
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስምንት ወራት በትግራይ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ላይ የተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ቢሆንም እሳት ለኩሶ፣ እሳት እየሞቁ ሌሎችን ማቃጠል እንደማይቻል አሁን ያለው ሁኔታ ለሌሎቻችንም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ በ2014 ረቂቅ በጀትና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንደገለፁት አገራችን አሁን ወዳለችበት ነባራዊ ሁኔታ እንድትገባ ህወሓት የፈጠራቸው አራት ዋና ዋና ወሳኝ ምክንያቶች በአገራችን ላይ ግልጽ አደጋ ደቅነው እንደነበር ጠቁመዋል።
የመጀመሪያው ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የፌደራል መንግስት ከዚህም ከዚያም የሚሰጠውን በጀትና ቀድሞ ያከማቸውን ሀብት በመጠቀም ከመከላከያ የሚስተካከል ተቋም በመገንባት እዚህ ያለውን ሃይል የማዳከም ስራ ሲሰራ እንደነበር የጠቆሙት ዶክተር ዐብይ፤ የሀገር ህልውና አደጋ የሆነውም ይኸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር ቅጥረኝነትና ቅጥረኞችን የማስፋፋት ባህል ማዳበሩ ሌላው ምክንያት ነው ያሉት ዶክተር ዐብይ፤ በዚህም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ቅጥረኞችን እያደራጁ ገንዘብ እየሰጡ እና እያስታጠቁ፤ አጀንዳ እየሰጡ በማሰማራት የትኛውም አካባቢ ሰላም እንዳይኖር በግልጽና በእቅድ የሚመራ ሙከራዎችን ሲያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም እነዚህ ሃይሎች በፕሮፓጋንዳ ቡድናቸው አማካኝነት አፈናቅለው ዜናውን የሚነግሩን እነሱ ነበሩ ያሉት ዶክተር ዐብይ፤ የስላቃቸው ክፋት ደግሞ ሰላማዊ ክልል እኛ ብቻ ነን ማለታቸው ነው ብለዋል። “እኛ ነን የምንሻለው፤ እኛ እያለን አትበጣበጡም፤ እኛ እንምጣልህ” አይነት እምብዛም ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ ያልሆነ ግብዣ ለመጋበዝ ሞክረዋልም ብለዋል።
ሶስተኛውና አደገኛው ነገር የትግራይን ህዝብ ለጦርነት መቀስቀሳቸው ነው ያሉት ዶክተር ዐብይ፤ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ምንም ያላደረጉለትን ህዝብ ለጦርነት መቀስቀስ ትልቁ ስህተታቸው ነው ብለዋል። በመጨረሻም ሰሜን እዝ ላይ የፈጸሙት ተግባር የመጨረሻው ትልቁ የጥፋታቸው ጥግ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ያም ሆኖ ግን መንግስት ከብዙ ትዕግስት በኋላ የገባበት የህግ ማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት፤ ውጤቶች ውስጥ አንዱ የችግሩ ተጠያቂዎችና አመንጪዎች ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፤ ለህግ ቀርበዋል፤ የተቀሩትም ዳግም እንዲህ አይነት ጥፋት እንዳያጠፉ ሆነዋል።
በዚህም መሰረት የሰሜን እዝን ማውጣት መቻሉ፤ ትጥቅ እንዲመለስ መደረጉ፤ ወደጎንደር፣ ባህርዳር እና አስመራ የሚተኮስ ሚሳኤል አለመኖሩ ከስኬቶቹ ውስጥ ዋነኞቹ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ መከላከያ ሰራዊት ሃገራዊ ቁመና ይዞ ጠንካራ ሆኖ እንዲወጣ በምንም መንገድ የማይገኝ እድልና ልምድ የሰጠ እንደነበር ዶክተር ዐብይ ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል፣ ግጭት ለመፍጠር፣ ለመለያየት የነበረው ፍላጎት ዜሮ ሆነ ባይባልም በከፍተኛ ደረጃ ውጤት ማምጣቱን ዶክተር ዐብይ በማብራሪያቸው አንስተዋል።
ዶክተር ዐብይ “ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ ብዙ ድካም ደክመናል። በደከምነው ልክ 40 ዓመት የተዘራውን የዘረኝነት መርዝ ልናጸዳ አልቻልንም። የዘረኝነት መርዙ ሌሎች ተጨማሪ ጊዜዎችንና ሁኔታን ይፈልጋል” ሲሉም የጥፋት ቡድኑ ምን ያህል የከፋ ጉዳት እንዳስከተለ አብራርተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም