥሩ መሰረዝ
‹‹ያጠፋነው ምንድን ነው፤ ቅሬታውስ በግልፅ ለምን አይነገረንም›› በሚል ላቀረቡት ጥያቄ ‹‹የፅሁፍ ፈተና ስትፈተኑ ኮድ አልነበረውም። ›› የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። እንደዶክተር አስማማው ገለፃ፤ በእርግጥ የፅሁፍ ፈተናው ኮድ አልነበረውም። እዛው መልስ መስጫው ላይ ስማችሁን ፃፉ ይል ነበር። ስማችሁን ፃፉ በተባለው መሰረት እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ተፈታኞች ስማቸውን ፅፈው መልሱን ሰርተው ሰጥተዋል።
‹‹ ቅሬታ የተነሳው በእኛ ጥፋት ምክንያት አይደለም ። ኮድም ሆነ ሌላ ከፈተናው ሂደት ጋር የተያያዘ ጉዳይ የሚመለከተው ዩኒቨርስቲውን ነው። ስለዚህ ስህተቱን መውሰድ ያለበት ተቋሙ ነው›› የሚል ሃሳብ አንስተው የተከራከሩት ዶክተር አስማማው፤ በኋላም ‹ይጣራል› የሚል ምላሽ የተሰጣቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
በዋነኛነት ጉዳዩን የያዙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሲሆኑ፤ ፈተና አሰጣጡ ትክክል አይደለም የሚል ምላሽ የሰጡትም እራሳቸው መሆናቸውን ይናገራሉ። በመጨረሻ ‹‹በኮሚቴ ታይቶ፤ የፅሁፍ ፈተናው ተገቢውን አካሔድ እንዳልተከተለ ማረጋገጥ ተችሏል። ኮድ መሆን ነበረበት። በዚህ ምክንያት ቅጥሩ ተሰርዟል። ›› በሚል በቀጥታ ጥያቄውን ላቀረቡት እና በፈተናው ላለፉት ሰዎች ከመግለፅ ይልቅ በዩኒቨርስቲው የፌስ ቡክ ገፅ ላይ የፈተናው መሰረዝ ምክንያት ተገልፆ እንደነበር ዶክተር አስማማው ያብራራሉ። ውሳኔው ፈተናው በድጋሚ እንዲሰጥ የሚል ነበር ይላሉ።
እነዶክተር አስማማው በተሰጠው ውሳኔ ባለመስማማት ቅሬታቸውን ‹‹ፈተናው ተካሂዶ አልፋችኋል ካላችሁበት ቦታ ሥራ ለቃችሁ ኑ ከተባለ እና እኛም መልቀቂያ ይዘን በተቋሙ ከተገኘን በኋል እንደገና ፈተና ይካሄድ የሚለው ውሳኔ መተላለፉ አግባብነት የለውም። ›› በሚል ተደጋጋሚ ለዩኒቨርስቲው ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ ዩኒቨርስቲው ፈተናው በኮሚቴ ታይቶ ተሰርዟል ከማለት ውጪ ምላሽ ባለመስጠቱ፤ እርሳቸው እና ሌላም ፈተናውን ያለፉ ግለሰብ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ እና ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደር በደል ተፈፅሞብናል በማለት አቤቱታ ማቅረባቸውን ይገልፃሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ሂደት
አቤቱታ የቀረበለት የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም መርማሪ ዳናይት ዘሩ እንደሚናገሩት፤ በእርግጥም እነዶክተር አስማማው ቢሆነኝ ‹በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ህክምና ትምህርት ክፍል የመምህርነት ቅጥር ወጥቶ ተወዳድረው ማለፋቸውን ገልፀው፤ ጥሪ ከተደረገ በኋላ ወደ ተቋሙ በሄዱበት ወቅት የቅጥር ሒደቱ ባልታወቀ ምክንያት በዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ፕሬዚዳንት እንደታገደ እና ለጊዜው ቅጥሩ መፈፀም እንደማይችል ተገልፆላቸዋል።
ለዩኒቨርስቲው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምንም መፍትሔ ሳይገኙ መቆየታቸውን እና እንደውም አካዳሚክ ፕሬዚዳንቱ ለተቋሙ ሰው ሃብት ዳይሬክቶሬት በሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር ወዩ/13989/ 02-ኣካ/1 በተፃፈ ደብዳቤ ፈተናው እንደገና እንዲሰጥ በማለት ውሳኔ በማስተላለፉ አስተዳደራዊ በደል ያደረሳባቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ እነዶክተር አስማማው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ ማቅረባቸውን መርማሪ ዳናዊት ይናገራሉ።
እንደመርማሪዋ ገለፃ፤ ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 1142/2011 በተሰጠው ስልጣን እና ተግባር መሰረት ዜጎች ተፈፀመብን የሚሉትን አስተዳደራዊ በደሎች ተቀብሎ በመመርመር ተገቢውን የመፍትሔ ሃሳብ ሰጥቷል። በዚሁ መሰረት አቤት ባዮች ማለትም እነዶክተር አስማማው ሰኔ 06 ቀን 2011 ዓ.ም ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ምርመራ ሲያደርግ ዩኒቨርስቲው ቅጥር መሰረዙን የገለፀበት ምክንያት አንደኛው የፅሁፉ ፈተና ኮድ የለውም፤ ሁለተኛው ደግሞ ቃለመጠይቅ ሲደረግ በተመሳሳይ ሰዎች መሆን ሲገባው የተለያዩ ሰዎች ቃለመጠይቁን በማድረጋቸው ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ በመሆኑ ፈተናው ይሰረዝ መባሉን ለማወቅ ተችሏል።
አቤቱታ አቅራቢዎቹ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ድረስ ከመምጣታቸው በፊት ለወልዲያ ዩኒቨርስቲ ቅሬታ ሰሚ አካል ያቀረቡ ሲሆን፤ ቅሬታ ሰሚው ሲያጣራ ደግሞ ፈታኞቹ አዲስ በመሆናቸው የተፈጠረ ስህተት እንጂ ሆን ተብሎ የተፈፀመ አለመሆኑን ገልፆ፤ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ሲያቀርብ እርሳቸው ‹‹ቅጥሩ መሰረዝ አለበት›› ማለታቸውን ማወቃቸውን መርማሪዋ አመልክተዋል።
ተቋሙ ጉዳዩን ካጣራ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ሰኔ 2011 ዓ.ም ደብዳቤ ሲፅፍ፤ የወልዲያ ዩኒቨርስቲ በበኩሉ ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር ወዩ /7016/11-አስ/2011 ምላሽ የሰጠ መሆኑን መርማሪ ዳናዊት ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከዩኒቨርስቲው በተጨማሪ ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ጥያቄ ያቀረበ መሆኑን የሚናገሩት መርማሪ ዳናዊት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምንም እንኳ ለእንባ ጠባቂ ተቋም በደብዳቤ ምላሽ ባይሰጥም፤ ባለሙያዎችን ቦታው ድረስ በመላክ የማጣራት ሥራ በመስራት የተፈፀመውን ሁኔታ ማረጋገጥ መቻላቸውን አብራርተዋል።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትዕዛዝ
ከዚህ ቀድሞ ዶክተር አስማማው እንደገለፁት፤ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ብቻ ሳይሆን ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ጭምር በመሆኑ፤ ወዲያውኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፈተናው ተሰርዞ ሊደረግ የነበረውን አዲስ የቅጥር ማስታወቂያ እንዲቆም አስደርጓል።
በመሃል አቤቱታ ያቀረቡ ሰዎች ለደብዳቢያቸው ምላሽ ሳይሰጣቸው፤ ሌላ የቅጥር ማስታወቂያ መውጣት የለበትም ያለው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሁለት ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ወልዲያ ዩኒቨርስቲ በመላክ፤ ዋናው ኮሚቴ ከዩኒቨርስቲው የበላይ አመራሮች ጋር፤ ሌላኛው ኮሚቴ ደግሞ ከእንስሳት ትምህርት ኮሌጅ ሃላፊዎች ጋር የፈተናውን ሂደት እና የነበረውን ሁኔታ መረጃ ሰብስበው የማጣራት ስራ እንዲሰራ መደረጉን ዶክተር አስማማው ያስረዳሉ።
በኋላ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በፈተና አሰጣጥ ጊዜ የሚሳተፉ አካላት ተግባር እና ሃላፊነት የፈታኞችም ሆነ የተፈታኞችን ግዴታ መመሪያን በማየት ኮድ የመስጠት ሃላፊነት የተቋሙ መሆኑን ለይታችሁ አስቀምጡ በማለት፤ ኮድ መስጠት የተፈታኞቹ ሃላፊነት ሳይሆን የተቋሙ ሃላፊነት መሆኑን ገልፀዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ባካሄደው የማጣራት ስራ ተግባሩ የተፈፀመው ሆን ተብሎ አንድን ግለሰብ ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት ሳይሆን ፈታኞቹ አዲስ በመሆናቸው የተፈፀመ መሆኑን አረጋግጧል። ነገር ግን ተፈትነው ያለፉት ሰዎች ተጠርተው ከነበሩበት ተቋም ለቀው ተጎጂ በመሆናቸው መመለስ አለባቸው በማለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዩኒቨርስቲው ምላሽ ቢሰጣቸውም ዩኒቨርስቲው በፈተና ያለፉትን ሰዎች አልቀጥርም ብሎ እንደነበር መርማሪ ዳናዊት ያስረዳሉ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለፉት ሰዎች ቅጥር እንዲፈፀም ቢያዙም ዩኒቨርስቲው በጊዜው ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረታቸውን ዶክተር አስማማውም ይናገራሉ።
እንደዶክተር አስማማው ገለፃ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ‹‹ሰዎቹ ፈተናውን ወሰዱ። ፈተናውን ከወሰዱ በኋላ የቅሬታ ማቅረቢያ ጊዜ ነበር። የፅሁፍ ፈተናው ተካሂዶ ቃለመጠይቅ ተደርጎ አሥራ አምስት ቀን ከቆየ በኋላ ለመቀጠር ቅረቡ ከመባላቸው በፊት፤ ቅሬታ ማቅረብ ይቻል ነበር። ሆኖም በጊዜው ቅሬታ አልቀረበም። ስለዚህ ሰዎቹን ቀጥራችሁ እንድታሳውቁን›› ብሏቸዋል። በሌላ በኩል እንባ ጠባቂም በበኩሉ ቅጥር ይፈፀም የሚል ደብዳቤ የላከ ቢሆንም የደብዳቤውን ትዕዛዝ ላለመቀበል አንገራግረው እንደነበር ይገልፃሉ።
ከኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ የተላከ ደብዳቤ
በደብዳቤው ላይ እንደተገለፀው፤ የወልድያ ዩኒቨርስቲ የቀረበውን ቅሬታ የሚያጣራ ኮሚቴ በማቋቋም ውሳኔ የተሰጠበት ማስረጃ ልኳል። ማስረጃው እንደሚያመለክተው በኮሚቴው የተሰጠው ውሳኔ መነሻው ፈተናው መስጠት የነበረበት በኮድ ሲሆን፤ ነገር ግን ፈተናው በተካሄደበት ወቅት ፈታኞች ኮድ የሌለው ፈተና መፈተናቸው ብቻ ሳይሆን፤ ፈታኞች ለመፈተን የተጠሩት በድንገት ተመርጠው መሆኑ እና ፈተና የሚዘጋጅበት ቦታ ዘግይተው መድረሳቸው እንዲሁም በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ሥራውን ከመስራት ያለፈ አለመሆኑን በተጨማሪ ግለሰባዊ አስተሳሰብን ለማራመድ የሚቻልበት ሁኔታ አለመኖሩን አረጋግጧል።
በተጨማሪ ለዩኒቨርሲቲ ፈተና አዘገጃጀት ስርዕት አዲስ ስለሆኑ እና በአግባቡ ስለፈተና አሰጣጥ ስርዓት ገለፃ ስላልተሰጣቸው ክፍተቱ መፈጠሩን የኮሚቴው የማጣራት ሂደት ግኝት እንደሚያመለክት በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ውሳኔው ላይ መካተቱ ተብራርቷ። በመሆኑም ቀድሞ የቀረበው ቅሬታ ተጨባጭነት ያለው በመሆኑ ጥፋቱ ከዩኒቨርስቲው አሰራር ያፈነገጠ መሆኑ ስለተረጋገጠ፤ የጥፋቱ ተዋንያን በተዋረድ አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም መገለፁ በደብዳቤው ላይ ተብራርቷል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ኮሌጅ የእንስሳ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህራን ቅጥር የተሰረዘበት ምክንያት አግባብ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጭብጥ ይዞ መመርመሩን እና ተጠሪ መስሪያቤት ቅጥሩ የተሰረዘበት ምክንያት አንደኛው ፈተናው ኮድ ባለመኖሩ ቢሆንም ተፈታኞች ላይ ምን አይነት ተፅኖ እንዳሳደረ በግልጽ ባልተቀመጠበት ሁኔታ እና ኮሚቴው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ፈታኝ መምህራን ተመርጠው የተላኩት በድንገት በመሆኑና በመካከላቸው የነበረው መግባባት ስራውን ከመስራት ያለፈ ባለመሆኑ ግለሰባዊ አስተሳሰብን ለማራመድ እንዳልሆነ ያመኑበት በመሆኑ እንዲሁም ፈተና ኮድ እንዳለው እና እንደሌላው የማረጋገጥ የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ግዴታ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብሏል።
አቤት ባዮች ማለፋቸው ተረጋግጦ እና ከሚሰሩበት መስሪያቤት ህጋዊ መልቀቂያ አምጥተው ቅጥር እንዲፈፅሙ በማስታወቂያ ጥሪ ከተደረገላቸው በኋላ በቂ ማስረጃ ባልቀረበበት ማለትም ኮድ አለመኖሩ በፈተና ውጤቱ እና በእርማት ሂደቱ ተፅዕኖ ስለመፍጠሩ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ቅጥሩ እንዲሰረዝ ማድረጉ አቤት ባዮች ላይ የተፈፀመ አስተዳደራዊ በደል መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እንዳረጋገጠ በደብዳቤው ላይ በዝርዝር ተብራርቷል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራ ግኝት እና የመፍትሔ ሃሳብ
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራ ግኝትም እንደሚመለክተው፤ መስሪያቤት በግብርና ኮሌጅ የእንስሳት ህክምና ትምህርት ክፍል የመምህራን ቅጥር መሰረዙ አግባብ የለውም። እነዚህ ሰዎች ያለአግባብ ከነበሩበት ሥራ እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። ስለዚህ ቅጥሩ ይደረግ የሚል የመፍትሔ ሃሳቡን የያዘ ሶስት ገፅ ደብዳቤ በህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ለወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በመላክ ደብዳቤው በደረሰ በ30 ቀን ውስጥ ዩኒቨርስቲው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰባቸውን መርማሪ ዳናዊት ገልፀዋል።
ዶክተር አስማማው በበኩላቸው፤ እንባ ጠባቂም ሆነ ሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የፃፉትን ደብዳቤዎች አልፈፅምም ያሉበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ እርሳቸው ደግሞ ‹‹ አልፈፅምም ማለት ምን ማለት ነው?›› በማለት ወደ ፍርድ ቤት ሄደው እንደሚከሱ እና ቅጥሩ በፍርድ ቤትም ቢሆን እንደሚፈፀም በመግለፅ፤ ነገር ግን ተቋሙም ከሳሽ የሚሆኑት ዶክተር አስማማውም ለተጨማሪ ወጪ እንዳይዳረጉ ማለታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ባዘዘው መሰረት ዩኒቨርስቲው ቅጥሩን ለመፈፀም የተስማማ መሆኑን ያመለክታሉ።
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ፈተናው በ2011 ጥር አካባቢ ተካሂዶ፤ በ2012 ታህሳስ ቅጥሩ የተፈፀመ ሲሆን፤ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መስከረም ላይ ደብዳቤውን ቢፅፍም ዩኒቨርስቲው እስከ ታህሳስ ቅጥር ላለመፈፀም ሲያንገላታቸው እንደነበር ተናግረዋል።
የመደወላቡ ዩኒቨርስቲ የቅጥር ውዝግብ
ሌላው ከቅጥር ጋር ተያይዞ በተመሳሳይ መልኩ ችግር ያጋጠማቸው አቶ ፍቅሩ ባንቲ ናቸው። በህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም በመደወላቡ ዩኒቨርስቲ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በወጣው ክፍት የሥራ ማስታወቂያ መሰረት በሲቪል ምህንድስና ለአስተማሪነት ተወዳድረዋል። ዩኒቨርስቲው ለመደቡ ብቁ መሆናቸውን አውቆ ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ከቃለመጠይቅ በተጨማሪ በስልክ የቅሬታ ጊዜ ገደብ እስከ ታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከናወን መሆኑን እና በታህሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ያለፋችሁ በአካል ቀርባችሁ የቅጥር ፎርም እንድትሞሉ ተብሎ ተነግሯቸዋል።
ከተነገራቸው በኋላ ረዥም መንገድ ተጉዘው በተባለው ጊዜ ውስጥ በታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም የቅጥር ፎርም ለመሙላት ሲሄዱ የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ሃላፊ ለሴቶች የሚጨምር ድጎማ በትክክል አልተጨመረም በማለት፤ ሁለተኛ የወጣችው ሴት ማለፍ አለባት የሚል ቅሬታ ስለተነሳ የቅጥር ፎርም ከመሙላት ተከልክለዋል።
ጉዳዩ እንዲጣራ በቅሬታ ማመልከቻ ለዩኒቨርስቲው ማኔጅመንት አቅርበው ለሶስት ሳምንት ሆቴል ሆነው ቢከታተሉም ውሳኔ ሳይሰጣቸው በስልክ ውሳኔውን ተከታተሉ ተብለዋል። ሆኖም አቶ ፍቅሩ፤ በጊዜው ምላሽ ቢጠብቁም ስላላገኙ፤ ጉዳዩ እንዲጣራላቸው በቅሬታ ማመልከቻ ለዩኒቨርስቲው ማኔጅመንት አቅርበው ለሶስት ሳምንታት ሆቴል ሆነው ቢከታተሉም ምላሽ ስላልተሰጣቸው ‹‹ዝርዝር ነጥቦች እንዲጣሩልኝ ፤ ተገቢና አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠኝ እና የደረሰብኝ የገንዘብ የሞራል ፤ የጊዜ እና የጉልበት ኪሳራ ዩኒቨርስቲው እንዲከፍለኝ›› በማለት በመጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ቅሬታ አቅርበዋል።
በቀረበው ቅሬታ መሰረት ዩኒቨርስቲው በ15 ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ እና ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሪፖርት እንዲያደርግ የተፃፈውን ደብዳቤ በኣካል ሂደው ለዩኒቨርስቲው ቢሰጡም ውሳኔ ባለማግኘታቸው ኣስተዳደራዊ በደል እንደደረሰባቸው ጠቅሰው ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ አቅርበዋል።
አቶ ፍቅሩ ያቀረቡት አቤቱታ
በህዳር 03 ቀን 2011 ዓ.ም በመደወላቡ ዩኒቨርስቲ በወጣው ክፍት የስራ ማስታወቂያ መሰረት በሲቪል ምህንድስና ለአስተማሪነት መወዳደራቸውን ገልፀው፤ ዩኒቨርስቲው ለመደቡ ብቁ መሆናቸውን በህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ከቃለ መጠይቅ በተጨማሪም በስልክ የቅሬታ ጊዜ ገደብ እስከ ታህሳስ 08 ቀን 2011 ዓ.ም መሆኑን እና ከታህሳስ 09 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ያለፋችሁ በአካል ቀርባችሁ የቅጥር ፎርም እንድትሞሉ ተብሎ ከተነገራቸው በኋላ ረዥም መንገድ ተጉዘው በተባለው ጊዜ ውስጥ በታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም የቅጥር ፎርም ለመሙላት ሲሄዱ ‹‹የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ሃላፊ ለሴቶች የሚጨመር ድጎማ በትክክል አልተጨመረም›› በማለት ሁለተኛ የወጣችውን ሴት ማለፍ አለባት ብሎ ቅሬታ ስላነሳ የቅጥር ፎርም ከመሙላት መከልከላቸውን አመልክተዋል። የአቶ ፍቅሩን አቤቱታ ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ለመደ-ወላቡ ዩኒቨርስቲ እና ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ ያቀርባል።
የመደ–ወላቡ ዩኒቨርስቲ መልስ
ዩኒቨርስቲው በነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር mu-32/72/1068 ላይ በተፃፈ ደብዳቤ በሰጠው ምላሽ እንደገለፀው አቶ ፍቅሩ በንቲ በመደ ወላቡ ዩኒቨርስቲ ለኢንጅነሪንግ ኮሌጅ የመምህራን ቅጥር በህዳር 03 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባወጣው የስራ ማስታወቂያ መሰረት የተወዳደሩ መሆናቸውን በማስታወስ፤ ሆኖም በቅጥር ኮሚቴውና በኮሌጅ መካከል በነጥብ አያያዝ ላይ ልዩነት ተፈጥሯል ይላል።
ልዩነቱ ኮሚቴው በሲቪል ሰርቪስ መመሪያ መሰረት ለሴት ተወዳደሪ መጨመር ያለበት አዎንታዊ ድጋፍ 3 መቶኛ ነው ሲል ክፍት የስራ መደቡ የሚገኝበት ኮሌጅ ደግሞ እስከ ዛሬ ቅጥር ሲፈፀምበት በነበረው በዩኒቨርሲቲው የውስጥ መመሪያ መሰረት ለሴት ተወዳዳሪዎች የሚሰጠው ወይም የሚጨመረው አውንታዊ ድጋፍ 5 ነጥብ ነው ይላል::
ስለዚህ የዩኒቨርስቲው ማኔጅመንት በመጋቢት 27 ቀን 2011 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ መሰረት የአዎንታዊ ድጋፍ ነጥብ አያያዝ አወዛጋቢ በመሆኑ ወደ ፊት የቅጥር የውስጥ መመሪያ ሲፀድቅ የቅጥር ማስታወቂያ እንዲወጣ ሆኖ ለአሁኑ ግን ለክርክሩ መነሻ የሆነው ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ የስራ መደብ እንደተሰረዘ ዩኒቨርስቲው ምላሽ ሰጠ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ
ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሰኔ 14 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር ሳከት/አስ/ሪ/ጀዳ/8.91/785/11 በተፃፋ ደብዳቤ መሰረት ለሴቶች የሚሰጠው የማበረታቻ ነጥብ በተቋሙ የውስጥ መመሪያ መሰረት የትምህርት ክፍሉ አምስት በመቶ ሲጨመር ሰው ሃብት ልማት ዳሬክቶሬት ደግሞ በሲቪል ሰርቪስ መመሪያ መሰረት ሶስት በመቶ መሆን አለበት በሚል አለመግባባት ስለተፈጠረ የመደ- ወላቡ ዩኒቨርስቲው ማኔጅመንት በመጋቢት 27ቀን 2011 ባደረገው ስብሰባ የውስጥ መመሪያው የቆየ በመሆኑ መመሪያው እስኪስተካከል ድረስ ቅጥሩ የተሰረዘ በመሆኑ እና በቀጣይ በማስታወቂያ አዲስ ቅጥር እንዲፈጸም በማለት አስታውቀናል ሲል ሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራ
የቅጥሩ መሰረዝ አግባብነት ያለው እና ህጋዊ ነው ወይስ አይደለም በማለት ባካሄደው ምርመራ ዩኒቨርስቲው በሲቪል ሰርቪስ መመሪያ መሰረት የሚተዳደር መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ የቀረበው አቤቱታም መታየት ያለበት በሲቪል ሰርቪስ የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር በቁጥር ፐ/ሰ/ሚ30/ጠ10/91/158 በግንቦት 4 ቀን 2009 ዓ.ም ባፀደቀው መመሪያ መሆን እንደሚገባው ተቋሙ አረጋግጧል።
በዚህ መሰረት መመሪያው አንቀጽ 3 ላይ ስለአዎንታዊ ድጋፍ እንደተገለፀው ለሴት ተወዳዳሪዎች ከአገኙት ነጥብ ላይ ሶስት መቶኛ አዎንታዊ ድጋፍ እንደሚጨመር በግልፅ ተደንግጎ እያለ እና ጉዳዩ በዚህ መመሪያ መሰረት እልባት ሊሰጠው ሲገባ የዩኒቨርስቲው የውስጥ መመሪያ ለሴት ተወዳዳሪ አውንታዊ ድጋፍ 5 ነጥብ ነው በሚል የተፈጠረው አለመግባባት የህግ ድጋፍ የሌለው እና ከሲቪል ሰርቪስ መመሪያ ጋር የሚተጣረስ ነው።
በመሆኑም በህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም በወጣው የውድድር ውጤት መሠረት አቶ ፍቅሩ 59 ነጥብ 6 ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ የወጡት ሴት ተወዳዳሪ ደግሞ 58 ያገኙ በመሆኑ ለሁለተኛ ሴት ተወዳዳሪ 3 መቶኛ ማለትም የ58 ሶስት መቶኛ 1ነጥብ 74 ሲሆን ውጤታቸው ላይ ሲጨመር 59 ነጥብ 492 ስለሚሆን እና አቶ ፍቅሩን የማይበልጡ በመሆኑ መደወላቡ ዩኒቨርስቲ ቅጥሩ መፈፀም ሲገባው መሰረዙ ኣግባብ ባለመሆኑ አስተዳደራዊ በደል እንደደረሰ ተቋሙ አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመፍትሔ ሃሳብ
መደ-ወላቡ ዩኒቨርስቲ የአቶ ፍቅሩን ቅጥር ማካሄድ ሲገባው ከመመሪያ ውጪ በአዎንታዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ ግልፅነት የለም በማለት የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ትምህርት ክፍል የመምህራን ቅጥር መሰረዙ አግባብ ባለመሆኑ ቅጥሩ እንዲፈፀም በማድረግ ውጤቱን በ30 ቀናት ውስጥ ለተቋሙ እንድታስታውቁ እናሳስባለን፤ በማለታቸው እንባ ጠባቂ ተቋም በላከው ደብዳቤ መሰረት በአንድ ወር ውስጥ ቅጥሩ መፈፀሙን ምርመራ ያካሄዱት መርማሪ ዳናይት ዘሩ ገልፀዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2013