
አዲስ አበባ፦ የአሸባሪው ህወሓት አባላት በራያ ህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እያከናወነ እንደሆነ የራያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ራዴፓ/ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል መምህር እያሱ በርሄ አስታወቁ። መንግስት ንጹሀንን እንዲታደግ ጥሪ አቀረበ።
መምህር እያሱ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ መንግስት በድንገት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ተከትሎ በረሀ የነበሩ የጁንታው አባላት በራያ ህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እያከናወኑ ይገኛል።
ከአደጋው ያመለጡ ሰዎች ባደረሱን መረጃ እስካሁን ከሃምሳ በላይ ንጹሀን መገደላቸውን ያስታወቁት መምህር እያሱ፣ በዚህም ሰላሳ ሺ የሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ አማራ ክልል ቆቦ አካባቢ መሰደዳቸውን አመልክተዋል።
የአሸባሪው ህወሓት አባላት ዛሬም ድረስ በርካታ ሰዎችን የመንግስት ደጋፊዎች ናችሁ በሚል ለስቃይ እየተዳረጉ ነው። ሁለት ሺ የሚደርሱ የራያ ተወላጆች ቤታቸው ተቃጥሎ ንብረቶቻቸው ወድሟል ብለዋል።
የጁንታው አባላት ጫማ ጠራጊዎችን ሳይቀር የመከላከያን ጫማ ስትጠርጉ ነበር በማለት ድብደባና የአካል ማጉደል ፈጽመዋል። ህዝቡንም ሰልፍ ወጥታችኋል መከላከያን ውሃ አጠጥታችኋል በማለት እያሰቃዩና እየገደሉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ከቀናት በፊት በአንድ ኤፍ ኤስ አር አይሱዙና በአንድ ገልባጭ መኪና እንዲሁም በሌሎች ሚኒባሶች ሙሉ ወጣቶችን እናስተምራችኋለን፣ እናሰለጥናችኋለን በሚል በግዳጅ ወደ መሀል ትግራይ እንደወሰዷቸው ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት እነዚህ ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም፤ መከላከያ ደርሶ የሚያስጥላቸው ካልሆነ የእነሱም እጣ ፈንታ መጨፍጨፍ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን አስታውቀዋል።
አሸባሪ ህወሓት በራያ ህዝብ ላይ ሲያደርስ የነበረው ግፍ የትጥቅ ትግሉን ከጀመሩ አንስቶ ላለፉት አርባ አመታት የዘለቀ ነው። በእነዚህ ጊዜያት የራያ ህዝብ ከለም መሬቱ በተደጋጋሚ እንዲፈናቀል ተደርጓል፤ ካለ ፍላጎቱም ማንነቱን ተነጥቆ ቆይቷል ብለዋል።
በትጥቅ ትግሉ ወቅት ለእነሱ ተደርበው ከደርግ ጋር ሲዋጉ የነበሩ የራያ ተወላጅ ታጋዮችንም ካለበቂ ምክንያት እንዲሁ ካለበቂ ካሳ እንዲሰናበቱ ተደርጓል። አሁን ግን ይህ ግፍ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም ለዚህ ደግሞ ጊዜው አሁን መሆኑን አመልክተዋል።
መንግስት በወቅቱ በመግባት አስፈላጊውን ጥበቃ ካልተደረገለት የተጀመረው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ተባብሶ የከፋ ነገር ሊከሰት ይችላል ያሉት መምህር እያሱ፣ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል። ይህንን ማድረግ የማይችል ከሆነ በአካባቢው ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲከላከሉ ሊያስታጥቅ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊነቱን የማይደራደረው የራያ ህዝብ ዛሬም ከመንግስት የሚደረግለትን ጥሪ ተቀብሎ ራሱን ለመከላከልና የሀገሩን አንድነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑንም መምህር እያሱ አስታውቀዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም