ቅድስት ሰለሞን
አንድን አገር ለማቆርቆዝ የሚከፈለው ዋጋ አንዳንዴ ግርም ይለኛል፤ አግራሞቱ ደግሞ ባስ የሚለው አቆርቋዡ አካል ሥራዬ በማለት ጉዳዩን በረጅም እቀድ ይዞ ለዓመታት ሲንከላወስ በማስተዋሌም ጭምር ነው። በተለይ ደግሞ በአንዲት ሉዓላዊት በሆነች፤ ግን ደግሞ በኢኮኖሚ ባልፈረጠመች አገር ላይ ያን ያህል ውርጂብኝ ለማውረድ የምዕራባውያንም የግብፅም መሸቀዳደም ከአግራሞትም በላይ የሚሆንብኝ ጊዜ ብዙ ነው።
ይህን ሲያደርጉ እቅዳቸው ግቡን ይምታላቸው እንጂ ስለአካሄዳቸው ትክክለኛነት ቁብ የሚሰጡት አይደለም። የትኛውንም መንገድ የተከተለ ቢሆንም በሰው ቁስል እንጨት ሰደው በግፍ የተሞላ ስኬትን ማጣጣም ነው የሚፈልት። እንዚህ አካላት እርስ በእርሳችን በማባላት ኢኮኖሚያችን እንዲዳካም የማይቧጥጡት ተራራ የለም። አንዱን በአንዱ ላይ በማስነሳት ኢትዮጵያ ጉዳዬ ብላ የያዘቻቸውን ምርጫ 2013 እና ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳታሳካ አለኝ የሚሉትን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት እፈጽማቸዋለሁ በማለት ወገቧን ሸብ አድርጋ በአንኳርነት ከያዘቻቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በአገር አቀፍ ደረጃ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ያካሄደችው ምርጫ ዓይናቸው እያየ በስኬት ከማጠናቀቋም በላይ የብዙዎችን ቀልብ የሳበችበት ሳምንት ሆኖ ማለፉም የአደባባይ ምስጢር ሆኗል።
ኢትዮጵያ የሚያስቧትን ያህል አትቆረቁዝላቸውም እንጂ ባሳለፍነው ምርጫ 2013 ብዙዎቹ አቆርቋዦቿ የጠበቁት ቀርቶ ያልጠበቁት በመሆኑና አሉታዊ ትንበያቸው ስላልሰመረ ስጋት ብጤ ጎሸም አድርጓቸው እንዳለፈም አያጠራጥርም፤ ምክንያት ብትሉኝ ደግሞ በምርጫው ዕለት ጥቂት በማይባሉ የምዕራባውያን አገራት የሚተዳደሩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን፤ የመረጃ መቀበያና ማቀበያ መሳሪያዎቻቸውን አፈሙዝ ወደኢትዮጵያ ወድረው ክፉ ክፉውን ለመቃረም አጥብቀው ቢሹም፤ የልባቸው ሊደርስ የሚችል መረጃ ለማግኘት ቀርቶ በተቃራኒው ሊሰሙት የማይፈልጉትን እና የሚያንገሸግሻቸውን ሁነት ለመጋት ብሎም ለማጣጠም መገደዳቸው ነው።
በተለይ በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያ በርካታ ተግዳሮት ያጋጥማታል በማለት አስቀድመው የተነበዩ ቢሆንም፤ ትንቢታቸው ግን ሊሰምር አልቻለም። ይልቁኑ ኢትዮጵያውያኑ ከመቼው ጊዜ በላይ የሰላም ዘብ በመሆን በየትኛውም ጥግ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት ላይ የጀመረው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ረፋድ ላይም ሲያዩት በሰከነ እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሲካሄድ፤ አመሻሽ ላይ ይኸው ስክነቱ ሲቀጥል፤ አልፎ ተርፎ ሁሉም ካርድ ያወጣ ዜጋ ሳይመርጥ እንዳያልፈው በሚል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ አሰጣጡ ማብቂያ የሆነው የምሽት 12 ሰዓት ገደብን ወደ 3 ሰዓት ከፍ ማድረጉን ተከትሎ ሲካሄድ የነበረውም ምርጫ ሰላም ሆኖ ሂደቱ ያለምንም ችግር መጠቃለሉን ሲያዩ ውለዋል። ድካም ይሏል ይህም አይደል!
እነሱ ዓላማቸው የረጅም ጊዜ ነው፤ ቢሆንላቸው ኢትዮጵያን ማዳከም ነው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት ኢትዮጵያን ማዳከም ግን ትርፉ ድካም ነው። ኢትዮጵያ፣ ክንዳችን የፈረጠመ ነው በሚሉ አገራት ስትኮረኮም ይበልጥ እየጠነከረች በመምጣት ላይ ትገኛለች። ያሻቸውን ነፈጓት፤ የወደዱትንም ተነበዩባት፤ ያስደሰታቸውን ጫኑባት፤ ኢትዮጵያ ግን መሰረቷ ሊናጋ አልቻለም። መሰረቷ ደግሞ የጸና ሲሆን፣ ለመጽናቱ የአንበሳውን ድርሻ በመጫወት ላይ ያለው ዜጋዋ ብሎም መንግሥት ነው።
ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ የሚባክን ተጨማሪ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ የላትም፤ ሁሉም የየራሱ ድርሻ ተሰጥቶታል። ምርጫ 2013ን ለብዙዎች እንደ ሬት መርሮ ቢያጥወለውላቸውም በማይታመን መልኩ በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል። ይህ ግን እንዲሁ በዋዛ የመጣ ሳይሆን በተከናወነ ከፍተኛ ተግባር ነው። ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላምን ተርቧል፤ በመሆኑም ነው በአገር አቀፍ ደረጃ ሲስተጋባ የነበረው የህዝብ አስተያየት ሰላምን በማስቀደም አንድ ዓይነት ሆኖ የተደመጠው።
በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት ኢትዮጵያ ዋና ጉዳዮቼ ናቸው ብላ ከያዘችው ሁለት ታላላቅ ጉዳዮች መካከል ምርጫ አንዱ እንደመሆኑ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አከናውና ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ቁርጠኝነቷን በሚገባ አሳይታለች፤ ቀጣዩ የሁላችንም የልብ ትርታ የሆነውና ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ ብቻ የቀረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው።
የህዳሴ ግድባችን የጥቂቶቻችን አሊያም የመንግሥት ድርሻ ብቻ እንዳልሆነ የመሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ ያለንን በመለገስ እያደረግን ባለው ትብብር አሳምረን የምናውቅ ነን። ትልቅ ጉዳያችን ነው ብለንም የየበኩላችንን አሻራ ማኖር ከጀመርንም ድፍን አስር ዓመት ሞልቶናል። እኛ እንደ ዓይን ብሌናችን የምናየውን ይህን ምልክት የሆነውን ግድባችንን ሌሎች ዓይኑን ለማውጣት ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ግን ትርፉ ድካም ብቻ ሆኖባቸዋል። አገር ቤት ካለው ወሮበላ ጀምሮ በውጭ አገር እስካለው ባንዳ ድረስ በመጠቀም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍና አገራችን ሲጠሯት አቤት! እንድትልላቸው አጥብቀው ቢሹም በድካም ዛሉ እንጂ ኢትዮጵያን ማዳካም አልሆነላቸውም።
አሁን ጊዜው ቀርቧል፤ የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌቱ እንዳይሳካ ብዙዎች ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በተለይም ግብፅ የውጭ አገራት ጣልቃ እንዲገቡላት ያልረገጠችው ደጅ የለም። ከአረብ ሊግ እስከ የተባበሩት መንግሥታት፤ ከአንዳንድ አፍሪካ አገራት እስከ አሜሪካ ድረስ እግሯ እስኪነቃ ተጉዛለች፤ ሃሳቧንና የእርዱኝ አቤቱታዋን አንዴ በአካል በመገኘት፤ ሲላት ደግሞ በቃላት ከሽና እና በኤንቨሎፕ አሸጋ ለክፉ ቀን ይሆኑኛል ወዳለችው ልካለች። ነገር ግን ያተረፈችው ነገር ቢኖር እንደፈለገችው ኢትዮጵያን ማዳከም ሳይሆን ራሷ መድከምን ነው።
የኢትዮጵያውያን ትኩረት ወደምርጫው እንደነበር ሁሉ አሁን ደግሞ ወደ ህዳሴ ግድቡ ሊሆን የግድ ነው። ትኩረት የምናደርግበት መንገድ ግቡ አንድ ዓይነት ቢሆንም ሁሉ የየድርሻውን መውጣት የሚያስችለውን ሥራ መከወንም ይጠበቅበታል። አንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዛሬም ድጋፉን ባለማቋረጥ የተቻለውን ሊያደርግ ይችላል፤ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ የውጭ አገር ጣልቃ ገብነትን በሚችለው ሁሉ በመመከት ከንቱ ለሆኑ ትርክቶች ተገቢውን የመልስ ምት በመስጠት ቅጥፈትን በእውነት የመተካትን ሥራ ሊሠራ ይችላል። ቀሪው ኢትዮጵያዊ ደግሞ የውስጥ አንድነታችን አሁን ካለው ይልቅ እንዲጎለብትና ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ የበኩሉን ሊወጣ ይችላል። በዚህ መልኩ በመተባበር አላሳልፍ ያለውን ተራራ መደርመስ እንችላለን።
ታች ላይ በማለት ሊያቆረቁዘን የሚዳዳ አካል ይህን ህብረት በትኖ የመግባት አቅም አይኖረውም። እኛ በተቀደደልን ቦይ የምንፈሰም አይደለንም። ነገሮችን ቆም ብለን በማየት የራሳችንን አካሄድ መምረጥ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰናችን እስቀድመን ቆም ብለን እናስተውል፤ ሊያዳክሙን የሚሹትን በጥንካሬያችን እናዝላቸው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም