የ8ኛው ዓመት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር «የታላቁ ህዳሴ ግድባችን መጠናቀቅ ብሄራዊ ኩራታችን» በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውድድሩ ዝግጅት ዙሪያ ትናንት በጎልደን ቱ ሊፕ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የፅህፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም እንደተናገሩት፤ የ8ኛውን ዓመት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በዐል ምክንያት በማድረግ ከየካቲት 22 እስከ 24 ዓ᎐ም ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል። የእግር ኳስ ውድድሩ ዋነኛ ዓላማ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያና በግድቡ ዙሪያ ህዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር መሆኑን ጠቅሰው፤ ውድድሩ ብሄራዊ አንድነትን ያጠናክራል፤ የስፖርት ቤተሰቡ በህዳሴው ግድብ ላይ ያለውን ተሳትፎም ያሳድጋል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከውድድሩ የሚገኘው ገቢ ለግድቡ ግንባታ እንደሚውል ገልጸው፤ በስድስት ዙር ውድድርም 1.6 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል። በዘንድሮው ውድድርም ከስታዲየም ቲኬት የሚገኘው ገቢ በተመሳሳይ ለግንባታው ገቢ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል።
ብሄራዊ መግባባትን መፍጠር ከተቻለ፣ የአገርን ሰላም በአንድነት ማስጠበቅ ከተቻለ ገንዘቡን መሰብሰብ አዳጋች አይደለም የሚሉት አቶ ኃይሉ፤ የውድድሩ ቀዳሚውና ዋነኛው አላማ በውድድሩ ብሄራዊ መግባባቱን ማጠናከር ነውና የስፖርት ቤተሰቡ ውድድሩን እንዲታደም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ በበኩላቸው፤ የስፖርት ቤተሰቡ ውድድሩን ሲመለከት ስለ ግድቡ ይመለከተኛል የሚል እሳቤ በመያዝ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያደርገው ተናግረዋል። በእግር ኳስ ውድድሩ አራት ክለቦች፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አዳማ እና ሲዳማ ቡና በውድድሩ ይሳተፋሉ። ክለቦቹ የተመረጡበትም ባላቸው የደጋፊ ብዛት፣ በውድድሩ ቀደም ሲል የነበራቸውን የተሳትፎ ልምድ፣ በወቅታዊ አቋም መሰረት በማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል።
በእለቱ የእጣ ድልድል የተደረገ ሲሆን የካቲት 22 በአዲስ አበባ ስታዲየም 9 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ፤አዳማ ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ሰዓት ይጫወታሉ። የሁለቱ ጨዋታ አሸናፊዎች ለፍጻሜና ተሸናፊዎች ለደረጃ የካቲት 24 ቀን በሚያደርጉት ጨዋታ ውድድሩ ይጠናቀቃል። ቀደም ሲል በተደረጉ ውድድሮች ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ጊዜ ዋንጫ ሲያነሳ፤ ወላይታ ዲቻ ሁለት ጊዜ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ጊዜ ዋንጫ ማንሳታቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ዳንኤል ዘነበ