የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ሚናው የጎላ እንደሆነ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ገለፀ።
የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል «የባህል ስፖርት ተሳትፎአችን ለሰላምና ለአንድነታችን» በሚል መሪ ቃል ከካቲት 16 እስከ 24 ዓ.ም በአምቦ ከተማ አዘጋጅነት የሚካሄደውን ውድድር በተመለከተ በትናንትናው እለት መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አሰፋ እንደተናገሩት፤ የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል አንዱን ክልል ከሌላው ማገናኘትንና የልምድ ልውውጥ መፍጠርን አላማ ያደረገ ስፖርታዊ ክንውን ነው። ይህም በኢትዮጵያ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የእርስ በአርስ ቅርርብ ይፈጥራል ብለዋል።
እንደ አቶ ሰለሞን፤ የስፖርቱ ክንውን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል። ውድድሩና ፌስቲቫሉ የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ውድድሮቹን በብቃት የሚመሩ ዳኞችን አሰልጥኗል። ፌዴሬሽኑ ለባህል ስፖርት ኢንስትራክተሮችና በከፍተኛ ደረጃ ለሚገኙ ዳኞች የዳኝነት ስልጠናዎችን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር እንዲሰጥ አድርጓል::
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ በላይነህ ሀይሌ በበኩላቸው፤ ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሚካሄደው 16ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 12ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በ13 የስፖርት አይነቶች ይካሄዳል። እነዚህም፤ ትግል፣ ገና ፣ በገበጣ፣ ፈረስ ጉግስ፣ ፈረስ ሸርጥ፣ ኮርቦ፣ ድብልቅ ኮርቦ፣ ሻህ፣ ቡብ፣ ሁሩቤ ፣ ቀስት ፣ ድብልቅ ቀስት እና ባህላዊ ጨዋታዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
አቶ በላይነህ አክለውም፤ በአምቦ ከተማ በሚካሄደው 16 ኛው የባህል ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ላይ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ውጪ ሁሉም ክልሎ እና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ ይሆናሉ። ተሳታፊ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የየራሳቸውን ውድድሮች እንዳጠናቀቁ ታውቋል። ከ900 በላይ ስፖርተኞች ይሳተፉሉ ተብሎም ይጠበቃል። የዘንድሮው ውድድር በ‹‹ቀስትና በኮረቦ ድብልቅ›› ወንድና ሴት ተደባልቀው የሚጫወቱበት የስፖርት ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ በመሆኑ ውድድሩንና ፌስቲቫሉን ልዩ እንደሚያደር ገው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ዳንኤል ዘነበ