የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ባሳለፍነው እሁድ በሚሊኒየም አዳራሽ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ና ደጋፊዎች በተገኙበት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያካሂድ፤ የክለቡን የ2010 ዓ.ም የሂሳብ ምርመራ ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ዘመድኩን አዳነ እንደተናገሩ፤ ክለቡ በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ምንጮች 49 ሚሊዮን 717ሺህ 438 ብር ገቢ ሰብስቧል ። አጠቃላይ ወጪው ደግሞ 44 ሚሊዮን 251 ሺህ 602 ብር ሆኖ እንደተመዘገበ ገልጸው፤ ክለቡ ከወጪ ቀሪ 5 ሚሊዮን 465ሺህ 835 ብር ገቢ አስመዝግቧል ብለዋል። ክለቡ በነበረው የፋይናንስ እንቅስቃሴ መሰረት ለመንግሥት የታክስ ግብር ብር 7 ሚሊዮን 554ሺህ 494 ብር ገቢ ማድረጉን በሪፖርቱ ላይ ጠቅሰው፤ የማኅበሩ አጠቃላይ ሀብት 97 ሚሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል።
የስፖርት ማኅበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ንዋይ በየነ በበኩላቸው፤ የ2011 ዓ.ም የሥራ ዘመን ዝርዝር ዕቅዶችን መሰረት አድርገው የክለቡን የፋይናንስ አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱም የሚሠሩት ሥራዎች የክለቡን የፋይናንስ ምንጮች ማስፋት እና ማጠናከር፣ የማርኬቲንግ፣ ፕሮሞሽን እና የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ማጠናከር፣ በውድድሮች የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እና ሌሎች ተያያዥ የፋይናንሱን አቅም ለማጎልበት ሊሠ ሩ የታቀዱ ውጥኖች እንደሆኑ አስረድተዋል። በተለይ የአክሲዮን ሽያጩ ተግባራዊ ማድረጉ ክለቡ የገቢ ምንጩን ለማሳደግ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ዋነኛው መሆኑንም አክለው ገልጸዋል ።
እንደ አቶ ንዋይ ማብራሪያ፤ የክለቡን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ የአክሲዮን ሽያጩን የተመለከተ ጥናት በሙያተኞች አስደርጓል። በዚህም መሰረት አክሲዮኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሼር ካምፓኒ የሚል ጊዜያዊ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ አጠቃላይ የ244 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይኖረዋል። የአክሲዮኑ ሽያጭ መነሻ ዋጋም አንድ ሺህ ብር ይሆናል። ከመጋቢት 23 ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጎ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሽያጭ የሚከናወን መሆኑንና ዝርዝር መረጃውም በቀጣይ እንደሚገለጽ ታውቋል።
የክለቡን ገቢ ከሚያሳድጉ አማራጮች አንዱ የማሊያ ሽያጭ እንደመሆኑና የማሊያ አቅርቦቱ ፍላጎቱን ያገናዘበ አይደለም። በ2010 ዓ.ም የደጋፊውን ፍላጎት ለማርካት ባይችልም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የተመረቱ ከ13 ሺህ በላይ ማሊያዎች ሽያጭ ተከናውኗል። የማሊያው አቅርቦት የደጋፊውን ፍላጎቱን ያላላ እንደመሆኑ ክለቡ ቀጣይ በተሻለ የደጋፊውን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ማሊያዎች የሚቀርቡ መሆኑንና በእቅድ መያዙን አስታውቀዋል ።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች በኩል የውጭ ተጫዋቾች የዝውውር ሂደት እና የሚመጡበት መንገድ እንዴት ነው? የቴሌቪዥን ስርጭቱ ይጀመራል ቢባልም እስካሁን አለመጀመሩ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ለቦርዱ አመራሮች ቀርበዋል። የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረመስቀል በሰጡት ምላሽ፤ ክለቡ የሚያስፈርማቸውን የውጭ ተጫዋቾች ብቁ ባለሙያዎችን ያሉበት ሀገር ድረስ በመላክ ምልመላ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሠልጣኞቹ ይጠቅማል ሲሉ ይፈርማሉ። ተጫዋቾቹ እንደተጠበቁ ሳይሆኑ ሲቀር እናሰናብታለን ብለዋል።
እንደአቶ አብነት ማብራሪያ፤ በእግር ኳስ የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው የሚከሰቱት። አሁንም በአሠልጣኙ ምርጫ የውጭ ተጫዋቾች በማስመጣት በውድድር ዓመቱ ሁለተኛው ዙር ላይ የሚካተቱ ይሆናል። ሌሎች ስፖንሰር አድራጊዎች ከክለቡ ጋር ለመሥራት ከፈለጉ በራችን ክፍት ነው። ሆኖም፤ እንደ ቢ ጂ አይ ያሉ ባለውለታዎችን መርሳት አይገባም። « ቢ ጂ አይ እስካሁንም በስፖንሰር ሺፕ በየዓመቱ 35 ሚሊዮን ብር ይከፍላል። ይህ እንደቀላል መወሰድ የለበትም። አሁን ከደርባን እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አዲስ ውል ተዋውለናል። ይህ ከስፖንሰር የምናገኘውን ገቢ ክለቡን ያሳድጋል» ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ አብነት አክለው፤ የቴሌቪዥን ስርጭትን በተመለከተ እየሠራንበት ነው። ቀስ በቀስ ጥናቱን ስንጨርስ ወደሚቀጥለው ሥራ እንገባለን። ነገር ግን መጀመራችን የማይቀር መሆኑን አረጋግጣለሁ ብለዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው የተነሳው ሌላው ጉዳይ ክለቡ እያስገነባው የሚገኘው ስታዲየም የተመለከተ ነበር። በተሰጠው ምላሽም፤ ክለቡ ከአያት መንደር በ63 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ስታዲየም ለማስገንባት ጀምሮ ግንባታው 2 በመቶ ከደረሰ በኋላ መቋረጡን፤ ምክንያቱም የፋይናንስ አቅም ማነስ መሆኑንና የተቋረጠ ውንም ሥራ ለማስጀመር መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ቦሌ የሚገኘው የልምምድ ሜዳ ለልማት በመፈለጉ ምክንያት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስታዲየም መገንቢያው አጠገብ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ምትክ ቦታ መገኘቱን አስታውሰው፤ የቀድሞ የክለቡ የቦርድ አባል የነበሩት ባለሀብቱ አቶ ጀማል የልምምድ ሜዳውን፣ የተጫዋቾችን ማረፊያ፣ የመታጠቢያ ሻወር እንዲሁም ሌሎች የሚያስፈልጉትን ወጪዎች በሙሉ እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል። ደርባን ሲሚንቶም የሲሚንቶ አቅርቦቱን እንደሚሸፍን ከሶከር ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ዳንኤል ዘነበ