ሀገራችን በታሪኳ ከውስጥም ከውጭም እንዲህ ያለ የተንሰላሰለ፣ የተናበበና የተቀናጀ ጫና ተፈጥሮባት አያውቅም። በውስጥ አሁን ጋብ ቢልም ማንነትን ኢላማ ያደረገ ጥቃት፤ የኮሮና ወረርሽኝ፣ የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፤ ተስፋ የቆረጠው አሸባሪው ህወሓት የመረጠው የአጥፍቶ ጠፊነት አደገኛ መንገድ፤ ሱዳን ድንበራችንን አልፋ የፈጸመችው ወረራ፤ ግብፅ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ታካ የከፈተችብን የዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘመቻ፤ ምዕራባውያን የሰሜኑን የሀገራችን ክፍል በተመለከተ ሆን ብለው በያዙት የተዛባ መረጃ የደረሱበት የተሳሳተ መደምደሚያና ሌሎች ጫናዎች በአንድ ላይ በአንድ ጊዜ ናዳ ሆነው መጥተውብናል። ሁሉንም ናዳዎች በአንድ ጊዜ ለመመከት ደግሞ አቅም የለንም። ስለሆነም አቅማችንን በልኩ የመረመረና የሚመጥን ምላሽ መስጠት ያሻል። እየመጡ ካሉ ናዳዎችም ቀድሞ የሚደርሰውንና የባሰ አደጋ የሚያስከትለውን በመለየት ቀድሞ መመከት ግዴታ ነው። በዕለት ተዕለት ኑሮአችንም የምናደርገው ይኸን ነው። የሚቀድመውን እናስቀደማለን። የሚከተለውን እናስከትላለን። እንደ አንገብጋቢነት ደረጃው በቅደም ተከተል ማስተናገድ ወይም መጋፈጥ ይጠይቃል ።
አሸባሪው ህወሓት ታሪክም ሆነ ትውልድ ይቅር የማይለውን ክህደትና ጥቃት በሰሜን ዕዝና በሀገር ላይ ጥቅምት 24 በፈጸመ ጊዜ ከሀገር ህልውናና ከሕዝብ ሉዓላዊነት የሚቀድም ምንም ነገር ስላልነበር ቅድሚያ ተሰጥቶት በሶስት ሳምንት ውስጥ አሸባሪው ህወሓት አከርካሪው ተሰብሯል። የቀረው ስራ መልሶ ማቋቋምና የመሠረተ ልማት ጠግኖ ወደ አገልግሎት ማስገባትና የዕለት ደራሽ እርዳታ ማድረስና የፈረጠጠውን ርዝራዥ አድኖ ለሕግ ማቅረብ ነበር። ባለፉት ስምንት ወራት የተከናወነው ይኸው ነበር። ሆኖም ብዙኃኑ ትግራዋይ ለዘመናት ሲጋተው በኖረ ሀሰተኛ መረጃ፣ በፕሮፓጋንዳና በፍርሀት ዝምታን በመምረጡ፤ የአሸባሪው ርዝራዥ ሰብዓዊ ፍጡርን እንደ ጋሻ እየተጠቀመ ሊጠብቀውና ሊረዳው በሄደ ሰራዊትና ሲቪል ላይ አደጋ እየጣለ ጦሩን ወደ አልሆነ መንገድ እየመራው ስለሆነ ፖለቲካዊ ውሳኔ መወሰን ማስፈለጉን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 22 ለጋዜጠኞች በስፋት አብራርተዋል። እውነት ለመናገር ከእሳቸው ማብራሪያ በፊት ውሳኔው ለአብዛኛው ሀገር ወዳድ ዜጋ ዱብ እዳ፣ ግራ አጋቢና አስደንጋጭ ነበር። የእሳቸውን ተከትሎ የሌተናል ባጫ ደበሌና የአምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ማብራሪያ ብዥታን ከማጥራቱ ባሻገር የዜጋውን ልብ አሳርፏል። በአንድ በኩል በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ከውስጥ የሚደርሱበት በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ላይ ከውጭ እየደረሱ ያሉ ጫናዎች፣ የሚከፈለው ዋጋ ትርጉም እንዳይኖረው አድርጎታል። ዋጋ የሚከፈለውስ ለማን ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል። መንግሥት እየሞተ ካለ ቡድን ጋር አብሮ ላለመሞት የታክቲክ ለውጥ አድርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተናጠል የተኩስ አቁም ለማድረግ የተደረሰበትን ውሳኔ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሳምንት ሙሉ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ መከላከያ መጀመሪያ ጦርነቱ እንደተጀመረ የገጠመው የተደራጀ፣ የታጠቀና ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሰ ኃይል ነበር። እሱን በሁለት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ከተወገደ በኋላ የተወሰነ የጎሬላ ውጊያ አጋጥሟል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን መከላከያ በየመንደሩ በመሄድ ማጣራት ሲያደርግ የሚገጥመው ጦር ሳይሆን ህዝብ ነው። በቃ ሰላም ነው ብሎ ሲያልፍ ግን ከጀርባው ደጀን ነው ባለው ህዝብ ተጠቅቷል።
መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለመወሰኑ ዋናው ምክንያቱ መከላከያ ሠራዊታችን በአገሩና መስዋዕትነት ሊከፍልለት በተዘጋጀው ህዝብ እንደ ባዕድ መታየቱ ነው ያሉት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፤ ሠራዊቱ ደጀን ወደሚያገኝበት አካባቢ እንዲመጣ ህዝቡም ከስህተቱ የሚማርበት የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም እውነታውን መረዳት እንዲችል ነው። ይሁንና ጦሩ ትግራይን ለቆ እንዲወጣ ከወሰነበት ሌሊት ጀምሮ ከብዙ የዓለም አገራት መሪዎች የስልክ ጥሪ እንደደረሳቸው፤ በተለይም ጦሩን ሲከሱና ሲወቅሱ የነበሩ ሁሉ በጦሩ መውጣት መበሳጨታቸውን እንደነገሯቸው አስታውቀዋል።
መንግሥት መቀሌን ለቆ ቢወጣም ምንም የሚያጣው ነገር የለም። በክልሉ ብሎም በመቀሌ የነበሩ ዋና ዋናና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ወጥተዋል። አሁን መቀሌ ምንም አይነት የስበት ማዕከል ካለመሆኗም በላይ በምንም መልኩ ለወታደራዊ ስትራቴጂነት የቀራት ነገር የለም። መያዝ በሚገባንና መቆየት በሚያስፈልገን ቦታዎች እንቆያለን። ወደዛ በተደራጀ መንገድ የሚመጣ ኃይል ካለም እናስተናግደዋለን። ይህም ሆኖ እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች ሲወሰኑ ኢትዮጵያውያን ቶሎ የማሸነፍ ፍላጎት ስላላቸው ለመቀበል ይቸገራሉ። እኛ መሪዎቹ በእንደዛ አይነት ስሜት ልንነዳ ሳይሆን ቆም ብለን አገርን ሊያሻግር የሚችል ውሳኔ ለመወሰን የተቀመጥን መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ማስረዳታቸውን የ”አዲስ ዘመን “ ጋዜጣ ዘግቧል ።
በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሬድዋን ሁሴንና የመከላከያ የግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ባለፈው ረቡዕ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አምባሳደር ሬድዋን እንዳስታወቁት፤ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ከአስተላለፈና የመከላከያ ሠራዊቱ ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ በትግራይ ክልል ሰዎች እየተገደሉ ነው። ከአሁን በኋላ ቀውስ፣ ግድያ ካለና ሰብዓዊ ዕርዳታ ከተስተጓጎለ የሚወቀሰውና የሚጠየቀው ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ቡድን ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህን ቡድን ተጠያቂ ማድረግ አለበት። መንግሥት በቅርቡ በተናጠል ባወጀው የተኩስ አቁም ውሳኔ መሠረት ሠራዊቱን ከትግራይ አስወጥቷል። ለህዝቡ ዕርዳታ ለማድረስ ተቸግረናል በሚል እንደ ሰበብ በመቁጠር መከላከያ ሠራዊታችን ሲወቅሱ የቆዩ አካላት ያልተገደበና ተደራሽነት ያለው ዕርዳታ መስጠት እንፈልጋለን ካሉ ገብተው እንደፈለጉ ዕርዳታ መስጠት ይችላሉ። ከአሁን በኋላም በትግራይ ለሚከሰተው ችግር ሽብርተኛውን ቡድን ተጠያቂና ተወቃሽ ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አምባሳደር አስገንዝበዋል።
