ሰውዬው የታወቀ ነጋዴ ነበር አሉ። ሁሌም በእሱ ሆቴል የሚመገቡ ደንበኞቹ ስፍር ቁጥር የላቸውም። በየቀኑ የሚቆጥረው ገንዘብም ከሌሎች አቻዎቹ በተለየ በርከት የሚል ነው። ይህ ሰው ዘወትር የእንግዶቹን ፍላጎት ለመሙላት ቦዝኖ አያውቅም። ከትላንት በተሻለ ነገን በልጦ ለመገኘት የሚያደርገው ጥረትም የተለየ ነበር። ስመጥሩ ባለሆቴል ታዲያ አንድ ችግር ነበረበት። ምን የተሻለ ቢያገኝና ኪስ ሙሉ ቢያስገባ ግብር መክፈልን ሞክሮት አያውቅም። ነጋዴው ሁሌም የግብርን ጉዳይ መስማት አይፈልግም። ገና ቃሉን ሲያነሱበት ይናደዳል። በእሱ ዕምነት የሚሰራው የራሱ ላብ እንጂ የሌሎች ጭምር መሆን የለበትም። ግብርን ተንተርሰው የሚነሱ ተለምዷዊ ጉዳዮችም ፈጽሞ አይገቡትም። መስማትና ማወቅ ስለማይፈል ግም «ጆሮ ዳባ ልበስ» ሲል ዓመታትን በዋዛ አሳልፏል። ይህ መሆኑ ደግሞ ከሚመለከተው አካል ጋር ሊያግባባው አልቻለም። የግብር መሰብሰቢያ ወቅት በደረሰ ቁጥር ገቢውን ደብቆና እውነታውን ሸሽጎ ለማለፍ የሚሞክረው ባለሀብት በአንድም ይሁን በሌላ ሰበብ ሲሳካለት ቆይቷል። እንዲህ ለመሆኑ ደግሞ ከግብር ሰብሳቢዎቹ መንደር ቀድሞ የሚደርሰው መረጃ አጋሩ ነበር። በውስጥ አዋቂነት የሚያግዙትና ከእጁ ፍርፋሪ የለመዱ አንዳንዶች ሁሌም «አለንህ » እንዳሉት ነው።
እነዚህ ሰዎች ስለግብር የታሰበውን ሁሉ ቀድመው «ሹክ ይሉታል። ሚስጥር የተባለውንም አንድም ሳይስቀሩ ይዘረግፉለታል። ይህን ሲያውቅ ታዲያ እንደታሰበው ሆኖ ላለመገኘት ጥንቃቄ በማድረግ የሚያህለው የለም። እንዲያውም የተካነ ነው ማለት ይቻላል። መረጃ ላለመተውም አስቀድሞ ይዘጋጃል። ባለሀብቱ የዕለት ገቢውን ቀንሶ፣ የኑሮ ውድነቱን ከገበያ መጥፋት ጋር አስታኮ ማለቃቀስ ልማዱ ነው። በዚህ የማሳሳት ተግባሩም ተገቢውን ግብር ላለመክፈል ሲንሸራተት ኖሯል። ይህን ሀቅ ሳይሆን ትክክለኛውን እውነታ የሚያውቁት የግብር ሰብሳቢ አካላት በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለላ አድርገው ስለማንነቱ ደርሰው በታል።
በዚህ ታዋቂ ነጋዴ ሆቴል የሚደራው ገበያ ከሌሎች በተለየ ነው። በተለይም ዕለተ ቅዳሜ ሲሆንና ገበያተኛው ከአዋሳኝ የገጠር አካባቢዎች ወደ መሀል አገር ሲዘልቅ የምርጫው ሚዛን ለዚህ ሰው ያጋድላል። ከገበያ መልስ ሻጭና ገዢው ያሻውን ተገባብዞ የብርሌውን አንገት፤ የብርጭቆውን ወገብ የሚጨብጠው በእርሱ ሆቴል ነው። ዘመድ አዝማድና ወዳጅ ጓደኛም ቢሆን የመገናኛ ቀጠሮ የሚቀናው በእሱ እልፍኝ ሲሆን ነው። በዚህ ቀን አስተናጋጁ ከተጋባዡ ሲተራመስ መዋሉ አዲስ አይደለም። ይሄኔ ወፍራሙ ባለሀብት ከፍ ካለ ስፍራ አረፍ ብሎ ወጪ ገቢውን ያማትራል። ከየአቅጣጫው የሚጎርፈውን ገቢም ከተቀባዩ እየተቀበለ አንድ ሁለት ሲል ይቆጥራል። በማግስቱ ግን የዚህ ሰው ቋንቋ እንደተለ መደው በማለቃቀስ ይተካል። ምንም አላገኘሁ፤ ኑሮ ተወደደ፣ ገበያ ጠፋ፣ አቅም አነሰ… ሌላም ሌላም፤ የዚህ ሰው መለያው ነው። «ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል» እንዲሉ የሚለው ሁሉ የማይዋጥላቸው ግብር ሰብሳቢዎች መቆጨታቸው አይቀርም፤ ሁሌም ይመክሩበታል። አንድ ቀንም ድንገት ተገኝተው በማስረጃ ሊይዙት ይስማማሉ። በስፍራው ደርሰው ሁሉን ካረጋገጡ በኋላም የበሰለ የተደገሰው በቤት ውስጥ እንዳለ ቤቱን በመላ ለማሸግ ይነጋገራሉ። ይማማላሉ። የማስጠንቀቂያ ደብዳቤውን ከበርና ከመስኮቱ ለመለጠፍ ይስማማሉ። የምክክሩ አካል ከነበረው አንደኛው የነጋዴው የቅርብ ወሬ አቀባይ እንደመሆኑ የተወሰነውን ሁሉ በጥንቃቄ እያዳመጠ በውሳኔው ይተባበራል። ይህ ውሳኔ ለሰውዬው ወሬ በማቀበል ብቻ እንደማይቆም ያውቃል። እንደፍትፍት አጣፍጦ ከሚያጎርሰው እፍታ ባሻገር ለእሱ የሚተርፈው ሲሳይ ቀላል እንደማይሆን እርግጠኛ ነው። እናም ውሎ ሳያድር ከባለ ሆቴሉ ሳሎን ገስግሶ ደረሰ። የያዘውን ሚስጥርና በእሱ ላይ የታሰበውን ዕቅድም አጣፍጦ ነገረው። ባለሀብቱ በዕለተ ቅዳሜ የገበያ ውሎ በሆቴሉ የሚያገኘውን ገቢ አሳምሮ ያውቀዋል። በዚህ ቀን ግብር ሰብሳቢዎቹ ደርሰው እውነታውን ካዩና ጉዳዩን በማስረጃ ካረጋገጡ በህግ እንደሚያስጠይቀው ተረድቷል። ከሁሉም ደግሞ ውስጥ አዋቂው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤውን በበርና መስኮቱ ለመለጠፍ ማሰባቸውን አረጋግጦለታል። ያ ከሆነ ደግሞ የበሰለ ምግብ ካለ በሙሉ ይበላሻል። አስቀድሞ ጥንቃቄ አድርጎ ምግብ ካላዘጋጀም የእለቱ ከፍተኛ ገቢ ይቀራል። ለእርሱ ሁለቱም ኪሳራ ነው። ይህን ማወቁ በጉዳዩ ይበልጥ እንዲያስብ እያደረገው ነው። ለእርሱ ማስጠንቀቂያ ደረሰው ማለትም ትክክለኛና ቋሚ ግብር ከፋይ ሆነ ማለት ነው። ልማደኛው ወሬ አቀባይ የሚገባውን ተቀብሎ ከሄደ በኋላ ዝነኛው ባለሆቴል መልሶ መላልሶ ማሰቡን ቀጠለ። በመጨረሻም የሀሳቡ ውጤት ከአንድ ጥግ ሲያደርሰው ልቡ በሀሴት ተሞልቶ ፊቱ በፈገግታ መውዛት ያዘ። ድንገት ከመቀመጫው ፈጥኖ የተነሳው ባለሀብት ሰራተኞቹን በአፍታ ሰብስቦ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ ጊዜ አልፈጀም። ይህን ሲያደርግ ልበ ሙሉነት ይነበብበት ነበር ። በተባለው ቀን ግብር ሰብሳቢዎቹ ያሻቸውን አስበው በስፍራው ቢደርሱ ሰውዬው ላይደነቅ ወስኗል። ሁሌም እንደሚያደርገው የልመና ቃላት ማዥጎድጎድ አያስፈልገውም። በድንገ ቴዎቹ እንግዶች መድረስም ተደናግጦ ለመስተ ንግዶ «ሽርጉድ» ለማለት አልፈለገም። እነሱ በዕቅዳቸው ቆርጠዋል። እሱም ቢሆን ያሰበውን አስቧል። አሁን ዕለተ ቅዳሜ ነግቷል። በዚህ ቀን በሰፊው የሆቴል ግቢ ገበያው ይደራል። እንግዶችን በመስተንግዶ የሚያስደስቱት ብርቱ ሰራተኞች እንደተለመደው በስራ ተወጥረው ይውላሉ። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን የታዋቂው ሆቴል ጠንካራ በርና መስኮቶች ወለል ብለዋል። በርና መስኮቶቹ እንደወትሮው አልነበሩም። ክንዶቻቸው ተገንጥለው መዝጊያዎቻቸው ተነቃቅለው ከንፈር እንደሌለው ጥርስ ሆነዋል።
ለወትሮው በር አሊያም መስኮት የሚያስብላቸው አካል አብሯቸው አይታይም። መለመላቸውን ቆመው ክንፍ እንደሌለው አሞራ ሆነዋል። የቤት ሳይሆን የዋሻ መግቢያ መስለው ቧ ብለዋል። ገበያው ደርቶ ወጪ ወራጁ በሚተራመስበት የሆቴል አዳራሽ በሰዓቱ የደረሱት ግብር ሰብሳቢዎች የሚያደርጉትን አልዘነጉም። ድንገት በመምጣታቸው የሚደናገጠውን ባለ ሆቴል እያሰቡ በእጅ መንሻ አሊያም በግብዣ እንዳይደልላቸው አስቀድመው ተማምለዋል። የእነሱን ድንገት መድረስ የተመለከተው ሰው ግን እንደታሰበው ሆኖ አልደነገጠም። መሽቆጥቆጥም ሆነ መደናበር አልታየበትም። ሹሞቹን እንደማንኛውም እንግዳ ገርመም አድርጓቸው ወደ ጨዋታው ይመለሳል። እንግዶቹ በዚህ ስሜቱ ቢገረሙም ወደዕቅዳቸው ለመዝለቅ በርና መስኮቶችን ፍለጋ ይዘዋል። የሆቴሉን ዋና መግቢያ እንዳገኙ በሩን በአይኖቻ ቸው መቃኘት ያዙ። ተፈላጊው በር መቃኑ እንጂ ሙሉ አካሉ የለም። አለፍ ብለው የመስኮቶቹን ግራና ቀኝ አሰሱ። እነሱም ቢሆኑ ክንፉ እንደተመታ አሞራ ሆነዋል። ግራና ቀኝ የነበሯቸው መዝጊያዎች አሁን አብረዋቸው የሉም። መለስ ብለው ደግሞ ወደጓሮ በር አመሩ። እሱም ቢሆን መዝጊያው ወላልቆ እርቃኑን ቆሟል።
የሆቴሉን ዙሪያ ገባ በጥንቃቄ ሲዞሩ የቆዩት አሳሾች አንድም በርና መስኮት የሚባል እውነት አላገኙም። እናም ምኑን ዘግተው በምን ላይ ወረቀት ለጥፈው ቤቱን አሸግን ይበሉ? በተደበላለቀ ስሜት ተውጠው ወደመጡበት ስፍራ ተመለሱ። ይህ ሁሉ ሲሆን ባለሆቴሉ ከነበረበት ሆኖ በልቡ ይስቅባቸው ነበር። ሰዎቹ አስቀድመው እንዳሰቡት ማስጠንቀቂያውን ለመለጠፍ ያሰቡት በበርና መስኮቶቹ ላይ ነው። ለጊዜው ይህን ለማድረግ ስፍራ ስላላገኙ ተያይዘው ተመለሱ። ይህ የሆነው ለጊዜው ነው። የነገውን እውነት ግን እነሱም ሆኑ ሰውዬው አሳምረው ያውቁታል። ወዳጆቼ! ይህ አጋጣሚ ማንም ቢሆን ከእውነታው ሊርቅ የሚችለው ለጊዜው እንጂ ለዘለቄታው አለመሆኑን ይጠቁመናል። በአብዛኛው እንደሚስተዋለው አንዳንድ ነጋዴዎች ሰርተው በሚከብሩባት፣ ነግደው በሚያተርፉባት ሀገራቸው ከዚህም በላይ የረቀቀ ዘዴ መጠቀማቸው አዲስ አይደለም። ግብር ለማንም ቢሆን የማይቀር ሀገራዊ ግዴታ ነው። ይህ ይሆን ዘንድም ሀይማኖታዊና ታሪካዊ እውነታዎች ጭምር ይጠቁሙናል። ማንም ለሚኖርባት ሀገር ከሚያገኘው ደመወዙ፣ ከሚያፍሰው ምርቱ፣ ነግዶ ከሚያተርፈው ጥሪቱ የሚጠበቅበትን ሊያበረክት ግድ ይለዋል። ግብርን በወቅቱ አስቦ መክፈልም የአዋቂነት ምልክት ነው። ሁሉም ዜጋ በሚከፍለው ግብር ሀገሩን፤ ወገኑንና ራሱን ይጠቅማል። በዚህ ግዴታው ውስጥም መብቱን አስጠብቆ እርሱነቱን ያኮራል። «ግዴታዬን እወጣለሁ፣ መብቴን እጠይቃለሁ» ሲባል ደግሞ በአባባል ላይ ብቻ ተመስርቶ አይደለም። መብትን ለመጠየቅ ግዴታን መወጣት ግድ ሊል እንጂ፤
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
መልካምስራ አፈወርቅ