ሽብርተኛው ቡድን ሆን ብሎ የትግራይ ህዝብ ዕርዳታ እንዳያገኝና እንዲራብ በማድረግ ረሃብን ለቅስቀሳ ይጠቀምበት ነበረ። እሱ ለሚፈጸመው ወንጀል ሰበብ ላለመሆን፤ የትግራይ አርሶ አደር ያለ ስጋት እርሻውን እንዲያካሂድ፤ ህዝቡ የመንግሥትን ጥረት በጥሞና እንዲገነዘበውና ኢትዮጵያ ውጫዊ የደህንነት ስጋት ስላለባት የአገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ መውጣቱንና መንግሥት በቅርቡ በተናጠል ያወጀው የተኩስ አቁምም ወታደራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። በትግራይ ክልል ህግ ማስከበሩ ርምጃ ከመጀመሩ በፊት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። በሃይማኖት አባቶች፣ በታዋቂ ሰዎችና በአገር ሽማግሌዎች በኩል የተደረጉት ጥረቶች ሽብርተኛው ህወሓት ለስሜቱ በመገዛቱና ለራሱ የተጋነነ ግምት በመስጠቱ ምክንያት ወደ ግጭት መገባቱን አምባሳደር ሬድዋን አውስተዋል።
የመከላከያ የግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ በበኩላቸው፤ መቀሌን መልቀቅ ከወታደራዊ ትርፍና ኪሳራ አኳያ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል። ሽብርተኛ ቡድኑ ፈትቶ ከለቀቀው 10ሺ ያህል ዘራፊዎች ከተማዋን መጠበቅና በየስርቻው የተደበቀውን የተኮላሸ ሽብርተኛ ቡድን መፈለግ ለሠራዊታችን ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ጥቃት በመፈፀሙ መንግሥት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ ማካሄዱን አስታውሰው፤ ሠራዊቱ በአጭር ቀን ዘመቻውን ማጠናቀቁን፤ የቡድኑ ከፍተኛ እና ዋና ዋና አመራሮች በቁጥጥር ስር ማዋሉና መደምሰሱን፤ ቡድኑ ይዟቸው የነበሩትን ከፍተኛ መሳሪያዎችን ማስመለሱና ሽብርተኛውን ቡድን አከርካሪውን መስበር መቻሉን አመልክተዋል። ሽብርተኛ ቡድኑ አቅም ቢኖረው ኖሮ ከሁለት እስከ ሶስት ሺህ ተሽከርካሪ በእጀባ/በኮንቮይ/ወደ ሌሎች አካባቢዎች ስናንቀሳቅስም መሰናክል መፍጠር ይችል ነበር። ነገር ግን ይህን እንኳ የሚተናኮስ አቅም የለውም። ከዚህ በኋላ መከላከያ ሠራዊት መቐሌ መቆየቱ ወታደራዊ አስፈላጊነት እንደሌለው ገልጸው፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ ቢወጣም ሽብርተኛው ቡድን አሁንም አማራንና ኤርትራን እወራለሁ በሚል ባዶ ምላሱ ኤርትራን ወደ ጦርነት እየጋበዛት መሆኑን ጠቁመዋል። የመከላከያ ሠራዊታችን አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሮኬት፣ ታንክና ሚሳኤል ታጥቆ በነበረው ጊዜ እንኳን በሦስት ሳምንት መቀሌ መግባት ተችሏል። ሌተናል ጀነራል ባጫ በማከልም፣ አሁን ቡድኑ የኢትዮጵያ ስጋት አይደለም። ስጋት እንዳይሆንም እንሰራለን። ከዚህ አልፎ በራያ፣ በሁመራ፣ በአፋርና በሌሎች አካባቢዎች ትንኮሳ አካሄዳለሁ ካለ የመከላከያ ሠራዊታችን በየአካባቢዎቹ በተጠንቀቅ በቅርብ ስለሚገኝ ይኮረኩመዋል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ሠራዊቱ መቀሌን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጁነት አለው ።
እንደ መውጫ
ዛሬ አሸባሪው ህወሓት ከስምንት ወራት በፊት በነበረው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ቁመና ላይ ሳይሆን 95 በመቶ የሚሆነው አመራሩ የተደመሰሰ ወይም በሕግ ጥላ ስር የዋለ፤ ከ200ሺህ በላይ የአሸባሪው ልዩ ኃይል፣ ከጂና ሚሊሽያ የተደመሰሰበት፣ ከአንጋችነት ወደ ጀሌነት የተቀየረበት፤ ዘርፎትና አግቶት የነበረው 80 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የጦር መሳሪያና ሰራዊት የተመለሰበት ሁኔታ ላይ ስለሆነ የትግራይም ሆነ የመቀሌ ወታደራዊና ፖለቲካዊ የስበት ማዕከልነት ምንም ስለሆነ፤ እንዳያርስ እንዳይዘራ ተከለከለ የተባለው አርሶ አደርም ክረምቱን እንዲጠቀም፤ ያለገደብ እርዳታ ለማድረስ ይመቻችል ሲሉ ለነበሩ ምዕራባውያንም ሰበበ ላለመሆኑ፤ የሰብዓዊነት የተናጠል የተኩስ አቁም ለማድረግና ሰራዊቱን ማስወጣት አስፈላጊ ሆኗል። ትግራዋይም የሚበጃቸውን መለየት እንዲችሉ ከራሳቸው ከቁርበታቸው ጋር የመምከሪያ የጥሞና ጊዜ እንዲያገኙ ፖለቲካዊ ወሳኔው ተላልፏል። ሀገሪቱ በሌለ አቅሟ ወታደራዊ ወጭዋን ሳይጨምር የትግራዋይን ልብ ለማሸነፍ፣ ለዕለት ደራሽ እርዳታ፣ ለመሠረተ ልማት ጥገናና ግንባታ ብቻ 100 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርጋለች። ይህ የክልሉን ዓመታዊ በጀት 13 ወይም 14 እጥፍ መሆኑ ነው። ቢያንስ የትግራይ ክልል የ10 ዓመት በጀት ነው እንግዲህ በስምንት ወር ወጭ የሆነው። ከሀገሪቱ አጠቃላይ በጀት ወደ 20 በመቶ የሚጠጋ ማለት መሆኑ ነው እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ። ሌላ ስምንት ወር፣ ዓመት፣ ዓመታት ቢቆይ ሊወጣ የሚችለውን አስቡት። ሀገሪቱን ወዴት ወዴት ሊወስዳት እንደሚችል እዩት። በነገራችን ላይ ወደፊት በጥናት የሚረጋገጥ ሆኖ በመላ ሀገሪቱ ለተከሰተው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትም ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ አለው። በዚህ ይቀጥል ማለት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሊሸከመው ወደማይችል ሁለንተናዊ አዘቀት ውስጥ መግባት ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር እንዳስረዱት ይህ አካሄድ ደግሞ የአሸባሪው ህወሓት አጀንዳ የሆነውን ማለትም ተያይዞ መውደቅን ማስፈጸም ነው። ሀገሪቱ ለ27 ዓመታት በአደባባይ በጠራራ የተዘረፈችው፤ በስሟ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር ወስዶ ማሸሹ ሳያንስ ከዚህ በኋላ ከዚህ ሙት ጋር ተያይዞ መሞት አያሻም የሚለው ውሳኔ ተገቢ የሚሆነው ለዚህ ነው። ከታላቁ የህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ የተደቀነው አደጋ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ስትራቴጂካዊ ጉዳይ መሆኑ ሌላው የውሳኔው መግፍኤ ነው። በምዕራቡ የሀገራችን ክፍል ያንዣበበው የስጋት ዳመና መጣሁ መጣሁ እያለ መሆኑ ትኩረትን ወደ እሱ ማዞር ተገቢ ነው። ከፍ ብሎ የተዘረዘሩት ፖለቲካዊ ውሳኔዎች በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመርኩዘው የተላለፉ ፕራግማቲስት ውሳኔዎች ናቸው። ይህን መሰል መርህ ነባራዊ ኅልዮት/pragmatic theory /ይሰኛል። “ተግባራዊ እውነትን ያስቀደመ ውሳኔ” ማለቴ ለዚህ ነው። ነባራዊ ኀልዮው የአሜሪካውያኑ ሲ ኤስ ፒርስ እና ዊሊያም ጀምስ የፍልስፍና ንቅናቄ አካል ሲሆን፤ በአጭሩ ሲተረጎምም ሁኔታዎችን፣ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተጠይቃዊና አመክኖአዊ በሆነ አግባብ መከወን፣ መፍታት ነው። ከፅንሰ፣ ከንድፈ ሀሳብ ይልቅ፤ በተጨባጭ፣ መሬት ላይ ባለ እውነታ፣ በነባራዊ አውድ መመራትን የሚለፍፍ ፍልስፍና ነው ።
ኅልዮቱ እንደ ዜጋም እንደ ሀገርም ይበጀናል ብዬ የማምነው ለዚህ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም